ካለሁበት 30፡ መስቀል እና አረፋን ሳስታውስ ውስጤ ይረበሻል

ስሜ አሸናፊ ተስፋዬ ይባላል፡፡በአሁኑ ወቅት በደቡባዊ አፍሪካ ክፍል በምትገኘው አንጎላ በመኖር ላይ እገኛለሁ። ከኢትዮጵያ ወጥቼ አንጎላ እስክደርስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ የተለያዩ ፈታኝ ሁነቶችን አልፌለሁ።

ከጋዜጠኝነት ወደ እስረኝነት

ሀገር ቤት በነበርኩበት ወቅት በፋና ሬዲዮ ውስጥ በጋዜጠኝነት አገለግል ነበር። በ2004 ዓ.ም የተሻለ ኑሮን በመሻት የመጀመሪያ ጉዞዬን ወደ ሱዳን ካርቱም አደረግኩ። የካርቱም ኑሮዬ ብዙ ሳይገፋ ‹ኡምዱርማን› በተባለ እስር ቤት ውስጥ ለአንድ ወር ያህል ያቆየኝ ክስተት ተፈጠረ። በዚህ እስር ቤት ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ዜግነትህን እንድትጠላ የሚያደርግህ ቦታ ነው።

የእህቴ ባለቤት ኤፍሬም ገ/እዝጊ ዋስ ሆኖ እና የሚከፈለውን ከፍሎ ከኡምዱርማን እስር ቤት ከወጣሁ በኋላ "አንጎላ ለሥራ ጥሩ ነው" ሲባል እሰማ ስለነበር ወደዚያ ለማቅናት ወሰንኩ።

ወደ አንጎላ ለማምራት በማሰብ መተላለፊያ እንድትሆነኝ ወደ መረጥኳት ኬንያ በረርኩ። ሆኖም ጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ማረፊያ በደረስኩ ጊዜ የያዝከው ቪዛ ህጋዊ አይደለም በሚል ለድጋሚ እስር ተዳረግኩ። ኬንያ ውስጥ ለአምስት ቀናት ያህል ታስሬያለሁ።

ከሰግባት ካሾፉ የሚጠፉባት ሀገር

እግዚአብሔር አሳክቶሎኝ በድጋሚ ከተፈታሁ በኋላ ወደ አንጎላ አቀናሁ። በዚህ ሀገር ውስጥ ከሌሎች ሀገራት የመጡ ስደተኞች ይኖራሉ። በርከት ያሉ ኤርትራዊያን እና ጥቂት የማይባሉ ኢትዮጵያዊን ኑሯቸውን በዚህች ሀገር ውስጥ ይመራሉ።

ኢትዮጵዊያን እና ኤርትራዊያን ተፈቃቅረው የሚኖሩበት ቦታ ነው። የሁለቱ ሃገራት ዜጎች በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ብዙ ጊዜ አንድ "ሀበሻ መጣ!" ሲባል ሥራ የሚጀምረው ከኤርትራዊያን ጋር አብሮ በመስራት ነው፡፡

ከኤርትራ የመጡ ዶክተሮች፣ ከኢትዮጵያ የመጡ እንጂነሮች እዚህ ሱቅ በሱቅ ውስጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው ሊገኙ ይችላሉ። አንጎላ ከሰራህ የምታድግባት ካሾፍክ ደግሞ የምትገደልህ ሀገር ናት፡፡

አንጎላ ውስጥ እየኖርኩ ያለሁት ከባለቤቴ እና ከአንድ ልጄ ጋር ነው። የምተዳደረው ፎቶ በማንሳትና ሠርግና የመሳሰሉ ዝግጅቶችን ቪዲዮ በመቅረጽ ነው። ይሄን የማከናውነው 'አሹ' በሚሰኝ ስቱዲዮዬ በኩል ነው፡፡

ከቦም ዲያ እስከ ፉንጂ (አንጎላን በጥቂቱ)

ሞቃት የአየር ንብረት ያላት አንጎላ ህዝቦቿ ሰው አክባሪና ቂም የማይይዙ ናቸው። አንዳንዴ በጥቅማቸው ከመጣህ ግን እስከ መግደል የሚያደርስ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።

የመግባቢያ ቋንቋቸው ፖርቹጊዝ ነው፣ 'ቦን ዲያ' ማለት እንደምን አደርክ፣ 'ቦአ ታርድ' ማለት ደግሞ እንደምን ዋልክ ማለት ሲሆን፣ 'ቦን ናይት' ደግሞ ደህና እደር እንደምንለው ዓይነት ነው።

የኢትዮጵያ ምግብ አንጎላ ውስጥም ይገኛል። በጤፍ ቦታ ሩዝና ስንዴ ተፈጭቶ ለእንጀራነት ይውላል። ሽሮ እና በርበሬ ከኢትዮጵያ አሊያም በቅርባችን ካለችው ደቡብ አፍሪካ እንዲመጣ እንደርጋለን። ሆኖም አንጎላዊያንም ጣፋጭ ምግብ አላቸው። ተወዳጁ ምግብ ፉንጂ ይባላል፣ ፉንጂ እንደ እኛ ሀገር ገንፎ ያለ ሲሆን ከበቆሎ ዱቄት ነው የሚሰራ።

የሀገር ናፍቆትና ህልም

ከሀገሬ ብዙ ነገር ይናፍቀኛል። በጉራጌ ማህበረሰብ ባህል እንደማደጌ መስቀል በጣም ይናፍቀኛል፣ ግርግሩ፣ ባህሉ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት እየተጠራራን የምናደርገው ነገር የኢትዮጵያዊነት ፍቅር ደስ ይለኝ ነበር።

በጋዜጠኝነት ህይወቴ ወቅት 'አሸናፊ ጉራጌ ነው' ተብሎ ነበር የመስቀል መሰናዶዎችን እንድዘግብ በዚያውም ወደ ቤተሰብ እንድሄድ የሚደረገው ነገርም ይታወሰኛል። መስቀል እና አረፋን ሳስታውስ ውስጤ ይረበሻል።

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በጋዜጠኝነት ህይወቴ በተለይ በመስሪያ ቤት ውስጥ የነበሩ አስቂኝ ትውስታዎች ይመጡብኛል። አንዳንዶቹንም ሳስታውስ ፈገግ ያሰኙኛል። አንደኛው ከአነስተኛ ደሞዛችን አንጻር የምናዘወትረው 'አደይ አበባ' የሚባለው ምግብ ነው።

ምግቡ 'አደይ አበባ' የተባለው ብዙ የእንጀራ ፍርፍር ላይ ለናሙና ያክል ሁለት እንቁላሎች ተፈርፍረው ስለሚነሰነሱበት ነው፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቃል የተናገሩትን በተግባር የሚደግሙት ከሆነና በሀገራችን የእኩልነት መንፈስ የሚመጣ ከሆነ፣ ወደ ሀገሬ ተመልሼ የምወደውን ሥራ መቀጠል እፈልጋለሁ። የራሴን የአየር ሰዓት ገዝቼ አሊያም የራሴን ስቱዲዮ አቋቁሜ የጋዜጠኝነት ሥራዬን ለመቀጠል፣ በፊልም ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ህልምም አለኝ።

በጋዜጠኝነት ዘመኔ ሕይወት በየፈርጁ የሚባል መሰናዶ ነበረኝ። የመቃብር ቆፋሪዎችን፣ የምሽት ቤት ጠበቂዎችን(ጋርዶችን)፣ የሌሊት የታክሲ ሾፌሮችን የመሳሰሉ ብዙ ታሪካቸው ያልተገለጡ ሰዎችን ህይወት አስፍቼ የማሳየቱ ህልምም አለኝ።

ማን ያውቃል የተሰደድን ጋዜጠኞች የእኛ የምንለው ሬዲዮ ጣቢያ ይከፈትና ያለምነውን የምንሰራበት ዘመን ይመጣል። እስከዚው ድረስ የእኛ ሰው በአንጎላ በሚለው ገጼ በኩል ሥራዎቼን እያጋራሁ እቆያለሁ፡፡

በቸር ያገናኘን

ለሐብታሙ ስዩም እንደነገረው

የ'ካለሁበት' ቀጣይ ክፍሎችን ለማግኘት ፦