የቀለጠ አለት የሚተፋው የፊሊፒንስ እሳተ-ገሞራ አደጋው የከፋ እንደሆነ ተገምቷል

ፊሊፒንስ ውስጥ የፈነዳው እሣተ-ገሞራ የቀለጥ አለት መትፋት መጀመሩንና አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል የሃገሪቱ ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

አሣተ-ገሞራው ከፊሊፒንስ ዋና ከተማ ማኒላ 70 ኪሎሜትር ራቅ ብሎ 'ታል' በመባል ከሚታወቀው ሥፋራ ከሚገኝ ተራራ ነው አለቱ በመቅለጥ ላይ ያለው።

በአካባቢው የሚኖሩ 8 ሺህ ገደማ ሰዎች እሣተ-ገሞራው በተፋው አመድ ምክንያት ከአካባቢው እንዲርቁ ተደርገዋል።

ታል ፊሊፒንስ ውስጥ ከሚገኙ እሣተ-ገሞራዎች ብዙ ጊዜ በመፈንዳት ሁለተኛው ነው።

አንድ ሐይቅ መሃል ላይ ጉብ ያለው ይህ እሣተ-ገሞራ ባለፉት 450 ዓመታት ቢያንስ 34 ጊዜ ፈንድቷል።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እሣተ-ገሞራው ሱናሚ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ይህ ደግሞ የሚፈጠረው እሣተ-ገሞራው የሚገፍትራቸው ግዙፋ አለቶች ወደ ሐይቁ ተመዘግዝገው ወርደው በሚፈጥሩት ማዕበል ነው።

እሁድ ዕለት እሣተ-ገሞራው ሲፈንዳ አካባቢው በአመድ ከማፈኑም በላይ አስደማሚ ድምፅ ተመስቷል፤ መብረቅም ወርዷል።

ታል በሚባለው የሚታወቀው ሥፍራ በእሣተ-ገሞራ የታወቀ ሲሆን በጠቅላላው 75 ጊዜ ገሞራ መፈንዳቱን የአካባቢው ባለሥልጣናት መዝግበው አስቀምጠዋል።

የተባባሩት መንግሥታት ከአካባቢው 14 ኪሎ ሜትር ርቀው የሚኖሩ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች አደጋ ላይ ናቸው ይላል።

የታል ሰዎች እሣተ-ገሞራው የሚለቀው አመድ እንዳያፍናቸው በማለት ጭምብል አጥለቀው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።