ኮሮናቫይረስ ፡ ዝነኛው ጃፓናዊ የፋሽን ዲዛይነር በኮቪድ-19 ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፈረንሳይ ውስጥ ዝነኛ የሆኑት ጃፓናዊው የፋሽን ዲዛይነር ኬንዞ ታካዳ በ81 ዓመታቸው ሕይወታቸው አለፈ።
ኬንዞ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ባጋጠማቸው ውስብስብ የጤና ችግር ፓሪስ በሚገኘው የአሜሪካ ሆስፒታል ሕክምና ሲደርገላቸው ቆይቶ ማለፋቸው ተገልጿል።
ዲዛይነሩ 'ኬንዞ' የተሰኘ የፋሽን ብራንድ (መለያ) መስራች ናቸው።
በፋሽን ኢንዱስትሪው ገናና የሆኑትን ዲዛይነር ሕልፈት ተከትሎም በርካቶች ሃዘናቸውን እየገለፁ ነው።
በሚሰሯቸው ውብ ዲዛይኖች፣ ሕትመቶች እና በቀለም አጠቃቀማቸው በፈረንሳይ የፋሽን ጥበብ የመጀመሪያው ዝነኛ ጃፓናዊ ዲዛይነር ነበሩ።
ኬንዞ ፈረንሳይ የከተሙት በጎርጎሮሳዊያኑ 1960ዎቹ ሲሆን ከዚያ በኋላ ሙሉ የሥራ ዘመናቸውን ያሳለፉት በዚያው ነው።
ወደ 8 ሺህ የሚጠጉ ዲዛይኖች ያሏቸው ኬንዞ፤ ከፋሽን ዘርፉ አንዴም ወደ ኋላ ብለው እንደማያውቁ ቃል አቀባያቸው ተናግረዋል።
የፓሪስ ከንቲባ አኔ ሂዳልጎም በዲዛይነሩ ሕልፈት የተሰማቸውን ሃዘን "ጥልቅ ችሎታ ያላቸው ዲዛይነር ነበሩ፤ ለፋሽኑ ዘርፍ ቀለምና ተስፋን የሰጡ ነበሩ። ፓሪስ ከልጆቿ አንዱን በማጣቷ ሃዘን ላይ ነች" ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ላይ ገልፀዋል።
የኬንዞ ብራንድ ባለቤት የሆነው ኤልቪኤምኤች ሥራ አስፈፃሚ ሲዲኒ ቶሌዳኖም "ኬንዞ ሥራውን በጀመረበት በ1970ዎቹ አካባቢ የነበሩት ብራንድ አድናቂ ነበርኩ፤ በጣም ጎበዝ ዲዛይነር ነበር" ብለዋል።
በርካታ ጃፓናዊያንም በትዊተር ገፃቸው ሃዘናቸውን ገልፀዋል። አንዳንዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የነበራቸውን የኬንዞን የቅንጦት ምርት አጋርተዋል።
ከእነዚህ መካከል አንዷ"ከእናቴ የወረስኩት የኬንዞ ሙሉ ልብስ ነበረኝ፤ እስካሁንም ድረስ እለብሰዋለሁ" ብላለች ለምርቶቹ ያላትን ፍቅር ስትገልፅ።
በጎርጎሮሳዊያኑ 1939 በኦሳካ አቅራቢያ የተወለዱት ኬንዞ ታካዳ፤ ምንም እንኳን የፈረንይኛ ቋንቋ እምብዛም መናገር ባይችሉም ወደ ፈረንሳይ ለማቅናት የወሰኑት በ1965 ነበር።
እዚያም በመጀመሪያ ለፋሽን ቤቶች ዲዛይን ይሸጡ ነበር። በኋላ ላይ ግን የራሳቸውን "ጀንግል ጃፕ" የተሰኘ አነስተኛ ሱቅ ከፍተው መስራት ጀመሩ።
"ባለችኝ ትንሽ ገንዘብ የራሴን ሱቅ አሰማመርኳት" ሲሉም ለመጨረሻ ጊዜ ቃለምልልስ ከሰጡበት መገናኛ ብዙሃን አንዱ ለሆነው የደቡብ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ጋዜጣ ስለ ሥራቸው አጀማመር ተናግረዋል።
ዲዛይን የሚያደርጓቸው ልብሶች የጃፓን ዲዛይን ተፅዕኖ ያረፈባቸው ነበሩ። ምክንያታቸው ደግሞ የፈረንሳይ ዲዛይነሮች ይሰሩት የነበረውን መድገም ስለማይፈልጉ እንደሆነ አስረድተዋል።
ኬንዞ በ1971 የዓለም አቀፍ የፋሽን መጽሔት አርታኢዎች በተገኙበት የፋሽን ትርዒት አዘጋጅተው ነበር።
በዚህ ጊዜም ኢሌ በተሰኘው የፈረንሳይ የፋሽን መጽሄት የፊት ገጽ ላይ ወጥተው ነበር።














