የ5 ሚሊዮን ብር እራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር

የፎቶው ባለመብት, @PMEthiopia
በቅርቡ ይፋ የተደረገውን የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቻቸውን የማልማት ሥራን እውን ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አማካይነት በነፍስ ወከፍ አምስት ሚሊዮን ብር ተከፍሎ የሚታደሙበት የእራት ድግስ ተዘጋጅቷል።
'ገበታ ለሸገር' በሚል ስያሜ የተዘጋጀው የእራት ዝግጅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሚታደሙበት ሲሆን አምስት ሚሊዮን ብር ከፍለው የዝግጅቱ ተሳታፊ ለሚሆኑ ሰዎች የተለያዩ መታሰቢያ ተዘጋጅቷል።
ይህ የልማት ሥራ ሲጠናቀቅ በተለያዩ የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻዎች ላይ የእራት ዝግጅቱ ታዳሚዎቹ ስም በተናጠል ተጽፎ የሚቀመጥ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋርም የአንድ ለአንድ ፎቶ የመነሳት እድልን ያገኛሉ ተብሏል።
ይህም ፎቶግራፍ የአዲስ አበባን ገጽታ የቀየሩ ግለሰቦች በሚል ተሰባስቦ በአንድ ጥራዝ ላይ እንዲቀርብ ይደረጋል ተብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ባቀረበው የግብዣ ጥሪም የንግድ ተቋማት ባለቤቶችና አመራሮች እንዲሁም የዓለም አቀፍና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት በዚሁ የእራት ዝግጅት ላይ እንዲታደሙ ጋብዟል።
በቫርኔሮ ኩባንያ የሚከናወነው የአዲስ አበባን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ይለውጣል ተብሎ የታሰበው ፕሮጀክት በ29 ቢሊየን ብር ወጪ የሚከናወን ሲሆን በሦስት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለታል።
ሥራው የአዲስ አበባ ከተማን ለሁለት ከፍለው የሚያልፉ ወንዞችን መሰረት ያደረገ ሲሆን ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ ያለውን 56 ኪሎ ሜትር እርቀት የሚሸፍን ነው።
የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎች ልማት ሥራ ሲጠናቀቅ 4 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚለማ የተነገረ ሲሆን፤ በውስጡም አስፈላጊው ነገር የተሟላላቸው የመዝናኛ፣ የመጓጓዣ፣ የንግድ ማዕከላትና አረንጓዴ ስፍራዎች ይኖሩታል ተብሏል።












