በሳዑዲ አረቢያ 3ሺህ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች መኖራቸው ተገለፀ

ከ45 ሺህ በላይ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ሲመለሱ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ከ45 ሺህ በላይ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል

በሳዑዲ አረቢያ በሚገኙ ሰባት ክልልሎች ወደ 3ሺህ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ እስር ቤቶች በእስር ውስጥ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኮንሱላር ጀኔራል አቶ አብዱ ያሲን ለቢቢሲ ገለፁ።

በጂዛን እስር ቤት ብቻ ከ30 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች እንዳሉም አቶ አብዱ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እስረኞች ከ40 ቀናት በላይ መታሰራቸው ገልፀው በእስርቤቱ ያለው አያያዝ ጥሩ እንዳልሆነ ተናግረዋል። እስረኞቹም ወደ ሃገሪቱ በሕጋዊ መንገድ እንደገቡ እና ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በሽ ከተባለ አካባቢ ተወስዶ የታሰረው ካህሳይ ብርሃነ ''ያገሪቱ ፖሊሶች አፍሰው አሰሩን፤ እኛ ከስድስት ዓመታት በላይ የኖርን እና የመኖሪያ ፍቃድ ያለን ነን'' ብሏል።

"'የመኖሪያ ፍቃዳችሁ ትክክለኛ አይደለም፤ እናጣራዋለን' ብለው እስርቤት ውስጥ አስገቡን። ከዚያም አሻራችሁን ስጡ አሉን፤ እኛ ዓረብኛ መጻፍና ማንበብ አንችልም፤ ምንድን ነው? ስንላቸው፤ ዝም ብላችሁ አድርጉ አሉን። አሻራ አንሰጥም ስንላቸው ደብድበው በኃይል አሻራ እንድንሰጥ አደረጉን'' ይላል ስለ ሁኔታው ሲያስረዳ።

አክሎም "ለ 10 ቀናት ያለ ምግብ እና ውሃ፤ ሽንት ቤት ዘግተው እንድንታመም እና እንድንሰቃይ አድርገውናል፤ እያንዳዳንዳችን እያስወጡ በመግረፍ አሰቃይተውናል'' ሲል እስር ቤቱ ውስጥ የደረሰባቸው ግፍ ገልጿል።

ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ድጋፍ ቢጠይቁም ኤምባሲው ችላ እንዳላቸው በመግለፅ ቅሬታቸው ተናግረዋል።

ሌላኛው ቢቢሲ ያነጋገረው እስረኛ ''ጂዛን ወዳለው ትልቅ እስር ቤት ወሰዱን፤ እነሱም አንቀበላቸውም ምን አድርገው ነው? ውሰዷቸው አሉ፤ እንደገና ተመልሰን ወደዛ ሄድን'' ይላል።

ከዚያም ወደ ጂዛን እንደተመለሱ እና አሁንም እዚያው መሆናቸውን ተናግሯል።

ከካህሳይ ጋር ታስሮ የሚገኘው ኪዳኔ ሺበሺ በበኩሉ ሕክምና ተከልክለው፤ እንዲሁም ያለ በቂ ልብስ ለተባይ እንደተጋለጡ ለቢቢሲ አስረድቷል።

ኪዳኔ ለሰባት ዓመታት በሹፌርነት ሥራ ሕጋዊ ሆኖ ይሠራ እንደነበር ገልፆ የመኖሪያ ፈቃዱ ተመልሶለት ወደ ሥራው እንዲመለስ ይጠይቃል።

ብዙ ንብረት እንዳፈሩ የሚናገሩት ኢትዮጵያዊያኑ አሠሪዎቻቸው ሊያሰሩዋቸው እንደሚፈልጉ ቢገልጹም ባለስልጣናቱ ለመፍታት ፍቃደኛ አለመሆናቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

የአስርኞቹን ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ አብዱ፤ በጂዛን የሚገኙት እስረኞች ለእስር የተዳረጉት የአገሪቷን ሕግ ባለማክበራቸው ነው ብለዋል። በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አካላትን ያነጋገሩም ሲሆን 'በአገሪቷ በሚፈቅደው ሕግ መሠረት ሲሠሩ አላገኘናቸውም' የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ገልፀዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት በአገሪቱ ሕግ መሠረት የመኖሪያ ፍቃድ መያዝ ብቻ ሕጋዊ አያደርግም። መኖሪያ ፈቃድ ኖሯቸውም በተመደቡበት የሥራ መደብ ሲሰሩ ካልተገኙ ሕጋዊ እንዳልሆኑ ነው የሚቆጠረው።

"ጉዳዩ አጠቃላይ ከስደተኞች ጋር የሚያያዝ ነው፤ በአየር መንገድ ብቻ ተሳፍረው ስለመጡ ሕጋዊ የሆኑ ይመስላቸዋል" የሚሉት አቶ አብዱ በሕጋዊ መንገድ መጥተው ስለማይመለሱ ሕገ ወጥ ይሆናሉ ይላሉ። ሌላኛው ጉዳይ በተመደቡበት የሥራ መደብም አለመገኘት ነው።

"የእኛ ዜጎች ስለ መብታቸው እንጂ፤ ስለ ግዴታቸው አያውቁም። ለዚያም ነው ችግር የሚያጋጥማቸው" ሲሉም ስደተኞቹ ለችግር የሚዳረጉበትን ዋና ምክንያት ያነሳሉ።

ይሁን እንጂ የእስረኞቹን ጉዳይ የኤምባሲው ጉዳይ ፈፃሚ በቅርበት እየተከታተሉት ሲሆን በምህረት እንዲለቀቁም የተለያዩ ጫናዎችን እያሳድሩ መሆኑን ይገልፃሉ።

"ምንም እንኳን በቦታው የተመደቡ ሰዎች ቢኖሩም፤ በጂዛን ቆንስላ ጽ/ቤት የለንም" የሚሉት ኮንሱላር ጀኔራሉ ቀይ ባህርን ተሻግረው የሚመጡ ስደተኞች የሚበዙበት አካባቢም በመሆኑ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለባቸው ይገልፃሉ።

ለዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ቀይ ባህርን ተሻግረው የመጡት ስደተኞችም 70 ሺህ የሚጠጉ እንደሆኑ በመጥቀስ ባላቸው የሰው ኃይል እነዚህን ማስተናገድ ፈታኝ እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

በሳዑዲ አረቢያ ሰባት ክልሎች እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ብቻ 3 ሺህ የሚጠጉ እስረኞች ይገኙ እንደነበር ገልፀውልናል።

እስረኞቹ ከቀላል እስከ ከባድ ወንጀሎች ሲፈፅሙ ተይዘው የታሰሩ ናቸው ብለዋል። እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት በሁለት መንገድ ሥራቸውን ያከናውናሉ።

አንደኛው የኢኮኖሚ ስደተኞች በመሆናቸው ምህረት ተደርጎላቸው እንዲሰሩ እርዳታ መጠየቅ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በእስር ላይ የሚገኙትም መብታቸው እንዳይነካ ማድረግ ነው።

ከዚህ አልፎ ወደ አገር ቤት የሚመልሷቸው ከሆነ እስከሚሄዱ በቆዩባቸው ጊዜያት መብታቸው እንዲከበርና ሲሄዱም የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት ንብረታቸውን ይዘው እንዲሄዱ እንደሚሠሩ ነግረውናል።