“ኦዲፒ ዋጋ የተከፈለባቸውን ጥያቄዎች ወደ ጎን መተው አይገባውም” ፕ/ር መረራ ጉዲና

የፎቶው ባለመብት, OPDO - Official
የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትርና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ፤ የኢሕአዴግን ውህደት እንደማያምኑበት ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ገልፀዋል።
"መዋሀዱ ትክክል አይደለም። ከሆነም በችኮላ መሆን የለበትም፤ ወቅቱም አይደለም" ያሉት አቶ ለማ፤ በመደመር ፍልስፍናም እንደማይስማሙ ከራድዮ ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ መናገራቸው ተዘግቧል።
አቶ ለማ፤ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የፓርቲዎችን ውህደት ባፀደቀ ጊዜ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው እንደነበር አስታውቀው ስለ ሂደቱ ግን ለጣቢያው ከማብራራት ተቆጥበዋል።
አቶ ለማ መደመርን የተቃወሙበትን ምክንያት ለቪኦኤ ሲያስረዱም፤ በአጠቃላይ ከመጀመሪያ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ድረስ የፓርቲዎች ውህደትን በተመለከተ የተለየ ሀሳብ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ይህንንም ለሥራ አስፈጻሚውና ለሁሉም መናገራቸውን መግለፃቸው በጣቢያው ላይ ተላልፏል።
አቶ ታየ ደንደኣ ስለ ብልፅግና ፓርቲ አመሠራረት ሂደት፣ ፋይዳዎቹና የአቶ ለማ በውህደቱ አላምንም ማለትን አስመልክተው ከኤስቢኤስ አማርኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማድረጋቸውን በፌስቡክ ገፁ ላይ አስነብቧል።
የሚፈልጉት ይዘት የለም
በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.የ Facebook ይዘት መጨረሻ, 1
ሬዲዮው አክሎም አቶ ታዬ፣ "አቶ ለማ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ውህደቱ አስፈላጊ እንደሆነና የመደመር ዕሳቤ ከኢትዮጵያ ዐልፎ ለምሥራቅ አፍሪካም ጠቃሚ ሃሳብ እንደሆነ ተስማምተው ነው ያጸደቁት፤ የልዩነት ሃሳብ አልሰማንም። ከዚያም አልፎ በኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴና ጉባኤ፣ በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ የተለየ አቋም አላንጸባረቁም። በዚህ መሄድ አለብን የሚል የተለየ አማራጭ ሃሳብም አላቀረቡም" ማለታቸውን አስታውቋል።
ይህንን የአቶ ለማ አቋም አስመልክተን ያነጋገርናቸው በዋሺንግተንና ሊ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ሔኖክ ገቢሳ (ዶ/ር) ውህደት ብለን የምንናገር ከሆነ ለዚች አገር ከፍተኛ ውለታ ዋሉ እንደ አቶ ለማ መገርሳ ያሉትን ሰዎች እየቀነስን ውህደቱን እውን ማድረግ አስቸጋሪ ነው ብለውናል።
ዶ/ር ሔኖክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሰዎችን፣ ሀሳባቸውንና እምነታቸውን ሳያካትቱ ውህደቱን ማካሄድ ከባድ ይሆናል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ፣ ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት 'ለዐቢይ ትልቁ ተግዳሮት የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝቦችን መርቶ ማሻገር ሳይሆን ኢህአዴግን እንደ ኢህአዴግ መርቶ መሻገር መቻልና አለመቻል ላይ ይመሰረታል' ማለታቸውን በማስታወስ፣ በአሁኑ ሰዓትም በግንባሩ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች መጠላለፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖበታል ብለው እንደሚያምኑ ይገልጻሉ።
"ከዚህም የተነሳ እንደሚፈለገው አብሮ ወደፊት መሄድ አልቻሉም" በማለት የእርሳቸው ፓርቲ ኢህአዴግ ተዋሀደም አልተዋሀደም የሚጠብቅበት ነገር እንዳለ አጽንኦት ሰጥተው ያስረዳሉ።
በውህደቱ ላይ አቶ ለማ እንደማይስማሙ በተባራሪ ወሬ ሲሰሙ መቆየታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ሔኖክ ደግሞ፤ እንዲህ ዓይነት መከፋፈል በአሁኑ ሰዓት መፈጠር አልነበረበትም ብለው እንደሚያምኑ ያስረዳሉ።
ለዚህም ምክንያት ነው ያሉትን ሲጠቅሱም፤ "በእነርሱ መካከል በሚፈጠር አለመግባባት የኦሮሞ ትግል መከፋፈል የለበትም ብዬ ስለማምን ነው" ብለዋል።
"አቶ ለማም ሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ትልቅ ውለታ የዋሉ ሰዎች ስለሆኑ ሃሳባቸውን ወደ አንድ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል" በማለትም፤ "የኦሮሞን ሕዝብ ጥያቄ እንመልሳለን ብለው ካመኑ፤ የኦሮሞ ሕዝብ መሪዎች ነን ብለው ካሉ፤ መደማመጥ አስፈላጊ ነው" ሲሉ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።
የኢትዮጵያ መሪዎች ዲሞክራሲን አንገነባለን ሲሉ ተቃራኒ ሀሳቦችንም ማስታገድ አለባቸው ብዬ አምናለሁ የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ አሁንም ያለመግባባት መንስዔ የሆነው የውህደት ውሳኔ እንደገና መታየት አለበት ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አቶ ለማ ኦዲፒን ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በማስታረቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም በማንሳት፤ የእርሳቸው አቋም የደጋፊዎቻቸውንም አቋም እንደሚለውጠው ዶ/ር ሔኖክ ይገልጻሉ።
ከዚህም በመነሳት የአቶ ለማ አስተያየት ወደኋላ ከተተወ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ዶ/ር ሔኖክ "ለማ መገርሳን የቀነሰ መደመር፣ መደመር አይሆንም" ሲሉም አስረድተዋል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዶ/ር ዐቢይ ይህንን የሚቀበሉ አይመስሉም የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ የኦሮሞና ሌሎች የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ እንዲመለስ የሚፈልጉ ከሆነ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ የግድ በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ያሰምሩበታል።
'ፖለቲካ የሰጥቶ መቀበል ጥበብ ነው'
"ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይና አቶ ለማ አንድ ባህል እና አንድ ቋንቋ ኖሯቸው፣ ለተመሳሳይ ሕዝብ እየታገሉ፣ በመግባባት አብሮ መሥራት ካቃታቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ አስቸጋሪ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል ዶ/ር ሔኖክ።
ይህ ትግል እዚህ የደረሰው በኦሮሞ ልጆች ደምና በሕዝቦች መስዋዕትነት ነው ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ፓርቲው ዋጋ የተከፈለባቸውን ጥያቄዎችን ወደ ጎን መተው አይገባውም ይላሉ።
ፖለቲካ በራሱ የሰጥቶ መቀበል ጥበብ ነው የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ በበኩላቸው፤ በፖለቲካ አካሄድ ውስጥ መደማመጥና ሚዛን ለሚደፋ ተፎካካሪ ሀሳብ መሸነፍ ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።
ውህደት የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ የሚመልስ እስከሆነ ድረስ ምንም ችግር የለበትም የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ ይሁን እንጂ አዲሱ መዋቅር እንደ ሕዝብ ለሚነሱ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ይሰጣል መባሉ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራሉ።
በመሆኑም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባትን ለማምጣት፣ ቆም ብለው ግልፅና ፍትሀዊ የሆነ ምክክር ከአቶ ለማ ጋር ቢያደርጉ የበለጠ ጠቀሜታ አለው ብለው እንደሚያምኑ አብራርተዋል።
አለመግባባቱ ቢቀጥል ምን ሊፈጠር ይችላል?
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መካከል በተከሰተው አለመግባባት፣ ስለወደፊቱ የሀገሪቱ ሁኔታ ፓርቲያቸው ስጋት እንዳለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ፣ "እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም ሰፍኖ፣ ሕዝቦች በቀያቸው እኩል ባለቤትነት ኖሯቸው ትግላችንን ግብ እስኪመታ ድረስ መስጋታችን አይቀርም" ብለዋል።
የአገሪቱን ፖለቲካ በሚፈለገው ፍጥነት ወደፊት ለማስኬድ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መካከል ያለው መግባባት ወሳኝ ነው የሚሉት ዶ/ር ሔኖክ፤ ይህንንም መግባባት ለማምጣት ትልቁ ሚና የሚጠበቀው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ይናገራሉ።
በመካከላቸው መግባባት ባይፈጠር ግን የአገሪቱ ፖለቲካ ወዳልተፈለገ ጎዳና ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አልሸሸጉም።
ይህንንም ሲያብራሩም፤ "ምናልባትም አቶ ለማ ሥልጣን ወደ መልቀቅ እርምጃ ሊያመሩ ይችላሉ" በማለት፤ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሩ ወደ ተቃዋሚነት ተሸጋገሩ ማለት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ከዚህም በተጨማሪ አቶ ለማ የተቃዋሚነትን አቋም የሚከተሉ ከሆነ በእርሳቸው አመራር የሚያምኑ አካላት ስላሉ ትልቅ የፖለቲካ ክፍፍል ይፈጥራል ብለዋል።
ይህም በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ላይ የራሱ ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ። በተለይም በመጪው ምርጫ ላይ የሕዝብ ድምጽ መከፋፈልን ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው በዚህ ወሳኝ ሰዓት ሁሉም የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ቄሮ በተረጋጋ መንፈስ አብሮ ሊቆም ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የብልፅግና ፓርቲ ፅ/ቤት ሃላፊዎች በወቅታዊ የፓርቲው ሁኔታ ላይ እየመከሩ መሆኑን የኢህአዴግ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ ላይ ተጽፏል።
የሚፈልጉት ይዘት የለም
በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.የ Facebook ይዘት መጨረሻ, 2
የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ እንዲሁም የኦዲፒ አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ደጋግመን የሞከርን ቢሆንም ለጊዜው ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፤ ነገር ግን ምላሻቸውን እንዳገኘን የምናካትት መሆንን መግለፅ እንወዳለን።
















