የአይ ኤስ ወታደሮች በኒጀር ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒጀር መከላከያ ሚኒስትር 18 የአይ ኤስ እስላማዊ ቡድን ወታደሮች በአሜሪካ፣ በፈረንሳይና በኒጀር ጥምር ጦር ሃይል መግደላቸውን አስታወቁ።
12 ቀን በፈጀው በዚህ ዘመቻ አምስት የ አይ ኤስ ወታደሮች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲሉም ገልፀዋል።
ይህ ዘመቻ የተካሄደው ኒጀር ከማሊ ጋር በምትዋሰንበት ቶንጎ ቶንጎ አቅራቢያ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ባለፈው ወር እስላማዊ ቡድን በአካባቢው ደፈጣ በመፈፀም 28 የኒጀር መከላከያ አባላትን መግደላቸውን አስታውሰዋል።
በዘመቻው የእስላማዊ ቡድኑ የደፈጣ ጥቃት በፈፀመበት ወቅት የዘረፋቸው የተለያዩ "የጦር መሳሪያዎች" የተያዙ ሲሆን በተጨማሪም "ጠቃሚ መረጃ" ማግኘታቸውን ገልፀዋል።
የፈረንሳይ ጦር ለብቻው በሰጠው መግለጫ ዘመቻው መካሄዱን አረጋግጦ የማሊ ወታደሮችም መሳተፋቸውን ሲገልፅ የአሜሪካ ተሳትፎን ግን ሳይጠቅስ አልፎታል።
አሜሪካ ስለ ዘመቻው እስካሁን ድረስ ያለችው ነገር የለም።
ዘመቻው የተካሄደበት አካባቢ ትልቅ ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሚገኝ ሲሆን በማሰልጠኛው በማሊ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ጦር ውስጥ ለመካተት የተመለመሉ ወታደሮች የሚሰለጥኑበት ነው ተብሏል።
ኒጀር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገር ውስጥ ግጭቶች ስትታመስ የቆየች ሲሆን ይህም ሰርገው በገቡ የእስላማዊ ቡድኖች ቆስቋሽነት መሆኑ ይነገራል።












