ቀጥታ, ኢራን "የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት በፍጹም አልፈቅድም” - ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በመግለጽ አገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመግታት እንድትስማማ አስጠነቀቁ። አንድ የኢራን ባለሥልጣን ለትራምፕ ንግግር በሰጡት ምላሽ ቴህራን ላይ የቀረበውን ክስ "ትልቅ ውሸት" ሲሉ አጣጥለዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ለመነጋገር አዲስ አበባ ገቡ

    የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ጠዋት አዲስ አበባ መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና በምክትላቸው አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተገልጿል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት አስመልክቶ ባሰራጨው መረጃ፤ ሄርዞግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር እንደሚገናኙ አስታውቋል። ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋርም እንደሚነጋገሩ ጠቅሷል።

    እንደ የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ‘ቤተ እስራኤላውያን’ ተብለው የሚጠሩት የኢትዮጵያ የአይሑድ ማኅበረሰብ አባላት መሪም ከፕሬዝዳንት ሄርዞግ ጋር ይገናኛሉ።

    “ኢትዮጵያ አፍሪካ ውስጥ ወሳኝ አገር” እንደሆነች የገለጸው የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ጉብኝቱ "በእስራኤል እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ትብብር፤ በአጠቃላይም ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው” ብሏል።

    የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ወደ ኢትዮጵያ በመጡ በሳምንቱ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው የቱርኩ ፕሬዝዳንት በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የአገርነት ዕውቅና መተቸታቸው ይታወሳል።

    ኤርዶዋን፤ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የአገርነት ዕውቅና "ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ ምንም ጥቅም" አይኖረውም ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ንግግራቸው ሶማሊላንድን አስቆጥቷል።

    "የመላው ዓለም ዐይን ወደ የአፍሪካ ቀንድ” የዞረበት ጊዜ እንደሆነ የገለጹት ኤርዶዋን፤ ቱርክ በቀጣናው አዲስ ግጭት እንዲነሳ እንደማትፈልግ ተናግረው ነበር። "የዚህ ቀጣና ችግሮች በራሳቸው በቀጣናው አገራት ሊፈቱ እንደሚገባ እንዲሁም የአፍሪካ ቀንድ የውጭ ኃይሎች የጦር ሜዳ መሆን እንደሌለበት እናምናለን" ብለውም ነበር።

    ከትናንት በስቲያ ሰኞ ደግሞ የሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አልኬሬጂ አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጋር ተነጋግረዋል።

    ስለ ቀጠናዊ ሰላም እና ሁለቱን አገራት በሚመለከቱ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል የተባሉት ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አንድ ሳምንት አስቀድሞ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተነጋግረው ነበር።

    ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

  2. ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት “አልፈቅድም” አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት እንደማይፈቅዱ በመግለጽ አገሪቱ የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ለመግታት እንድትስማማ አስጠነቀቁ።

    ትራምፕ ለኮንግረስ አባላት ባደረጉት ንግግር “የእኔ ምርጫ ችግሩን በዲፕሎማሲ መፍታት ነው። አንድ ጉዳይ ግን እርግጥ ነው። እሱም፤ የዓለም ቁጥር አንድ የሽብር ደጋፊ የኒውክሌር መሣሪያ እንዲኖራት አልፈቅድም” ብለዋል።

    ሁለት ሰዓት ገደማ በቆየው የ ‘ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን’ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት፤ ኢራን በአሜሪካ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይሰነዘርባት በሚል ስምምነት ላይ መድረስ ትፈልጋለች።

    ሆኖም ግን ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ ግንባታን በተመለከተ ምንም ስምምነት እንዳላደረገች አክለዋል።

    አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ የጦር መርከቦቿን ማሰማራቷን ተከትሎ ከኢራን ጋር ግጭት ይፈጠራል የሚል ስጋት አንዣቧል።

    ትራምፕ በዛሬው ንግግራቸው ኢራን ታጣቂዎችን እንደምትደግፍ እንዲሁም ተቃዋሚዎችን እንደገደለች ገልጸዋል።

    በተጨማሪም “የኢራን መንግሥት እና ገዳይ የሆኑት አጋሮቹ ሽብር፣ ሞት እና ጥላቻን ነዝተዋል” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ኢራን ላይ ሊወሰድ ስለሚችል እርምጃ ቢገልጹም ዝርዝር መረጃዎችን አልሰጡም።

  3. ሄዝቦላህ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ ከተሳተፈ እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት እንደምትፈጸም ማስጠንቀቋ ተነገረ

    ሄዝቦላህ በማንኛውም መንገድ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ፤ እስራኤል አየር ማረፊያን ጨምሮ የሲቪል መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት በሊባኖስ ላይ እንደምትፈጽም ማስጠንቀቋን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ሁለት የሊባኖስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ እስራኤል የማስጠንቀቂያ መልዕክቷን ያደረሰችው ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እንደሆነ ገልጸዋል ተብሏል።

    የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ራጂ በበኩላቸው በጄኔቫ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ሄዝቦላህ በአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ አገሪቱ ከእስራኤል ጋር አዲስ ግጭት ውስጥ ልትገባ ትችላለች የሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ በምንም ዓይነት የዋሽንግተን እና ቴህራን ውጊያ ውስጥ ተሳትፎ እንዳያደርግ ማሳሰባቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

    የሊባኖስ መንግሥት ይህን ጥሪ ያቀረበው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚል ስጋት ባየለበት በዚህ ጊዜ ነው። ሁለተኛው የአሜሪካ የጦር አውሮፕላን ጫኝ መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እየተቃረበ ሲሆን ኢራንም ከሩሲያ ጋር የምታደርገውን ዓመታዊ የጦርነት ልምምድ ጀምራለች።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከኢራን ጋር በምታደርገው የኒውክሌር ድርድር ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ፤ ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

    የሊባኖሱ ሄዝቦላህ በአውሮፓውያኑ 2024 የተካሄደውን ጨምሮ ከእስራኤል ጋር ለበርካታ ጊዜያት ተዋግቷል። አሁንም ቡድኑ በአሜሪካ እና ኢራን ጉዳይ ሊሳተፍ ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው የሊባኖስ ባለሥልጣናት ሄዝቦላህ በአገሪቱ ዜጎች ላይ “መጥፎ ሁኔታን” ሊያመጣ በሚችል መልኩ ምላሽ እንዳይሰጥ ጥያቄ እንዳቀረቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራጂ ተናግረዋል ተብሏል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጄኔቫ ውስጥ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ "እስራኤላውያን የሲቪል መሠረተ ልማቶችን፤ ምናልባትም ቤሩት የሚገኘውን አየር ማረፊያ ልትመታ እንደምትችል የሚያሳዩ ምልክቶች ለሊባኖስ ደርሰዋል" ብለዋል።

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ማክሰኞ ዕለት በታተመ ጋዜጣ ላይ በወጣ ቃለ መጠይቃቸው ፤ ሄዝቦላህ ሊባኖስን ወደ "ሌላ ጀብዱ" እንዳያስገባት አሳስበዋል።

    አዲሱ የሄዝቦላህ መሪ ናኢም ቃሲም በአንጻሩ ባለፈው ወር በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው፤ ቡድኖ በዋሽንግተን እና ቴህራን ጉዳይ “ገለልተኛ እንዳልሆነ” ተናግረዋል። በዚህ ጦርነት "ሊፈጸም የሚችል ጥቃት ዒላማ እንደሆነም" መግለጻቸውን የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

  4. የአዲስ ስታንዳርድ የሥራ ፈቃድ ተሰረዘ

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃንን የምዝገባ ምስክር ወረቀት መሰረዙን አስታወቀ።

    አዲስ ስታንዳርድ በእንግሊዝኛ፣ በአማርኛ እና በኦሮምኛ በበይነ መረብ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ዜና፣ ትንታኔ እና አስተያየት የሚያቀርብ የመገናኛ ብዙኃን ነው።

    ባለሥልጣኑ አዲስ ስታንዳርድ “የሚዲያ ሥነ ምግባርን፣ የኢትዮጵያ ሕጎች እና የሀገርን እና የሕዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በማሠራጨት... ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለመታረም ፈቃደኛ አልሆነም” በማለት ለውሳኔው ምክንያት አቅርቧል።

    በዚህም ውሳኔ መሠረት የአዲስ ስታንዳርድ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የምዝገባ ምስክር ወረቀት ከሰኞ የካቲት 17/ 2018 ዓ. ም. ጀምሮ መሰረዙን ገልጿል።

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በዚህ ዓመት በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና ጋዜጠኞች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል።

    ባለሥልጣኑ የጀርመን ድምጽ ራድዮ የኢትዮጵያ ዘጋቢዎችን የሥራ ፈቃድ ለወራት ካገደ በኋላ በታኅሣሥ ወር ሁለቱን ዘጋቢዎች በዘላቂነት በማገድ ለሌሎቹ ፈቃድ ሰጥቷል።

    በጥር ወር አጋማሽ ላይ ደግሞ ዋዜማ ራድዮ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን “የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት እና የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ እንዲሁም መመሪያዎች እና የሙያ ሥነ ምግባር” ባለማክበር የተሰጠው ፈቃድ “ተመላሽ” መደረጉን ባለሥልጣኑ ገልጿል።

    በተጨማሪም ከሳምንት በፊት ዓለም አቀፉ የዜና ወኪል የሮይተርስ ዘጋቢዎች የሥራ ፍቃድ እንደማይታደስላቸው እንደተናገራቸው ድርጅቱ አሳውቋል።

  5. አሜሪካ እግረኛ ጦር ሳታሰማራ በኢራን ላይ ለመጠነ ሰፊ ጥቃት እየተዘጋጀች ነው ተባለ

    አሜሪካ እግረኛ ሠራዊት ሳታዘምት ለቀናት የሚዘልቅ ወታደራዊ ጥቃት በኢራን ላይ ለመፈጸም የሚያስፈልጓትን የባሕር ኃይል እና የአየር ኃይል መሣሪያዎቿን በኢራን አቅራቢያ ማስጠጋቷን የሳተላይት ምሥሎች እና የአውሮፕላን መከታተያ መረጃዎች አመለከቱ።

    ባለፈው ሳምንት ስዊዘርላንድ ውስጥ የተደረገው ድርድር ያለ ውጤት ማብቃቱን ተከትሎ አሜሪካ ከ150 በላይ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ወደሚገኙ ጦር ሰፈሮቿ ማንቀሳቀሷን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።

    ባለፉት ሳምንታት አሜሪካ ያሏትን ሁለት ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች እና ሌሎች የጦር መርከቦችን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤው አንቀሳቅሳለች።

    አሜሪካ ከሃያ ዓመት በፊት በኢራቅ ላይ ወረራ ካካሄደች በኋላ በባሕረ ሰላጤው አካባቢ ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል ስታሰማራ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ተዘግቧል።

    ወታደራዊ ታዛቢዎች እንደሚሉት የአሜሪካ ጦር ሠራዊት በአካባቢው አሁን ያለበት መጠን ባለፈው ዓመት ሰኔ በኢራቅ ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ጊዜ ከነበረው የበለጠ ነው።

    ይህም አሜሪካ እግረኛ ሠራዊት ሳታዘምት በኢራን ላይ ለበርካታ ቀናት የሚዘልቅ ወታደራዊ ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀች መሆኑን ያመለክታል ሲሉ ተናግረዋል።

    ነገር ግን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ አሁንም ድረስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ማግኘት ምርጫዋ መሆኑን እና ነገር ግን ድርድሩ ከከሸፈ ሌላ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ጨምረውም ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖራት አሜሪካ እንደማትፈቅድ በመጥቀስ፣ ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

    የእስራኤል የመገናኛ ብዙኃን አሜሪካ በመጪዎቹ ቀናት በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷ አይቀሬ መሆኑን እየዘገቡ ናቸው።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት የምትፈጽም ከሆነ እስራኤል በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተሳታፊ መሆኗ የማይቀር ሲሆን፣ ከኢራን በኩል ጥቃት የሚከፈትባት ከሆነ ከባድ አጸፋ እንደምትመልስ እያስጠነቀቀች ነው።

  6. በኢራን ዩኒቨርስቲዎች ተቃውሞው በቀጠለበት ጊዜ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ

    በኢራን ዩኒቨርስቲዎች የሚካሄደው ተቃውሞ አራተኛ ቀኑን በያዘበት በአሁኑ ወቅት መንግሥት በተቃዋሚ ተማሪዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሯል።

    የሻሪፍ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት የአገሪቱ “ዐቃቤ ሕግ በዩኒቨርስቲዎች የሚካሄደውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር በጉዳዩ ውስጥ ገብቷል” ያሉ ሲሆን፣ የአሚርካቢር ዩኒቨርስቲ ባወጣው መግለጫ “ሕግ የሚጥሱ ተማሪዎች ጉዳይ በፍጥነት እየታየ ያለማወላወል እርምጃ ይወሰዳል” ሲል አስታውቋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘም በርካታ ተማሪዎችም ወደ ዩኒቨርስቲዎች እንዳይገቡ ዕግድ ተጥሎባቸዋል።

    የኢራን መንግሥት ቃል አቀባይ በዩኒቨርስቲዎች እየተካሄዱ ያሉትን ተቃውሞዎች በሚመለከት “ተማሪዎች ተቃውሞ የማሰማት መብት አላቸው፤ ነገር ግን “የተቀደሱ ቦታዎች እና ሰንደቅ ዓላማችን የማይታለፉ ሁለት ቀይ መመስሮች ናቸው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    በዩኒቨርስቲዎች እየተካሄዱ ባሉት ተቃውሞዎች ውስጥ ተማሪዎች የቀድሞው የኢራን ንጉሣዊ መንግሥት ዓርማ ያለበትን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ በምሥሎች እና በቪዲዮዎች ላይ ታይተዋል።

    የኢራን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዩኒቨርስቲዎች የሚካሄደውን ተቃውሞ በተመለከተ “የሚመለከታቸው አካላት የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ” አዝዟል።

    ዐቃቤ ሕጉ ሞሐመድ ሞቫሄዲ አዛድ "መንግሥት ድርድር በሚያደርግበት ጊዜ በጠላት የሚመሩ እንቅስቃሴዎች በአገር ውስጥ ያለ ችግርን ለማባባስ ጥረት ያደርጋሉ። እነዚህን ግለሰቦች መቆጣጠር ደግሞ የፀጥታ እና የሕግ ተቋማት ግልጽ ኃላፊነት ነው” ብለዋል።

    ጨምረውም “የሳይንስ ማዕከሎቻችን ሰላም እንዲናጋ አንፈቅድም” ብለው የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

  7. በኢራን እና አሜሪካ ውጥረት ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ በሰባት ወራት ባልታየ መጠን ጨመረ

    ውጥረት ውስጥ ያሉት ኢራን እና አሜሪካ የሚያደርጉት ሦስተኛው ዙር ድርድር በተቃረበበት ወቅት የነዳጅ ዋጋ ባለፉት ሰባት ወራት ከነበረው በከፍተኛ መጠን መናሩ ተገለጸ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል የሚሸጥበት ዋጋ ባለበት (71.49 ዶላር) ቢሆንም የአሜሪካ ድፍድፍ ነዳጅ በበርሜል የሚሸጥበት ዋጋ የ0.2% ጭማሪ አሳይቶ 66.42 ዶላር ገብቷል።

    ድፍድፍ ነዳጅ ባለፈው ነሐሴ ከሚሸጥበት ዋጋው ዛሬ ጭማሪ ማሳየቱን ዘገባው ይጠቁማል።

    ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን መዝጋት እንዳለባት አሜሪካ ብትገልጽም፤ ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ የመሥራት ዕቅድ እንደሌላት እና ኒውክሌር ማብላላትም እንደማታቆም ገልጻለች።

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ኃላፊ እንደገለጹት፤ ጉልህ ኃላፊነት የሌላቸው ሠራተኞች እና ቤተሰቦቻቸው ሊባኖስ በቤይሩት ካለው የአሜሪካ ኤምባሲ ለቅቀው እንዲወጡ ታዘዋል።

    ኢራን ስምምነት ላይ ካልደረሰች “በጣም በጣም መጥፎ ይሆናል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።

    ሮይተርስ የጠቀሳቸው የነዳጅ ንግድ ተንታኝ “ጦርነት ይነሳል ከሚለው ስጋት ይልቅ ውጥረቱ መባባሱ ለነዳጅ ዋጋ አለመረጋጋት ምክንያት ሆኗል” ብለዋል።

  8. ኢራን ፀረ መርከብ ሱፐርሶኒክ ሚሳዔሎችን ከቻይና ለመግዛት ከጫፍ መድረሷ ተዘገበ

    ኢራን ከቻይና ፀረ መርከብ ክሩዝ ሚሳዔሎችን መግዛት የሚያስችላትን ስምምነት ለመፈጸም ከጫፍ መድረሷን ሮይተርስ የዜና ወኪል ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ስድስት ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

    ኢራን ፀረ መርከብ ሚሳዔሎችን ልትገዛ እንደሆነ የተሰማው፤ ቴህራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች ያለችው አሜሪካ የባሕር ኃይሏን በኢራን ባሕር ዳርቻ ባሰማራችበት በዚህ ጊዜ ነው።

    ቻይና ሠራሹን ‘ሲኤም-302’ ሚሳዔል ለመግዛት የሚደረገው ድርድር ፍጻሜው ላይ ቢሆንም ኢራን መሳሪያውን የምትረከብበትን ቀን በተመለከተ ስምምነት ላይ አለመደረሱን ምንጮች መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሲፐርሶኒክ ሚሳዔሎቹ 290 ኪሎ ሜትር ድረስ የመወንጨፍ አቅም ያላቸው ሲሆን በከፍታ እና በዝቅታ በመምዘግዘግ የመርከብ ላይ መከላከያዎችን ማለፍ እንዲችሉ ሆነው የተሠሩ ናቸው።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ፤ ኢራን ይህንን መሳሪያ መታጠቋ የማጥቃት አቋሟን በከፈተኛ መጠን እንደሚያሳድግ እንዲሁም የአሜሪካ ባሕር ላይ የምትጋርጠው ስጋት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ሁለት የጦር መሳሪያ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

    ቢያንስ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የተጀመረው የኢራን እና ቻይና የሚሳዔል መሳሪያ ሥርዓት ግዢ፤ ባለፈው ሰኔ ላይ ከተካሄደው የእስራኤል እና ኢራን 12 ቀናት ጦርነት በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት ተፋጥኗል ተብሏል።

    ንግግሩ ከዚህ በኋላ በነበሩ የክረምት ወራት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ ከፍተኛ የኢራን የጦር መኮንኖች እና የመንግሥት ኃላፊዎች ወደ ቻይና እንደተጓዙ ሁለት የደኅንነት ምንጮች እንደነገሩት ሮይተርስ ገልጿል።

    አንድ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣን "ኢራን ከአጋሮቿ ጋር ወታደራዊ እና የደኅንነት ስምምነቶች አሏት፤ አሁን ደግሞ እነዚህን ስምምነቶች ለመጠቀም ተገቢው ጊዜ ነው" ሲሉ ለዜና ወኪሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የቻይና መንግሥት በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠም ተብሏል። የአሜሪካ መንግሥትም ስለ ኢራን እና ቻይና የሚሳዔል ግዢ ድርድር ለቀረበለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት እንደተቆጠበ ተገልጿል።

    አንድ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣን በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተካረረውን ፍጥጫ ጠቅሰው፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ወይ ስምምነት ላይ እንደርሳለን ወይም እንደ ባለፈው ጊዜ በጣም ጠንካራ የሆነ ነገር ማድረግ ይኖርብናል” የሚል አቋም እንዳላቸው አስታውሰዋል።

    ይህ የሚሳዔል ግዢ የሚፈጸም ከሆነ ከቻይና ወደ ኢራን የተላለፈ እጅግ ዘመናዊው ወታደራዊ መሳሪያ ይሆናል። ይሁን እንጂ በተባበሩት መንግሥታት ኢራን ላይ ተጣለነውን ማዕቀብ የሚጥስ እንደሆነም ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

  9. የግብፅ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ እና የሳዑዲው ልዑል ሳልማን በዝግ ተወያዩ

    የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ሰኞ ዕለት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ከሳዑዲው አልጋወራሽ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር መወያየታቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታወቀ።

    ሁለቱ ባለሥልጣናት በጋዛ፣ በቀጣናው ባለው ውጥረት እና በሌሎችም የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በአልጋ ወራሹ የግል መኖሪያ ቤት በዝግ ውይይት ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

    በአል ሲሲ ጉብኝት ሁለቱ አገራት የጋራ በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያደርጉትን ምክክር እና ትብብር በማጠናከር የረጅም ጊዜ ግንኙነታቸውን ማስቀጠልን በተመለከተ መነጋገራቸው ተገልጿል።

    ሁለቱ መሪዎች በቀጣናው ውጥረት እና ግጭት እንዳይኖር ለማድረግ፣ ሰላማዊ መፍትሄዎችን ለማምጣት፣ የአረብ አገራትን ትብብር ለማጠናከር እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሳይገባ የአገራትን ሉዓላዊነት እንዲሁም የግዛት አንድነት ለማስከበር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

  10. አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመች ጦርነቱ የሁለቱ አገራት ብቻ እንደማይሆን ኢራን አስጠነቀቀች

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም የተለያዩ አማራጮችን እያጤነች መሆኑ እየተገለጸ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፤ ኢራን ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ ጦርነቱ በሁለቱ አገራት መካከል ብቻ እንደማይሆን አስጠነቀቀች።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ሦስተኛ ዙር ድርድር ሊካሄድ በተቃረበበት ጊዜ አሜሪካ “ከውስን የመጀመሪያ ደረጃ የአየር ጥቃት አንስቶ፣ የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት ለቀናት የሚዘልቅ የአየር ጥቃት ዘመቻ” ለመፈጸም እያሰበች መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ነገር ግን ኢራን በአሜሪካ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ የሚከተለው ውጤት በሁለቱ አገራት ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ አስጠንቅቃለች።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ውስን የሚባል ጥቃት እንደሌለ እና የትኛውም ዓይነት በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ከባድ የሆነ የአጸፋ ምላሽ እንደሚጠብቀው አስጠንቅቀዋል።

    እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ኢራን ከአሜሪካ የሚቀርቡላትን ቅድመ ሁኔታዎችን እንድትቀበል ለማስገደድ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውስን ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ መሆናቸው ተዘግቦ ነበር።

    አሜሪካ የትኛውንም ዓይነት ወታደራዊ እርምጃ በኢራን ላይ ብትወስድ አደጋዎች እንዳሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናት መናገራቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    “ሁሉም አማራጮች አደጋ አላቸው። በተለይ ደግሞ የተራዘመ ጥቃት በአሜሪካ ሠራዊት እና በጦር መሳሪያ ላይ ከፍተኛ ዋጋን ከማስከተሉ በተጨማሪ ኢራን አጸፋ የምትመልስ ከሆነ በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ አጋሮችን ለመከላከል አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል” ሲሉ ባለሥልጣኑ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ይህ ስጋትም በከፍተኛ የአሜሪካ ወታደራዊ እና የደኅንነት ባለሥልጣናት ስብሰባዎች ላይ ተነስቶ መነጋገሪያ መሆኑ ተገልጿል።

    አሜሪካ ጥቃት ትፈጽማለች የሚለውን ዛቻ ተከትሎ ኢራን ጥቃት የሚሰነዘርባት ከሆነ በአካባቢው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር መርከቦች፣ የጦር ሰፈሮች እና አጋሮች ላይ ከባድ የአጸፋ ጥቃት እንደምትፈጽም በተደጋጋሚ አሳውቃለች።

    ኢራን የአጸፋ እርምጃ ዋነኛ ዒላማ የምትሆነው እስራኤል በበኩሏ ኢራን በእስራኤል ላይ የበቀል ጥቃት ከፈጸመች በእስላማዊ ሪፐብሊኩ ታሪክ ውስጥ ከባዱ ስህተት ይሆናል ስትል አስጠንቅቃለች።

    አሜሪካ ባለፉት ሳምንታት ግዙፍ አውሮፕላን ጫኝ እና ሌሎች የጦር መርከቦቿን እንዲሁም የጦር አውሮፕላኖችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በማሰማራት በኢራን ላይ ለጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀች ትገኛለች።

    ዘገባዎች እንዳመለከቱት በአውሮፓውያኑ 2003 አሜሪካ በኢራቅ ላይ ካካሄደችው ወረራ ወዲህ ከፍተኛውን ወታደራዊ አቅሟን በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ አሰማርታለች።

  11. በአሜሪካ በተከሰተ ከፍተኛ በረዶ ምክንያት 5,000 በረራዎች ተሰረዙ

    በአሜሪካ ‘ኢስት ኮስት’ አካባቢዎች በተከሰተው ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ መጠን ያለው በረዶ ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲስተጓጎሉ፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎች ተሰረዙ።

    በሮድ አይላንድ እና ማሳቹሴትስ ግዛቶች ውስጥ 94 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ በረዶ መመዝገቡን የአገሪቱ ብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት ገልጿል። ኒው ዮርክ ውስጥም ከፍተኛ በረዶ እንደተከሰተ ተቋሙ አስታውቋል።

    ኒው ዮርክ ውስጥ ጉዞ ማድረግ "የማይቻል" በሚባል ደረጃ ላይ እንደደረሰ የግዛቱ አስተዳደር አስጠንቅቋል።

    ኢስት ኮስት ውስጥ ከ600 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች እና ንግዶች ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውጪ ሲሆኑ፣ እንደ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴትስ ያሉ ግዛቶች ደግሞ በከፍተኛ መጠን ተጎድተዋል ተብሏል።

    በቦስተን የብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት የሜትሮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ካንዲሰን ሬንሴሲን የተመዘገበው የበረዶ መጠን ከዚህ ቀደም ከነበረው ሪከርድ የበለጠ እንደሆነ ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ተናግረዋል።

    “[ሪከርዱን] ሙሉ በሙሉ ጥሶት ሄዷል፤ እንደ ሁሉም ሰው ሁሉ እኛም ደንግጠናል” ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

    ተጎራባች በሆኑት ሮድ አይላንድ እና ኮኔቲከት ግዛቶች ውስጥ አስፈላጊ ያልሆኑ ጉዞዎች እንዳይደረጉ እገዳ ተጥሏል። የማሳቹሴትስ ገዥ ማውራ ሄሊም ተመሳሳይ እገዳ አስተላልፈዋል።

    ገዥዋ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ "በደቡብ ምሥራቅ ማሳቹሴትስ ውስጥ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር መኪና መንዳት ታግዷል። የዋና መንገዶች የፍጥነት ገደብም በሰዓት ወደ 25 ኪሎ ሜትር ዝቅ እንዲል አዝዣለሁ" ብለዋል።

    ጥቅጥቅ ያለው ዕይታን የሚጋርድ የበረዶ ንፋስ ከቦታ ቦታ መጓዝን “እጅግ አደገኛ” እያደረገው እንደሆነም አክለዋል።

    “ችግር ውስጥ የምትገቡ ከሆነ እርዳታ ወደ እናንተ እንዲደርስ ማድረግ አስቸጋሪ ነው... የምትኖሩት የትም ቢሆን ሁሉም ሰው ወደ መንገድ እንዳይወጣ በጥብቅ አሳበስባለሁ” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    ማሳቹሴትስ ወደ 300 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ እንደሆኑ የpoweroutage.us መረጃ ያመለክታል።

    በኒው ዮርክ ከተማ ተጥሎ የነበረው የጉዞ እገዳ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ካሉበት እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ ነበር። ሁሉም መንገዶች፣ የፍጥነት መንገዶች እና ድልድዮች ተዘግተው ታይተዋል።

    ኮኔቲከት እና ኒው ጀርሲ ውስጥ ደግሞ በበረዶው ምክንያት የሚወድቁ ዛፎች እና ቅርንጫፎች አደገኛ የመንገድ ሁኔታ ይፈጥራሉ እንዲሁም የኃይል መቋረጥ ሊያስከትሉ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።

  12. ከኢራን ጋር መካረር ውስጥ ያለችው አሜሪካ ከቤይሩት ኤምባሲዋ በከፊል ለቅቃ ወጣች

    የአሜሪካ መንግሥት የደኅንነት ግምገማ ካደረገ በኋላ፤ በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ከሚገኘው ኤምባሲ ሠራተኞች መከካል አስፈላጊ ያልሆኑት በሙሉ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።

    ውሳኔው የመጣው በቀጣናው ውጥረቱ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ሲሆን፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ ስምምነት ላይ የማትደረስ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

    ኢራን ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ አፃፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ገልጻለች። በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና ጣቢያዎችም ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እስራኤልን ለመጎብኘት የያዙትን ዕቅድ ያለምንም ምክንያት አራዝመዋል።

    አንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን “የደኅንነት ከባቢውን እንፈትሻለን። እናም ሰሞነኛ ፍተሻችን መሠረት አድርገን አስፈላጊ በሆኑ ሠራተኞች ብቻ ዱካችንን መገደብ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ደርሰንበታል” ብለዋል።

    ኤምባሲው ሥራውን እንደሚቀጥል የጠቆሙት ባለሥልጣኑ፤ የሠራተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል የተወሰደ ጊዜያዊ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።

    50 የሚሆኑ የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞች ከቤይሩት እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። 32 የኤምባሲው ባልደረቦች እና ቤተቦቻቸው ሠኞ ዕለት በቤይሩት ኤርፖርት እንዲበሩ እንደተደረገ የኤርፖርት ባለሥልጣናት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

    በከፊል ከቤይሩት ለቅቆ ለመውጣቱ ይህ ነው የተባለ ትክክለኛ ምክንያት በይፋ አልተሰጠም።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል እየተደረገ ያለው የቃላት ልውውጥ ቴህራን እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት ያስነሳ ሲሆን፤ የኢራን ታላቅ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሊሚኒ በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው የአሜሪካ ኃይሎች ላይ ዝተዋል።

    ዋሽንግተን እ.አ.አ በ1983 በቤይሩት ኤምባሲ የደረሰውን የቦምብ ጥቃት በኢራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ሂዝቦላ እንዳደረሰው ትናገራለች።

    ባለፈው ሐሙስ ትራምፕ ኢራን ስምምነት ላይ መድረሷን አሊያም አሜሪካ እርምጃ ትወስድባት ከሆነ “በሚቀጥሉት 10 ቀናት” ይታወቃል ብለው ነበር።

  13. በኢራን ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ተቃውሞ ማገርሸቱ ተዘገበ

    ባለፉት ቀናት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ውስጥ በሚገኙ በአምስት ዩኒቨርስቲዎች ፀረ መንግሥት ተቃውሞዎች መካሄቸዳውን ከስፍራው የወጡ ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎች አመለከቱ።

    የቢቢሲ የፋርስ ቋንቋ አገለግሎት እና የቢቢሲ መረጃ ማጣሪያ በምሥሎቹ ላይ ባደረጉት ማጣራት ባለፈው ጥር ወር ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ተቃውሞ በኋላ ትልቅ ተቃውሞ በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ መካሄዳቸውን አረጋግጠዋል።

    ባለፈው በመላዋ ኢራን በሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ከባድ ተቃውሞ ከተካሄደ እና ባለሥልጣናት በወሰዱት ከባድ እርምጃ በቁጥጥር ስር ካዋሉት በኋላ በዩኒቨርስቲዎች የተካሄደው ይህ ተቃውሞ የመጀመሪያው ነዋ።

    በዩኒቨርስቲዎች በተካሄደው ተቃውሞ ከኢራን አብዮት በፊት የአገሪቱ መለያ የሆነውን አንበሳ እና ፀሐይ ያለበትን የንጉሡ ዘመን ሰንደቅ ዓላማን ያየዙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

    በተመሳሳይ የኢራን መንግሥት ደጋፊ ሰልፈኞች የአሜሪካንን እና የእስራኤልን ሰንደቅ ዓላማ በማቃጠል ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    በቴህራን ዩኒቨርስቲ በተካሄደው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች የንጉሣዊ አስተዳደሩን የሚደግፉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

    ተመሳሳይ የተቃውሞ ሰልፎች በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች እና ካምፓሶች የተካሄዱ ሲሆን በአንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በመንግሥት ተቃዋሚዎች እና ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተከስቶ እንደነበር ታውቋል።

    ለሳምንታት በተካሄደው ቀደም ባለው የተቃውሞ ሰለፍ ቢያንስ ሰባት ሺህ ሰዎች መገደላቸውን መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የኢራን ሰብአዊ መብቶች ተቋም ዜና ምንጭ ገልጿል።

  14. በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ ቦታዎች ለብቻቸው ምርጫ እንዲደርግ ተወሰነ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ ቦታዎች “ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው” በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

    ቦርዱ እንዳለው ያወጣውን የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ዝርዝር ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥር 25/2018 ዓ.ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ በሁለቱ ክልሎች መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩ አምስት የምርጫ ክልሎች ጉዳይ እስኪፈታ ለብቻቸው ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

    እነዚህ በትግራይ እና በአማራ ክልል የይገባኛል ያቄ የተነሳባቸው እና ከሁለቱም ክልሎች ውጭ ሆነው በራሳቸው ምርጫ እንዲደረግባቸው የተወሰኑት የሁመራ፣ የአዲረመፅ፣ የኮረም አፍላ፣ የጠለምት እና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ናቸው።

    በእነዚህ አምስት የምርጫ ክልሎች የሚገኙ መራጮች ድምጸቸውን የሚሰጡት ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት ዕጩዎች ሲሆን፣ የክልል ምክር ቤት ምርጫው በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ መንግሥት ውሳኔ ከተፈታ በኋላ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማሳወቁን ቦርዱ ገልጿል።

    ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ ወር ለሚካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ጥር 22/2018 ዓ.ም. ምርጫ ክልሎች እና ምርጫ ጣቢያዎች ዝርዝር ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

  15. ቻድ ከሱዳን ጋር የሚያወስናትን ድንበር ዘጋች

    ቻድ ከሱዳን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ የሚደርስን ጥቃት ለመከላከል በሚል ከአገሪቱ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋች።

    የቻድ መንግሥት ከሱዳን ጋር የሚያዋስነውን ድንበር የዘጋው አል ቲና በተባለው የድንበር ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና የሱዳን ጦር አጋር በሆኑ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ ከተከፈተ በኋላ ነው።

    የአገሪቱ መንግሥት ድንበሩ ለምን ያህል ጊዜ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ አላስታወቀም።

    ቻድ ከሱዳን ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ለሰብዓዊ ድጋፎች ከሚደረግ ዝውውር ውጪ ማናቸውንም የሰው እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን አግዳለች።

    ቻድ በጦርነት ወደ ምትታመሰው ሱዳን የሚገባ እርዳታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ዋነኛ መተላለፊያ ብትሆንም፤ በተደጋጋሚ የጎረቤት አገር ሱዳን ግጭት ወደ ግዛቷ በመግባት የዜጎቿን ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሏል።

    የቻድ ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የሱዳን ግጭት ወደ አገራቸው እንዳይስፋፋ ለመከላከል እና የአገሪቱን ዜጎች እና ስደተኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ድንበሩ እንዲዘጋ መወሰኑን ገልጿል።

    የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ቅዳሜ ዕለት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በድንበር ከተማዋ አል ታይን የሚገኝ የቻድ ጦር ካምፕ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ዘግበዋል። መንግሥት ግን በጉዳዩ ላይ ምንም ያለው ነገር የለም።

  16. ኤርትራ የነበሩት የሳዑዲ ከፍተኛ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

    ከሳምንት በፊት ኤርትራ የነበሩት የሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አልኬሬጂ ዛሬ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር በአዲስ አበባ ተገናኝተው ተወያዩ።

    ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ዛሬ ሰኞ የካቲት 16/2018 ዓ.ም. ተገናኝተው በቀጠናዊ ሰላም እና ሁለቱን አገራት በሚመለከቱ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።

    የሳዑዲ አረቢያው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሳምንት በፊት በአሥመራ ተገኝተው ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በቀይ ባሕር እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተው ነበር።

    የሳዑዲው ውጭ ጉዳይ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር በተገናኙበት ወቅት በቀይ ባሕር ዳርቻ አገራቱ በሰላም እና በደኅንነት ጉዳዮች ላይ በሚኖራቸው አስተዋጽኦ ላይ ተነጋግረዋል።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው እንደነበር ይታወሳል።

    በወቅቱ የሳዑዲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በቁልፍ ዘርፎች ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እንዲሁም የሁለቱም አገራት ፍላጎት በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖራቸው ትብብር ላይ ያተኮረ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጾ ነበር።

    የሳዑዲ ምክትል ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አልኬሬጂ በዛሬው ዕለት ለሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ጋር በሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅም ላይ በተመሰረቱ ቀጣናዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ማድረጋቸው ተገልጿል።

    ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመጓዝ ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

    ከሳምንት በፊት አሥመራ የነበሩት የሳዑዲው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ባየለበት ጊዜ ነው።

  17. ታዋቂ ሶሪያዊት አሠሪዋን ገድላለች የተባለችው ኡጋንዳዊት የቤት ሠራተኛ በሞት ልትቀጣ ነው

    ሶሪያ ውስጥ ታዋቂዋን ተዋናይት አሠሪዋን ገድላለች የተባለችው ኡጋንዳዊቷ የቤት ሠራተኛ በዚህ ሳምንት ማብቂያ በሞት ልትቀጣ መሆኑ ተነገረ።

    ቪኪ አጆክ የተባለችው ኡጋንዳዊት በሶሪያ ውስጥ ታዋቂ በሆነ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመተወን የሚታወቁትን 87 ዓመቷ አሠሪዋን ሁዳ ሻራዊን በመግደል ነው ሞት የተፈረደባት።

    አጆኪ ባለፈው ጥር ወር ውስጥ በአገሪቱ ዋና ከተማ ውስጥ በሚገኘው የአሠሪዋ ቤት ውስጥ ከቀጣሪዋ ጋር አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ በጠንካራ ቁስ መትታቸው ለህልፈት እንደበቁ ተዘግቧል።

    ከድርጊቱ በኋላ ማምለጥ ችላ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ በቁጥጥር ስር ውላለች።

    አጆኪ በሶሪያ መገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርባ አሠሪዋ ለረጅም ጊዜ ጥቃት ይፈጸምባት እንደነበር እንዲሁም ደሞዝም እንደማይከፈላት በመግለጽ ለክስተቱ ምክንያት ናቸው ያለቻቸውን ነገሮች ተናግራለች።

    በዚህ ሳምንት ማብቂያ ላይ የሞት ቅጣት ሊፈጸም እንደሆነ መነገሩን ተከትሎ ለኡጋንዳ ስደተኛ ሠራተኞች መብት የሚከራከወቅ ቡድን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ሕይወቷን እንዲያተርፉ ግፊት እያደረገ ነው።

    መብት ቡድኑ ሠራተኛዋ ወንጀሉን የፈጸመችው በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ሆና ሊሆን ይችላል የሚለውን ጨምሮ ሕጋዊ ሁኔታው ከእንደገና እንዲመረመር እየጠየቀ ነው።

    ምንም እንኳን በኡጋንዳ እና በሶሪያ መካከል ሠራተኞችን በተመለከተ የሁለትዮሽ ስምምነት ባይኖርም፤ መንግሥት ዜጋው ምህረት ወይም ሌላ የሕግ አማራጭ እንድታገኝ በሁሉም የዲፕሎማሲ አማራጮችን ጥረት እንዲያደርግ ተጠይቋል።

    ነገር ግን አስካሁን የኡጋንዳ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጡም።

  18. ኪም ጆንግ ኡን በድጋሚ ለሰሜን ኮሪያ ገዢ ፓርቲ መሪነት ተመረጡ

    የሰሜን ኮሪያ ገዢ የሆነው የሠራተኞች ፓርቲ ኪም ጆንግ ኡንን በድጋሚ ዋና ጸሐፊው አድርጎ መምረጡን አገሪቱ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

    የኪም ቤተሰብ ከአውሮፓውያኑ 1940ዎቹ አንስቶ አምባገነኑን ሥርዓት ሲመራ የነበረ በመሆኑ፤ ሀሳቦችን ያለ ተቃውሞ የሚያጸድው የፓርቲው ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ማሳለፉ እምብዛም የሚያስገርም ነገር ሆኖ አልታየም።

    በመንግሥት የሚመራው ‘ኬሲኤንኤ’ የተባለው ዜና ወኪል፤ ሰሜን ኮሪያ በኪም ጆንግ ኡን አመራር ሥር ሆና “መሠረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች” ብሏል። “በኒውክሌር ኃይሎቹ” አማካኝነት ያሳየችው “ጦርነትን የመከላከል” እርምጃም “ወሳኝ” እንደሆነ የዜና ወኪሉ ገልጿል።

    ሰሜን ኮሪያ ምንም እንኳ ለረጅም ጊዜ የቆየ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ የተጣለባት ቢሆንም አሁንም የኒውክሌር አቅሟን መገንባቷን ቀጥላበታለች። በየጊዜውም ክልከላ ተጣለባቸውን የአገር አቋራጭ ሚሳዔሎች ሙከራ ታደርጋለች።

    ይሁን እንጂ የአገሪቱ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ያለው ሚስጥራዊነት ሠራዊቱ ምን ያህል እድገት እንዳሳየ መገምገም እንዳይቻል አድርጎታል።

    በአውሮፓውያኑ 2011 አባታቸው ከሞቱ በኋላ ሥልጣኑን የተረከቡት ኪም፤ በኒውክሌር ፕሮግራም ላይ በከፍተኛ መጠን ኢንቨስት አድርገዋል። ይህ እርምጃቸውም ሰሜን ኮሪያ ለምዕራቡ ዓለም በተለይም ለአሜሪካ ትልቅ ፈተና እንድትሆን አድርጓታል።

    ኪም፤ አራተኛ ቀኑን በያዘው የገዢው ፓርቲ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአገሪቱን የመሣሪያ ፕሮግራም ቀጣይ ምዕራፍ ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

    ስብሰባ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሰሜን ኮርያ የኒውክሌር መሣሪያን መሸከም ይችላሉ ያለቻቸውን የሮኬት ማስወንጨፊያዎች ይፋ አድርጋለች።

    ባለፈው አስር ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ የተሰበሰበው የፓርቲው ምክር ቤት ስብሰባውን የጀመረው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት ነው። የዜና ወኪሉ እንደዘገበው አምስት ሺህ ገደማ የፓርቲው አባላት ተገኝተዋል።

    ይህ ስብሰባ፤ ሰሜን ኮሪያን ጉዳይ በትኩረት ለሚከታተሉ አካላት እንኳ ግልጽ ስላልሆነው የአገሪቱ የፖለቲካ ሥልጣን አዋቃቀር ፍንጭ የሚሰጥ ሆኗል።

    እጅግ ወሳኝ ፖለቲካዊ ኹነት ተደርጎ የሚቆጠረው ይህ ስብሰባ፤ ከውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እስከ የኒውክሌር ፍላጎቷ ድረስ አገሪቱ ቅድሚያ የምትሰጣቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ ያመለክታል።

  19. የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለትራምፕ ፍላጎት የማንንበረከከው “ኢራናውያን" ስለሆንን ነው አሉ

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በቅርቡ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ኢራን ለምን ለፍላጎታቸው ተገዥ እንዳልሆነች እንደጠየቋቸው መናገራቸውን ተከትሎ በሰጡት ምላሽ “እኛ ኢራናዊ ስለሆንን” ነው ሲሉ ምላሽ ሰጡ።

    አራጋቺ እሁድ ዕለት ኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ዊትኮፍ "ኢራን ለዋሺንግተን ፍላጎቶች ለምን እንዳልተገዛች ተጠይቀው ነበር። "ምክንያቱም ኢራናውያን ስለሆንን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የአሜሪካ ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት ልዩ መልዕክተኛው ስቲፍቭ ዊትኮፍ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልስ ወቅት ትራምፕ ኢራን ይህ ሁሉ ጫና እየተደረገባት አልበገርም ለምን እንዳለች ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር።

    ልዩ መልዕክተኛው አሜሪካ በቀጣናው የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቧን ብታሰማራም "እጇን ያልሰጠችው" ለምን እንደሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማወቅ ይፈልጋሉ ብለዋል።

    "ዛሬ ጠዋት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀውኛል። ተስፋ ቆርጠዋል ማለት አልፈልግም። ምክንያቱም ብዙ አማራጮች እንዳሏቸው ያውቃሉ። ነገር ግን ለምን እጃቸውን እንዳልሰጡ፤ እንዳልተስማሙ ማወቅ ይፈልጋሉ።"

    ዊትኮፍ እንደሚሉት የትራምፕ አስተዳደር ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትታጠቅ እና ያንን ለማረጋገጥ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድትዘረዝር ይፈልጋል።

    ይህ አስተያየት የመጣው ሁለቱ አገራት ለሦስተኛ ዙር ውይይት ከመገናኘታቸው በፊት ነው። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በኦማን አደራዳሪነት ሁለቱ አገራት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

    አሜሪካ ጦር ጫኝ መርከቦቿን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ማንቀሳቀሷን ተከትሎ ጥቃቶቸ ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ተገልጾ ነበር።

    እሁድ ዕለት በተለያዩ የአገሪቱ ዩኒቨርስቲዎቸ የሚማሩ ኢራናውያን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው ነበር።