ትራምፕ ስደተኞችን ለማባረር አዲስ ዕቅድ እያቀዱ ነው

የትራምፕ አስተዳደር በሜክሲኮ እና በአሜሪካ መካከል ሊገነባ ከታሰበው አጨቃጫቂ አጥር ግንባታ ጀምሮ ሕጋዊ መኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ታዳጊ ስደተኞችን ከሃገሪቱ ለማስወጣት የሚያስችል ሰነድ በማርቀቅ ላይ ይገኛል።

ትራምፕ ሕጋዊ መኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውን ስደተኞች የማስወጣት ዕቅዳቸው ይሰምር ዘንድ በሺህ የሚቆጠሩ የስደተኛ ጉዳይ ሠራተኞችን ለመቅጠር አስበዋል።

ባለፈው ወር ፕሬዝደንቱ 'ዳካ' የተሰኘውን ለስደተኛ ታዳጊዎች ድጋፍ የሚሰጠውንና 800ሺህ ስደተኞች አስጠልሏል የሚባልለትን ዕቅድ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የዕቅዱ ይዘቶች

• በሜክሲኮ እና በአሜሪካ መካከል ስደተኞች እንዳይገቡ የሚያግድ አጥር ግንባታ

• 10ሺህ የስደተኛ ጉዳይ ሠራተኞችን እንዲሁም 1ሺህ የሕግ ባለሙያዎችን መቅጠር

• ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዳያመጡ ማገድ

• በኮምፕዩተር በታገዘ ዘዴ ኩባንያዎች ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞችን እንዳይቀጥሩ ማድረግ. . . የሚሉ አንቀፆችን አቅፏል።

'ዳካ' የተሰኘው ለስደተኛ ታዳጊዎች ድጋፍ የሚሰጠው ዕቅድ በቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ዘመን 2012 ላይ በተለይ ደግሞ ከደቡብ አሜሪካ የሚመጡ ሕፃናት ለመጠበቅ ሲባል የፀደቀ ሰነድ ነበር።

በሕጉ ስር የተጠለሉ ታዳጊዎች የትምህርት እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደርጋሉ።

ወርሃ መስከረም ላይ ፕሬዝደንት ትራምፕ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ኮንግረሳቸው አዲስ ተለዋጭ ዕቅድ ካላመጣ የታዳጊዎች ሕልም አደጋ ላይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

አዲሱን የትራምፕ ዕቅድ ቀዳሚ ተሠላፊ ዴሞክራቶች በጽኑ ተቃውመውታል።

ዴሞክራቷ ናንሲ ፔሎሲ እና አጋራቸው ቻክ ሹመር "አመራሮች ሕልመኛ ታዳጊዎችን የሚታደግ ዕቅድ በማርቀቅ ፈንታ ግድ የሌሽነትን የሚንያንጸባርቁ ሕጎችን ማርቀቅ ከጀመሩ፤ እኔ ከልባቸው ነው ብዬ አላስብም" ሲሉ ትችታቸውን አሰምተዋል።

ከ30 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መረጃዎቻቸውን ለሃገር ውስጥ ደህንነት እና ለኤፍ.ቢ.አይ በማስረከብ በሕጉ ለመጠለል ብቁ መሆን አለመሆናቸውን ያረጋግጣሉ።