በወልዲያ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ ሁለት ሰዎች ሞቱ

በወልዲያ ማረሚያ ቤት ትናንት በተነሳ የእሳት ቃጠሎ ሁለት ታራሚዎች ሲሞቱ ሦስቱ ላይ ደግሞ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደረሰ።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አንድ ታራሚ በወልዲያ ሆስፒታል ህክምና አግኝቶ ማታውኑ ሲመለስ አንዱ በሆስፒታል ተኝቶ እየታከመ ይገኛል። ሌላኛው ታራሚ ግን ጉዳቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ወደ ደሴ ሆስፒታል ለተሻለ ህክምና ተልኳል በማለት የወልዲያ ማረሚያ ቤት አዛዥ ኮማንደር ፈንታው ደሳለኝ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዛሬ ማለዳ በድጋሚ ታራሚዎች የምህረት አዋጁ እኛን ለምን አላካተተንም በሚል ግርግር ለማንሳት የሞከሩ መሆናቸውን አንስተው፤ ነገር ግን ገብተው እንዳነጋገሯቸውና አሁን በማረሚያ ቤቶቹ መረጋጋት መታየቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በቃጠሎው ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች ጥገና በማድረግ ላይ እንደሆኑም ማወቅ ችለናል።

በተመሳሳይ ትናንት ሐምሌ 18 ቀን 2010 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በመቀሌ ማረሚያ ቤት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ሁለት እስረኞች መሞታቸውንና ሌሎች መጎዳታቸውን የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ኮማንደር ይትባረክ አለነ ለቢቢሲ እንደገለፁ መዘገባችን ይታወሳል።

ማክሰኞ ዕለት ግርግርና ቃጠሎ አጋጥሞት የነበረው የደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤትም በዛሬ ጠዋት የተቃውሞና ግርግር አዝማሚያዎች እንደነበሩና የአካባቢው ሽማግሌዎች ወደ ማረሚያ ቤቱ በመግባት ታራሚዎቹን በማነጋገር ለማረጋጋት ጥረት እንዳደሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።