ናሳ፡ ከአውስትራሊያ ሰደድ እሣት የመነጨው ጭስ ዓለምን ይዞራል

የአሜሪካው የጠፈር ሳይንስ ተቋም ናሳ ከአውስትራሊያ ሰደድ እሣት የተነሳው ጭስ ዓለምን ዞሮ ወደ መጣበት ይመለሳል ሲል ተንብየዋል።

የአውስትራሊያ ምስራቃዊ ክፍልን ለወራት ሲያቃጥል የነበረው ሰደድ እሣት ጭስ የፓሲፊክ ውቅያኖስ ጣሪያ ላይ ተንሳፎ ይገኛል።

ናሳ እንደሚለው በአውⶂጳውያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ቀን ከአውስትራሊያ የተነሳው ጭስ የደቡብ አሜሪካ ሰማይ ላይ ታይቷል፤ በሳምንቱ ደግሞ የዓለምን ግማሽ ተንሸራሽሯል።

ጭሱ ዓለምን ቢያንስ አንድ ጊዜ ሊዞራት እንደሚችል ናሳ አሳውቋል።

የአውስትራሊያ ሰደድ እሣት ከ10 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ያቃጠለ ሲሆን 27 ሰዎችን ገድሏል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዱር እንሳስትም ሰለባ ሆነዋል። 2 ሺህ ገደማ መኖሪያ ቤቶች ደግሞ ዶጋ አመድ ሆነዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች የአውስትራሊያ ሰደድ እሣት የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ማሳያ ነው ይላሉ።

ናሳ የሰደድ እሣቱ ጭስ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ከእሣት የሚፈጠር መብረቅ መሥራት ችሏል ይላል። ጭስ በጣም ኃያል ከመሆኑ የተነሳ ከመሬት ወደ ሰማይ 17̌ ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ተጉዞ ስትራቶስፌር የተሰኘው የሰማይ ክፍል ላይ መስፈር ችሏል።

ተቋሙ፤ ጭሱ ወደ ሰማይ ከተመዝገዘገ በኋላ ሙቀት ወይስ ቅዝቃዜ ፈጠረ የሚለውን ለማወቅ ጥናት ላይ መሆኑንም አሳውቋል።

የደቡብ አሜሪካ ሃገራትና የአህጉረ-አውስትራሊያ አካል የሆነችው ኒው ዚላንድ በአውስትራሊያ ሰደድ እሣት ምክንያት ሰማያቸው ታፍኖ እንደነበር የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች የማሕበራዊ ድር-አምባ ተጠቃሚያዎች አጋርተዋል።

ኒው ዚላንድን ጨምሮ ሲድኒ፣ ሜልቦርን፣ ካንቤራ እና አደላይድን የመሳሰሉ ትላልቅ የአውስትራሊያ ከተሞች በሰደድ እሣቱ ምክንያት ንፁህ አየር መተንፈስ ተስኗቸው ሰንብተዋል።

አውስትራሊያ አሁንም እየተቃጠለች ነው። 100 ገደማ ጫካዎች አሁን እሣት ይዟቸዋል። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጣለ ያለው ዝናብ ሁኔታዎችን ቀዝቀዝ አድርጓቸዋል።

ጭሱ ግን መጓዙን እንደሚቀጥል ናሳ አሳውቋል። አፍሪቃን ጨምሮ ሁሉንም የዓለማችን አህጉሮች ሊነካ ይችላልም ተብሏል። የአውስትራሊያን ጭስ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እናየው ይሆን?