አሜሪካ፡ አዲሷ ሙሽራ ባሏን ከእሳተ ገሞራ አፍ ታደገችው

ጥንዶቹ በሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, GoFundMe

አዲሶቹ ተጋቢዎች ለጫጉላ ሽርሽር እሳቱ ወደማይንቀለቀልበት ፀጥ ብሎ ከሚያንቀላፋው እሳተ ገሞራ ለሽርሽር ነበር የሄዱት።

ክሌይ ቻስቴይን እና አካሚያ የጫጉላ ሽርሽራቸውን ያካሄዱት በተጋቡ ማግስት ነበር። ጋብቻቸውን በአሜሪካ ኢንዲያና ግዛት ፈፅመው ሊያሙኢጋ የተባለ ተራራን በመውጣት እሳተ ገሞራ የፈጠረውን ውበት እያዩ፣ ፍቅራቸውን ለማጣጣም ነበር ሀሳባቸው።

ተራራው ጫፍ ላይ እንደደረሱ አዲሱ ሙሽራ ክሌይ ቻስቴይን፣ ትንሽ የሀሳብ ሰበዝ ብልጭ አለችበት። 'ለምን ወደ እሳተ ገሞራው አፍ ወረድ ብለን አናየውም፣ በዛውም ጥሩ እይታን እናገኛለን' የሚል ነው ሀሳቡ።

ባለቤቱ የከፍታ ፍርሃት ስላለባት ባለችበት ለመቆየት ትወስናለች። እሱ የልቡን ለማድረስ ቁልቁለቱን ወረደ "ድንገት ከፍተኛ ድምፅ ሰማሁ፤ ከኮረብታው የሚንደረደር ቋጥኝ አይነት" ያለችው አካሚያ የባሏን የድረሱልኝ ጩኸት እንደሰማች ወደ እሱ አመራች።

በደም ተለውሶ ሞባይሉ ከእሱ ርቆ ወድቆ አገኘችው።

ክሌይ ያለ የሌለ ጉልበቷን አስተባብሯ፣ ሀዘኗን ዋጥ አድርጋ ባሏን አፋፍሳ አነሳችው።

እርሷ ላይ ተዝለፍልፎ፣ ወደላይ እያለው፣ በሕመም መላ አካሉ እየተሸቀሸቀ ወደ ተራራው ግርጌ ወረዱ።

ጥንዶቹ ሲሳሳሙ

የፎቶው ባለመብት, GoFundMe

የምስሉ መግለጫ, ጥንዶቹ የተጋቡት አደጋው ከመድረሱ ቀደም ብሎ ባሉት ቀናት ነበር

ወደ ተነሱበት ለመመለስ የሚረዳቸው አንድም አካል ስላልነበር ሁለቱ ብቻ ተደጋግፈው ሦስት ሰአት ያህል በመጓዝ እርዳታ የሚያገኝበት ሥፍራ ላይ ደርሰዋል።

"በጣም የምትደንቅ ሴት ናት" ብላል እንኳንም ሚስቴ ሆነች በሚል ድምፀት።

ቻስቴይን ተራራው ጋር ሲወርድ የራስ ቅሉ ተፈንክቶ እየደማ ነበር።

"ተደግፎኝ እየሄድን ደጋግሞ ምን ያህል ቀረን፣ አንደርስም እንዴ? እያለ ይጠይቀኝ ነበር" የምትለው አካሚያ፤ ወደ ፍሎሪዳ ሄዶ የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ የሚያስችል ገንዘብ እንደተሰባሰበለት ጠቅሳለች።

የራስ ቅሉ መሰበርና ቀላል የአጥንት መሰበር ቢገጥመውም ከባድ የሆነ ሌላ አደጋ የለውም። ነገር ግን ሐኪሞች ሴሬብራል ስፓይናል ፈሳሽ በአፍንጫው በኩል መፍሰሱን ተናግረዋል።

"ያን ያህል ጉዳት ገጥሞት በራሱን ኃይል ህክምና የሚያገኝበት ድረስ መሄዱ ትንግርት ነው" ብላለች ባለቤቱ።

አክላም በፌስ ቡክ ገጿ ላይ ፈጣሪን አመስግናለች።