"መንገድ መዝጋት የኋላ ቀር ፖለቲካ ውጤት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ

የፎቶው ባለመብት, FANA TV
ዛሬ ጥቅምት 11፣ 2012 ዓ. ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ስለ ምርጫ፣ ስለ ፌዴራል ሥርዓቱ፣ ሙስና፣ ሚዲያ፣ ፀጥታና ደህንነት፣ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና ሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላቱ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫን በሚመለከት ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ "በዘንድሮም ምርጫ ይሁን በሚቀጥለው ምርጫ ተግዳሮት የሌለው ምርጫ ማድረግ አይቻልም" በማለት ምርጫው ይራዘም የሚለው እንደማያስኬድ ተናግረዋል።
መንግሥት በቂ በጀት ለምርጫ ቦርድ መመደቡን እንዲሁም የቦርዱ አባላትም ከማንኛውም ጊዜ የተሻለ ነፃ ነው የሚያስብል እንደሆነም በመጥቀስ ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ምርጫ ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
"የመንግሥት ፍላጎትም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግሥት ዝግጁነትም ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
መንግሥት፣ ሕዝብ እና ምርጫ ቦርድ ተባብረው የተሻለ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።
በምርጫ ሕጉ ላይ ቅሬታ ያላቸው ፓርቲዎች ያቀረቡት ቅሬታ አግባብ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ሰብሰብ ማለት ለሁላችንም ያስፈልጋል" ብለዋል።
"ምርጫውን ማድረግ በብዙ መልኩ ይጠቅመናል፤ ፈተና አልባ ምርጫ ባይሆንም የተሳካ ምርጫ ማድረግ ይቻላል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢህአዴግ በውስጡ ያለውን ቅሬታ በሚመለከትም ሲናገሩ "ኢትዮጵያ የኢህአዴግ አባት እንጂ፤ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ አባት አይደለም" በማለት እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚል አስተሳሰብ ትክክል ያልሆነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ኢህአዴግ ውስጥ ላለፉት 5 እና 10 ዓመታት ውህደቱ ውይይት ሲደረግበት መቆየቱን አስታውሰው፤ ውህደት እንዲፈፀም በሀዋሳው ጉባኤ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን አስታውሰን "እየተወያየን ነው" ብለዋል።
ውህደቱ ጊዜው አሁን አይደለም የሚሉ ፓርቲዎችና አባላት ቢኖሩም እስካሁን ግን ውህደቱ አያስፈልግም ያለ አካል ሰምተው እንደማያውቁ ተናግረዋል።
በክልሎች መካከል ያለውን ፀጥታ በተመለከተም፤ የትጥቅና የቃላት ፉክክር እንደሚታይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "የውጊያ ቀስቃሾች ሁል ጊዜም አንድ ዓይነት ናቸው" በማለት በየጊዜው ግጭት እየቀሰቀሱ በዚያ ውስጥ መኖር የሚፈልጉ አሉ በማለት ወጣቶች እንዲነቁ መክረዋል።
የትግራይ ክልልን እየመሩ ያሉ አመራሮች የክልሉን ችግር መፍታት እንጂ ከአማራ ክልል ጋር መዋጋት አይፈልጉም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በመካከል የድራማው አካል የሆኑትን የመለየት ችግር ነው ያለው" ብለዋል።
የክልሎች ትጥቅ በሀገር ደረጃ የሚያሰጋ አይደለም በማለት ክልሎች መዘጋጀት ያለባቸው የራሳቸውን የክልል ውስጥ ደህንነት ለመጠበቅ እንጂ ከሌሎች ክልሎች ጋር ለመጋጨት መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥት የሚችለውን እያደረገ እንደሚሄድ ጠቅሰው በአማራና ቅማንት፣ በሶማሌና በአፋር መካከል የሦስት ቀበሌ ችግር ነው ያለው በማለት ችግሩን የፈጠሩት ሌሎች ናቸው ማለት የሚለው ስለማያዋጣ ኃላፊነት ወስዶ መሥራት ይጠይቃል ሲሉ አሳስበዋል።
"መንገድ መዝጋት የኋላ ቀር ፖለቲካ ውጤት ነው።" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፈጠረው ነገር የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል።
"የሚያባሉን እድሜ ጠገብ ሰዎች ናቸው" በማለት ባይሎጂም [ሥነ ሕይወትም] ከዚህ አንጻር የራሱ መፍትሔ ስላለው ሰላም ማደፍረሱ እንደማይቀጥል አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ሥፍራዎች በግላቸው በመንቀሳቀስ በርካቶችን ያነጋገሩት ሰላም ለኢትዮጵያ ቀዳሚ ስለሆነ ነው በሚል መርህን በመከተል እንደሆነና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ፣ በብሔሮች መካከል እርቅ እንዲፈጠር የእርቅ ኮሚሽን እንዲቋቋም የተሠራው የውስጥ ሰላም ወሳኝ ስለሆነ መሆኑን ተናግረዋል።
መፈናቀል ቁጥሩን ማጋነን ብቻ ሳይሆን በማለት "50 ሺህ ተፈናቃይ አለብን ያሉ 1ሺህ ተፈናቃይ ማቅረብ አልቻሉም በማለት ማፈናቀልና ተፈናቃይ መቀበል ንግድ ነው የሆነው" ብለዋል።
"በጌዲዮ የተፈናቀለው በሚሊየን ተጠርቶ ስንመልስ ግን አነስተኛ ቁጥር ብቻ እንዳላቸው ተረድተናል" ሲሉም ተናግረዋል።
መንግሥታቸው ለውስጥ ሰላም አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልፀው "የምንታገሰው የነበረውን ነገር ላለመድገም ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
የሕዳሴው ግድብን በተመለከተ ጠንከር ያለውን የግብፅ አቋም አስመልክቶ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ " የማንንም ፍላጎት ለመጉዳት የጀመርነው ፕሮጀክት አይደለም" በማለት በመግባባትና የግብፅን ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት እንቀጥላለን ብለዋል።
በሚቀጥሉት ቀናት ከግብፅ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም አስረድተዋል።
" ቁጭ ብለን እናወራለን፤ ማንም ይህንን ግንባታ ማስቆም አይችልም። ይህ ሊሰመርበት ይገባል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነት እንከፍታለን የሚሉ አስተያየቶቸን አስመልክተው ሲናገሩ "ማንንም አይጠቅምም ብለን እናምናለን" ብለዋል።
"ጦርነትም ከሆነ ኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ አላት፤ በሚሊዮን ማሰለፍ እንችላለን" ብለዋል።
አክለውም "በቀድሞ መሪዎች የተፈጠሩ ስህተቶችን እናስተካክላለን እንጂ የተጀመሩ ምርጥ ስራዎችን አናቋርጥም፤ እንዲህ አይነት ምርጥ ስራዎችን በማቋረጥ አገር አትገነባም" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሰራሽ የሆነም መዋቅራዊም የሆነ የዋጋ ንረት አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ 'ሆም ግሮውን' ኢኮኖሚ ማሻሸያ የተነሳው ነገር በማለት ማክሮ ኢኮኖሚ አለመመጣጠን ለማስተካከል መዋቅራዊና ዘርፋዊ (ሴክቶራል) ማሻሻያ ይካሄዳል ብለዋል።
በእነዚህ ውስጥ የኑሮ ውድነቱን ካመጡ ነገሮች መካከል አንዱ የቤት ኪራይ ውድነት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁለተኛው የምግብ ዋጋ መናር እንዲሁም ስራ አጥነትና የሚመረተው ምርት በገበያ ከሚፈለገው ያነሰ መሆን ነው ብለዋል።
አንደኛውን ነጥሎ በመፍታት ለሁሉም መፍትሄ አይሆንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት በሚመለከት እስካሁን ከተገነቡት ቤቶች በእጥፍ የሚልቅ በመንግሥትም በግል ባለሃብቶችም ለመገንባት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህ ግንባታ በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ ውጪም የሚካሄድ እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባታው በጥምረት ወይንም በሙሉ ኢንቨስትመንት እንደሚሆን አብራርተዋል።
ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የለገሃሩን ፕሮጀክትንም በማስታወስ ሌላ ጎተራ አካባቢ በተመሳሳይ ለባለሃብቶና ዲፕሎማቶች የቤት ፍላጎት የሚሆን አዲስ ቱሞሮ የተሰኘ አዲስ ፕሮጀክት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከቻይና መንግሥት ኩባንያ ጋር ሊፈራረሙ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገረዋል።
ሌላው የግል ባለሀብቶች መካከለኛ ገቢ ላላቸው ግለሰቦች የሚሰሯቸው ቤቶች ችግሩን እንደሚያስተነፍሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ እንደራሴዎቹ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሁለት ወር ውስጥ እስከ 4ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚሆን የቤቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን መጠለያ በመስጠት የተለያዩ ስራዎች ላይ ለማሰማራት ሁሉንም ታሳቢ ያደረገ ስራ መንግሥታቸው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ምግብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ወር ውስጥ የሚጠናቀቀው በቀን 1 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርተው ከግለሰቦች ጋር በመነጋገር እየተገነባ ያለው ፋብሪካ ቢያንስ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሰዎች በቅናሽ ዳቦ ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልፀዋል።
በዚህ ዓመት የበጀት ዓመት መጠናቀቂያ ድረስ የሚጠናቀቀውና ግዙፍ የሆነው ሌላ የዳቦ ፋብሪካ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ንጉስ በሰጡት ርዳታ በቀን ከ10 ሚሊየን ዳቦ የሚያመርት ፋብሪካ መሆኑንም ገልፀዋል።
ይህ ፋብሪካ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ላሉ ዜጎችም የዳቦ አቅርቦት ይኖረዋል ብለዋል።
የከተማ እርሻ ላይ በመሰማራት የስራ ፈጠራና የኑሮ ውድነቱን ለመቆጣጠር ይሰራል ሲሉም አክለዋል።
የመገናኛ ብዙኃንን አስመልክቶ ጠቅላዩ በተናገሩት ንግግር ሚዲያው ላይ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት ሚዲያ ነፃ እንዲሆን በተደጋጋሚ መጠያቃቸውን አውስተዋል።
"መቻል ላይ ግን ችግር አለ፤ ሚዲያ የዘር፣ የብሔር፣ የነጋዴዎች መቀለጃ ሆኗል።" በማለት ኢትዮጵያዊያን መረጃዎችን እያጣሩ እንዲሰሙና ኃላፊነት እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
የሌላ አገር ፓስፖርት ኖሯቸው የሚዲያ ባለቤት የሆኑ ሰዎችን በሚመለከትም "ትዕግሥት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው... እርምጃዎችን መውሰዳችን አይቀርም" በማለት "ሁለት ቤት መጫወት አይቻልም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በነጻነት ልማትን የሚያግዙ ከሆነ እንደሚበረታቱ፤ ካልሆነ ግን ዲሞክራሲን ለማደናቀፍ የሚሠሩትን መንግሥታቸው እንደማይታገስ በአፅንኦት አስጠንቅቀዋል።
















