በሺዎች የሚቆጠሩ የቦኮ ሃራም ተዋጊዎች ናይጄሪያ ውስጥ እጃቸውን ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ባለፉት ሳምንታት ውስጥ የቦኮ ሃራም አዛዦችን፣ ተዋጊዎችን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ 6000 የሚጠጉ የቡድኑ አባላት ለመንግሥት እጃቸውን እንደሰጡ የናይጄሪያ ሠራዊት ገለጸ።
በተጨማሪም በመቶዎች የሚቆጠሩ የቡድኑ ታጣቂዎች እጅ መስጠታቸውን የናይጄሪያ ጎረቤት የሆነው የካሜሩን መንግሥት በቅርቡ አስታውቋል።
የናይጄሪያ ጦር ሠራዊት እንዳለው በአገሪቱ ሰሜናዊ ምሥራቅ አካባቢዎች በቦኮ ሃራም ቡድን ላይ እየተካሄደ ያለው ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃት ታጣቂዎቹ በብዛት እጃውን እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የቦኮ ሃራም መሪ የነበረው አቡበከር ሼካዎ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ መገደሉም ለአባላቱ እጅ መስጠት ሌላኛው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ከመሪው ሞት በኋላ በርካታ የቡድኑ ተከታዮች ለናይጄሪያ መንግሥት እጃቸውን ሰጥተዋል ካልሆነ ደግሞ ወደ ተቀናቃኙ የአይኤስ የምዕራብ አፍሪካ ክንፍ - ኢስዋፕ በአባልነት ገብተዋል።
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እጃቸውን የሰጡትን የቡድኑን አባላት በመመዝገብ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከአክራሪ አመለካከት እንዲወጡ የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።
ነገር ግን አንዳንድ ናይጄሪያውያን ተዋጊዎቹ ወደ ኅብረተሰቡ መልሰው መቀላቀላቸውን በተመለከተ ሊኖሩ የሚችሉ አደጋዎችን በመጥቅስ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት እንቅስቃሴውን ከአስር ዓመት በፊት በጀመረው ቦኮ ሃራም ጥቃት ሳቢያ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል።
የቡድኑ እንቅስቃሴ ናይጄሪያን ጨምሮ በጎረቤት አገራት ውስጥ የተስፋፋ ሲሆን በቻድ ሐይቅ ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።
ቦኮ ሃራም በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀስ ጽንፈኛ ቡድን ሲሆን በተለይ በትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃት በመፈጸም በተደጋጋሚ ተማሪዎችን ጠልፎ በመውሰድ ይታወቃል።













