ካቲ ፓሲፊክ ኮሮኖቫይረስ ያሳደረውን ጫና ለመቋቋም ሠራተኞቹ እረፍ እንዲወጡ ጠየቀ

Cathay Pacific cabin crew with mask

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty

የሆንግ ኮንግ አየር መንገድ የሆነው ካቲ ፓሲፊክ ኮሮኖቫይረስ በሥራው ላይ ያሳደረበትን ጫና መቋቋም እንዲቻለው ሠራተኞቹ ሳይከፈላቸው ለሶስት ሳምንታት እረፍ እንዲወጡ ጠየቀ።

አየር መንገዱ ኮሮናቫይረስ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የደንበኞቹ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተነግሯል። ካቲ ፓስፊክ የተሰኘው የሆንግ ኮንግ አየር መንገድ በሆንግ ኮንግ በነበረው ተቃውሞ ቀድሞም የፋይናንስ ጫና አጋጥሞት ነበር ተብሏል።

አየር መንገዱ ሰራተኞቹ በፍቃዳቸው ለሶስት ሳምንታት የማይከፈልበት እረፍ እንዲወስዱ ጠይቋል።

"የንግድ እንቅስቃሴዬን ለማስቀጠል ጥሬ ገንዘብ መቆጠብ አለብኝ" ብሏል አየር መንገዱ።

ካቲ ፓስፊክ ባወጣው መግለጫ ከቻይና መዳረሻዎቹ መካከል 90 በመቶ በሚሆኑት በቀጣይ ሁለት ወራት መብረር እንደሚያቆም አስታውቋል።

"ዛሬ ላይ ሰራተኞቻችን ከየካቲት 22 እስከ ሰኔ 23 ባሉት ቀናት ለሶሰት ሳምንታት የማይከፈልበት እረፍት እንዲወስዱ በትህትና እንጠይቃን" ሲሉ የካቲ ፓሲፊክ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኦገስታስ ታንግ የቪዲዮ መልዕክት ለሠራተኞች መላካቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።

አውሮፕላን አምራቹ ኤርባስ በቻይና የሚገኙ ሰራተኞቹ ከቤት ሆነው እንዲሰሩ የቻይና መንግሥት መመሪያዎችን እያጤነ መሆኑን ያስታወቀ ሲሆን በቲያንጂን የሚገኘውን መገጣጠሚያውን መዝጋቱን አስታውቋል።

የእስፖርት ትጥቅ አምራቹ አዲዳስ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቻይና የሚገኙ አብዛኞቹ መደብሮቹን ለመዝጋት መገደዱን አስታውቋል።

የዴንማርኩ ቢራ አምራች ኩባንያ ካርስልበርግ በቻይና ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ሊገታ እንደሚችል ለሠራተኞቹ ማሳሰቢያ ሰጥቷል።