የቦትስዋናው አልማዝ በዓለም ሦስተኛው ትልቁ ሊሆን ይችላል ተባለ

አልማዝ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የዓለማችን ሦስተኛው ትልቅ አልማዝ ነው ተብሎ የሚታመነው ማዕድን በቦትስዋና ለእይታ በቅቷል፡፡

1,098 ካራት ክብደት ያለው ይህ የከበረ ድንጋይ ለፕሬዚዳንት ሞክዌትሲ ማሲሲ ለእይታ የቀረበ ሲሆን ደብስዋና በተሰኘ የአልማዝ ኩባንያ ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር በቁፋሮ የተገኘው፡፡

ይህኛው የከበረ ድንጋይ በተመሳሳይ ቦትስዋና ውስጥ እአአ በ2015 ከተገኘው ከሁለተኛው ትልቁ አልማዝ በጥቂቱ ነው የሚያንሰው፡፡

ቦትስዋና በአፍሪካ ትልቋ የአልማዝ አምራች ናት፡፡

"ይህ በደብስዋና ከ 50 ዓመታት በላይ የሥራ ዘመን ትልቁ አልማዝ ነው" ሲሉ የደብስዋና የአልማዝ ኩባንያ ተጠባባቂ ዳይሬክተር የሆኑት ሊኔት አርምስትሮንግ ገልጸዋል፡፡

"በቅድመ-ትንታኔያችን መሠረት ይህ በዓለም ሦስተኛው ትልቁ ጥራት ያለው አልማዝ ሊሆን ይችላል፡፡" ብለዋል

ደብስዋና በመንግሥትና በዓለም አቀፉ የአልማዝ ኩባንያ ደ ቢርስ መካከል በሽርክና የተመሠረተ ሲሆን እስከ 80 በመቶ የሚደርሰው የሽያጭ ገቢው በትርፍ ፣ በሮያሊቲ እና በግብር ለመንግሥት ይሆናል፡፡

የቦትስዋና የማዕድን ሚኒስትር ሌፎኮ ሞአጊ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአልማዝ ዋጋ በማሽቆልቆሉ አልማዙ ለቦትስዋና በጥሩ ጊዜ አልመጣም ብለዋል፡፡

ትልቁ አልማዝ እአአ በ 1905 በደቡብ አፍሪካ የተገኘው እና 3 ሺህ 106 ካራት የሆነው የኩሊንናን አልማዝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እአአ በ 2015 በቦትስዋና የተገኘው እና 1 ሺህ 109 ካራት የሆነው ሌሴዲ ላ ሮና ነው፡፡

በጃዋኔንግ ማዕድን ስፍራ የተገኘው አዲሱ አልማዝ እስካሁን ስም አልወጣለትም፡፡

እስካሁን በደ ቢርስም ሆነ በመንግስት ባለቤትነት በተያዘው የኦካቫንጎ የአልማዝ ኩባንያ በኩል "ብርቅዬ እና ልዩ የሆነው አልማዝ" ይሸጥ የሚለው ውሳኔ እንዳልተሰጠው አርምስትሮንግ ዴ ተናግረዋል፡፡