ኢትዮጵያና ኤርትራን የምታገናኘው ዛላምበሳ

ኢትዮጵያና ኤርትራ የሚዋሰኑበት የጉሎመኸዳ አካባቢ አርሶአደሮች መሃል አስፋልት መንገድ ላይ የታጨደ በመከመር እህል ከገለባ መለየቱን ተያይዘውታል። መንገዱ እንኳን መኪና ሰውም እየረገጠው አይደልም።
"የዛላምበሳና አምበሰት ገለባን ህዝብ ከመለያየት ወሃን ከወተት መለየት ይቀላል" ይላሉ አዋቂዎች። ያኔ ድሮ ወንድም ከወንድም አልያም እህት ከእህት ሲጋጩ፤ እረኞች ሲኮራረፉ ኩርፊያው በአገር ሽማግሌዎች ይቀዘቅዝ ነበር።
አምና መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ስምምነት ላይ ሲደርሱ ህዝቡ ለራሱ በማሰብ የሰላም ሂደቱን ደግፏል። ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው እንዲሉ በጦርነቱ ህዝቡ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል።
ድንበሩ ተዘግቶ በቆየባቸው 20 ዓመታት ውስጥ ከአንዱ ወገን የከበሮና ማሲንቆ ድምጽ ሲሰማ 'ማን ይሆን ወግ የደረሰው?' በማለት ባለበት ሆኖ ደስታውን ይጋራል። የጩኸትና ጥሩንባ ድምጽ በሰማ ቁጥርም ሐዘን እንደገጠመ ስለሚረዱ ገጻቸው ይገፋል።
የመንግሥታቱን ስምምነት ተከትሎ የተከፈተው ድንበር ተመልሶ ሲዘጋ ቀድሞ ወደ ነበረው መለያየትና ችግር አንመለስም ያለ ህዝብ ድንበር ጥሶ በሌሊት ሳይሆን በቀን እየተገናኘ ነው።
እንደገና ወደ ዛላምበሳ
አቶ ዳኘው መዝገቦ ከሁለቱም ወገን ይወለዳሉ። የዛሬን አያርገውና ዕድሜ ተቆጥሮ እግራቸው መራመድ ሳያቅተው ከ20 ዓመት በፊት በዛላምበሳ 'መረብ' የሚባል ሆቴል ከፍተው ይሰሩ ነበር።
ሁለቱ መንግሥታት ወደ ጦርነት በሚገቡበት ወቅት የጭነት መኪና እያሽከረከሩ ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ሲመለሱ ጎንደር ላይ "በመጠጥ ወሃ ላይ መርዝ ለመጨመር ሞክሯል" በማለት አንድ ሰው ጥቆማ ሰጠ። ለተወሰነ ጊዜ እዚያው ታስረው ከቆዩ በኋላ ወደ ኤርትራ ተባረሩ።
በዛላምበሳ ከተማ የነበረው መኖርያ ቤታቸውም በጦርነቱ ምክንያት ወደመ። ሆቴላቸውም በልጃቸው በኩል ለሌላ ሰው ተከራየ።
አቶ ዳኘው አንድ ቀን "መንጋቱ አይቀርም" በማለት በኤርትራ ዓዲ ቀይሕ በሚባል ቦታ ሌላ 'መረብ' የተባላ ሆቴል በመክፈት ሥራቸውን ቀጠሉ።
አቶ ዳኘው ሳይሞቱ ይጠብቁት የነበረው ቀን ደረሰ፤ የ75 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ሆነው ዘላምበሳ ገቡ። 'መረብ ሆቴል' የሚል ጽሑፍ የሰፈረባት ሰሌዳቸው በበርካታ ጥይቶች ተበሳስታ አገኗት።
በዚህ ተስፋ ሳይቆርጡ ሌላ ባለ አምስት ፎቅ ህንጻ ለመገንባት ቆርጠው ተነሱ። ዛሬ ላይ የህንጻው ሁለተኛው ፎቅ በማለቁ መረብ ሆቴልን በአዲስ መልኩ ከፍተው ሥራ ጀምረዋል። ለማስታወሻነትም በጥይት የተበሳችው ሰሌዳም ለማስታወሻነት ቦታዋ ላይ ትገኛለች።
"እኔ ግንባታ ከጀመርኩ በኋላ ብዙ ሰዎች ተከትለውኛል። እየዘዋወረ በከተማዋ ውስጥ እየተሰራ ያለውን ለሚያይ ከተማዋ እንዴት እየሰፋች መሆኗን አይቶ መመስከር ይችላል" ይላሉ።
በእርግጥም ዛላምበሳ መልሳ በሁለት እግሯ ለመቆም እየተነቃቃች ነው። ነዋሪዎቿ ዛሬም ተስፋ አልቆረጡም። ነገ ሌላ የተሻለ ቀን እንደሚመጣ ተስፋ በማድረግ ህንጻዎች መገንባታቸውን ቀጥለዋል።

የዛላምበሳ ገበያ
በዕለተ ቅዳሜ የዛላምበሳ ገበያ ይደራል:፤ ኤርትራዊያን የገለባ ገጠር ኗሪዎች በጧት ወደ ከትማዋ ይተማሉ። ምንም እንኳን በኬላው ይገባ የነበረው ህዝብ ቢከለከልም ገደልና ሸንተረሩን አቆራርጦ በሌላ አቅጣጫ መግባቱን እንዳልተወ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን ኤርትራዊያን መጀመሪያ ወደ ዛላምበሳ ሲገቡ ናቅፋን ወደ ብር የሚመነዝሩ ኢትዮጵያዊያን አግኝተው ለመገበያየት የሚፈልጉትን ያህል ብር የመነዝሩላቸዋል።
በከተማዋ አንድ መቶ ናቅፋ በ230 የኢትዮጵያ ብር በጥቁር ገበያ እንደሚመነዘር ይህንን ከሚሰሩት ሰዎች አንዱ ይናገራል። ወደ ኢትዮጵያ የገባውን ናቅፋ ደግሞ መልሰው ገንዘቡን ለሚፈልጉ ኤርትራዊያን በ232 ይሸጡላቸዋል።
ግልጽ ሜዳ ላይ በሚካሄደው የዛላምበሳ ገበያ ከሽንኩርት እስከ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች ይሸጣል። በሂደቱም ኢትዮጵያዊያን ይሸጣሉ ኤርትራዊያኑ ደግሞ ይገዛሉ። ቢቢሲ በገበያው ውስጥ ያገኛቸው አንዲት እናት እንደሚሉት ከኤርትራ የሚገባ የሚሸጥ ሸቀጥ የለም።
ጤናን ፍለጋ
ዛላምበሳ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የጤና ጣቢያ የሁለቱንም አገር ህዝቦች ያገለገላል። አገልግሎቱ ብቻም ሳይሆን ክፍያውም አንድ አይነት ነው።
የጤና ጣቢያው ተወካይ ሜዲካል ዳይሬክተር ሳምራዊት ብርሃነ እንደምትለው ኤርትራዊያኑ ወደ ጤና ጣቢያው የሚመጡበት ዋና ምክንያት በአቅራቢኣቸው የሚገለገሉበት ተቋም ስለሌላቸው መሆኑን እንደነገሯትና የተሻለ የህክም አገልግሎት ፍለጋም የሚመጡ እንዳሉም ትናገራለች።
ቢሆንም ግን የጤና ጣቢያው የላቦራቶሪ መሳሪያ እንደሌለውና ምርመራ ለማሰራት በአቅራብያ ወደምትገኘው የፋፂ ከተማ ሆስፒታል መሄድ እንደሚጠበቅባቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ለዚህ ደግሞ 17 ኪሎ ሜትር መጓዝ የግድ ነው።

ተስፋ
በጦርነቱ ወቅትና ከዚያም በኋላ በቅርብ ርቀት የሚያዩትን የእርሻ ማሳቸው እንኳን አርሰው ለመጠቀም ሳይችሉ መቆየታቸውን በማስታወስ መቀራረቡ ብዙ ነገሮችን እንደቀየረ ይናገራሉ።
በአሁኑ ጊዜ የሁለቱም ወገን ያሉ እረኞች በአንድ መስክ ላይ እንደሚውሉ እንዲሁም ህዝቡ በአንድ ጥላ ስር ሃዘኑንም ሆነ ደስታውን የመጋራት ዕድል አግኝቷል።
ከሁለቱም አገራት ህዝብ የሚሰማው ተስፋና ምኞት "ከአሁን በኋላ ወደ ነበርንበት መለያየት አንመለስም" የሚል ነው።
በመጪው የኅዳር ላይ በሚከበረው የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ ሐይማኖታዊ ጠበል ጸዲቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመታደም ከዛላምበሳ ከተማ ወደ ጎረቤት የገለባ የገጠር መንደር እንደሚሄድ አንድ ወጣት ለቢቢሲ ተናግሯል።
ይህም ምንም እንኳን የሁለቱም አገር መንግሥታት ቀጣይ ግንኙነታቸው የሚመራበትን ሥርዓት አስቀምጠው ባያጠናቅቁም ህዝቡ ግን ቀድሞ የተቋረጠውን ግንኙነት ጠግኖ ከመደበኛው ደረጃ ላይ ያደረሰው ይመስላል።
የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ የማይታይበት የዛላምበሳ የመኪና መንገድም ጭር ከማለት ተላቆ ተላቆ ድንበሩ በተከፈተበት ወቅት እንደነበረው ዳግም አውቶቡሶችን በቅርቡ ማስተናገድ ይጀምራል ብለው ነዋሪዎች ተስፋ እየተጠባበቁ ነው።















