በመጨረሻም ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት ተሰናበተች

እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት ወጣች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት ወጣች

ብሪታኒያ ለ47 ዓመታት በአባልነት የቆየችበትን የአውሮፓ ሕብረት በይፋ ወጣች።

ከሕብረቱ ለመሰናበት ከወሰነች ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረችውና በተለያዩ ምክንያቶች ሂደቱ ሲጓተትባት የነበረችው ብሪታኒያ ዛሬ በይፋ ከአውሮፓ ሕብረት ተሰናብታለች።

ታሪካዊ የተባለው የስንብት ውሳኔ እኩለ ሌሊት ላይ ሲሰማ በደጋፊዎች ደስታና በተቃዋሚዎች የቁጣ ድሞጽ ታጅቧል። በመላው ብሪታኒያ ይህንን ዜና ሲጠባበቁ የነበሩ ዜጎች ሌሊቱን ሙሉ ደስታቸውን ሲገልጹ አድረዋል።

እንቅልፍ ላይ የነበሩት ደግሞ "ተኝተን አድረን ነገር ግን ስንነቃ ራሳችንን ከአውሮፓ ሕብረት ውጭ አገኘነው" በማለት ክስተቱን ገልጸውታል።

አብዛኞቹ ከብሪታኒያ ፓርላማ አቅራቢያ ካለ አደባባይ በመሰባሰብ የአገራቸውን የጀግና መዝሙር በመዘመርና ይህን ጉዳይ ሲያሳልጡ የነበሩ ግለሰቦችን ንግግር እንዲያደርጉ በመጋበዝ ደስታቸውን አጣጥመዋል።

ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት ወጣች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት ወጣች

የብሬግዚት አስተባባሪ "ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ ልንደሰት ይገባል፣ ይህ በታላቋ አገራችን ወደር የማይገኝለት ክስተት ነው" በማለት ለተሰባሰበው ሕዝብ የደስታ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ይህ ኩነት ከመስተናገዱ ትንሽ ቀደም ብሎ ብሪታኒያ ከሕብረቱ እንዳትወጣ ይደግፉ የነበሩ ዜጎች በዋይትሃል ተሰባስበው ሕብረቱን አመስግነው ተሰናብተዋል። በኋላ ደግሞ በስኮትላንድ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።

በዚህ ደስታና ሃዘን በተቀላቀለበት ሂደት ውስጥ ሌሎች ስሜቶችም ተንጸባርቀዋል።

  • በብራስልስ የሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ከሕብረቱ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የኮከብ ምልክቱን አንስቷል
  • በ2016 ብሪታኒያ ከሕብረቱ እንድትወጣ በመደገፍ የሰንደርላንድ ከተማ ካቢኔ የመጀመሪያው መሆኑ ተገልጿል።
  • በ10 ጎዳናዎች የሕብረቱ ሰንደቅ ዓላማን የሚያጠፋ መብራት በህንጻዎች ትይዩ ተለቅቋል።
  • የ50 ፓውንድ ሳንቲም የብሪታኒያ ከሕብረቱ መውጣትን ለመዘከር በገበያ ላይ እንዲውል ተደርጓል።
ብሪታኒያ በሕብረቱ እንድትቀጥል የሚሹ ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ብሪታኒያ በሕብረቱ እንድትቀጥል የሚሹ ዜጎች

ታዲያ አሁን ምን ሊሆን ነው?

አሁን ብሪታኒያ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ስላልሆነች እንግሊዛዊያን ፈጣን ለውጦችን ማየት ይፈልጋሉ።

አብዛኛዎቹ የሕብረቱ ሕጎች ባሉበት ይቀጥላሉ፤ የሽግግር ጊዜው እስከሚያልቅበት ታኅሳስ 31 ድርስ ማለት ነው።

ልክ አውሮፓ ሕብረት ከካናዳ ጋር እንደተፈራረመው ሁሉ ብሪታኒያ እንደ አዲስ ነጻ የንግድ ስምምነት ከሕብረቱ ጋር ትፈራረማለች።

የአውሮፓ አገራት መሪዎች ግን በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት ብሪታኒያ ነጻ የንግድ ስምምነቱን ለመፈረም ብርቱ ፈተና ይጠብቃታል እያሉ ነው።

ከአውሮፓ የተሰጠው ግብረ መልስ?

የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ዴር ብሪታኒያና የአውሮፓ ሕብረት የንግድ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት ውይይት ብርቱ ፍትጊያ ይኖራል ብለዋል።

እንግሊዞች ለጉዳዮች ትኩረት በመስጠትና ጠቃሚ ሃሳቦችን ለውይይት በማምጣት የሚናፈቁ ተሳታፊዎች እንደነበሩ የሕብረቱ አባላት ትዝታቸውን ይናገራሉ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "በ70 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከሕብረቱ አንዲት አገር አስወጥተናል፤ ይህ ለሁላችንም የማንቂያ ደወል በመሆኑ ያሉብንን ችግሮች ወደ ውስጥ የምንመለከትበት ወቅት ነው" ብለዋል።

የአውሮፓ ካውንስል ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሸል "ብሪታኒያ ከአውሮፓ ሕብረት የምታገኘው ገበያ በስፋቱና ጥራቱ ያደገ ነበር፤ አሁን ግን ይህ ሊጠብ ስለሚቸል ጥሩ የሚሆን አይመስለኝም" በማለት አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካ ጉዳይስ?

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ "ብሪታኒያና አውሮፓ ሕብረት የእንግሊዝን ሕዝብ ፍላጎት በሚያስጠብቅ ጉዳይ ላይ ስምምነት በመድረሳቸው በውሳኔያቸው ደስ ብሎኛል" ብለዋል።

"አዲስ ምዕራፍ ከጀመሩት እንግሊዞች ጋር ፍሬያማና የሚያድግ ግንኙነት እንመሰርታለን" በማለትም ለእንግሊዝ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

በዋሺንግተን የብሪታኒያ አምባሳደር ዉዲ ጆንሰን "የብሬግዚት ሂደት ለረጅም ጊዜ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ድጋፍ አግኝቷል" ብለዋል።

ብሪታኒያ የአውሮፓ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ይባል የነበረውን ከሦስት ሙከራ በኋላ ነበር በጥር አንድ 1973 እ.አ.አ የተቀላቀለችው። ከሁለት ዓመት በኋላ በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ በስብስቡ ውስጥ ሆና እንድትቀጥል ተመርጣለች።

ከዚያ በኋላ ወግ አጥባቂው ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን በ2016 ሌላ ሕዝበ ውሳኔ አደረጉ። ይህም የሆነው ከራሳቸው የፓርላማ አባላትና ከኒጌል ፋራግ የእንግሊዝ ኢንዲፔንዳንት ፓርቲ በመጣ ጫና ነበር።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚንስትር ካሜሩን ብሪታኒያ በሕብረቱ እንድትቆይ ቢጥሩም በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ 52 ለ 48 በሆነ ውጤት ተሸንፈው እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የምትወጣበት ሰፊው በር ተከፈተ።

ካሜሩንን የተኩት ቴሪሳ ሜይ ያቀረቡት ከአውሮፓ ሕብረት የመውጫ ረቂቅ በተደጋጋሚ ውድቅ ስለተደረገባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ተክተዋቸዋል። ከመጀመሪያው ጀምሮ ብሪታኒያ ከሕብረቱ መውጣት አለባት ብለው ይከራረከሩ ስለነበር አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጆንሰን ይህን ሕልማቸውን ማሳካት ችለዋል።

ቦሪስ ጆንሰን
የምስሉ መግለጫ, ቦሪስ ጆንሰን

ብሪታኒያ ከሕብረቱ ከመውጣቷ ከሰዓታት በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ጠቅላይ ሚንስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት "ለብዙ ሰዎች ይሄ የሚያስደንቅ ቅጽበት ነው፤ ሌሎች ደግሞ ከነበረብን ጫና ነጻ ወጣን ብለው የሚያስቡ ይኖራሉ፤ ሦስተኛው ምድብ ደግሞ የፖለቲካ ዥዋዥዌው አላለቀም ብለው የሚጨነቁ ናቸው" ብለዋል።

"እንደ መንግሥት ሁሉንም ስሜቶች እረዳለሁ፤ የእኔ ሥራ የሚሆነውም ይህችን አገር በአንድነት ወደፊት ማራመድ ነው" ብለዋል።