አፍሪካ የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት አዲስ አሰራር እንዲኖር ትፈልጋለች

የአለም ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, Eduardo Parra

ሞሮኮ የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ተወዳድራ አለማሸነፏን ተከትሎ አፍሪካዊያን ፊፋ ውድድሩን ለማስተናገድ የሚሰጠው ዕድል በዙር እንዲሆን እንደሚፈልጉ አሳወቁ።

የሰሜን አፍሪካዊቷ ሃገር ሞሮኮ ከስምንት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ በጥምረት ከቀረቡት ከካናዳ፣ከሜክሲኮና ከአሜሪካ ጋር ተወዳድራ ረቡዕ እለት 134 ለ 64 በሆነ ድምፅ ተሸንፋለች።

በዚህ ውጤት ያልተደሰቱት አፍሪካዊያን ውድድሩን ለማዘጋጀት ሌላ አማራጭ አቅርበዋል። "ውድድሩ በዙር እንዲዘጋጅ ማድረግ መፍትሄ ነው" ሲሉ የማላዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዋልተር ኒያሚላንዱ ተናግረዋል።

ቀጣዮቹን የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከተደረጉት 23 ውድድሮች መካከል በአፍሪካ ውስጥ የተዘጋጀው አንድ ብቻ መሆኑ ጥያቄን አስነስቷል።

ከስምንት ዓመታት በፊት ደቡብ አፍሪካ ያዘጋጀችው በአፍሪካ ምድር የተስተናገደው የዓለም ዋንጫ ዕድል የተገኘው ፊፋ በዙር ውድድሩን የማዘጋጀት አሰራርን ፈቅዶ ስለነበር ነው።

ይህም ደቡብ አፍሪካ ውድድሩን ለማዘጋጀት ከጀርመን ጋር ተፎካክራ በጠባብ የድምፅ ልዩነት ከተሸነፈች በኋላ በወቅቱ የፊፋ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴፕ ብላተር እድሉ በዙር እንዲሰጥ ካስወሰኑ በኋላ ነበር።

ግፊቱ የሚቀጥል ከሆነ ፊፋ አስተናጋጅነቱን ለአህጉራት በዙር የመስጠቱን ጉዳይ መልሶ ሊያጤነውና ተግባራዊ ሊያደርገው እንደሚችል እየተነገረ ነው።

"የዓለም ዋንጫ ማለት እግር ኳስን ወደ ህዝቡ መውሰድ ማለት እስከ ሆነ ድረስ ፊፋ ይህንን ሃሳብ ይቀበለዋል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ አንድ የአፍሪካ እግር ኳስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ለቢቢሲ ስፖርት ተናገረዋል።

"በዓለም ዙሪያ በሃገራት መካከል የደረጃ ልዩነት አለ፤ ስለዚህም ይህንን ውድድር በዙር እንዲዘጋጅ ለማድረግ የሚያስችል ህግ ማውጣት ያስፈልጋል። በምርጫው ወቅት ሞሮኮ ያገኘችው ድምፅም ይህንን ያሳያል" ሲሉም አክለዋል።

ሞሮኮ በሦስቱ የሰሜን አሜሪካ ሃገራት ጥምረት በከፍተኛ ድምፅ ተበልጣ የዓለም ዋንጫን ከማስተናገድ ውጪ ከሆነች በኋላ፤ በድምፅ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የነበሩ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት ልኡካን በዚህ ሁኔታ አህጉሪቱ ውድድሩን የማዘጋጀት እድል ታገኝ ይሆን? የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባቸዋል።