የዚምባብዌ ጦር ገዢው ፓርቲ ላይ በሚደረገው ጣልቃ ገብነት ላይ ማስጠንቀቂያ ሰጠ

Zimbabwe Army General Constantino Chiwenga Commander of the Zimbabwe Defence Forces addresses a media conference held at the Zimbabwean Army Headquarters on November 13, 2017 i

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የዚምባብዌ ጦር ኃላፊ ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ

የዚምባብዌ የጦር ኃላፊ የሃገሪቱ ገዢ ፓርቲን ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ ካልሆነ ደግሞ ጦሩ ጣልቃ እንደሚገባ አስጠነቀቁ።

ብዙም ያልተለመደው የጣልቃ ገብነት ጉዳይ የተከሰተው ሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ምክትላቸው ኤመርሰን ምናንጋግዋን ከስራ ካሰናበቱ በኋላ ነው።

ከ90 ስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለጋዜጣዊ መግለጫ የቀረቡት ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የማንንም ስም አልጠቀሱም።

የሙጋቤን ቦታ ሊተኩ ይችላሉ ሲባል የነበሩት ምናንጋግዋ ሸሽተው ሃገሪቱን ጥለው ወጥተዋል።

አሁን የፕሬዝዳንት ሙጋቤ ባለቤት ግሬስ ሙጋቤ ባለቤታቸውን ለመተካት ቅድሚያውን አግኝተዋል። ምናንጋግዋንም "ጭንቅላቱ ሊደበደብ የሚገባ እባብ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ባላቸው ብልህ አስተሳሳብ "አዞው" በሚል ስም የሚታወቁት ምናንጋግዋ "ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ያንተና የሚስትህ እንደፈለጋችሁ የምታደርጉት የግል ንብረታችሁ አይደለም" ሲሉ ሙጋቤን ተችተዋል።

በጦሩ ዋና መስሪያ ቤት መግለጫ የሰጡት ጄነራል ቺዌንጋ፤ በነጻነት ትግሉ ውስጥ የነበሩ እና እንደምናንጋግዋን ያሉ ሰዎችን ማባረር በትዕግስት የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም ብለዋል።

President Robert Mugabe's wife Grace Mugabe and vice-President Emmerson Mnangagwa attend a gathering of the Zanu-PF party's top decision making body, the Politburo, in the capital Harare, Zimbabwe, February 10, 2016

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግሬስ ሙጋቤና ምክትል ፕሬዝዳንት ኤመርሰን መናንጋግዋ ቀጣይ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ ሲባል ነበር

"በነጻነት ትግሉ ውስጥ ያለፉና እና የፓርቲው አባላት የሆኑት ሰዎች ላይ ያነጣጠረው የማባረር ስራ መቆም አለበት" ብለዋል።

"ከአሁኑ ስራ ጀርባ ያሉ ሰዎች ሊገነዘቡት የሚገባው ጉዳይ አብዮታችንን በተመለከተ ጦሩ ጣልቃ ከመግባት ወደኋላ አይልም" ብለዋል።

ምናንጋግዋ ቀደም ሲል የመከላከያ እና የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

ሙጋቤ በበኩላቸው "ጀነሬሽን 40" (የአርባዎቹ ትውልድ) የሚባለው የዚምባብዌ ወጣት ፖለቲከኞች ድጋፍ አላቸው።

በፖለቲከኞች መካከል ያለው እሰጣ አገባ "ሃገሪቱ ላላፉት አምስት ዓመታት የተጨበጠ ዕድገት እንዳታስመዘግብ አድርጓታል" ሲሉ ጄነራል ቺዌንጋ ተናግረዋል።

በችግሩ ምክንያት ዚምባብዌ "በገንዘብ እጥረት፣ ግሽበትና በሸቀጦች ዋጋ መጨመር" እንድትሰቃይ አድርጓታል።