ብሪታኒያ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩቅ ደሴት ለመላክ እያሰበች ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ብሪታኒያ የጥገኝነት አመልካች ስደተኞችን የት ላስቀምጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ እየተብሰለሰለች ይመስላል፡፡
ፋይንናንሻል ታይምስ ጋዜጣ አገኘሁት ባለው አንድ የሾለከ መረጃ ከሆነ ለጊዜው ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ጀልባዎችን ጭምር የስደተኞች ማቆያና ቢሮ የማድረግ ሐሳብ አለ፡፡
ስደተኞችን አጭቀው ከፈረንሳይ የሚመጡ ታንኳዎችንም በምን መልኩ ልናስቆማቸው እንችላለን የሚለው ጉዳይ በጥሞና እየታየ ነው፡፡
አውቶቡሶች ሲያረጁ ዳቦ መሸጫ እንደሚደረጉት ሁሉ አሮጌ ታንኳዎች (ferries) የስደተኞችን ጉዳይ ለማየትና ለማቆያነት እንዲውሉ ለማድረግ ዩኬ እያጤነች ነው ተብሏል፡፡
ሪፊዩጂ አክሽን የተሰኘ ድርጅት ባወጣው አንድ አሐዛዊ መረጃ ባለፈው ዓመት ብቻ 35ሺህ 566 ሰዎች በዩናይትድ ኪንግደም የአስጠጉን ማመልከቻ አስገብተዋል፡፡
ይህ ቁጥር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየቀነሰ እንጂ እየጨመረ አልመጣም፡፡ ከፍተኛ የጥገኝነት ጥያቄ ቀርቦ የነበረው ግን በ2002 እንደነሱ አቆጣጠር ሲሆን ያን ዓመት ብቻ 84ሺህ ሰዎች ብሪታኒያ ጥገኝነት አመልክተው ነበር፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የጥገኞችን ጥያቄ የሚያስተናግድበትን ሁሉንም አማራጮች እያየ ነው ተብሏል፡፡
የሌበር ፓርቲ ይህንን ሐሳብ አምርሮ ተቃውሞታል፡፡ ጥገኝነት አመልካቾችን ሥራ ባቆሙ ጀልባዎች እያጎሩ የማንገላታቱን ሐሳብ ‹‹በፍጹም ያልተገባ ድርጊት› ብሎታል፡፡
በአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አንድ ከፍተኛ ኃላፊ ግን በዩኬ የጥገኝነት ጥያቄዎች የምናስተናግድበትን ሁሉንም አማራጮች እያየን ነው ሲሉ ሐሳቡ እንዳለ የሚጠቁም መረጃን ሰጥተዋል፡፡
የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሚኒስትሯ ፕሪቲ ፔተል በበኩሏ የሚመለከታቸውን የበታች ባለሥልጣናት ጥገኝነት አመልካች ስደተኞች ከዩኬ ውጭ ባሉ ቦታዎች ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንዲሠሩ መመርያ ሰጥተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ ታዲያ የስደተኞች ማረፍያ የት ይሁን የሚለው ነው፡፡ አሮጌ ጀልባዎች የታሰቡትን ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ፋይናንሺያል ታይምስ ያወጣው ዘገባ ነገሩን መነጋገርያ አድርጎታል፡፡ ይኸውም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ስደተኞች ራቅ ባሉ ደሴቶች አስቀምጦ ጉዳያቸውን የዩኬን ምድር ሳይረግጡ እንዲከታተሉ የማድረግ ሐሳብ እየተጤነ ስለመሆኑ ዘገባው ያትታል፡፡
ስደተኞችን አርቀን እናስቀምጣቸው የሚለውን ሐሳብ ተከትሎ የት የሚለው ጥያቄ ነው ያልተመለሰው፡፡
አሴሸን ደሴት አንዷ እጩ ናት፡፡ ይቺ ደሴት ከዩኬ ርቃ በአትላንቲክ ውቅያኖስ የምትገኝ ናት፡፡ እንዲያውም ከእንግሊዝ ይልቅ ለብራዚል ትቀርባለች፡፡
ብሪታኒያ ጥገኝነት አመልካቾችን እዚያች ሩቅ ደሴት ልኮ በማቆየት ጥገኝነታቸው አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝ ብቻ የብሪታኒያ ምድር እንዲረግጡ የማድረግ ሐሳብ ሳይኖር አይቀርም ይላሉ የጋዜጣው ምንጮች፡፡
ይህ ሐሳብ በባለሥልጣናት ደረጃ ሲውጠነጠን የመጀመርያው አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም ሐሳቡ ተነስቶ ውድቅ ተደርጎ እንደነበረ ይኸው ጋዜጣው አስታውሷል፡፡
ሆኖም አሁን ሐሳቡ መልሶ እየተንሸራሸረ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ምናልባት ከሥራ ውጭ የሆኑ ጀልባዎች ለስደተኞች አገልግሎት ጉዳዮች የማዋሉ ነገር እየተጤነ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ታንኳዎቹ የስደተኛ መኖርያ ይደረጉ ወይስ የስደተኞች ጉዳይ የሚታዩባቸው ቢሮዎች ዘገባው በግልጽ አላብራራም፡፡
ጋዜጣው ጨምሮ እንዳለው ሌሎች ከስኮትላንድ በብዙ ማይል ርቀው የሚገኙ ደሴቶችን እንደ ስደተኛ ጊዝያዊ ማቆያ የመጠቀሙ ሐሳብ ዳግም እየተጤነ ነው፡፡
የስኮትላንድ ሚኒስትር ኒኮላ ስተርጂዮን ግን ይህን ሐሳብ በትዊተር ሰሌዳቸው ክፉኛ ተችተውታል፡፡ ‹‹ሰዎችን እንደ ከብት የሚመለከትን ማንኛውንም ሐሳብ ውድቅ አደርጋለው›› ሲሉም ዝተዋል፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት የማኅበረሰብ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ስለጉዳዩ የተጠየቁት ማቲው ራይክሩፍ ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣው አገኘሁት ባለው መረጃ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ሆኖም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ሁሉንም አማራጮች እየተመለከተ እንደሆነ አልካዱም፡፡
‹‹ብዙ አገሮች እየተመለቱት ያሉትን አማራጮች እኛም እያየናቸው ነው፡፡ ለጊዜው ምንም ውሳኔ ላይ አልደርስንም›› ብለዋል፡፡ ሆኖም ዩኬ ሁሉንም ዓለም አቀፍ የስደተኛ አያያዝ ደንቦችን ታሟላለች፣ ስጋት ኤግባችሁ ብለዋል፡፡
የሌበር ፓርቲ ተጠሪና የአገር ውስጥ ሚኒስትር ተቆጣጣሪና ተጠባባቂ ሚኒስትር አባል ኒክ ቶማስ ፓርቲያቸው ይሄ ሰዎችን በታንኳዎች የማኖርን ሐሳብ በፍጹም እንደማይቀበለው፤ ሐሳቡም አሳፋሪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጆናና ቼሪ እንደምትለው ደግሞ ስደተኞቹን ከዩናይትድ ኪንግደም አርቆ የማስቀመጥ ሐሳብ እውነት ከሆነ ‹የሰው ልጅን እንደ ከብት ከመቁጠር አይተናነስም፤ እንቃወመዋለን›› ብላለች፡፡
ነገር ግን የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ተወካይ የምክር ቤት አባል አዳም ሆሎዌይ የአገር ውስጥ ሚኒስትር የታንኳም ሆነ የደሴቶችን አማራጭ ማየቱ ትክክልና ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ለምን ሲባሉ ምክንያቱም ስደትን ወደ ዩኬ ለሚያስቡ ሰዎች ተስፋ ያስቆርጣቸዋል ሲሉ መልሰዋል፡፡
የምክር ቤት አባሉ አዳም ለዕውቁ ቢቢሲ ሬዲዮ ፎር ፕሮግራም እንደተናገሩት ‹‹ስደተኞች ወደ እንግሊዝ መሰደድን ሲያስቡ 'ሆቴል አርፈን ጉዳያችን ይታያል፣ እንግሊዝ እየኖርን ሁሉ ነገር እየቀረበልን ተንደላቀን እንቆያለን' የሚለውን አስተሳሰብ መስበር አለብን ብለዋል፡፡
የምክ ቤት አባሉ አዳም ጨምረው እንዳሉት ብሪታኒያ ልክ እንደ አውስትራሊያ ስደተኞችን የማያበረታታ፣ እንዲያውም ተስፋ የሚያስቆርጥ አካሄድን መከተል አለባት፡፡ ይኸውም ከእንግሊዝ ምድር ራቅ ብሎ ወደሚገኙ ደሴቶች ስደተኞችን አርቆ የማስቀመጥ ሐሳብ ነው፡፡ ይህ አሰራር ሊኖራት ይገባ ነበር ብለዋል፡፡
አውስትራሊ በሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ትችትን ያስተናገደ የስደተኞች አያያዝን የምትከተል አገር ናት፡፡ ወደ አገሯ ለመግባት የሚሞክሩ ዜጎችን ናውሩ ደሴት ወይም ፓፓዎ ኒውጊኒ ደሴት ትልካቸዋለች፡፡
በብሪታኒያ ስደተኞችን የት እናድርጋቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ውይይቱ እየተጧጧፈ የመጣው ከጎረቤት አገራት በታንኳ በእንግዝ ቻናል በኩል በአንድ ቀን ብቻ 400 ሰዎች ከገቡበት ከመስከረም ወዲህ ነው፡፡
የአገር ውስጥ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአጎራባች አገሮች በትንንሽ ታንኳዎች ተሳፍረው ወደ ብሪታኒያ የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቆም አዳዲስ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አሳውቋል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ይፋ የሆነ አዲስ የቁጥጥር መንገድ የለም፡፡
በዚህ ዓመት ብቻ 7ሺ የሚሆኑ ስደተኞች 500 በሚሆኑ ትንንሽ ታንኳዎች ተሳፍረው ብሪታኒያ መግባት ችለዋል፡፡
በእንግሊዝ ጥገኝነት ጠያቂዎች ተቀባይነት ለማግኘት ካሻቸው ወደ ትውልድ አገራቸው ቢመለሱ በዘራቸው፣ በማንነታቸው፣ በአስተሳሰባቸው፣ በጾታቸው ወይም በተመሳሳይ ጾታ የፍላጎት ምርጫቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት ከባድ አደጋ እንደሚደርስባቸው መንግሥትን ማሳመን አለባቸው፡፡
የስደተኛ ጉዳይ ቢሮ የአመልካቾችን መረጃዎች ከፈተሸና ከመረመረ በኋላ በ6 ወራት ውስጥ የጥገኝነት ጥያቄው ተቀባይነት ሊሰጥ ወይም ውድቅ ሊያደርግ ይጠበቃል፡፡
ሆኖም የአመልካቾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አሁን አሁን ውሳኔዎች በከፍተኛ ሁኔታ ይዘገያሉ፡፡
የጥገኝነት አመልካቾች ማመልከቻቸው ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የመሥራት ፍቃድ አይሰጣቸውም፡፡ ሆኖም መጠለያን መንግሥት ያቀርብላቸዋል፡፡
አመልካቾች መጀመርያ በቡድን የጋራ መኖርያዎች ውስጥ (ሆስቴል) ካረፉ በኋላ ቀስ በቀስ ቋሚ መኖርያ እንዲያገኙ ይደረጋል፡












