ፍርድ ቤት እየሄደች ሳለ በእሳት የተቃጠለችው ሕንዳዊት ሞተች

አስገድዶ በደፈራት ግለሰብ ላይ ምስክርነት ለመስጠት ወደ ፍርድ ቤት እየሄደች ሳለች በእሳት የተቃጠለችው ሕንዳዊት ሕይወቷ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አስገድደው ደፍረውኛል ብላ በከሰሰቻቸው ግለሰቦች ላይ ምስክርነት ለመስጠት ወደ ፍርድ ቤት እየሄደች ሳለች በእሳት የተቃጠለችው ሕንዳዊት ሕይወቷ አለፈ።

የ23 ዓመቷ ሕንዳዊት፤ ባለፈው ሳምንት ሀሙስ ወደ ፍርድ ቤት እየሄደች ሳለ ነበር በእሳት የተቃጠለችው።

በሰሜናዊ ሕንድ ኡናዎ የተባለች ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ሁለት ወንዶችን በአስገድዶ መድፈር የከሰሰችው ሕንዳዊት፤ የእሳት ቃጠሎ ከደረሰባት በኋላ በደልሂ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተለች ነበር።

የአገሪቱ ፖሊስ እንዳለው፤ ተከሳሾቹን ጨምሮ አምስት ወንዶች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የሟቿ እህት፤ ቤተሰባቸው ክሱን እንደሚገፋበት እና ተጠርጣሪዎቹ በሞት እንዲቀጡ እንደምትፈልግም ለቢቢሲ ገልጻለች።

ከሰባት ዓመት በፊት፤ በሕንዷ መዲና ደልሂ፤ አንዲት ወጣት አውቶብስ ውስጥ በቡድን ተደፍራ ከተገደለች ወዲህ በአገሪቱ ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት የበርካቶች መነጋገሪያ ቢሆንም፤ የተጠቂዎችን ቁጥር መቀነስ አልተቻለም።

መንግሥት እንደሚለው፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2017 ብቻ 33,658 ሴቶች ተደፍረዋል። በዚህ አሀዝ መሰረት በቀን በአማካይ 92 ሴቶች ይደፈራሉ።

ከዚህ ቀደም፤ የሕንድ ገዢ ፓርቲ አባልን በአስገድዶ መድፈር የከሰሰች ሴት በመኪና አደጋ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ይታወሳል። ሁለት አክስቶቿ የተገደሉ ሲሆን፤ ጠበቃዋም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ፖሊስ በግለሰቡ ላይ የግድያ ክስ ከፍቷል።

ባለፈው ሳምንት በደቡባዊ ሕንድ በምትገኘው ሀይደርባድ ግዛት፤ አንዲት የእንስሳት ሀኪምን ደፍሮ በመግደል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በፖሊስ ተገድለዋል። የተጠርጣሪዎቹ መገደል ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።