''መከላከያ በሌሎች ስፍራዎች ያሳየውን ትዕግስት በምዕራብ ጎንደርም መድገም ነበረበት''

ጎንደር
የምስሉ መግለጫ, ጎንደር

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን በትናንትናው ዕለት ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ተከሰተ በተባለ ግጭት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ የገንዳ ውሃ ከተማ በትናንትናው ዕለት የተቃውሞ ሰልፍ አስተናግዳለች።

የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ለቢቢሲ እንደገለጹት በግጭቱ ላይ የተሳተፉ አካላት እነማን እንደሆኑ ለማጣራት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደቦታው ተንቀሳቅሷል። አቶ አሰማኸኝ ጨምረውም ''ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው። ያለውን ሁኔታ በአግባቡ ተወያይቶ መተማመን ላይ እስከሚደረስ ድረስ ተጠብቆ ነው እንቅስቃሴ መጀመር የነበረበት። ነገር ግን መተማመን ሳይፈጠር ነው መከላከያ እንቅስቃሴ ሊያደርግ የሞከረው። ኅብረተሰቡ ደግሞ የራሱ ጥርጣሬ አለው፤ ምን እንደጫነ አያውቅም፤ ስለዚህ ልፈትሽህ አለ፤ ግጭት ተፈጠረ። በግጭቱም የንፁሃን ህይወት እጦት እና ቁስለት ተከስቷል።'' ብለዋል።

''ከሰሞኑ እንደምንሰማው በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከልክ ያለፈ ትዕግስት ጭምር እያሳየ [መከላከያ] መተማ ላይ ግን ለተወሰነ ደቂቃ ወይንም ለውይይት መንገድ ባልሰጠ መልኩ፤ መተማመን ባለተደረሰበት ሁኔታ እንደዚህ ያለ እርምጃ መወሰዱ የሚያሳዝን ነው።'' ብለዋል የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ።

በትናንትናው ሰልፍ የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደገለፁት ግጭቱ አካባቢውን አቋርጠው ወደ ትግራይ ክልል ያመሩ ከነበሩ ንብረትነታቸው የሱር ኮንስትራክሽን ነው ከተባሉ የጭነት እና የግንባታ መኪናዎች ጋር የተገናኘ ነው።

በመኪኖቹ እንቅስቃሴ ላይ ጥርጣሬ እንደገባቸው በመግለፅ ለማስቆም የፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች መኪኖቹን ያጅቡ ከነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር መፋጠጣቸውን ይህም ወደተኩስ እና ሞት ማምራቱን ለቢቢሲ የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪ አቶ አገናኝ ካሱ ናቸው።

"ትናንትን ቀን ላይ ጀምሮ መኪኖቹ ሲመጡ [ወጣቱ] ድንጋይ መወርወር ጀመረ። መከላከያ ሠራዊት ድንጋይ የሚወረውረው ወጣት ላይ ተኩስ ከፈተ። መጨረሻ ላይ አንዳንድ ሚሊሻዎችም መከላከያ ሠራዊት ላይ ተኩስ ከፈቱ" ሲሉ የግጭቱን ሒደት የሚያስረዱት አቶ አገናኝ፤ ከሠራዊቱ በኩል ሞትም ሆነ የመቁሰል አደጋ ይኑር አይኑር መረጃው ባይኖራቸውም ዕቃ ለመግዛት የወጡ ህፃናት እና በህዝብ መጓጓዣ በመሳፈር ላይ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎች መሞታቸውን ይገልፃሉ።

ሰልፈኞቹ ዛሬ "የህፃናት ግድያ ይቁም፥ መከላከያ ሰራዊት እየወሰደ ያለው እርምጃ ትክክል አይደለም፥ ሲያስጨፈጭፉን የነበሩ መኪኖች ከክልላችን ሊወጡ አይገባም" የሚሉ መፈክሮችን ማሰማታቸውንም አቶ አገናኝ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ህፃናት በጥይት ተመትተው ሆስፒታል ውስጥ ገብተው ማየታቸውን ሌላ የከተማው ኗሪ እና የሰልፉ ተሳታፊም ገልፀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን የፀጥታ እና አስተዳደር ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ግጭቱ የበርካቶችን ሞት እና ቁስለት ማስከተሉን ለቢቢሲ አረጋግጠው የሰለባዎቹ ቁጥር በትክክል ምን ያህል እንደሆነ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

የፀጥታ ኃላፊው እንዳሉት የግጭቱ መንስዔ ናቸው የተባሉት ከአርባ በላይ ተሽከርካሪዎች ከገንዳ ውሃ ከተማ ወጣ ብለው አሁንም ቆመው የሚገኙ ሲሆን ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውን በሚመለከት የሚተላለፍ ውሳኔ ከህዝብ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የሚመሠረቱ ይሆናል።

ቀዳሚ የትኩረታቸው አቅጣጫ "ለግጭት መንስዔ የሆነው ጉዳይ እንዴት መልክ ይያዝ" የሚለው መሆኑን የገለፁት አቶ ደሳለኝ ዓላማቸው "ሰው የማይሞትበትን አማራጭ መጠቀም ነው" ብለዋል። "መኪናዎች ለአንድ ቀንም ሆነ ለሁለት ቀን ይቁሙ፤ ኅብረተሰቡ ይወያይ። ለምን ዓላማ እንደሚገቡ፤ ምን እንደሚሰሩ እናስረዳው፤ ከዚያ በኋላ ወደሚፈልጉበት አቅጣጫ ይሄዳሉ።" ብለዋል።