ስመ ጥሩ ጋዜጠኛ ሃሰተኛ ዜናዎችን በመፈብረኩ ከስራው ተባረረ

ስመ ጥሩው ጋዜጠኛ ሃሰተኛ ዜናዎችን በመፈብረክ ከስራው ተባረረ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዴር ስፒገል የተባለው የጀርመኑ የዜና መጽሄት ባልደረባ የነበረው ስመ ጥር ጋዜጠኛ ሃሰተኛ ዜናዎችን በመፈብረክ ከስራው ተባረረ።

በስራዎቹ ዝናን እና ሽልማቶችን መሰበሰብ ችሎ የነበረው ጋዜጠኛ በዘገባዎቹ ላይ ሃሰተኛ ዝርዝር መረጃዎችን በመጨመር እና ግለሰቦች ያላሉትን ብለዋል ብሎ በማካተቱ ነው የተወገዘው።

ጋዜጠኛ ክላስ ሬሎቲስ ''በከፍተኛ ደረጃ በዘገባዎች ላይ ሃሰተኛ መረጃዎችን አካቷል፤ እንዲሁም ገጸ ባህሪዎችን ፈጥሯል'' ሲል መጽሄቱ የቀድሞ ባልደረባውን ከሷል።

ሃሰተኛ መራጃዎች ተካቶባቸውል ከተባሉት ዘገባዎቹ መካከል ለሽልማት የታጨባቸው እና ሽልማት የተቀበለባቸው ሥራዎቹ ይገኙበታል።

የ33 ዓመቱ ጋዜጠኛ ክላስ ሬሎቲስ በመጽሄቱ ላይ በታተሙ 13 ሥራዎቹ ውስጥ ሃሰተኛ መረጃዎችን ስለ ማካተቱ አምኗል።

ረቡዕ ዕለት መጽሄቱ ባወጣው መግለጫ የጋዜጠኛው ባልደረባ በክላስ ሬሎቲስ ዘገባዎች ላይ ያለውን ጥርጣሬ ካሳወቀ በኋላ ጋዜጠኛው ሃሰተኛ ዜናዎችን ሲያዘጋጅ እንደነበረ ደርሼበታለሁ ብሏል።

የጀርመኑ መጽሄት ጨምሮም ክላስ ሬሎቲስ ምን ያክል ሃሰተኛ ዜናዎችን እንደሰራ እና በዘገባዎች ውስጥ ያካተታቸው ሃሰተኛ መረጃዎች እንደሆኑ ይፋ አደርጋለሁ ብሏል።

ከዚህ ቀደም የቀረበበትን ክስ ክዶ ተከራክሮ የነበረው ሬሎቲስ፤ ባሳለፈነው ሳምነት በዘገባዎቹ ውስጥ ፊት ለፊት አግኝቷቸው የማያውቃቸውን ወይም አነጋግሮ የማያቃቸውን ሰዎች ታሪክ ይጽፍ እንደነበረ እና እነሱ አሉ ብሎ ይዘግብ እንደነበረ ቃሉን ሰጥቷል።

''እሱ እንዳመነው ከሆነ ቢያንስ 14 ዘገባዎች ሃሰተኛ መረጃ የተካተተባቸው ናቸው'' መጽሄቱ ያለ ሲሆን፤ ጨምሮም ሃሰተኛ መረጃ የተካተተባቸው ዘገባዎች ከዚያ በላይ ሊሆኑ ይችላሉ።

ጋዜጠኛው የጀርመኑን መጼሄት የተቀላቀለው እአአ 2011 ላይ ሲሆን እስከ አሁን በቆይታው ከ60 በላይ ዘገባዎችን ሰርቷል።

በጥፋቴ ተጸጽቻለሁ እጅግም አፍሪያለሁ የሚለው ጋዜጠኛው ለመጽሄቱ ካበረከትኳቸው ዘገባዎች መካከል አብዛኛው እውነት ናቸው ብሏል።