"የረሃብ አድማን የመረጥነው ከራሳችን የምንጀምረው ተቃውሞ ስለሆነ ነው" አቶ ገረሱ ገሳ

የምርጫ ኮሮጆ

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

መላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ፣ አንድነት ለፍትህና ዴሞክራሲን ጨምሮ 70 የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫና ፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁን በመቃወም የፊታችን ጥቅምት 5 እና 6 የረሀብ አድማ ለመምታት እንዳሰቡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ ሰብሳቢ እና የ 70ዎቹ ፓርቲዎች አስተባባሪ ኮሚቴ ጸሀፊ አቶ ገረሱ ገሳ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቅርቡ በሰጣችሁት መግለጫ ላይ ለሁለት ቀንየረሃብ አድማ እናደርጋለን ብላችኋል። የረሃብ አድማ ለማድረግ የወሰናችሁት ለምንድን ነው?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ የረሃብ አድማውን ለማድረግ የተነሳንበት ምክንያት በምርጫና በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጁ የተነሳ ነው። በአዋጁ ላይ ለመንግሥት፣ ለምርጫ ቦርድም አዋጁ ትክክለኛ ያልሆነና የሚያሰራ ስላይደለ እንዲሁም የፖለቲካ ስነ ምህዳሩን የሚያጠብ ስለሆነ፣ ተስተካክሎ መውጣት እንዳለበት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበናል። ከዚህ በፊት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ የአዋጁ ረቂቅ ቀርቦ ተወያይተውበት ነበረ።

ነገር ግን ፓርቲዎቹ የተወያዩበት ረቂቅ ተቀይሮ ሌላ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ነው የፀደቀው። ስለዚህ ይኼ በአጠቃላይ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ማታለልም ጭምር ስለሆነ ይህንን በመቃወም ነው።

ሕጉ እንዳይፀድቅ አስቀድመን ተቃውመናል። ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት አሳውቀናል። ግን ተቀባይነት አጥቶ አዋጁ ፀድቋል። አሁን ደግሞ የምንቃወመው አዋጁ ሥራ ላይ እንዳይውል ነው።

ሙሉ አዋጁን ነው የምትቃወሙት ወይለይታችሁ በመነጠል የምትቃወሟቸው አንቀጾች አሉ?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ አዋጁ ላይ የምንቃወማቸው በርካታ አንቀጾች አሉ። አሁን እኛ የምናስተባብረው የፖለቲካ ፓርቲ በአንድ ላይ ከ30 በላይ አንቀጾች ላይ፣ መሰረዝ፣ መሻሻል ያለባቸው አንቀጾችን እና ማስተካከያ መደረግ ያለባቸውን አንቀጾች ለይተን በዝርዝር ከነዝርዝር ሀሳቡ አቅርበናል። ለምርጫ ቦርድ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ለፓርላማ አፈ ጉባዔ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሀገሪቱ ፕሬዝደንትም፣ ለፌዴሬሽን አፈ ጉባዔ ጭምር ዝርዝሩን በሙሉ አቅርበናል። ሕጉ ላይ ያለውን እንከንና ችግር ማለት ነው። ያንን ሁሉ አድርገን የሚሰማን አካል ጠፋ።

ከእኛ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ በተለያዩ አካላት በአዋጁ ላይ የቀረቡ ከ90 ባላነሱ አንቀጾች ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሻሻያ ጥያቄ ቀርቧል። ይህንን ሁሉ እንከን ይዞ ነው እንግዲህ አዋጁ የፀደቀው። ስለዚህ አዋጁ ላይ የማያሰሩ፣ የፖለቲካ ስነ ምህዳሩን የሚያጠቡ፣ የዜጎችን የመደራጀት መብት የሚገድቡ፣ እንዲሁም የመምረጥና የመመረጥ መብትን የሚያሳጡ፣ አንቀጾች ስላሉ እነዚህ አንቀጾች እንዲሻሻሉና እንዲቀየሩ ነው ተቃውሟችን።

ለምን የረሃብ አድማን መረጣችሁ?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ የረሃብ አድማን የመረጥነው ከራሳችን የምንጀምረው ተቃውሞ ስለሆነ ነው። ከራሳችን ከአስተባባሪ ኮሚቴዎቹና፣ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ከራሳችን የሚጀምር ተቃውሞ ስለሆነ ነው። የረሃብ አድማው ላይ ጥሪ ያደረግነውም በመጀመሪያ ደረጃ ለሁሉም የፖለቲካ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም በዚህ ተቃውሞ ለተሳተፉ 70 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች፣ አባላትና አመራሮች ነው። ከዚያ ውጪ ደግሞ ፈቃደኛ የሆነ የሕብረተሰብ አካል ተቃውሞውን መቀላቀል ይችላል።

ስለዚህ ከራሳችን የምንጀምረው ተቃውሞ ስለሆነ ነው።

መቼ ነው አድማውን ማካሄድ ያሰባችሁት?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ ጥቅምት አምስት እና ስድስት። ግን አንድ የተቀመጠ ቅድመ ሁኔታ አለ። ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ በመስከረም ወር ውስጥ ከአንድም ሁለት ሶስት የሥራ ቀናት አሉት። በእነዚህ ቀናት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ የሥራ ቀናት ማክሰኞና ሐሙስ እንደሆነ ይታወቃል፣ ስለዚህ በእነዚህ የስራ ቀናት ውስጥ አዋጁ ላይ ያለውን ችግር መልሶ የማያይና ይህንን የአስተባባሪ ኮሚቴ ጠርቶ የማያነጋግር ከሆነ ነው የረሃብ አድማውን የምናካሂደው።

ነገር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን እንደገና ለማየትና ለማሻሻል የሚወስደው እርምጃ ካለ የረሃብ አድማው ላይቀጥል ይችላል ማለት ነው። ስለዚህ ይህንን አንድ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠናል።

የረሃብ አድማው በመላ ሀገሪቱ ነው የሚካሄደው? ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳተፋሉ? ለምን ያህል ሰዓት ይቆያል?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ የረሃብ አድማው በአዲስ አበባ ደረጃ፣ የአስተባባሪ ኮሚቴውና በሰባዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የታቀፉት አመራሮችና ተወካዮች በአንድ ቦታ ተሰብስበን ነው የረሃብ አድማውን የምናደርገው።

በክልል ደረጃ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በያሉበት፣ በተደራጁበት አካባቢ ሆነው አመራሮቻቸው፣ ደጋፊዎቻቸውና አባሎቸቻቸው በረሃብ አድማው ይሳተፋሉ ማለት ነው።

ከዚያ ውጪ በረሃብ አድማው መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ በየስራውም ቦታ በየቤቱም ሆኖ የረሃብ አድማውን መቀላቀል ይችላል። ይህ ማለት ለዲሞክራሲ፣ ለሰብዓዊ መብት፣ ለነፃነት፣ ለእኩልነት የሚደረግ፣ ለእኛም ለህዝብም የሚደረግ ትግል መስዋዕትነት ስለሆነ ማንኛውም ዜጋ የረሃብ አድማውን በተመቸው ስፍራ ሊቀላቀለን ይችላል።

ለምሳሌ አዲስ አበባ የት ነው የረሃብ አድማው የሚካሄደው?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ በዋናነት ዋና አስተባባሪው የረሃብ አድማውን የሚያደርገው አዲስ አበባ ነው፤ ቦታውን ግን ከመስከረም 27 በኋላ ነው ይፋ የምናደርገው።

ለ48 ሰዓታት የሚቆይ የረሃብ አድማ ነው የሚሆነው?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ አንዳንድ ታሳቢ የሆኑ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ በጤና እክል ምክንያት መድሃኒት በመውሰድ ላይ ያሉ፣ ምግብ በተወሰነ ሰዓት መመገብ ያለባቸው አመራሮችና ተወካዮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነዚህ አካላት በዚህ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉበት ሁኔታ የተገደበ ነው።

በተገደበና በተመጠነ መልኩ ነው የሚሳተፉት። ከዚያ ውጪ ጤናማ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ በሐኪም ልዩ ትዕዛዝ የሌላቸው 48 ሰዓት ከቻሉ ደግሞ መቀጠልም ይችላሉ።

ውሃስ መጣት ቻላል?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ ዝርዝር ሁኔታውን ውሃና መድሃኒትን በሚመለከት መስከረም 27 እና ከዚያ በኋላ ይፋ እናደርጋለን።

በአድማው ላይ 48 ሰት መቆየት ሳይችሉ ቀርተው ተዝለፍልፈው ቢወድቁ ለእንደዚህ ዓይነት ድንገተኛ አደጋዎች ምን ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ቅድመ ሁኔታዎች እየተሰሩ ነው ያሉት። ምንድን ነው የምናደርገው? ምን ዓይነት ባለሙያዎች እናዘጋጃለን? የሚለው እየተሰራ ነው ያለው። የሕክምና ባለሙያዎችን፣ አስፈላጊ የምክር ባለሙያዎችንም፣ እያዘጋጀን ነው ያለነው።

ጉዳሰባዎቹም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማማችሁበትነው?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ አዎ። የተስማማንበት ጉዳይ ነው። ስምምነቱ ግን አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ነፃነትን ይከለክላል ማለት አይደለም። እስከዚያ ድረስ 'አይ እኔ በዚህ ስምምነት መቀጠል ያስቸግረኛል' የሚል ካለ ነፃነቱ የተጠበቀ ነው። መጀመሪያ እኛ ሂደቱን ስንጀምር በ33 ፓርቲዎች ነው የጀመርነው። ከዚያ በኋላ ሌሎች ፓርቲዎች ተቃውሞው ትክክል ነው ብለው እያመኑ ሲመጡና ሲቀላቀሉ ነው ቁጥሩ ጨምሮ ሰባ የደረሰው።

ስለዚህ በፈቃዳቸው መጥተው እንደተቀላቀሉን በፈቃዳቸው ደግሞ አንሳተፍም ካሉ የምናስገድድበት ሁኔታ የለም።

መቼ ነበር በ33 ፓርቲዎች ተቃውሞውን የጀመራችሁት?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ ተቃውሞውን ከጀመርን ሶስት ወር አካባቢ ይሆነናል።

እነማን ናቸው ፓርቲዎቹ ለምሳሌ ቢጠቅሱልኝ?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ እኔ ሰብሳቢ የሆንኩበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ኮንግረስ፣ መኢአድ፣ ኦብኮ፣ የገዳ ስርኣት አራማጅ ፓርቲ፣ ከኦሮሚያ ክልል ወደ ስድስት ፓርቲዎች፣ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር፣ እነዚህና አሁን ስማቸውን ዘርዝሬ የማልጨርሳቸው ፓርቲዎች አሉ። ከውጪ ከመጡ ፓርቲዎች መካከል አስር ፓርቲዎች ከእኛ ጋር በምናደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ አሉ።

የረሃብ አድማ ግን ምን ያሕል አዋጭ ነው ለፖለቲካ ትግላችሁ?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ የረሃብ አድማ ምን ያህል አዋጭ ነው? የሚለው ሕሊና ያለው አካል፣ ለሕዝብ ደንታ ያለው አካል፣ የሕዝብ ብሶት፣ ሮሮ፥ ጥያቄ፣ ሊሰማና ሊደመጥ ይገባል የሚል መንግሥታዊ ሥልጣን ላይ የተቀመጠ አካል ካለ፣ ከረሃብ አድማ በላይ አስከፊና አስነዋሪ ተቃውሞ የለም። በጣም አስከፊ ተቃውሞ ነው። መስማት፣ማዳመጥ የሚችል አካል ካለ።

አንድ ሰው ራሴን ለረሃብ አጋልጣለሁ ሲል እሞታለሁ ከሚል በምንም አይተናነስም። ስለዚህ ወደዚህ ተቃውሞ የሚገቡ አካላት ለምንድን ነው ወደዚህ ተቃውሞ የሚገቡት ማለትና መስማት የሚችል ባለስልጣን በሀገራችን ካለ፣ ዲሞክራት መሪ ካለ ይኼ ተቃውሞ መንግስት ሊሰማውና ሊያዳምጠው የሚገባው ተቃውሞ ነው።

ነገር ግን መንግሥት ላይ ድንጋይ እንደመወርወር፣ ጥይት እንደመተኮስ ወይንም የሆነ ተቋም እንደማቃጠል፣ አስደንጋጭ ላይሆን ይችላል።

አምባገነን መንግሥታት ጥይት ሲተኮስባቸው፣ ድንጋይ ሲወረወርባቸውና የሆነ የሚፈነዳ፣ የሚያቃጥል ነገር ሲመጣ ነው የሚደነግጡት። ለእንደዚህ ዓይነት ሌላ ተቃውሞ ጆሮም ግድም አይሰጡም።

ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ካለ ግን ከጥይት ጩኸትና ከቦምብ ፍንዳታ በላይ ይህ ትክክለኛ ተቃውሞ ነው። ለዚህ ነው እኛ እንደተቃዋሚ ይህንን የረሃብ አድማ መጀመሪያ በራሳችን የምንጀምረው።

በመቀጠልም ደረጃ በደረጃ የምንሄድነበት መሆኑን አስበን ነው የገባነው።

ለረሃብ አድማው ምላሽ ካልተሰጣችሁ ምንድን ነው የምታደርጉት?

አቶ ገረሱ ገሳ፡ በመላ ሀገሪቱ የተቃውሞ ፊርማ የማሰባሰብ እርምጃ ነው የምንሰራው። ከዚያ ጎን ለጎን ደግሞ ከተፈቀደልን በተለያዩ ስፍራዎች ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንጠራለን። በእነዚህ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ተቃውሞ የምናካሂድበትና አደባባይ ወጥተን ሰላማዊ ሰልፍ የምናካሄድበትን ሂደት እንከተላለን። ይኼ ደረጃ በደረጃ የምንከተለው ነው።