ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ውሉ ያልታወቀው ቻይና የተከሰተው ቫይረስ በርካቶችን ሳይበክል አልቀረም
ቻይና ውስጥ የተከሰተው ቫይረስ ባለሥልጣናት ከሚሉት ቁጥር በላይ ሰዎችን ሳይበክል እንዳልቀረ የሕክምና ባለሙያዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የቻይና መንግሥት በገዳዩ ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 60 ነው ቢልም የእንግሊዝ የሕክምና ባለሙያዎች ግን 1700 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል እያሉ ነው።
የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃው ይህ ቫይረስ የተከሰተው 'ዉሃን' የተሰኘ ግዛት ውስጥ ሲሆን እስካሁን ሁለት ሰዎች መሞታቸው ይፋ ተደርጓል።
ከሕክምና ባለሙያዎቹ አንዱ የሆኑት ፕሮፌሰር ኒል ፈርጉሰን ሁኔታው እጅግ እያሳሰባችው እንደመጣ አሳውቀዋል።
ምርምሩን ያከናወኑት የእንግሊዝ ሐኪሞች ሌሎች ተቋማትና ከዓለም ጤና ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን ነው።
ሲንጋፖር እና ሆንግ ኮንግ ከቻይና ውሃን ግዛት የሚመጡ ተጓዦችን መርምረው ማስገባት ጀምረዋል። ዩናይትድ ስቴትስም ብትሆን በሳን ፍራንሲስኮ፣ ሎስ አንጀለስ እና ኒው ዮርክ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች በኩል የሚያልፉ መንገደኞች እንዲመረመሩ ትዕዛዝ አሳልፋለች።
ምንም እንኳ ቫይረሱ መጀመሪያ ዉሃን ግዛት ላይ ይታይ እንጂ ታይላንድ ውስጥ ሁለት፤ ጃፓን ውስጥ ደግሞ አንድ ሰው በቫይረሱ መጠቃታቸው ተሰምቷል።
አሁን ላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ትክክለኛ ቁጥር ምን ያክል እንደሆነ መገመት አዳጋች ነው፤ ነገር ግን በሽታውን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው አካል ከአውሮፕላን ማረፊያዎች የሚገኙ መረጃዎች ቁጥሩን ሊጠቁሙ ይችላሉ ተብሏል።
የዉሃን አውሮፕላን ማረፊያ 19 ሚሊዮን ሰዎችን እንዲያስተናግድ ተብሎ የተገነባ ሲሆን የዓለም አቀፍ በረራ ተጠቃሚዎች ቁጥር ግን 3400 ብቻ ነው።
የቻይና መንግሥት ቫይረሱ ከሰው ሰው ተላላፊ መሆኑን የሚያሳይ ምልክት እስካሁን አልታየም ብሏል። በሽታው ከተበከለ የባሕር ውስጥ እንስሳ ሳይመጣ እንዳልቀረም ግምት አለ።
ቫይረሱ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቃ ሲሆን በፈረንጆቹ 2002 ቻይና ውስጥ ከተከሰተውና ሳርስ ተብሎ ከሚታወቀው ቫይረስ ጋር ተመሳሳይነት አለው ተብሏል።