ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በወታደሮቹ ድርጊት ተበሳጭተው እንደነበር ተናገሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ለሃገሪቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ የመንግሥታቸውን አቋም ሲያብራሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቆዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የዓመቱ መጀመሪያ የጋራ ስብሰባ ላይ መንግሥትን በዚህ ዓመት ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ላይ ጠቅላይ ሚኒስሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በማንሳት የመንግሥታቸውን ዓላማና ዕቅድ በማንሳት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በደሞዝ ጥያቄ ሰበብ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ስለሄዱ ወታደሮችም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ እንዳሉት ታጥቀው ወደ ጽህፈት ቤታቸው የመጡት የሠራዊቱ አባላት አካሄድ አደገኛ እንደነበረና በዚህ መሃል መንግሥት የኃይል እርምጃን በመውሰድ ቢሞከር ኖሮ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር ተናግረው፤ ይህም ለውጡን ለማጨናገፍ ሊውል ይችል እነደነበር አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ፍንጭ ባይሰጡም ከዚህ ክስተት ጋር ተያይዞ የለውጡን ሂደት ለማጨናገፍ ፍላጎት ያላቸው ወገኖች በስተጀርባ መኖራቸውን ተናግረዋል።
በድርጊቱ እጅጉን መበሳጨታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ቢሆንም ግን ሕዝቡን ለማረጋጋትና አላስፈላጊ ሁኔታዎች እንዳፈጠሩ በሚል በእርጋታና በፈገግታ ለጋዜጠኞች መግለጫ መስጠታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ "ሳንገድለው አመለጠን" የሚሉ ሰዎች እንደነበሩም ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ በሃገሪቱ እየመጣ ያለው ለውጥ ስኬታማ መሆን ካልቻለ የመጨንገፍ እድል ሊገጥመው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ለዚህ ደግሞ "ለውጡን ለማጨናገፍ እየሰሩ ያሉ አካላትን ማስቆም ያስፈልጋል። መንግሥትም ይህን ድርጊት በበላይነት የሚመሩትን አካላት በመለየት የማስቆም ሥራ የሚሰራበትን አካሄድ እየተከተለ ይገኛል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ላይ የካቢኔ ሚኒስተሮችን የመሰየሙ ሂደት ቀላል እንዳልነበረ አመልክተዋል። ሃያዎቹን ሚኒስትሮች ለመሾም የተደረገው ሥራ በርካታ ትግሎች የተካሄደበት በፈታኝ ሂደት ውስጥ ማለፉን ገልፀዋል።