ማዱሮ የቬንዝዌላ ምርጫን አሸነፉ

ማዱሮ የቬንዝዌላ ምርጫ አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ምንም እንኳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው ፍትሃዊ አይደለም ብለው ቢወቅሱም የቬንዝዌላው ፕሬዝደንት ኒኮላስ ማዱሮ በሃገራቸው የተደረገውን ምርጫ በማሸነፍ ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት መንበረ-ሥልጣኑን መቆጣጠር ተቆጣጥረዋ።

የምግብ እጥረት ምጣኔ ሀብቱ ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ እየጎለበተ በመጣበት ወቅት የተካሄደው ምርጫ 46 በመቶ ያክል ሰው ብቻ ለምርጫ እንደወጣ እየተዘገበ ነው።

ቀንደኛ ተቃዋሚ የሆነው ሄንሪ ፋልኮን የተባለ ግለሰብ ምርጫው በተጠናቀቀ ሰዓታት ልዩነት ውጤቶቹ ተቀባይነት የላቸውም በማለት አውግዟል።

"የምርጫ ሂደቱ ትክክለኛውን መንገድ የተከተለ አይደለም፤ ቬንዝዌላ ሌላ ምርጫ ያስፈልጋታል" ሲልም ተደምጧል።

ከተሰበሰው ድምፅ 90 በመቶ ያክሉ በተቆጠረ ሰዓት የ55 ዓመቱ ማዱሮ 67.7 በመቶ ድምፅ እንዳመጡ የተዘገበ ሲሆን ተቃዋሚው ሄንሪ ደግሞ 21.2 በመቶ ድምፅ እንዳመጡ የሃገሪቱ የምርጫ ምክር ቤት አስታውቋል።

የምርጫው አሸናፊ መሆናቸው የተነገረላቸው ማዱሮ "ተንቄ ነበር" ሲሉ ድላቸውን ለመጋራት ካራካስ ከተማ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የትራምፕ አስተዳደር የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበለው በተወካዩ በኩል ግልፅ አድርጓል።

የቬንዝዌላ ምርጫ በአውሮፓውያኑ ወርሃ ታህሳስ 2018 ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም የሃገሪቱ ምርጫ ጉባዔ ለማዱሮ ደጋፊዎች ሲባል ቀደም ብሎ እንዲከናወን መደረጉን አስታውቋል።

ተፎካካሪው 'ዴሞክራሲያዊ አንድነት' ፓርቲ የምርጫው ከቀጠሮ ቀደም ብሎ መካሄድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ ጫና ለማሳደር ታቅዶ የተደረገ ነው ሲል ይኮንናል።

በሁጎ ቻቬዝ ዘመነ መንግሥት ሥልጣን ላይ የነበሩት እና ከገዥው ሶሻሊስት ፓርቲ የዛሬ 8 ዓመት ገደማ የተገነጠሉት ሄንሪ ፕሬዚዳንት ማዱሮን በእጅጉ ይፈትናሉ ተብለው ሲጠበቁ እንደነበረም አይዘነጋም።

"እመኑኝ አብዛኛው የቬንዝዌላ ሰው ማዱሮን ሥልጣን እንዲለቁ አጥብቆ ይፈልጋል" ብለዋል።

ቬንዝዌላ ወደ ቀውስ ከገባች ሰሞን አንስቶ የሃገሪቱ ምጣኔ ሃብት እያሽቆለቆለ ያለ ሲሆን የዋጋ ግሽበቱም ጣሪያ መንካቱን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

አልፎም በርካታ ሺዎች ሃገራቸውን በመተው እንደብራዚልና ኮሎምቢያ ወደመሳሰሉ ጎረቤት ሃገራት መሰደድ ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል።