ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስህተት ላልታሰበ ሰው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ተደረገ
የኒውጀርሲ ሆስፒታል በስም መመሳሰል ለአንድ ሰው በስህተት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማድረጉን ያወቀው ቀዶ ህክምናው በተደረገ በማግስቱ ነበር።
ስለዚህም ንቅለ ተከላ ለማድረግ ቀጠሯቸውን ሲጠብቁ የነበሩት ዋናው ታካሚ ከሳምንት በኋላ ህክምናውን ሊያደርጉ ግድ ሆኗል።
በመጨረሻም በተፈጠረው ስህተት ተመሳሳይ ስም ላላቸው ሁለቱም ሰዎች ንቅለ ተካላ እንደተደረገና ሁለቱም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ሆስፒታሉ አስታውቋል።
የህክምና ስህተቱ የተፈፀመበት ቬርቹዋ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሬጅናልድ ብላበር እንደዚህ ዓይነት ስህተት በጣም ያልተለመደ እንደሆነ ገልፀው፤ ከስም ባሻገር የታካሚዎቹን መረጃ በደምብ በማጣራት ስህተቱ እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻል እንደነበር ተናግረዋል።
በቀጣይ እንደዚህ ዓይነት ስህተት እንዳይፈፀምም ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እንደጀመሩም ጠቁመዋል።
በሆስፒታሉ 113 ሺህ ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ያለ ሲሆን፤ ከነዚህ 95 ሺህ የሚሆኑት ኩላሊት እስኪገኝላቸው ተራ በመጠበቅ ላይ እንደሆኑ ሆስፒታሉ አስታውቋል።
ሆስፒታሉ እስካሁን የታካሚዎቹን ስም ይፋ አላደረገም።
በስህተት ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው የ51 ዓመቱ ግለሰብ ስም ምንም እንኳ ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ህመምተኞች ዝርዝር ውስጥ ቢኖርም ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ኩላሊት እየተፈለገላቸው ካሉት 95 ሺህ ሰዎች መካከል አልነበሩም።