ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እስከ ምጽዋ ሽብርን የሚከላከል 'ኤሊት ፎርስ’ ገንብታለች" አሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ "ሽብርን" የሚከላከል “ኤሊት ፎርስ” መገንባቷን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት እሁድ የካቲት 15/2018 ዓ.ም. በሐዋሳ በተከበረው የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ወቅት ነው።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሱዳን የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሜሴቪኒ ላይ ቅሬታ አቀረበች

    የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ አዛዥ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ሲወያዩ

    የፎቶው ባለመብት, @KagutaMuseveni

    ሱዳን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዡን ተቀብላ ያስተናገደችው ኡጋንዳ ላይ ተቃውሞዋን አሰማች።

    የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ከአርኤስኤፍ አዛዥ ሞሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ራሳቸውን እንዲያርቁ ጠይቀዋል።

    የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ በቤተመንግሥታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት አርብ የካቲት 13/2018 ዓ.ም. ነበር

    የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን በቀጠለው የእርስ በእርስ ጦርነት ውሰጥ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽሟል በሚል ይከሰሳል።

    ካርቱም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለመጠበቅ እንደምትፈልግ ገልጻ በውስጥ ጉዳይዋ ግንማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል ተናግራለች።

    ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአደባባይ የታዩት የአርኤስኤፍ መሪ ሃምዳን ዳጋሎ ጉብኝት ብዙዎችን አስገርሟል።

    ሱዳን፣ ኡጋንዳ የግጭቱን አሳሳቢነት ችላ በማለት እና ዓለም አቀፍ ደንቦችን በመጣስ ከአማፅያን አዛዥ ጋር በመገናኘቷ ወቀሳዋን ሰንዝራለች።

    ነገርግን በአፍሪካ ኅብረት ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች እንዲያደራድሩ የተሾሙት ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ከሄሜቲ ጋር አርብ የተካሄዱት ስብሰባ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት የሚያበቃበትን መንገድ በማፈላለግ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

    የቀጠናው መንግሥታት በግጭቱ ውስጥ ካሉ ተቀናቃኝ ወገኖች ጋር በመወገን ትችት ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል።

  2. የአሜሪካ አምባሳደር እስራኤል አብዛኛው መካከለኛው ምሥራቅ ላይ መብት አላት ማለታቸው ውዝግብ አስነሳ

    አምባሳደር ማይክ ሀክቤ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ማይክ ሀክቤ እስራኤል አብዛኛው መካከለኛው ምሥራቅ የመግዛት መብት አላት ማለታቸው በአረብ እና ሙስሊም አገራት ተኮንኗል።

    አምባሳደሩ ከአሜሪካዊው ወግ አጥባቂ ታከር ካርሰን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው ይህን ያሉት።

    አሶሼትድ ፕረስ እንደዘገበው ካርሰን መፅሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ የአብርሃም ዘሮች ዛሬ ሙሉውን መካከለኛውን ምሥራቅ የሚይዘውን መሬት መያዝ እንደሚችሉ በመግለፅ፤ አምበሳደሩ እስራኤል ይህን መሬት የመያዝ መብት እንዳላት ጠይቋል።

    “ሁሉንም ቢወስዱት ምንም አይደለም” በማለት አምበሳደር ሀክቤ መልሰዋል።

    ሆኖም ያሉት አምባሳደሩ እስራኤል ከግዛቷ የመስፋፋት ፍላጎት እንደሌላት እና አሁን የያዘችውን መሬት ደኅንነት የመጠበቅ መብት አላት ብለዋል።

    አስተያየታቸው ከጎረቤት ግብፅ እና ዮርዳኖስ ጀምሮ በሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌት፣ ኦማን እና በእስላሚክ ትብብር ድርጅት እና የአረብ ሊግ በኩል ወዲያው ተቃውሞ አስነስቷል።

    ከእስራኤልም ሆነ ከአሜሪካ ወዲያው አስተያየት አልተሰጠም።

    እ.አ.አ ከ1948 ምስረታዋ በኋላ እስራኤል እውቅና ያለው ድንበር የላትም። ከአረብ አገራት ጋር የምትጋራቸው ድንበሮች በጦርነቶች፣ ግዛቶችን በመጠቅለል እና በተኩስ አቁም እና በሰላም ስምምነት ምክንያት ተቀያይሯል።

  3. ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ "ኢትዮጵያ ከሶማሊያ እስከ ምጽዋ ሽብርን የሚከላከል 'ኤሊት ፎርስ’ ገንብታለች" አሉ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ሲያደርጉ

    የፎቶው ባለመብት, ebc

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሽብርን የሚከላከል “ኤሊት ፎርስ” [ልዩ ኃይል] መገንባቷን ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በዛሬው ዕለት በሐዋሳ ከተማ በተከበረው የመከላከያ ሠራዊት የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ 65ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

    “የእኛ ዝግጅት በድፍን አፍሪካ ሰላም ለማረጋገጥ” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በቀጠናችን ላሉ አገራት አለኝታ፣ መከታ፣ ጋሻ ለመሆን ነው” ብለዋል።

    ለዚህም ሲባል በምድር፣ በተራራ እና በጅረት የነበረውን፣ ባሕር ላይ ወደሚደረግ ሥልጠና መሸጋገሩን ተናግረዋል።

    “ከሶማሊያ ጫፍ እስከ ምጽዋ ጫፍ” በባሕር የሚያጋጥሙ ሽብሮችን “ወንድም ሕዝቦችን ደግፈን” ሽብርን ለማስቀረት ልማት ብልጽግናን በቀጠናችን ለማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው በቂ የሆነ ኤሊት ፎርስ መገንባቱን ተናግረዋል።

    በበዓሉ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባሻገር ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና ሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ፖቲካዊ እና ወታደራዊ ባለሥልጣነት ተገኝተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ “ቀይ ቦኔት ለባሾቹ ውጊያ የሚጨርሱ እና ውጊያ የሚያስቀሩ ናቸው” ብለዋል፡፡

    ኢትዮጵያ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም፣ በምሽግ ብቻ ሳይሆን በስትራቴጂክ ቦታዎች “ውጊያን የሚያጧጡፍ እና የሚያሳጥር ተቋም” ስለገነባች መላው አፍሪካውያን እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

    ኢትዮጵያ ኤሊት ፎርስ የምትገነባው በቀጣናችን ውጊያ እና ሽብር እንዳይፈጠር፤ ሲፈጠርም በአጭር ጊዜ ለመቋጨት እንደሆነም ተናግረዋል።

  4. ፓኪስታን በአፍጋኒስታን ላይ በፈጸመችው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን ታሊባን አስታወቀ

    ኢዝላማባድ ጥቃቱ የተካሄደው በቅርቡ በፓኪስታን የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃትን ተከትሎ መሆኑን አስታውቃለች

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    ፓኪስታን ምሽቱን አፍጋኒስታን ላይ በፈጸመችው ጥቃት በርካቶች መገደላቸውን እና መቁሰላቸውን ታሊባን አስታወቀ።

    ታሊባን ከሞቱት እና ከቆሰሉት መካከል ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል ብሏል።

    ኢዝላማባድ ጥቃቱ ሰባት የወታደራዊ ካምፖች ላይ እና በፓኪስታን እና አፍጋኒስታን ድንበር አቅራቢያ የሚገኙ መደበቂያዎች ላይ ትኩርት ማድረጋቸውን ገልጻለች።

    ጥቃቱ የተፈጸመው በቅርቡ በፓኪስታን የደረሰ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተከትሎ ነው።

    አፍጋኒስታን ጥቃቱን አውግዛ በርካታ የሰላማዊ ዜጎች መኖሪያዎች እና የሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች ዒላማዎች መሆናቸውን ገልጻለች።

    ጥቃቱ የተፈጸመው ሁለቱ አገራት በጥቅምት ወር ድንበር ተሻጋሪ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ነው።

    የታሊባን መከላከያ ሚኒስቴር ጥቃቱ በኒካራጉዋ እና ፓክቲካ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች መኖረያ ቤቶች ዒላማ ተደርገዋል ብሏል።

    በኒካራግዋ የሚገኙ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ የአንድ ግለሰብ ቤት ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 20 የቤተሰቡ አባላት መገደላቸውን ገልጸዋል።

    የፓኪስታን ማስታወቂያ እና ብሮድካስት ሚኒስቴር ጥቃቱ የተካሄደው “የስለላ መረጃዎች ላይ በመመስረት በተመረጡ ሰባት የአሸባሪዎች ካምፖች እና መደበቂያዎች ላይ ነው” ብሏል።

  5. ትራምፕ ኢራን የአሜሪካን ፍላጎቶች ለምን እንዳልተቀበለች ማወቅ እንደሚፈልጉ ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ ተናገሩ

    ትራምፕ እና ልዩ ምልዕክተኛው ዊትኮፍ

    የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE/REX/Shutterstock

    የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ኢራን ከአሜሪካ ለሚደርስባት ከፍተኛ ወታደራዊ ጫና ለምን እጇን እንዳልሰጠች ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የማወቅ “ጉጉት አላቸው” ሲሉ ተናገሩ።

    ዊትኮፍ ቅዳሜ ዕለት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ልልስ ላይ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው የኒውክሌር ድርድር በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

    ልዩ መልዕክተኛው አሜሪካ በቀጣናው የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቧን ብታሰማራም "እጇን ያልሰጠችው" ለምን እንደሆነ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማወቅ ይፈልጋሉ ብለዋል።

    "ዛሬ ጠዋት ፕሬዚዳንቱ ጠይቀውኛል። ተስፋ ቆርጠዋል ማለት አልፈልግም። ምክንያቱም ብዙ አማራጮች እንዳሏቸው ያውቃሉ። ነገር ግን ለምን እጃቸውን እንዳልሰጡ፤ እንዳልተስማሙ ማወቅ ይፈልጋሉ።"

    ዊትኮፍ እንደሚሉት የትራምፕ አስተዳደር ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትታጠቅ እና ያንን ለማረጋገጥ ተጨባጭ እርምጃዎችን እንድትዘረዝር ይፈልጋል።

    ዊትኮፍ ይህንን ያሉት በሁለቱ አገራት መካከል ለሁለት ዙር የተካሄደው ድርድር መሠረታዊ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችል ከቀረ በኋላ ነው።

    ሁለቱ አገራት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት በስዊዘርላንድ ውይይት ከካደረጉ በኋላ አሜሪካ ወሳኝ ክፍተቶች ይቀራሉ ብትልም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ግን "በመሠረታዊ መርሆዎች" ላይ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ኢራን በሚቀጥሉት ቀናት ምክረ ሃሳቦችን በጽሐፍ እንድታቀርብ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን አራጋቺ አርብ ዕለት በቀናት ውሰጥ ረቂቅ ምክረ ሃሰብ በጽሑፍ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

  6. ከ1500 በላይ ቬንዙዌላውያን የፖለቲካ እስረኞች ምህረት እነዲደረግላቸው ጠየቁ

    የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ እና ወንድማቸው የብሄራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ሮድሪጌዝ በካራካስ በሚገኘው ሚራፍሎረስ ቤተ መንግሥት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ እና ወንድማቸው የብሄራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጆርጅ ሮድሪጌዝ በካራካስ በሚገኘው ሚራፍሎረስ ቤተ መንግሥት

    የቬንዙዌላ ብሔራዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐሙስ ዕለት ባወጣው አዲስ ሕግ መሠረት 1,557 የፖለቲካ እስረኞች ምህረት እንዲደረግላቸው አመለከቱ።

    የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ወንድም እና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ አጋር የሆኑት ሆርጌ ሮድሪጌዝ “በመቶዎች” የሚቆጠሩ እስረኞች አስቀድመው መፈታታቸውን ተናግረዋል።

    ከእነዚህም መካከል ፖለቲከኛ ሁዋን ፓብሎ ጉዋኒፓ የሚገኙበት ሲሆን አዲሱ ሕግ የተወሰኑ እስረኞችን ያገላል ሲሉ ተችተዋል።

    ዩናይትድ ስቴትስ የአገሪቱን የቀድሞ ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ሥር ካዋለች በኋላ ቬንዙዌላ የፖለቲካ እስረኞችን እንድትፈታ አሳስባለች።

    የቬንዙዌላ የሶሻሊስት መንግሥት የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን ይክዳል።

  7. ካሜሮን ባልተለመደ ሁኔታ 21 ንጹኃን ሰዎችን የገደሉ ወታደሮቿን በእስራት ቀጣች

    መሣሪያ የያዘ የካሜሮን ወታደር

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ግጭት በሚበዛበት የካሜሮን ሰሜን ምሥራቃዊ ግዛት ውስጥ ቢያንስ 21 ንጹኃን ሰዎችን ገድለዋል የተባሉ የአገሪቱ ወታደሮች እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስር ተፈረደባቸው።

    የካሜሮን ወታደሮች ከአምስት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲፈረድባቸው ያደረገው ድርጊት የተፈጸመው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር።

    ይህ የቅጣት ውሳኔ ከመተላለፉ አስቀድሞ፤ የአገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ወታደሮቹን ግድያ በመፈጸም እንዲሁም ቃጠሎ እና ውድመት በማድረስ ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

    ካሜሮን ውስጥ በንጹኃን ላይ ግፎችን የፈጸሙ ወታደሮች የወንጀል ተጠያቂነት ሲሰፍንባቸው መመልከት ያልተለመደ ነው።

    የተጎጂዎች ጠበቆች ግን የተፈረደው የእስር ጊዜ አጭር መሆኑን በመጥቀስ ቅሬታቸው ገልጸዋል።

    ከተጎጂዎቹ ጠበቆች አንዱ የሆኑት ሶዘር መንከም፤ "ቅጣቱ በጣም አነስተኛ ነው። የወዳጅነት ብዬ ልገልጸውም እችላለሁ፤ ምክንያቱን እየተነጋገርን ያለነው ስለ ጭፍጨፋ ነው" ብለዋል።

    ፍርድ የተላለፈበት ይህ የወንጀል ድርጊት የተፈጸመው በአውሮፓውያኑ 2020 የአገሪቱ ወታደሮች ከታጠቁ የፉላኒ ጎሳ አባላት ጋር ሆነው ንጋርቡህን ወደተባለ መንደር በገቡበት ወቅት ነው።

    ሁለቱ አካላት በወሰዱት እርምጃ ንጹኃን ተገድለዋል። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ቡድን ሂውማን ራይትስ ዎች ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው ከተጎጂዎቹ መካከል የ13 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕጻናት ይገኙበታል።

    በተጨማሪም ኃይሎቹ ቤቶችን የማቃጠል እና ነዋሪዎችን የመደብደብ ድርጊቶችን ፈጽመዋል።

    ባልተለመደ ሁኔታ የካሜሩን መንግስት ወታደሮቹ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚገኙበት አካባቢ ወንጀል ስለመፈጸማቸው እውቅና ሰጥቷል።

    ባለስልጣናቱ መጀመሪያ ላይ በንጋርቡህ ስለተፈጸው ጥቃት ኃላፊነት ክደው የነበረ ቢሆንም የነበረው ዓለም ዓቀፍ ግፊት እና የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ እንዲካሄድ ያዘዙት ምርመራ ተመሳሳይ ግኝት ላይ መድረሱ ሃሳባቸውን አስቀይሯቸዋል።

  8. አሜሪካ የኢራኑን መሪ እና ልጃቸውን ዒላማ የማድረግ ዕቅድ እንዳላት ተዘገበ

    የኢራ ንጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አሜሪካ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀች ባለበት በአሁኑ ሰዓት ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ልጃቸው ዋነኛ ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተነገረ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ባለፉት ሳምንታት በሁለት ዙር የተካሄዱት ድርድሮች ከስምምነት አለማድረሳቸውን ተከትሎ አሜሪካ ወታደራዊ አማራጮችን እያጤነች መሆኑ በስፋት እየተገለጸ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ባለፉት ቀናት የተለያዩ አማራጮች የቀረቡላቸው ሲሆን፣ ኢራን ወደ ስምምነት እንድትደርስ ለማስገደድ ውስን የአየር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ፕሬዝዳንቱ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናቶቻቸው ፍንጭ ሰጥተዋል።

    የአየር ጥቃት በኢራን ላይ የሚፈጸም ከሆነ የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮች በተናጠል እና ቁልፍ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ በማድረግ የመንግሥት ለውጥን ለማካሄድ ዕቅድ መውጣቱን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    አክሲዮስ የተባለው የአሜሪካ የዜና ድረገጽ እንደዘገበው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከመከላከያ ሚኒስቴር፣ ፔንታጎን አማካሪዎች የተለያዩ አማራጮች ቀርበውላቸዋል። ከእነዚህም መካከል የኢራን ጠቅላይ መሪን እና በዙሪያቸው ያሉ ቁልፍ ሰዎችን ዒላማ ማድረግ አንዱ እንደሆነ አመልክቷል።

    አንድ አማካሪ ለድረ ገጹ እንደተናገሩት አንደኛው አማራጭ “አያቶላውን እና ወንድ ልጃቻውን እንዲሁም በዙሪያቸው ያሉ አመራሮችን ማስወገድ” ነው። የኻሜኒ ልጅ ሞጅታባ ዒላማ የሆነው የመሪነቱን ቦታ ሊረከብ የሚችል ቀጥተኛ ወራሽ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው።

    ሌላ ምንጭ በተመሳሳይ ለአክሲዮስ እንዳረጋገጠው ይህ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን እና ልጃቸውን ዒላማ የማድረግ ሃሳብ ከበርካታ ሳምንታት በፊት አንስቶ የቀረበ ነው።

    አንድ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ "ትራምፕ ያሉትን አማራጮች ክፍት አድርገዋቸዋል። በየትኛውም ሰዓት ጥቃት እንዲፈጸም ውሳኔ ሊያሳልፉ ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ከስምምነት እንዲደረስ ኢራን በተወሰነ ደረጃ ዩራኒየም እንድታዳብር የሚፈቅድ ሃሳብ ለማቅረብ እየተዘጋጀች መሆኑ እየተነገረ ነው። ነገር ግን ይህ ሃሳብ ኢራን ለጦር መሳሪያነት በሚውል ደረጃ የሚደርስ ዩራኒየም እንዲኖራት የሚፈቅድ አይደለም።

    ኢራን የኒውክሌር መረሃ ግብሯ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል እንደሆነ በመግለጽ ስትከላከል ቆይታለች። ከአሜሪካ ጋር በሚደረገው ድርድር ላይም ሊታለፉ የማይችሉ “ቀይ መስመሮች’ እንዳሏት አስታውቃለች።

  9. በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ናይጄርያውያን የተሳተፉበት የዓሣ ፌስቲቫል

    በዘንድሮው ውድድር ያሸነፈው ዓሣ አስጋሪ 59 ኪሎግራም የሚመዝን ዓሣ በመያዙ 1 ሚሊዮን ናይራ ተሸልሟል።

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በዘንድሮው ውድድር ያሸነፈው ዓሣ አስጋሪ 59 ኪሎግራም የሚመዝን ዓሣ በመያዙ 1 ሚሊዮን ናይራ ተሸልሟል

    በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለስድስት ዓመታት ተቋርጦ የነበረው የናይጄርያ የዓሣ ፌስቲቫል በድጋሚ ተጀምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዓሣ አስጋሪዎች ተሳትፈዋል።

    የካባዋ ሕዝብ ባህላዊ ክንውን የተጀመረው ከበሮ ተደልቆ ሲሆን፤ የወንዝ ጠባቂ የሚባሉት መሪዎች የዓሣ ማጥመድ ውድድር አስጀምረዋል።

    የዓሣ ፌስቲቫል ለአሥርታት የዘለቀ ክንውን ነው። ዓሣ አስጋሪዎች ግዙፍ ዓሣ በመያዝ ውድድሩን ለማሸነፍ ማታን ፋዳ ወንዝ ላይ ይሰማራሉ። በዚህ ፌስቲቫል የሚያዙ ዓሣዎች ትልቅ እንዲሆኑ ስለሚፈለግ ከፌስቲቫሉ ቀን በፊት ለአንድ ዓመት ያህል በወንዙ ላይ ዓሣ ማስገር የተከለከለ ነው።

    ‘አርጉንጉ’ የተባለው የዓሣ ፌስቲቫል ለአራት ቀናት ይቆያል። በዘንድሮው ፌስቲቫል ላይ የናይጄርያ ፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ታድመዋል።

    ‘ሳኪን ሩዋን’ ወይም ‘የወንዝ ጠባቂ’ የሚባሉት ባህላዊ መሪዎች ዓሣ አስጋሪዎችን እስከ ውድድሩ መጨረሻ ድረስ ይከታተላሉ።

    በዘንድሮው ውድድር ያሸነፈው ዓሣ አስጋሪ 59 ኪሎግራም የሚመዝን ዓሣ በመያዙ 1 ሚሊዮን ናይራ (740 ዶላር ገደማ) ተሸልሟል።

    ፌስቲቫሉ በይፋ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1934 ነው። በካቢ ሥርወ መንግሥት እና በሶኮቶ ኻሊፋ መካከል የነበረው ጦርነት ማክተሙን ምክንያት በማድረግ የሰላም ምልክት እንዲሆን ፌስቲቫሉ ተጀምሯል።

    ፌስቲቫሉ በይፋ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1934 ነው።

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ፌስቲቫሉ በይፋ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1934 ነው
  10. የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ዕዝ ካምፖች እንዲሰፍር ተስማምቷል መባሉን አስተባበለ

    የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ

    የፎቶው ባለመብት, Office of the President-Tigray

    የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ ተላልፏል በሚል የተሰራጨው መረጃ “ፍፁም ሐሰት” ነው አለ።

    በሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ይህንን የገለጸው ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 14/2018 ዓ. ም በፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት የፌስቡክ ገጽ ላይ ባወጣው መረጃ ነው።

    ከሰሞኑ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጸች ላይ የፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ ክልል እንደሚገባ ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ማሳወቁን የሚገልጹ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር።

    በትናንትናው ዕለት ደግሞ መከላከያ ሠራዊት በክልሉ በሚገኙ ካምፖች ውስጥ እንዲሰፍር መግባባት ላይ መደረሱን የሚጠቅስ ሌላ ልጥፍ ተሰራጭቷል።

    ጊዜያዊ አስተዳደሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አስተባብሏል። “የፌዴራል መንግሥት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ እንዲገባ ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ” መረጃ እየተሰራጨ እንደሆነ መግለጫው ጠቅሷል።

    “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ደግሞ በቀድሞ የሰሜን ዕዝ ካምፖች እንዲሰፍር እንደተስማማ ተደርጎ በተለያዩ መንገዶች እየተሰራጨ ነው” ብሏል።

    የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፎቹን “የተጣመመ እና የተሳሳተ” ሲል የጠራው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ ይህን ዓይነቱ መረጃ ወደ ኅብረተሰቡ የተሰራጨበት “ስትራቴጂ፣ ምንጩም ሆነ ሊያሳከው የተፈለገው ግብ ግልጽ ነው” ብሏል።

    “የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ሐሰት መሆኑን መግለጽ ይወዳል” ሲልም አስተባብሏል።

    የፕሬዝዳንቱ ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ጽሕፈት ቤት ይህንን መግለጫ ያወጣው በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ወደ ግጭት ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት በተፈጠበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

    ጥር ላይ የፌደራል እና የትግራይ ኃይች ክልሉን ከአማራ እንዲሁም አፋር ክልሎች ጋር በሚያዋስኑ ሥፍራዎች ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር።

    በዚያው ሰሞን አንድ ሰው የተገደለባቸው የድሮን ጥቃቶች በተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች እንደተፈጸሙ ተገልጿል። እነዚህን ጥቃቶች በተመለከተ እስካሁን ድረስ በፌደራል መንግሥት በኩል የተሰጠ ይፋዊ አስተያየት የለም።

  11. የቀድሞው ልዑል አንድሪውን ከንጉሣዊ ቤተሰብ ወራሽነት የሚያስወግድ ድንጋጌ ሊወጣ ነው

    አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቀድሞው የብሪታኒያ ልዑል አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ከንጉሣዊ ቤተሰብ ወራሽነት እንዲወገዱ የሚያደርግ ድንጋጌ ሊወጣ መሆኑ ተገለጸ።

    የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስትር ሉክ ፖላንድ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ አንድሪው ንጉሥ እንዳይሆኑ የሚያግደውን ድንጋጌ ማውጣት “ትክክለኛ ውሳኔ ነው”።

    አንድሪው በብልሹ አሠራር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ መለቀቃቸው አይዘነጋም።

    የንጉሥ ቻርልስ ሦስተኛ ወንድም የሆኑት አንድሪው፤ ንጉሥ መሆን ከሚችሉ የቤተሰቡ አባላት ስምንተኛው ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

    አንድሪው ስማቸው በወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ሰነድ ውስጥ ከተገኘ በኋላ፤ ያለፈው ጥቅምት ላይ ልዑል የሚለው የንጉሣዊ ቤተሰብ የማዕረግ መጠሪያቸውን ተነጥቀዋል።

    ያለፈው ሐሙስ የ66 ዓመቱ የቀድሞ ልዑል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ከ11 ሰዓታት በኋላ ተለቅቀዋል።

    አንድሪው ከኤፕስቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት እና ምሥጢራዊ መረጃዎችን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ጥርጣሬ ፖሊስ ምርመራ እንደሚከፍት አስታውቆ ነበር።

    ከወሲብ ወንጀለኛው ኤፕስቲን ጋር በተያያዘ ለዓመታት ስማቸው ሲነሳ የነበሩት የቀድሞው ልዑል ከዚህ በፊትም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    አንድሪው ምንም ወንጀል እንዳልፈጸሙ በተደጋጋሚ ተናግረዋል። ፖሊስ ካደረገው “ጥልቅ ግምገማ” በኋላ በአንድሪው ላይ ይፋዊ ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።

  12. አሜሪካ ለጥቃት ስትዘጋጅ፤ ኢራን የራሷን የድርድር ዕቅድ እያረቀቀች መሆኑን ገለጸች

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በዚህ ሳምንት ከአሜሪካ ጋር የኒውክሌር ድርድር ስታደርግ የቆየችው ኢራን፤ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የራሷን የድርድር ዕቅድ እያዘጋጀች እንደምታቀርብ መግለጿን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘገበ።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቴህራን በድርድሩ እንድትስማማ ለማድረግ ውስን ወታደራዊ ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ ባሉበት ጊዜ ነው።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ ኢራን ላይ ለሚወሰደው እርምጃ የሚደረገው ወታደራዊ ዝግጅት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን እንደገለጹ ተዘግቧል። ትራምፕ ትዕዛዝ የሚሰጡ ከሆነ ግለሰቦችን ዒላማ ለማድረግ እንዲሁም የኢራንን መንግሥት የመለወጥ አማራጭ ላይ ጭምር ዝግጅት እንደተደረገ ተነግሯል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ፤ ጄኔቫ ውስጥ በተካሄደው ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ሁለቱ ወገኖች “የሚመሩባቸው መርሆዎችን” በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። ይህ ግን ስምምነት ላይ መደረሱ አይቀሬ ነው ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

    አራግቺ ለአሜሪካው ‘ኤምኤስ ናው’ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወይም ሦስት ቀናት ውስጥ ለኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለግምገማ የሚቀርብ የአጸፋ የድርድር ዕቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በመጪው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አሜሪካ እና ኢራን ሌላ ዙር ንግግር ሊያደርጉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ ስምምነት ላይ የመድረስ ጉዳይን የተወሳሰበ እንደሚያደርገው አክለዋል።

    አራግቺ፤ የኢራን የድርድር ዕቅድ ለአሜሪካ ልዑካን ማለትም ለትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ለአማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር የሚቀርብበትን የተቆረጠ ቀን አልጠቀሱም። ነገር ግን "በጣም ባጠረ ጊዜ ውስጥ" ዲፕሎማሲያዊ ስምምነት ላይ ይደረሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

    ወታደራዊ እርምጃ ወደመፈጸም እያዘነበሉ ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን ስምምነት ላይ እንድትደርስ ከ10 እስከ 15 ቀን የሚደርስ የጊዜ ገደብ ሰጥተዋል። ይህ ካልሆነ ግን "መጥፎ ነገሮች ይፈጠራሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኢራን ላይ ውስን ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ እንደሆነ አርብ ዕለት በዋይት ሀውስ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዝዳንቱ፤ “እያሰብኩበት ነው ማለት የምችል ይመስለኛል” ብለዋል። “ፍትሐዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቢደራደሩ ይሻላቸዋል" ሲሉም አክለዋል።

  13. አሜሪካ የኢራን ባለሥልጣናትን ዒላማ ለማድረግ ማቀዷ ተነገረ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በኢራን ውስጥ ለምትፈጽመው ወደታራዊ ጥቃት የአገሪቱን አመራሮች በተናጠል ዒላማ ማድረግን ጨምሮ የመንግሥት ለውጥን ለማካሄድ ዕቅድ መውጣቱን ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ባለሥልጣናቱ ከዕቅዱ ምሥጢራዊነት የተነሳ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ ሲሆን፣ ተጨማሪ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል። ነገር ግን ይህ ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆነው ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ ሲተለላፍ መሆኑን ገልጸዋል።

    እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ካላስገኘ አሜሪካ ወደ ወታደራዊ እርምጃ ፊቷን እንደምታዞር እየተነገረ ሲሆን፣ የኢራንን የደኅንነት ተቋማት እና የኒውክሌር ማዕከላት ዒላማ ለሚያደርጉ ለተከታታይ ለሳምንታት የሚዘልቁ ዘመቻዎች የአሜሪካ ሠራዊት እየተዘጋጀ መሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል።

    ባለፉት ሳምንታት ትራምፕ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የጦር መሣሪያዎቻቸውን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲንቀሳቀሱ አድርገዋል። ነገር ግን ዋነኛው ኃይሏ በግዙፍ የጦር መርከቦች እና በተዋጊ አውሮፕላኖች ላይ የተመሠረተ ነው።

    አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ በኢራን ላይ ከከፈተች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ዒላማ እንደሚደረጉ እየተነገረ ነው። እስራኤል ባለፈው ዓመት በኢራን ላይ ጥቃት ባካሄደችበት ጊዜ ጥቂት የማይባሉ ወደታራዊ እና ፖቲካዊ አመራሮች ላይ ጉዳት አድርሳለች።

    በኢራን ላይ ስለሚካሄደው ዘመቻ ዕቅድ ለሮይተርስ የገለጹት ባለሥልጣናት፣ አሜሪካ የኢራን መሪዎችን ዒላማ ለማድረግ የሚያስችል ምን ያህል አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ እንዳላቸው አልገለጹም።

    የአሜሪካ ዕቅድን በተመለከተ ሮይተርስ ከዋይት ሐውስ እና ከመከላከያ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ ወዲያውኑ መልስ አላገኘም።

  14. የአሜሪካ የጦር መርከብ በሜዲትራኒያን በኩል ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ እያመራ መሆኑ ታወቀ

    የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በጂብራልታር ሰርጥ ተሻግሯል

    የፎቶው ባለመብት, David Parody

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በጂብራልታር ሰርጥ ተሻግሯል

    የአሜሪካ ግዙፍ አውሮላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በሰሜን አፍሪካ በጂብራልታር ሰርጥ በኩል መሻገሩን የቢቢሲ መረጃ አጣሪ ቡድን ‘ቢቢሲ ቬሪፋይ’ አረጋገጠ።

    የአየር ኃይል አውሮፕላኖች እና ጦር መሣሪያ ጫኝ የሆነው ይህ የዓለም ትልቁ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በጂብራልታር ሰርጥ በኩል ሲሻገር የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተዘዋውረዋል።

    ምሥሎቹ እንደሚያሳዩት ግዙፉ የጦር መርከብ በጂብራልታር ሰርጥ አድርጎ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደ ሜድትራኒያን ባሕር ተሻግሯል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የመርከቦችን እንቅስቃሴ በሚከታተለው ድረ ገጽ አማካኝነት ጉዞውን ማረጋገጥ ችሏል።

    ከጦር መርከቡ በቅርብ ርቀት የሞሮኮ ተራሮች ይታያሉ። በዚህ ሳምንት ውስጥ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተቃረበ ሁለተኛው የአሜሪካ የጦር መርከብ ነው።

    አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እንድታቋርጥ ጫና ማሳደሯን ቀጥላለች። በጂብራልታር ሰርጥ የተሻገረው ይህ ግዙፍ መርከብ አሜሪካ ካሏት ዘመናዊ የጦር መርከቦች ዋነኛው ነው።

    ከዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ የጦር መርከብ በተጨማሪ ዩኤስኤስ ማሀን የጦር መርከብም በጂብራልታር ሰርጥ አልፎ ሜድትራኒያን ደርሷል።

    ይህ አውሮፕላን ተሸሚ የጦር መርከብ አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ጥቃት ከመሰንዘሯ በፊት ወደኢያው አሰማርታው የነበረ ሲሆን፣ አሜሪካ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ ወሳኝ ሚና ነበረው።

    አሁን ደግሞ ከኢራን ጋር ውዝግብ በበረታበት እና አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ እየገለጸችበት ባለበት ጊዜ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ስምሪት ተሰጥቶት ወቀጣናው እመያራ ነው።

  15. ኢራናውያን የቴክኖሎጂ ምሥጢሮችን በመስረቅ ወደ ኢራን በማስተላለፍ አሜሪካ ውስጥ ተከሰሱ

    የጉግል ዋና መሥሪያ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሠሩ ሦስት ኢራናውያን የኮምፒውተር ኢንጂነሮች ከጉግል እና ከሌሎች ተቋማት የንግድ ምሥጢሮችን በመስረቅ መረጃን በሕገ ወጥ መንገድ ኢራንን ጨምሮ ወደ ሌሎች አስተላልፈዋል በሚል ተከሰሱ።

    ሦስቱ ኢራናውያን የቤተሰብ እና የጋብች ትስስር ያላቸው ሲሆን በአሜሪካ ሲሊከን ቫሊ ውስጥ ከሚገኙት ከጉግል እና ከሌሎች ዋነኛ የቴክኖሎጂ ተቋማት የንግድ ምሥጢር ለመስረቅ በማሴር እና ፍትሕን በማደናቀፍ ተከስሰዋል።

    እዚያው አሜሪካ ሳንሆዜ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ሦስቱ ኢራናውያን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከአንድ ቀን በፊት ሲሆን፣ ፌደራል ፍርድ ቤት የቀረቡት ካሊፎርኒያ ውስጥ ነው።

    ጉዳዩን የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እና በአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያለ ልዩ ክፍል እንዲሁም ምርመራውን በማካሄድ ኤፍቢአይ ይዘውታል።

    “የንግድ ምሥጢር ስርቆት ድርጊቱ ውስጥ ተካሳሾቹ ያላቸውን ኃላፊነት ምሥጢራዊ እና ጥብቅ መረጃዎችን ለማግኘት ችለዋል” ሲል የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

    ጨምሮም ግለሰቦቹ የመረጃ መረብ ደኅንነትን የሚመለከቱ፣ የተመሰጠሩ ቀመሮችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የያዙ መረጃዎችን ጨምሮ ከጉግል እና ከሌሎችም ተቋማት ኢራንን ጨምሮ ወዳልተፈቀዱ ሥፍራዎች አሸጋግረዋል ብሏል።

    ግለሰቦቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ እያንዳንዳቸው እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስር እና የ250 ሺህ ዶላር ቅጣት ለእያንዳንዱ የንግድ ምሥጢር ስርቆት እንዲሁም አስከ 20 ዓመት እስር እና 250 ሺህ ዶላር ቅጣት ደግሞ ፍትሕን በማደናቀፍ ይጠብቃቸዋል።

  16. ማንነታቸው ያልታወቀ ግለሰብ የጃፓኗ ከተማ የውሃ መስመር እንዲታደስ 21 ኪሎ ወርቅ አበረከቱ

    ወርቅ

    የፎቶው ባለመብት, Osaka City Waterworks Bureau

    የጃፓኗ ኦሳካ ከተማ ያረጀውን የውሃ አቅርቦት መስመሯን እንድታድስ በሚል ማንነታቸው ካልታወቀ ግለሰብ 21 ኪሎግራም የሚመዝን ወርቅ በስጦታ ተበረከተላት።

    3.6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን ወርቅ ለከተማዋ ያበረከቱት ግለሰብ ማንነታቸው እንዲገለጽ እንደማይሹ የኦሳካ ከተማ ከንቲባ ሂዴዩኪ ዮኮማያ ተናግረዋል።

    በጃፓን ካንሳይ ግዛት በምትገኘው ኦሳካ ከተማ ወደ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ይገኛሉ።

    በጃፓን ሦስተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ኦሳካ ውስጥ የውሃ መስመሮች በማርጀታቸው የጤና ስጋት ደቅነዋል። በአውሮፓውያኑ 2024 ብቻ ከ90 በላይ የውሃ መስመሮች ፈንድተዋል።

    ከንቲባው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ያረጁትን የውሃ መስመሮች ለማደስ ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል” ብለው የወርቅ ስጦታ ያበረከቱትን ግለሰብ አመስግነዋል።

    ለከተማዋ የተሰጠው ወርቅ “እጅግ ብዙ” እንደሆነ ገልጸው፤ ስሜታቸውን ለመግለጽ “ቃላት እንደሚያጥራቸው” አክለዋል።

    ማንነታቸው ያልታወቀው ለጋሽ ከዚህ ቀደም ለማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች 500 ሺህ የን (የጃፓን ገንዘብ) አበርክተዋል።

    በጃፓን ከ20 በመቶ በላይ የውሃ መስመሮች አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው ጊዜ (40 ዓመታት) አልፏል።

    በተለያዩ ከተሞች የውሃ መስመሮች ፈንድተው የተፈጠሩ ጉድጓዶችም ለሕዝቡ አደገኛ ሆነዋል። አምና ያልተደፈነ ጉድጓድ ውስጥ ታክሲ ገብቶ አሽከርካሪው ሞቷል።

    የጃፓን መንግሥት ያረጁ የውሃ መስመሮችን ለማደስ ዕቅድ ቢይዝም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ሥራው ተጓትቷል።

  17. ትራምፕ ኢራን ከስምምነት እንድትደርስ ውስን ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ መሆኑ ተነገረ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከአሜሪካ ጋር እያካሄደች ባለው ድርድር ላይ ከስምምነት እንድትደርስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ውስን የአየር ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ መሆናቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ጋዜጣው ስማቸው ያልተገለጸ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ትራምፕ እያሰቡት ያለው “ቀዳሚ ጥቃት በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ የሚፈጸም ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ይሁንታቸውን ከሰጡ የተወሰደኑ ወታደራዊ እና መንግሥታዊ ተቋማት ዒላማ ይሆናሉ” ብለዋል።

    ምንጮቹ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆነች “አሜሪካ ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደምታካሂድ እና ይህም የኢራን መንግሥትን ለመጣል የሚካሄድ ዘመቻ ይሆናል” ማለታቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ሐሙስ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ስለሚፈጸመው ጥቃት አማራጮች ገለጻ እንደተደረገላቸው እና በቀጣይ አስር ቀናት “ትርጉም ያለው ስምምነት” ላይ ካልተደተሰ “መጥፎ ነገሮች እንደሚከሰቱ” መናገራቸው ተዘግቧል።

    ባለፉት ሳምንታት እና ቀናት አሜሪካ ቁልፍ የባሕር ኃይል መርከቦችን እና የአየር ኃይል ተዋጊ እንዲሁም ደጋፊ አውሮፕላኖችን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ አሰማርታለች።

    ከኢራን ጋር ውጤታማ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ለረዥም ዓመታት በተደረጉ ሙከራዎች መረጋገጡን የጠቀሱት ትራምፕ፤ አሁንም በዚያው የሚቀጥሉ ከሆነ “ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ከኢራን ጋር ለ12 ቀናት ጦርነት ውስጥ የገባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ኢራን “ስህተት ፈጽማ የምታጠቃን ከሆነ፣ ከሚያስቡት በላይ የሆነ ምላሽ ይጠብቃቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  18. ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቱኒዚያው ፕሬዝዳንት የተሳለቁት የፓርላማ አባል ተፈረደባቸው

    የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ የሚወርፍ ጽሁፍ ያጋሩት የፓርላማ አባል የስምንት ወር እስር እንደተፈረደባቸው የአገሪቱ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

    አህመድ ሳይዳኒ የተባሉት ሕግ አውጪ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋሩት ልጥፍ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ጥር መጨረሻ ላይ ነበር።

    የፓርላማ አባሉ፤ በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን የጎበኙትን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት “የንህፅና እና የዝናብ ፍሳሽ ጠቅላይ አዛዥ” ሲሉ ጠርተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ዋና ከተማዋ ቱኒስን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ የደረሰባቸውን አካባቢዎች በጎበኙበት ወቅት የፓርላማ አባሉ ባጋሩት ጽሁፍ፤ "በትርፍ ጊዜያቸው ከድሆች እና ችግረኞች ጋር ፎቶ የመነሳት ልምድ አካብተዋል” ሲሉ ተሳልቀዋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ በኮሚዩኒኬሽን አውታር ሰዎችን በመስደብ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የአገሪቱ የዳኝነት መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

    የአገሪቱን የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሕግ በመጣስ የተከሰሱት ሳይዳኒ፤ “በማኅበራዊ ሚዲያ ሌሎችን መጉዳት” የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ጠበቃቸው ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።

    የፓርላማ አባሉ የተከሰሱበት ሕግ እስከ ሁለት ዓመት በሚደረስ እስራት የሚያስቀጣ ነው።

    ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሥልጣናቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲሁም የተቃዋሚዎችን እስር ሲደግፉ የነበሩት የፓርላማ አባሉ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆነዋል።

    ፕሬዝዳንቱን የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቱን በብቸኝነት እንደተቆጣጠሩ እንዲሁም ኃላፊነት ሳይወስዱ ሌሎችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ በመግለጽም ከስሰዋል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው የፓርላማ አባሉ አጋር የሆኑ ሌላ ተመራጭ፤ እስሩን “ሕገ ወጥ” ሲሉ ጠርተውታል። “ይህ የሕግ ጥሰት እና በተቋማት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው።

    ፓርላማው በሂሳዊ ዕይታ ምክንያት ሕገ ወጥ እስር የሚፈጽም ከሆነ እንዴት አድርጎ አስፈፃሚውን አካል ተጠያቂ ማድረግ ይችላል?” ብለዋል።

  19. ኢራን ጥቃት ከተፈጸመባት በቀጣናው የሚገኙ የጦር ሰፈሮች ዒላማ እንደሚሆኑ ለተመድ አስታወቀች

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒም

    የፎቶው ባለመብት, EPA/UN

    ከአሜሪካ ጋር የተካረረ ውጥረት ውስጥ የገባችው ኢራን፤ ወታደራዊ እርምጃ የሚወሰድባት ከሆነ በቀጣናው የሚገኙ "የጠላት ኃይሎች” የጦር ሰፈሮችን፣ ተቋማትን እና ይዞታዎችን ሕጋዊ የጥቃት ዒላማ አድርጋ እንደምትቆጥር ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አስታወቀች።

    በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ቋሚ ልዑክ ለአንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ፤ ኢራን ለሚሰነዘርባት ጥቃት “ቆራጥ እና ተመጣጣኝ" ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን በተመለከተ የሚያራምዱት ትርክት "እውነተኛ የወታደራዊ ጥቃት ስጋት" እንዳለ እንደሚጠቁም ደብዳቤው መግለጹን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ቋሚ ልዑኩ፤ ኢራን ጦርነት እንደማትፈልግም ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ አስረድቷል።

    ደብዳቤው "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ውጥረትም ሆነ ጦርነት እንደማትፈልግ እንዲሁም ማንኛውንም ጦርነት እንደማትጀምር በተደጋጋሚ በከፍተኛ ደረጃ ገልጻለች" ይላል።

    "ይሁን እንጂ፤ ወታደራዊ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ ኢራን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 51 መሠረት ያላትን ተፈጥሯዊ ራስን የመከላከል መብት በመጠቀም ቆራጥ እና ተመጣጣኝ ምላሽ ትሰጣለች" ሲል ማስፈሩንም የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል።

    "በኢራን ራስን የመከላከል ምላሽ ውስጥ፤ በቀጣናው የሚገኙ የጠላት ኃይሎች የጦር ሠፈሮች፣ ተቋማት እና ይዞታዎች በሙሉ ሕጋዊ የጥቃት ዒላማዎች ይሆናሉ" ሲልም አስጠንቅቋል።

    ይህንን ተከትሎ ለሚመጣው "ተገማች ያልሆነ እና መቆጣጠር የማይቻል መዘዝ አሜሪካ ሙሉ እና ቀጥተኛ ኃላፊነት ትወስዳለች" ሲልም አሳስቧል።

    ኢራን ቋሚ ልዑክ፤ የተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት እና ዋና ፀሐፊው “ጊዜው ከመርፈዱ አስቀድሞ፣ ሳይዘገዩ” እርምጃ እንዲወስዱም ጠይቋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አገራቸው ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ትደርስ ወይም ወታደራዊ እርምጃ ትወስድ እንደሆነ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ እንደሚታወቅ ተናግረዋል።

  20. አሜሪካ በኢራን ላይ ለምትፈጽመው ጥቃት የዩኬ የጦር ሰፈሮችን ለመጠቀም እንዳልተፈቀደላት ተገለጸ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዩናይትድ ኪንግደም ብሪታኒያ መንግሥት፤ አሜሪካ ኢራን ላይ ልትፈጽም ለምትችለውን ጥቃት የዩናይትድ ኪንግደም ሠራዊትን የጦር ሰፈር እንድትጠቀም ፈቃድ አለመስጠቱን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ አሳየ።

    ከዚህ ቀደም አሜሪካ መካለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጥቃቶችን ለመፈጸም የእንግሊዝ ከተማ በሆነችው ግሎስተርሻየር የሚገኘውን ‘አርኤኤፍ ፌይርፎርድ’ የጦር ሰፈር ትጠቀም ነበር።

    ዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ማዶ ግዛት እንደሆነ የሚቆጠረው በዲዬጎ ጋርሲያ የሚገኘው የጦር ሰፈርንም በቀጣናው ለምትፈጸመው ጥቃት ተጠቅማ ታውቃለች።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስቲያ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "ዲያጎ ጋርሲያን አትስጡ" ሲሉ ዩናይትድ ኪንግደም የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሺየስ ለማስረከብ ማቀዷን ተቃውመው ነበር።

    ዩናይትድ ኪንግደም ደሴቶቹን ካስረከበች በኋላ ከአሜሪካ ጋር የጦር ሰፈር ለመመሥረት መልሳ በሊዝ ለመከራየት አቅዳለች።

    የብሪታኒያው ‘ዘ ታይምስ’ ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ትራምፕ እዚህ ዕቅድ ላይ ወቀሳ ያሰሙት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አሜሪካ የጦር ሰፈሩን እንዳትጠቀም ፈቃድ ባለመስጠቷ ነው።

    ስለ ጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ “እንደ ሁልጊዜው ሁሉ፤ በወታደራዊ ኦፕሬሽን ጉዳዮች ላይ አስተያየት አንሰጥም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመሰረዝ እንድትስማማ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። ስምምነት ላይ ማይደረስ ከሆነም ጥቃት እንደሚፈጽም ዝቷል።

    በቀጣናው ሊፈጸም ለሚችለው ጥቃት ዝግጅ እያደረገ ያለው የአሜሪካ መንግሥት የጦር መርከቦች፣ ተዋጊ አውሮፕላኖች እና ሌሎች ወታደራዊ ኃይሎቹን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አስጠግቷል።

    በሌላ በኩል አሜሪካ እና ኢራን ስዊትዘርላንድ ውስጥ ያደረጉት ንግግር የተወሰነ መሻሻል እየታየበት እንደሆነ ተገልጿል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ፤ “በአሜሪካ እና ኢራን መካከል እየተደረገ ያለ ፖለቲካዊ ሂደት አለ፤ ዩኬ የምትደግፈው እርሱን ነው” ብለዋል።

    “ኢራን በጭራሽ የኒውክሌር መሣሪያ መገንባት መቻል የለባትም፤ እኛ ቅድሚያ የምንሰጠውም ለቀጠናው ደኅንነት ነው" ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።