ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዛሬ ቦሪስ ጆንሰን ሥልጣን ተረክበው ካቢኔያቸውን ያሳውቃሉ
ቦሪስ ጆንሰን ዛሬ ከሰዓት የእንግሊዝ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ሆነው ሥራ የሚጀምሩበት ሥነ ሥርዓት ንግሥቲቷ በተገኙበት ይካሄዳል። ሥልጣኑን ከቴሬዛ ሜይ የተረከቡት ቦሪስ አስከትለውም የመንግሥት አስተዳደራቸውን ወደማዋቀር ይገባሉ።
ቦሪስ የካቢኔ አባላት፣ ቻንስለርና የአገር ደህንነት ጸሀፊ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ለአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የቀረቡ ምንጮች እንዳሉት የሚመረጡት ባለሥልጣኖች "የዘመነኛ እንግሊዝ መገለጫ" ይሆናሉ። በካቢኔያቸው ውስጥ የሴቶችን እንዲሁም በዘር ሀረጋቸው ምክንያት ተገልለው የነበሩ ግለሰቦችን ወደ ኃላፊነት ያመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ቦሪስ ጆንሰን ወደ ሥልጣን የመጡት ከተፎካካሪያቸው ጀርሚ ሀንት 66.4 በመቶ የድምፅ ብልጫ ካገኙ በኋላ ነው።
ድል መቀዳጀታቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ፤ በሥልጣን ዘመናቸው ቅድሚያ የሚሰጡት ብሬግዚትን እውን ለማድረግ፣ አገሪቱን ለማዋሀድና የሌበር ፓርቲው ጀርሚ ኮርቢን ለማሸነፍ እንደሆነ ተናገረዋል።
የቀድሞው የለንደን ከንቲባ ቦሪስ ጆንሰን ከንግሥቲቷ የመንግሥት አስተዳደራቸውን የማዋቀር ጥሪ ከተቀበሉ በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ ሥነ ሥርዓት በፊት ቴሬዛ ሜይ ከጠቅላይ ሚንስተርነት መልቀቃቸውን በበርኪንግሀም ቤተ መንግሥት በይፋ ይናገራሉ።
የቦሪስ የፖለቲካ ሕይወት
የቦሪስ የፖለቲካ ሕይወት የተመሰቃቀለ ነው። የሕዝብ እንደራሴዎች አብላጫ ድጋፍ የለውም። ምርጫው የተካሄደው በወግ አጥባቂው ፓርቲ ውሳኔ እንደመሆኑ የሕዝቡን ፍላጎት የጠበቀ ነው ለማለትም አይቻልም።
በአሁን ቅት በርካታ የፖሊሲ ችግሮች አሉ። በብሬግዚት ላይ የአቋም ልዩነት ያለው ፓርቲን ጨምሮ ሌሎችም አገራዊ ችግሮችም አሉ።
ምንም እንኳን ደጋፊዎች ቢኖሯቸውም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ብዙም እምነት አይጥሉባቸውም።
ቦሪስ ስለ ብሬግዚት እቅዳቸው ነገ ፓርላማ ፊት ቀርበው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከሕዝብ ተወካዮች የሚቀርቡላቸውን ጥያቄዎችም ይመልሳሉ።
የቢቢሲ የፖለቲካ አርታኢ ላውራ ኩንስበርግ እንደሚሉት፤ ቦሪስ ጆንሰን የሚመርጧቸው የካቢኔ አባላት ፓርቲውን በማዋሀድ ረገድ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል።
የፍትሕ ሚንስትርን ጨምሮ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የሚኖረው ለውጥ እየተጠበቀ ነው።
ለቦሪስ የቀረቡ ምንጮች የሚመረጡት የካቢኔ አባላት "በፓርቲው ውስጥ ያለውን ችሎታ የሚያንጸባርቁና የዘመነኛ እንግሊዝ መገለጫ" ይሆናሉ ብለዋል።