የታንዛንያ ፖሊስ ሴቶችን በደቦ በመድፈር የተጠረጠሩትን በቁጥጥር ስር አዋለ

በሰሜን ምዕራብ ታንዛንያ ሴቶችን በደቦ በመድፈር የተጠረጠሩ ዘጠኝ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል።

ተጠርጣሪዎቹ ከሶስት አመት በፊት ወንጀሉን ፈፅመዋል ተብሏል።

ኪጎማ ተብሎ በሚጠራው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ሴቶች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ራሳቸውን "ተሌዛ" ብለው የሚጠሩ ወንዶች ሴቶችን በደቦ በመድፈር ለህይወታቸው አስጊ ሁኔታ መፍጠራቸውን ነው።

ግለሰቦቹ በመድፈርና በስለት ጥቃት በማድረስ ወንጀል ተጠርጥረዋል።

በአካባቢው ያሉ የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን ለቢቢሲ እንደገለፁት በሶስት አመታት ብቻ አርባ ሶስት የመደፈር ጥቃቶች ተከስተዋል።

ብዙ ሴቶችም ለደህንነታቸው በመስጋት በቡድን መኖር መጀመራቸውም ተገልጿል።

"ከኪጎማ መውጣት እፈልጋለሁ" በማለት ጥቃት የደረሰባት አንዲት ሴት ጠባሳዋን በማሳየት ለቢቢሲ ስዋሂሊ ገልፃለች።

ቴሌዛ ተብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት ስያሜያቸውን ያገኙት ጥቃት ከማድረሳቸው በፊት በቆሻሻ ዘይት ፊታቸውን ስለሚቀቡ ነው ተብሏል።