የሰራዊት አባላቱ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውይይት

የፎቶው ባለመብት, FITSUM AREGA TWITTER PAGE
በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ ሰሞኑን በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ በተለያዩ ግዳጆች ላይ ተሰማርተው የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት የልዩ ሃይል አባላት ተወያይተዋል።
የሰራዊት አባላቱ የሚያገኙት ዝቅተኛ ክፍያ ህይወታቸውን ለመምራት አዳጋች ስለሆነ በዚህ ረገድ የመከላለከያ ተቋማዊ አሰራር ሊፈተሽ እንደሚገባው አሳስበዋል።
ከውይይቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል መወያየት እንደፈለጉና የወደፊት ዕጣፈንታቸውንና በዘላቂነት መፈታት ስላለባቸውና ጉዳዮችም እንደተወያዩ ተናግረዋል።
"በውይይታችን ያነሱት ነገር እኛ ለሀገራችን፣ ለባንዲራችን ዛሬም እንደ ትናትናው የገባነውን ቃልም ሆነ ሀገራችንን እንጠብቃለን። ኑሯችን ግን ጉዳት አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ በደላችንን አያውቅም። በየቦታው እየሞትን እየቆሰልን እንደ ጠላት ወታደር እንታያለን። ደሞዛችን አነስተኛ ነው። ህዝባችን ካልረዳን እንቸገራለን" እንዳሉ ገልፀዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሰሞኑን በተሰማሩባቸው አካባቢዎች በቡራዩ የአካባቢው ህዝብ በምግብ እንደረዳቸው ገልፀው፤ በሌሎች አካባቢዎች ተሰማርተው የነበሩት ግን ለሀያ ቀናት ያህል በቂ ምግብ እንዳላገኙ እንደነገሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ውይይቱ በአጠቃላይ ጠቃሚ እንደነበረም ተናግረዋል።
የሰራዊት አባላቱ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ላይ በቂ ክፍያ እንደሌለ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዋናው አላማችን ወጪ ቆጥበን ወደ ልማታዊ ሀብት ማዞር ነው። እኛ ደመወዛችንን ከፍ አድርገን ከበላነው ልማት የሚባል ነገር የለም። ሁለት አማራጭ አለን። ያለንን ሀብት ከፍተኛ ደመወዝ እየበላን ልማታዊ ነገር ማቆም። በዘላቂነት የሚያድግ አገር አንፈጥርም። ትንሽ ተጎድተን ዋጋ ከፍለን የተሻለ አገር መፍጠር ይቻላል። የዚህ ችግር ዳፋ መከላከያንም ይመለከታል" ብለዋል።
የሰራዊቱንም ሆነ የሌሎች ዘርፎች አባላት ክፍያ የሚሻሻልበት መንገድ ጥናት እንደሚደረግ የተናገሩ ሲሆን ዋናው ትኩረት ሀብት ሰብስቦ ልማት ላይ ማዋልና የህዝቡን ህይወት ማሻሻል እንደሆነም ተናግረዋል።
በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲሰራጭ የነበረው መረጃ እውነተኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል። "መሳሪያ ይዘዋል። አንድም ጥይት የተኮሰ ሰው የለም። ሰላማዊ ነበር። መከላከያ ማሻሻል የሚገባውን በዝርዝር ጠቃሚ መረጃዎች አጋርተውኛል። ዋና ፍላጎታቸው በኔ መደመጥ ነው" ብለዋል።












