''ማን ይለቀቅ ፤ ማን አይለቀቅ እስካሁን አላወቅንም'' የታጋች ቤተሰቦች

በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ በታጣቂዎች የታገቱ 21 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መለቀቃቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ትናንት አስታውቋል።
በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት መከሰቱን ተከትሎ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሄድ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ጫካ ውስጥ ታግተው መቆየታቸውን የፅ/ቤቱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ተናግረዋል።
ታግተው ከነበሩ ተማሪዎች ውስጥ 13 ሴትና 8 ወንድ በድምሩ 21 ተማሪዎች የተለቀቁ ሲሆን አሁንም ቀሪ 5 ተማሪዎችና አንድ የአካባቢው ተወላጅ ታግተው እንደሚገኙና በአካባቢው የፀጥታ ኃይል መሰማራቱን ኃላፊው አክለዋል።
ኃላፊው ይህንን ይበሉ እንጅ፤ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገና እህቱ እንደታገተችበት የነገረን አንድ ግለሰብ ግን አሁንም ድረስ እህቱም ሆነች ሌሎቹ ተማሪዎች በምን አይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃው እንደሌለው ነግሮናል።
''እህቴ እስካሁን አልደወለችልኝም፤ ማንም የደወለልኝም ሰው የለም። ተማሪዎች ተለቅቀዋል የሚለውን ዜና ከሰማሁ በኋላም ሌሎች ልጆቻቸው የታገቱባቸው ቤተሰቦች ጋር በስልክ ተገናንኝተን ነበር፤ እነሱም እስካሁን ምንም መረጃ የላቸውም'' ብሏል።
አክሎም ''እኔም ደወልኩላቸው፤ እነሱም ደወሉልኝ። ነገር ግን ማንኛችንም ተማሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ ከመንግሥትም ሆነ ከተማሪዎቹ ራሳቸው የተነገረን ነገር የለም'' ብሏል።
''ትናንት ተማሪዎች ተለቅቀዋል የሚለውን ዜና ስንሰማ በጣም ደስ ብሎናል። ነገር ግን የተለቀቁ ተማሪዎች ዝርዝር ስላልታወቀ ግራ ገብቶናል። በጣም ደስ ቢለንም ማን ይለቀቅ ማን ይቅር ስላላወቅን አስቸጋሪ ሆኖብናል።''
ለሁለት ሳምንታት ከእህቱ ጋር በስልክ ሲገናኙ ስለአወሩት ነገር ጠይቀነው ''በደወሉ ቁጥር ቦታው ምን ይመስላል? ንገሩን ወይ እራሳችን ወይ ፖሊስ እንዲመጣ ስንላቸው ማውራት አንችልም፤ አጠገባችን አሉ ይሉን ነበር። በተጨማሪ ደግሞ ማታ ላይ ለሁለት ወይም ለሶስት ሰዓታት ያክል በጫካ ውስጥ እንድንጓዝ ያደርጉናል ብላኝ ነበር'' ብሎናል።
''ከዋልንበት አናድርም፤ ካደርንበት አንውልም። ሁሌም ማታ ማታ እንጓዛለን'' የሚል ምለሽ ትሰጠው እንደነበር ያስታውሳል።
ሌላኛዋ ያነጋገርናትና ወንድሟ ከታጋች ተማሪዎች መካካል አንዱ እንደሆነ የነገረችን ወጣትም እስካሁን ተለቀቁ የተባሉት ተማሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የሰማችው ነገር እንደሌለ ትናገራለች።
''ትናንት ዜናውን ከሰማንበት ሰዓት ጀምሮ በጉጉት እየተጠባበቅን ነበር፤ ነገር ግን እስካሁን ወንድሜም አልደወለም፤ ሌላ የደወለልኝም አካል የለም'' ብላለች።
''ሌሎች የቤተሰብ አባሎቻቸው ከታገቱባቸው ጋር እንገናኛለን፤ እነሱም ቢሆኑ እስካሁን የሰሙት ነገር እንደሌለ ነግረውኛል። ማን እንደተለቀቀና ማን እንዳልተለቀቀ ይነግሩናል ብለን ብንጠብቅም እስካሁን ምንም ነገር የለም'' የታጋች እህት የሰጠችው ምላሽ ነው።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የታገቱት ተማሪዎች ስለተለቀቁበት ሁኔታ እና አሁን የት እንደሚገኙ የጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
"ከታገቱት መካከል አንዷ ነበርኩ፤ በሦስተኛ ቀኔ አምልጫለሁ" ተማሪ አስምራ ሹሜ
ተማሪ አስምራ ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነበረች። የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ታስረዳለች።
"በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የኢንጅነሪንግ ተማሪ ነበርኩ። አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በመዘጋቱ ወደ ትውልድ አካባቢዬ ተመልሼ አዲስ ዘመን ከተማ ነው ያለሁት።
ከታገቱት ተማሪዎች መካከል አንዷ ነኝ። መጀመሪያ በአጋቾቹ የተያዝነው 18 ተማሪዎች ነበርን። እኔ ማምለጥ ስለቻልኩ አሁን ታግተው ያሉት ተማሪዎች ቁጥር 17 ነው። ከእነዚህ መካከል 4ቱ ወንዶች ሲሆኑ 13ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው። አሁን ታግተው ያሉት ተመራቂ ተማሪዎች እና የኢንጅነሪንግ አንደኛ ዓመት ተማሪዎች ናቸው።
በወቅቱ በደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ስለነበር ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ወጥተው ነበር። እኛም መውጣት አሰብን ወደ አዲስ አበባ በቀጥታ የሚያስመጣው ዋና መንገድ በመዘጋቱ ከደምቢ ዶሎ በጋምቤላ በኩል አድርገን አዲስ አበባ ለመግባት ወሰንን።
ሁላችንም ከአማራ ክልል አካባቢዎች የመጣን ተማሪዎች ነን።
ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ የ30 ብር ትራንስፖርት ሲሆን እቅዳችን ጋምቤላ አድረን ወደ አዲስ አበባ ነበር። ነገር ግን ያሰብነው ቦታ ሳንደርስ ደምቢ ዶሎ እና ጋምቤላ መካከል 'ሱድ' የምትባል ቦታ ላይ ስንደርስ መኪናውን አስቁመው፤ ወጠምሻ ወጣቶች መጥተው አፈኑን። የአፋኞቹ ቁጥር ከእኛ ቁጥር በላይ ነበር።
አካባቢው ጥቅጥቅ ያለ ጫካ በመሆኑ በእርሱ ውስጥ ይዘውን ገቡ። ይዘውን ሲሄዱ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ከማየት ውጭ ለማስጣል የሞከረ አልነበረም።
እየጮህን ነው ይዘውን የሄዱት። የጫካውን ግማሽ እንደተራመድን የተወሰኑት ሴቶች መራመድ አቃታቸውና ወደቁ። ታዲያ እነርሱን 'ተነሱ፤ አትነሱ' እያሉ ለማንሳት ሲሞክሩ ነበር እኔ ከአይናቸው የተሰወርኩት።
በጫካው ውስጥ ለሁለት ቀናት ያህል ካደርኩ በኋላ፤ በሦስተኛው ቀን ወደ ዋናው የመኪና መስመር መውጣት ቻልኩ። ግራ ተጋባሁ፤ ስልኬን ስለወሰዱት ስልክ መደወል አልቻልኩም፤ ምንም ማድረግ አልቻልኩም ነበር።
እንደምንም ብዬ ወደ መስመር ስወጣ አንድ አማርኛ በትንሹም ቢሆን መናገር የሚችሉ አባት አገኘሁ። እርሳቸው እንዳዩኝ 'የእኔስ ልጆች እንዲህ አይደል የሚሆኑት' ብለው በማዘን ኮታቸውን አለበሱኝ።
'ከታየሁ እኔም እገደላለሁ' ብለው ደብቀው አስቀመጡኝ። 'የት ነው መሄድ የምትፈልጊው' አሉኝ። 'ደምቢ ዶሎ ለፌደራል ፖሊሶች ስጡኝ' አልኳቸው። ከዚያም መኪና ለምነው አሳፍረው ላኩኝ። መረጃውንም ለፌደራል ፖሊሶቹ ተናግሬያለሁ። ፌደራል ፖሊሶቹ 'ቦታው እንኳን ለተማሪ ለወታደርም አስጊ ነው፤ እንከታተላለን' አሉኝ።
ከታገቱት መካከል አንዷ ጓደኛዬ መጀመሪያ አካባቢ ስልክ እየሰጧት ትደውልልኝ ነበር። ለማውራት ብዙም ነፃነት ባይኖራትም 'በጣም እያሰቃዩን ነው፤ ምግብም ሲያሻቸው ይሰጡናል፤ ሲፈልጉ ደግሞ ይከልክሉናል' ስትል ነግራኛለች። የምትደውልበትን ስልክ 'የእነርሱ ነው ያዥው' ብላኝ ነበር። ከዛን ቀን በኋላ ግን አይሰራም፤ እነርሱም ደውለው አያውቁም፤ እኛም አግኝተናቸው አናውቅም።
ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት፤ ለአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፀጥታ እና ደህንነት መረጃውን ሰጥቻለሁ፤ ጠይቄያለሁ። 'እንከታተላለን' ነው ያሉኝ።
ከዚያ መምጣቴን የሚያውቁ የተማሪዎቹ ወላጆችም ያለሁበት ድረስ እየመጡ ያለቅሳሉ፤ እኔ ግን 'መንግሥት ይዟቸዋል፤ አሁን ይመጣሉ' እያልኩ ከማረጋጋት ውጭ የማደርገው ጠፍቶኛል።"
የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ምን ይላሉ?
ተማሪዎቹ ተለቀዋል የሚለው ዜና ከመሰማቱ በፊት ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸውን ለልጆቹ ደህንነት ስንል ያልጠቀስናቸው የታገቱት ተማሪ ቤተሰቦች፤ ተማሪዎቹ ከታገቱ አንድ ወር እንዳለፋቸው ይናገራሉ። "በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ስልክ ይደውሉ ነበር፤ አሁን ግን ድምፃቸውን ከሰማን ሦስት ሳምንታት አልፈዋል" ይላሉ።
እህቱ እንደታገተችበት የነገረን አንድ ግለሰብ፤ በዩኒቨርሲቲው ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ሲወጡ፤ እርሱም እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ቢነግራቸውም እነርሱ ግን ከአሁን አሁን ይረጋጋል እያሉ መቆየታቸውን ያስረዳል።
ይህ ግለሰብ እንደሚለው ስልክ ተደውሎለት እህቱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎች ስለመታፈናቸው የሰሙት ሕዳር 24፣ 2012 ዓ.ም ነው።
ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ በነበሩት ሁለት ሳምንታት በተማሪዎቹ ስልክ ከዚያ በኋላ 'የአጋቾቹ ነው' ባሏቸው ስልክ ይደውሉላቸው ነበር። ቦታውን ሲጠይቋቸው ግን እንደማያውቁት ነበር ሲነግሯቸው የቆዩት።
"የሆነ ሰዓት ላይ ስልክ ተሰጥቷት የፅሁፍ መልዕክት ላከችልኝ፤ ''አሻና አፋን ገደራ' የሚባል ቦታ ነው ያለነው፤ ለመከላከያ ደውሉና እዚህ አካባቢ ይፈልጉን' ብላ ፃፈችልኝ" ይላል።
በመጨረሻው የስልክ ልውውጣቸው፤ "አሁንም እዚያው ቦታ ነሽ ወይ?" ብሎ ሲጠይቃት "በፊት ቢሆን ጥሩ ነበር፤ አሁን ቦታ ቀይረናል፤ ሌሊት ሌሊት ደግሞ የሁለት የሦስት ሰዓት መንገድ በጫካ እንጓዛለን፤ አታገኙንም፤ አሁንም ልትንቀሳቀሱ ነው ተብለናል፤ እስካሁን ባለው ደህና ነን'' ስትል ስልኩን ከዘጋች ወዲህ እህቱን በስልክ ማግኘት እንዳልቻለ ይናገራል።
ከታጋች ተማሪዎች ወላጆች መካከል ሁለት ሰዎች፤ ስለ ልጆቻቸው መረጃ ፍለጋ ወደ ደምቢ ዶሎ ተጉዘው እንደነበረ ይሄው እህቱ የታገተችበት ወንድም ይናገራል።
እሱ እንደሚለው ወደ ሥፍራው የሄዱት ሰዎች ከዩኒቨርሲቲውም ሆነ ከሚመለከታቸው የክልሉ መንግሥት ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።
ሌላኛዋ የታጋች ተማሪ እህት እንደነገረችን፤ ቀደም ብሎ በዩኒቨርሲቲው አንድ የአማራ ተወላጅ ተማሪ መገደሉን ተከትሎ ወንድሟ ከፍተኛ ስጋት አድሮበት እርሷ ጋር ደውሎ ገንዘብ እንድትልክለት መጠየቁን ታስታውሳለች።
"የደወለው ቅዳሜ ቀን ስለነበር እስከ ሰኞ እንዲታገስ ነገርኩት፤ ሰኞ ዕለት ብር ልልክለት ስደውል ስልኩ አይሰራም። በማግስቱ ደውሎ መያዛቸውን ነገረኝ። ከተያዙ ጀምሮ ሁለት ሳምንታት ድረስ ይደውሉ ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ድምፃቸው አልተሰማም" ትላለች።
እስካሁን የምንችለውን ነገር ሁሉ እያደረግን ነው የምትለው የተማሪው እህት፤ በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የምታገኛቸው የታጋች ወላጆች በከፍተኛ ሃዘንና ጭንቀት ላይ እንደሚገኙ ትናገራለች።
"አንጀታቸውን በገመድ አስረው መሬት ላይ ተኝተው ይፀልያሉ፤ 'ሞተው ከሆነ አስክሬናቸው ይምጣልን'" እያሉ ነጋ ጠባ እያለቀሱ ነው" ትላለች።
ተማሪዎቹ ላይ ወሲባዊ ጥቃት እንደሚፈፀምባቸውና እየተሰቃዩ እንደሚገኙ መስማታቸውንም አክላለች።
የአጋቾቹ ፍላጎት ምንድነው?
ወንድሟ የታገተባት እህት ከወንድሟ ባገኘችው መረጃ መሠረት አጋቾቹ ገንዘብ አይፈልጉም።
ከአጋቾቹ እጅ ያመለጠችው አስምራ እንደምትናገረው፤ አጋቾቹ በተደጋጋሚ "ከእናንተ ጋር ጸብ የለንም። ጸባችን ከመንግሥት ጋር ነው" እንደሚሉ ትናገራለች።
አጋቾቹ "የአማራ ሕዝብ ልጆቻችን ታግተዋል ብሎ ሰልፍ ሲወጣ፤ መንግሥት እኛን ያነጋግራል። የዛኔ እኛ ጥያቄያችንን ለመንግሥት እናቀርባለን፤ ጥያቄያችንም ይመለሳል" እንዳሉ አስምራ ገልፃልናለች።
የመንግሥት አካላት ምላሽ?
ኦሮሚያ
ቅዳሜ ጥር 2/2012 ዓ.ም. ያነጋገርናቸው የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ በምዕራብ ኦሮሚያ ስላለው ጠቅላላ ሁኔታ "ምንም አይነት መረጃ የለኝም። እኔ የሰማሁት ነገር የለም" ይላሉ።
ጉዳዩ እርሳቸው የሚመሩትን ቢሮ በቀጥታ የሚመለከት መሆኑን በመጥቀስ ስለጉዳይ እንዴት መረጃ ሳይኖራቸው እንደቀረ የተጠየቁት ኮሎኔል አበበ ገረሱ፤ "እኔ ምንም አልሰማሁም ነው የምልህ። ለምድን ነው የምትጠይቀኝ?" በማለት መልሰዋል።
የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በበኩላቸው ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎች የሉም ብለዋል።
ኃላፊው "ታፍኖ የተወሰደ ተማሪ የለም" ከማለት ውጪ ማብራሪያ መስጠት አልፈለጉም።
አማራ
በዕለቱ ያነጋገርናቸው የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘው ተሻገርም፤ "አሁን ማውራት የማልችልበት ቦታ ነው ያለሁት" በማለት የእጅ ስልካቸውን ዘግተውታል። አቶ አገኘው ተሻገርን መልሰን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከአምስት ቀናት በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ "አራት ተማሪዎች ታግተው እንደሚገኙ መረጃው አለኝ" ማለታቸው ይታወሳል።
ርዕሰ መስተዳደሩ ተማሪዎቹ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ከአባ ገዳዎች፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት እያደረግንም ነው ብለው ነበር።












