ጄይ-ዚ፡ የመጀመሪያው ቢሊየነር 'ራፐር' ሆኗል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፎርብስ የተሰኘው መፅሄት እንደገለጠው ጄይ-ዚ ሙዚቃን ጨምሮ፣ ፋሽን እና ሌሎች ኢንቨስትመንቶቨች ላይ ያፈሰሰው ንዋይ ቱጃር አድርጎታል።
ዓለም ላይ ካሉ ራፐሮች ልቆ ቢሊየነር መሆን የቻለው የቢዮንሴ ባል ጄይ-ዚ ከሙዚቃ ብቻ ያካበተው ሃብት ቀላል የሚባል አይደለም።
ሾን ካርተር በተሰኘ የመዝገብ ስሙ የሚታወቀው ጄይ-ዚ፤ ኒው ዮርክ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ኑሮ የከበደበት ሥፍራ ነው ተወልዶ ያደገው።
1996 ላይ ባወጣው የመጀመሪያ ዓልበሙ እውቅና ማትረፍ የቻለው ካርተር፤ 2001 ላይ የለቀቀው 'ብሉፕሪንት' የተሰኘ ዓልበሙ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ጥበባዊ ዳራው የላቀ ሆኖ በመገኘቱ ሙዚዬም ሊገባለት ችሏል።
እጀ-ረዥሙ ጄይ-ዚ ከኮኛክ እስከ ኡበር ባለ ኢንቨስተመንቶች ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛል።
ባለቤቱ ቢዮንሴ በበኩሏ 335 ሚሊዮን ዶላር በማካበት አሉ ከሚባሉ እንስት ሙዚቀኞች አናት ላይ መቀመጥ ችላለች። ይህ ማለት የጥንዶቹ የሃብት መጠን ሲጠቃለል ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ ቁጭ።
2014 ላይ ሌላኛው ጥቁር የሙዚቃ ሰው ዶር ድሬ ቢሊየነር ሆኗል ተብሎ ቢነገርም ፎርብስ ግን የግለሰቡ ሃብት 770 ሚሊየን እንጂ ቢሊዮን አልገባም ሲል አጣጥሏል።
ጄይ-ዚን በ40 ዓመት የሚበልጡት ሌላኛው ቢሊየነር ዋረን በፌት አንድ ጊዜ «እኔ ከጀይ-ዚ ብዙ ልማር የሚገባኝ ነኝ፤ ይህ ወጣት ሰው ገና ብዙ ቦታ ይደርሳል» ሲሉ ተናግረው ነበር።












