ሰዎች 'ፖፒ' የተሰኘችውን ቀይ አበባ ለምን ደረታቸው ላይ ያደርጓታል?

Poppies

የፎቶው ባለመብት, PA

"ፖፒ" የተሰኘውን ቀይ አበባ ብዙዎች ደረታቸው ላይ አድርገውት በቴሌቪዥን መስኮቶች ተመልክተው ይሆናል።

"ፖፒ" በመባል የምትታወቀው ቀይ አበባ ደረት ላይ የምትደረገው በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ህይወታቸውን ለሃገራቸው መስዋዕት ያደረጉት ሰዎችን ለመዘከር ነው።

ከዚህ በተጨማሪም በሽብር ጥቃት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ለማስታወስ እና የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ቤተሰቦች አስተዋጽኦን ለማጉላት በፈረንጆቹ ኖቬምበር ወር ላይ ደረት ላይ ይደረጋል።

"ፖፒ" እ.አ.አ. ከ1921 ጀምሮ በጦር ሜዳ መስዕዋት የሆኑትን ለማሰብ በተለይ ደግሞ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ሲደረግ ቆይቷል።

በየዓመቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች "ፖፒ" ደረታቸው ላይ ያደርጋሉ።

Poppies growing

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ, የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ጦርነቱን በተካሄደባቸው ሜዳዎች ላይ "ፖፒ" በቅሎ ነበር።

ቀይዋ አበባ "ፖፒ" ለምን ተመረጠች?

የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ጦርነቱን በተካሄደባቸው ሜዳዎች ላይ "ፖፒ" በቅሎ ነበር።

ከዚያ በኋላ በጦርነቱ ለሃገራቸውን ህይወታቸውን የገበሩ ሰዎችን ለመዘከር ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።

በዚህ በፈረንጆቹ ወር ከአበባው ሽያጭ የሚገኘው ገንዘብ በህይወት የሚገኙ እና ለሃገራቸው የተዋደቁ አርበኞችን ለመደገፍ ይውላል።

አርበኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንግሊዝ ውስጥ የሚካሄዱ እግር ኳስ ጨዋታዎች እና መሰል ዝግጅቶች የአንድ ደቂቃ የኅሊና ፀሎት በማድረግ በጦርነት የወደቁትን ያስባሉ።

አልፎም ቴሌቪዥን ላይ የሚታዩ አቅራቢዎችም ሆኑ እንግዶች ቀይዋን አበባ ደረታቸው ላይ ሰቅለው ማየት የተለመደ ነው።

በስፋት ጥቅም ላይ ከምትውለው ቀይዋ 'ፖፒ' በተጨማሪ ነጭ፣ ሮዝ፣ ጥቁር እና የቀስተደመና ቀለማት ያሏቸው ፖፒዎች ለመዘከሪያነት ጥቅም ላይ ይውላሉ።