ትራምፕ በትልቁ ቡሽ ግብዓተ መሬት ላይ ይገኙ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ እና ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ካፒቶል በተሰኘው አዳራሽ ተገኝተው የጆርጅ ቡሽ ትልቁን አስከሬን ተሰናብተዋል።
በሙሉ ስማቸው ጆርጅ ኸርበርት ዎከር ቡሽ በ94 ዓመታቸው ነው ባለፈው አርብ ይቺን ዓለም በሞት የተሰናበቱት።
በአሜሪካ ባንዲራ እና በአበቦች የተከበበው አስክሬናቸው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ካፒቶል ሕንፃ ውስጥ ለሚሰናበቱ ሰዎች ይሆን ዘንድ ተደርጎ ተቀምጧል።
የትልቁ ቡሽ ሬሳ 21 መድፍ ከተተኮሰ በኋላ መኖሪያ ሥፋራቸው የነበረው ቴክሳስን ለቆ ኤይር ፎርስ ዋን በተሰኘው ግዙፉ የዋይት ሃውስ አውሮፕላን ወደ ዋሽንግተን መጥቷል።
41ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ትልቁ ፓርኪንሰን በተሰኘው በሽታ ተጠቅተው ሆስፒታል ውስጥ እርዳታ ሲያገኙ ነበር።
ከቡሽ ቤተሰብ ጋር ብዙ ስምምነት የሌላቸው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከባለቤታቸው ጋር አጠር ያለ ስንብት ያደረጉ ሲሆን ግብዓተ መሬቱም ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ትራምፕም ሆነ ሚስታቸው ሜላኒያ በግብዓት መሬቱ ላይ ይገኙ እንጂ ንግግር ግን እንደማያደርጉ እየተነገረ ነው።
እንደውስጥ አዋቂዎች ከሆነ ሪፐብሊካኑ የቡሽ ቤተሰብ ባለፈው ምርጫ ድምፃቸውን የሰጡት ለትራምፕ ተቀናቃኝ ሂላሪ ክሊንተን ነው።
ጆርጅ ቡሽ ትልቁ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጄት አብራሪ ነበሩ፤ የአሜሪካው ስለላ ድርጅት ሲዓይዔ ኃላፊም ሆነው ሰርተዋል፤ ወደፕሬዚዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት ደግሞ የሮናልድ ሬገን ምክትል ሆነው አገልግለዋል።












