ኮሮናቫይረስ፡ ጣልያን ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ 133 ሰዎች ሞተዋል

ኮሮናቫይረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በየዘመኑ ወረርሽኞች የሚሊዮኖችን ሕይወት ቀጥፈዋል። ሕክምና በዘመነበት ዘመን በመፈጠራችን በሽታዎች እንደተፈለፈሉ በአጭሩ ስለሚቀጩ የቀድሞ ትውልድ ወረርሽኝ እንደሚያስጨንቀው እኛን ላያስጨንቀን ይችላል።

ኮሮናቫይረስ ግን አሁን ዓለምን ሰቅዞ ይዟል። አገራት ምጣኔ ሐብታቸው ብርክ ይዞታል። የዓለም 'የምርት ፋብሪካ' የምትባለው ቻይና እንኳን ኮሮና ፍዳዋን እያበላት ነው።

በቁጥር ከዩናይትድ ኪንግደምን ሕዝብ የሚልቀውን የሁቤ ግዛት ነዋሪ ከቤትህ ንቅንቅ እንዳትል ብላዋለች። 60 ሚሊዯን የሚጠጋው የግዛቲቱ ነዋሪ አምራች ሕዝብ ቤቱ ሲቀመጥ ቻይና በድምሩ የምታጣው ገንዘብ የዋዛ አይሆንም።

ለመሆኑ ኮሮናቫይረስን በተመለከተ ምን አዳዲስ መረጃ አለ?

  • እስካሁን ቫይረሱ ሰተት ብሎ ገብቶባቸዋል የተባሉት የዓለም አገራት 93 ደርሰዋል።
  • እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 106ሺ 161 አልፏል።
  • ከዚህ ቁጥር ውሰጥ 80ሺ 813 የተመዘገበው በቻይና ነው።
  • በድምሩ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ3 ሺህ 600 በላይ ነው።
  • በቻይና የሟቾች ቁጥር 3097 አልፏል።
  • ከቻይና ውጭ የሟቾች ቁጥር 497 አልፏል።
  • በሰሜን ኮሪያ ቫይረሱ አለባቸው የተባሉት ሰዎች ቁጥር 7ሺ 134 አልፏል።
  • አውስትራሊያ 76 ተይዘዋል፣ 3 ሞተዋል።
  • በፈረንሳይ 949 የተያዙ ሲኖሩ 11 ሞተዋል።

በጀርመን ተያዙ የተባሉ 800 ሰዎች አሉ።

  • በጃፓን 461 ተይዘው፣ 6 ሞተዋል።
  • በቻይና ትናንት ቅዳሜ በቫይረሱ መያዛቸው የተደረሰባቸው 44 ሰዎች ብቻ ናቸው። ይህም እስካሁን ትንሹ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።
  • ቫቲካን፣ ሰርቢያ፣ ስሎቫኪያ፣ ፔሩ፣ ካሜሮን እና ቶጎ ከሰሞኑ የተቀላቀሉ ናቸው።
  • ኮሎምቢያ፣ ቡልጋሪያ፣ ኮስታሪካ፣ ማልታ፣ ማልዲቭስ እና ፓራጓይ እያንዳንዳቸው አንድ አንድ የቫይረሱ ተጠቂ አግኝተናል ሲሉ አውጀዋል።
  • ኔዘርላንድስ አርብ ዕለት በኮሮናቫይረስ የመጀመርያውን የአገሯን ሰው አጥታለች። የተያዙ 188 ሰዎች አሉ።

በሰሜን ጣሊያን ሎምባርዲ ክልል 16 ሚሊዮን ሰዎች ገለል ተደርገው እንዲቀመጡ አድርጋለች። ይህ ቁጥር የሕዝቧ አንድ አራተኛ ይጠጋል። በነዚህ የእንቅስቃሴ እቀባ በተደረገባቸው 14 አውራጃዎች አይደለም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሰርግና ቀብር እንኳ በሰዎች ስብስብ መሀል እንዳይከወን ተወስኗል። ይህ ደንብ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑትን ሚላንና ቬነስን ይመለከታል። የጣልያን ሴሪ-አ ጨዋታዎችም በባዲስ ስታድዬም ተከናውነዋል።

  • በጣሊያን የሞቱት 366፣ በቫይረሱ የተጠቁ ደግሞ 7375 ደርሰዋል።
  • ኒውዯርክ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጃለች። እዚያ ተያዙ የተባሉት ሰዎች 76 ደርሰዋል።
  • አሜሪካ በድምሩ 19 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ሞተዋል።
  • በፕሪምየር ሊግ ተጨዋጮች እርስ በርስ እንዳይጨባበጡ ተወስኗል።
  • የእንግሊዝ ፓርላማ አባላትም መጨባበጡን እርግፍ አድርገው ትተውታል።
  • በኢራን የተያዙ ሰዎች ቁጥር 6ሺ 566 ይጠጋሉ። ሟቾች 194 ደርሰዋል። ይህ ቁጥር እርግጡ ግን ከዚህ በብዙ እጥፍ እንደሚሆን ይጠረጠራል።
  • እስራኤል 1ሺ 200 መቶ ወታደሮችን ገለል ባለ ሥፍራ እንዲሆኑ ወስናለች።
  • በዩናይትድ ኪንግደም በቫይረሱ የተያዙት 206 ደርሰዋል። የሞቱት እስካሁን 2 ብቻ ናቸው።
  • የካቶሊኩ ጳጳስ የእሑዱን ጸሎት የሚመሩት በቀጥታ የቪዲዮ ሥርጭት ነው ተብሏል። የሰዎችን ስብስብ ለማስቀረት።

ቫይረሱ ለዓለማችን ትንሿ አገር ቫቲካንም አልራራላትም።

  • ደቡብ ኮሪያ የፊት ጭንብልን በፈረቃ እያደለች ነው። አንድ ሰው በሳምንት ሊገዛ የሚችለው የጭምብል መጠንም ተወስኗል።
  • በደቡብ ኮሪያ ጸሎት ቤት መሄድ ተከልክሏል። በአገሪቱ ትልቁ የፕሮቴስታንት ቸርች የሆነው የዊዶ ጎስፕል ቤተክርስቲያን ግማሽ ሚሊዮን ለሚሆኑ አባላቱ በቀጥታ የኦንላይን ጸሎት ሥነ ሥርዓት አድርጓል።
  • ጀርመን፣ ደቡቡ ኮሪያና ሌሎች በርካታ አገሮች የፊት ጭምብል ወደ ውጭ አገር መላክን ከልክለዋል።

በቻይና ጉዋንዡ ከቫይረሱ የሚያገግሙ ሰዎች የሚጠለሉበት ባለ አምስት ፎቅ ሆቴል ተደርምሶ 10 ሰዎች ሞተዋል፤ 28ቱ ፍለጋ ላይ ናቸው። 70ዎቹ ፍርስራሽ ተጭኗቸዋል። የሕንጻው ባለቤት በፖሊስ ቁጥጥር ውሏል።

  • የአሜሪካ ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲ የመጀመርያውን የቫይረሱን ተጠቂ መዝግቢያለሁ ብላለች።
  • በዩናይትድ ኪንግደም ነገሮች ቢከፉ ቢከፉ የሚሞተው ሰው ቁጥር 100ሺ እንደሚሆን የጤና ባለሞያዎች ለሰንደይ ታይምስ ተናግረዋል።