በኮሮናቫይረስ ስጋት ሰዎች እቃዎችን በገፍ እየገዙ እንዳያጠራቅሙ ምን ይደረግ?.

በተለያዩ አገራት የኮሮናቫይረስ ሕሙማን ሪፖርት መደረግን ተከትሎ የድንጋጤ የገፍ ግዥ (panic buying) በስፋት ተስተውሏል።

ይህንን የድንጋጤ የጥድፊያ ገበያ መቆጣጠር ይቻላል?

በሱፐር ማርኬቶች፣ በሰፈር መደብሮች እና ማከፋፈያዎች የተወሰኑ አስፈላጊ የሆኑ እንደ ምግብ፣ የንፅህና መጠበቂያ ሳሙናና ሶፍት እንዲሁም ሌሎች የፍጆታ እቃዎችን በገፍ ገዝተው ሌሎች ሰዎች ጥቂት እንኳ እንዳያገኙ ሆኗል።

ባለፈው ሳምንት አርብ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች በኢትዮጵያም በኬንያም መገኘታቸው መገለፁን ተከትሎ አዲስ አበባ እና ናይሮቢ ላይም በየሱፐርማርኬቶች የገፍ ሸመታ በከፍተኛ ሁኔታ ተስተውሏል።

ይህ ከጥቂት ቀናት በፊት እንደ አውስትራሊያ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካና ጃፓን ባሉ አገራትም ታይቷል።

ዜናው በተሰማ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አዲስ አበባ ውስጥ ዲቶል ሳሙና፣ አልኮል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም ሳኒታይዘር ማግኘት የማይታሰብ ሆኗል።

ፓስታ፣ ሩዝ፣ ረዥም ቀን ያላቸው ወተቶች የህመም ማስታገሻዎችን ጭምር ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር።

በማግስቱም የተለያዩ የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች፣ የህፃናት የታሸጉ ምግቦች በሱፐርማርኬት መደርደሪያዎች ላይ አልነበሩም።

በሌላ በኩል በቀላሉ በወፍጮ ቤቶች ጤፍ ማግኘት አለመቻላቸውን የሚገልፁም አልታጡም።

ሰዎች ይኼና ያኛው ሳይሉና ምን ያህል ያስፈልገኛል ሳይሉ ያገኙትን ነገር ሁሉ እያፈሱ ገዝተዋል። ይህን የሚያሳዩ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎችም በማህበራዊ ሚዲያ ተሰራጭተዋል።

ሰዎች መሰረታዊ ፍጆታዎችን በገፍ እየገዙ በመሆናቸው እጥረት እንዳይፈጠር ሱፐር ማርኬቶች ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ዜጎቻቸው እቃዎችን ሲሸምቱ ምክንያታዊ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። ሱፐርማርኬቶችም ደንበኞቻቸውን ተመሳሳይ ጥያቄ ጠይቀዋል።

በእንግሊዝ ታዋቂ ሱፐርማርኬቶች ሰዎች ከአንድ ምርት ምን ያህል መግዛት እንደሚችሉ ገደብ ለማስቀመጥ ተገድደዋል።

በኢንተርኔት ገበያም ቢሆን ሰዎች የሚገዙት የእቃ ብዛት ላይ ገደብ ይጥላሉ ሱፐርማርኬቶቹ።

የድንጋጤ የገፍ ግዥ በትክክልም እጥረት በሌለበት የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች እጥረት ከማስከተሉ ባሻገር ለግዥ የሚደረገው ያልተገባ ግርግርና መገፋፋት ለቫይረሱ ስርጭት መንገድ ይከፍታል።

በትናንትናው እለት አዲስ አበባ ፋርማሲዎች ደጃፍ ላይ ሳኒታይዘር ለመግዛት የነበረው ግርግርም የዚሁ ማሳያ ነው።

በዚህ ረገድ በእንግሊዝ ያሉ ሱፐርማርኬቶች ደንበኞች በሱፐርማርከኬቶች እንቅስቃሴአቸው በምን ያህል ርቀት መሆን አለበት የሚሉና ሌሎችንም ጉዳዮች በማስመልከት መመሪያ አውጥተዋል።

ለምሳሌ በእድሜ የገፉ እንዲሁም አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ለብቻቸው መስተናገድ የሚችሉበት የተለየ ሰዓትንም ጭምር ይፋ አድርገዋል ሱፐርማርኬቶቹ።

የሰዎችን ማህበራዊ መስተጋብር ለመቀነስ በማሰብ እዚያው ሱፐርማርኬት ውስጥ የሚገኙ ካፍቴሪያዎችንም ዘግተዋል።

በሌላ በኩል በእንግሊዝ መንግሥት በበኩሉ ዜጎች እቃዎችን እየገዙ የሚያጠራቅሙበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ለዜጎቹ ገልጿል።