የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ ተጠናቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Yemedemerguzo
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አህመድ ''ግንቡን እናፍርስ፤ ደልድዩንም እንገንባ'' በሚል መሪ ቃል እያደረጉት ያለው የአሜሪካ ጉዞ ዛሬ በሚኒሶታ በሚያደርጉት ጉብኝት ይጠናቀቃል።
እስካሁን በነበራቸው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለዓመታት በአሜሪካና በኢትዮጵያ ተከፋፍለው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ሲኖዶሶች ጋር ተገናኝተዋል። ሁለቱ ሲኖዶሶች ተዋህደው ለመስራት መስማማታቸው ይታወሳል።
ባሳለፍነው ዓርብ በአሜሪካ ከሚገኙ የፖለቲካ ፖርቲዎች ጋርም ውይይት አድርገው ነበር። በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን በጠቅላይ ሚንስትሩ መልስ ተሰጥቶባቸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በተሳታፊዎቹ የቀረቡትን ጥያቄዎች መመለስ ከመጀመራቸው በፊት ''አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ጊዜ ተወስዶባቸው ልንመክርባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው። የእራሴን ምልከታ ብቻ የማሳይባቸውን ጥያቄዎች ግን እመልሳለሁ'' ብለው።
ሁሉን አቀፍ የሆነ አገራዊ ጉባኤ ይዘጋጅ
አገራዊ መግባባት ሊያመጣ የሚችል የፖለቲካ ምሁራንና የሚመለከታቸውን ተቋማት የሚያሳትፍ ጉባዬ እንዲዘጋጅ ጥያቄ ካቀረቡ ተወካዮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር መስፍን አብዲ የሁሉን አቀፍ የአገራዊ መግባባት ኮሚቴን ተወካይ ናቸው።
ከዶ/ር መስፍን በተጨማሪም ብሩህ የሚባል ድርጅትን ወክለው የተገኙት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ጉባዬ ማካሄድ አገራዊ ፍይዳው ላቅ ያለ ነው ብለዋል። ከእሳቸው በተጨማሪ የብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤትን ወክለው የተገኙት ግለሰብም ሀሉን አቀፍ ህዝባዊ የምክክር አገራዊ ጉባኤ ይካሄድ በማለት ተመሳሳይ ጥያቄ አቀርበዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩም በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሲሰጡ ''በየቀኑ ሰው በሚሞትበት አገር ውስጥ እየኖርን ዕርቅ አያስፈልግም ማለት እንችልም። ነገር ግን እርቁን እንዴት ማድረግ እንችላለን የሚለው ላይ ትኩረት መሰጠት አለባት'' ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጨምረው እንደተናገሩት ''ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠበኛው እኩል ሽማግሌው በዝቷል። ሽምግልና ንግድ እየሆነ መጥቷል። በዚህም ሽማግሌ ዋሽቶ አያጣላም እንጂ እያስታረቀ አይደለም'' ያሉ ሲሆን ''እኔ ይበጃል የምለው በቅድሚያ መሰረታዊ የሆኑ ልዩነቶቻችንን ማጥበብ አለብን ከዚያም የተቀሩ ልዩነቶቻችንን መፍታት እንችላለን'' ብለዋል።
የፌደራል ሥርዓት አያስፈልግም
ፌደራላዊውን የመንግሥት ሥርዓትን ከነቀፉ ተወካዮች መካከል አንዱ የአማራ ህልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን ወክለው የተገኙት አቶ ተክሌ የሻው ናቸው። አቶ ተክሌ ኢትዮጵያን በዘር ከፋፍሎ መመራት አይበጃትም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ ''የፌደራል ሥርዓቱን እንናደው ከማለታችን በፊት ለኢትዮጵያ ምን አይነት የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልጋታል የሚለውን ለይተን ማወቅ አለብን'' በለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የማንነት ጥያቄዎች ላለፉት 40 ዓመታት ሲነሱ መቆየታቸውን በማስታወስ አገሪቱ ያስፈልጋታል የሚባሉት የፖለቲካ ሥርዓት በጥናት መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል።
የሽግግር መንግሥት ይቋቋም
በርካታ የውይይቱ ተሳታፊዎች የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጥያቄ አቅርበዋል። ከእነዚህም መካከል አንዱ የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄን ወክለው የተገኙት አቶ ኦማን ጎራ ናቸው። ፓርቲያቸው በትጥቅ ትግል ላይ አሥመራ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጥያቄ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ለሚሉት ጥያቄዎች መላሽ ሲሰጡ ''እኔ በሽግግር መንግሥት ሃሳብ አላምንም። ምክንያቱም ሁሉም መንግሥት የሽግግር መንግሥት ነው። ቆይታው አምስት ዓመት ብቻ ነው'' ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ፤ ''የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚልው ጥያቄያችሁ ከዚህ በፊት የነበሩት መሪዎች ከስልጣናቸው አልነሳ እያሉ ስላስቸገሯችሁ ስጋት ገብቷችሁ የምታነሱት ጥያቄ ነው'' ሲሉ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ቢባል እንኳ ሽግግሩን ሊያቀላጥፍ የሚችል መንግሥታዊ መዋቅር እና ተቋማት እንደሌለም ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል።
የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ያስፈልጋል
አቶ ደጀኔ አያሌው መድህን የተባለን ድርጅትን ወክለው የተገኙ ሲሆን የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ እንዲኖር ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩም የፕሬስ፣ የምርጫ ቦርድ እና ፍርድ ቤቶች የተመለከቱ ሕጎችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ ካመኑ በኋላ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የፕሬስ ሕጉን ማሻሻል ስለማስፈለጉ እያነሱ ባሉበት ወቅት ነበር ኢኤንኤን የተባለው የሚዲያ ተቋም የመንግሥት ንብረትን ለድርጅቱ ሥራ ማስፈጸሚያነት ይጠቀም እንደነበር የተናገሩት። ''ኢኤንኤን የግለሰቦች ልሳን ነበር። መንግሥት ለእንዲህ አይነት የሚዲያ ተቋም ድጋፍ አያደርግም'' ሲሉም ተደምጠዋል።
ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ይረጋገጥ
ከተሳታፊዎች ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ሌላኛው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲረጋገጥ የሚጠይቀው ይገኘበታል። ጠቅላይ ሚንስትሩም ''እኔ የማረጋግጥላችሁ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይሰፍናል። ይህንንም በተግባር ትመለከቱታለችሁ'' ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አንድ ሆነው ወደ አገር ተመልሰው ኢህአዴግን እንዲፈታተኑም ጋብዘዋል።
ሌሎች ጥያቄዎች
ኢሕአፓን ከመሰረቱት መካከል አንዱ ነኝ ያሉት አቶ በላይነህ ንጋቱ፤ ኢሕአፓ አገር ውስጥ ገብቶ መንቀሳቀስ እንደሚፈልግ ከተናገሩ በኋላ የፓርቲያቸው አባላት ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ እንደተሰወሩ እና እስከሁን ድርስ የት እንዳሉ እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአቶ በላይነህ ምላሻቸውን በሰጡበት ወቅት ኢሕአፓ እንደማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ወደ አገር ቤት ተመልሶ የፖለቲካ ምህዳሩን መቀላቀል እንደሚችል አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ተሰውረዋል ስለተባሉት የፓርቲው አባላት ጉዳይ ምላሽ ሲሰጡ ''እነሱ የኢሃፓ አባላት ብቻ አይደሉም ኢትዮጵያዊያንም ጭምር ናቸው። ጉዳዩን እንመለከተዋለን'' ብለዋል።
ከኢሮብ ብሔረሰብ እንደመጡ የተናገሩት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ተወካዩ፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ የድንበር ጉዳይ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ይሰራ ብለው ጠይቀው ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩም የደንበር ጉዳይ ሁለተኛ ነገር ነው። ከድንበሩ በፊት የህዝብ ለህዝብ ግነኙነት መቅደም አለበት ብለዋል።
እስካሁን ስለደንበር ጉዳይ ከኤርትራ ጋር የተወሰነ ነገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ''ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን የሚመለከተው የፌደራል መንግሥቱን ነው። የፌደራል መንግሥቱን የሚመራው ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትሩ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይወክለኛል እስካሉ ደረስ ለእኔ ይተዉት'' ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ እያደረጉት ባለው ጉብኝት ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝድነት ማይክ ፔንስ፣ ከዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኃላፊ ክርስቲያን ላጋርድ ጋርም ውይይት አካሂደዋል።
ይህ ጉብኝት የተሳካ እንዲሆን በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዋሽንግተን ከሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ እና ሎስ አንጀለስ ከሚገኘው የኢፌዲሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት ጋር ተባብረው እየሰሩ ነው ሲል የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ቢሮ አሳውቋል።














