ዛሬ በሱዳን የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 13 ደረሰ

የሱዳን ተቃውሞ፡ ካርቱም በጥይት ድምፅ የታጀበ ቀን ጀምራለች

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

አልበሽርን ከመንበራቸው የፈነገለው የሱዳን ተቃውሞ አሁንም የበረደ አይመስልም፤ ወታደራዊውን ጊዜያዊ መንግሥት የተቃወሙ ሰልፈኞች ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

የመብት ተከራካሪዎች የሱዳን ጦር በተቃዋሚዎች ላይ በከፈተው ተኩስ በርካቶችን ገድሏል ብለዋል።

የሆስፒታል ምንጮች ደግሞ 13 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸው ይጠቁማሉ።

በሱዳን መዲና ካርቱም በሚገኝ አንድ ሥፍራ አድማ ላይ የነበሩ ዜጎች የተከፈተባቸውን ተኩስ በመሸሽ ላይ እንደሆኑ ከካርቱም የሚወጡ ዘገባዎች እየጠቆሙ ነው።

ሮይተርስ የተሰኘው የዜና ወኪል የታጠቁ ወታደሮች አድማ የሚደረግበት ሥፍራን ሰብረው እንደገቡ አስነብቧል።

ተቃዋሚዎች ከወታደሩ ጋር ያላቸውን ንግግር ከዛሬ ጀምሮ አቋርጠናል ያሉ ሲሆን ተቃዋሚዎች ከወታደሩ ጋር በፈጠሩት ግጭት ሳቢያ ነው 13 ሰዎች መሞታቸው የተዘገበው።

የዓይን እማኝ የታጠቁ ወታደሮች የታቃደ ጥቃት ሰላማዊ ዜጎች ላይ ፈፅመዋል ሲል ይወነጅላል።

''የሱዳን ጦር አድማውን ለመበትን አልሞከረም ይልቁንም በጦሩ ዋና መስሪያ ቤት አካባቢው እየተደረገ ያለው አድማ ለሱዳን ዜጎች ደህንነት አስጊ ሆኖ ስለተገኝ እሱ ላይ ነው ትኩረት የተደረገው'' ሲሉ የሱዳን ጊዜያዊ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ቃል አቀባይ ሌተናል ጄኔራል ሸመስ አል-ዲን ካባሺ ስካይ ኒውስ አረቢያ ተናግረዋል።

በማሕበራዊ ድር አምባዎች የሚለቀቁ ምስሎችም በጭስ ከታፈነችው ካርቱም የሚወጡ የጥይት ድምፆችን የሚያስደምጡ ናቸው። አልፎም ተቃዋሚዎች ጎማ በማቃጠል ራሳቸውን ከወታደሮች ለመከላከል እየጣሩ እንዳለ ታውቋል።

ከሱዳን ጦር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት እየተደረገ ያለው ተቃውሞ ወታደራዊው ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣኑን ለሲቪል እንዲያስረክብ የሚጠይቅ ነው።

ለቢቢሲ ድምጿን የሰጠችው ፋቢያ ካላፍ ተቃውሞው ላይ ለመሳተፍ የካርቱም መንገዶችን እያካለለች እንደሆነ ትናገራለች።

ፀረ-መንግሥት የሆኑ ሰልፎችን በማቀነባበር የሚታወቀው 'ሱዳኒዝ ፕሮፌሽናል አሶሴሽን' ሱዳናውያን ወታደራዊውን አስተዳደር ተቃውመው ሰልፍ እንዲወጡ አዟል።

ፋቢያ «ወታደራዊው አገዛዝ ሥልጣን ለሲቪል እስኪሰጥ ድረስ ድምፃችንን ማሰማት አናቆምም» ትላለች።