ቀጥታ, ግዙፉ የአሜሪካ የጦር መርከብ በሜዲትራኒያን በኩል ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ እያመራ መሆኑ ተረጋገጠ

የአሜሪካ ግዙፍ አውሮላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በሰሜን አፍሪካ በጂብራልታር ሰርጥ በኩል መሻገሩን የቢቢሲ መረጃ አጣሪ ቡድን ‘ቢቢሲ ቬሪፋይ’ አረጋገጠ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. አሜሪካ የኢራን ባለሥልጣናትን ዒላማ ለማድረግ ማቀዷ ተነገረ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ በኢራን ውስጥ ለምትፈጽመው ወደታራዊ ጥቃት የአገሪቱን አመራሮች በተናጠል ዒላማ ማድረግን ጨምሮ የመንግሥት ለውጥን ለማካሄድ ዕቅድ መውጣቱን ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ባለሥልጣናቱ ከዕቅዱ ምሥጢራዊነት የተነሳ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱ ሲሆን፣ ተጨማሪ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል። ነገር ግን ይህ ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆነው ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ትዕዛዝ ሲተለላፍ መሆኑን ገልጸዋል።

    እየተደረገ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ካላስገኘ አሜሪካ ወደ ወታደራዊ እርምጃ ፊቷን እንደምታዞር እየተነገረ ሲሆን፣ የኢራንን የደኅንነት ተቋማት እና የኒውክሌር ማዕከላት ዒላማ ለሚያደርጉ ለተከታታይ ለሳምንታት የሚዘልቁ ዘመቻዎች የአሜሪካ ሠራዊት እየተዘጋጀ መሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል።

    ባለፉት ሳምንታት ትራምፕ ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የጦር መሣሪያዎቻቸውን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲንቀሳቀሱ አድርገዋል። ነገር ግን ዋነኛው ኃይሏ በግዙፍ የጦር መርከቦች እና በተዋጊ አውሮፕላኖች ላይ የተመሠረተ ነው።

    አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ በኢራን ላይ ከከፈተች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ዒላማ እንደሚደረጉ እየተነገረ ነው። እስራኤል ባለፈው ዓመት በኢራን ላይ ጥቃት ባካሄደችበት ጊዜ ጥቂት የማይባሉ ወደታራዊ እና ፖቲካዊ አመራሮች ላይ ጉዳት አድርሳለች።

    በኢራን ላይ ስለሚካሄደው ዘመቻ ዕቅድ ለሮይተርስ የገለጹት ባለሥልጣናት፣ አሜሪካ የኢራን መሪዎችን ዒላማ ለማድረግ የሚያስችል ምን ያህል አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ እንዳላቸው አልገለጹም።

    የአሜሪካ ዕቅድን በተመለከተ ሮይተርስ ከዋይት ሐውስ እና ከመከላከያ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቦ ወዲያውኑ መልስ አላገኘም።

  2. የአሜሪካ የጦር መርከብ በሜዲትራኒያን በኩል ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ እያመራ መሆኑ ታወቀ

    የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በጂብራልታር ሰርጥ ተሻግሯል

    የፎቶው ባለመብት, David Parody

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በጂብራልታር ሰርጥ ተሻግሯል

    የአሜሪካ ግዙፍ አውሮላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በሰሜን አፍሪካ በጂብራልታር ሰርጥ በኩል መሻገሩን የቢቢሲ መረጃ አጣሪ ቡድን ‘ቢቢሲ ቬሪፋይ’ አረጋገጠ።

    የአየር ኃይል አውሮፕላኖች እና ጦር መሣሪያ ጫኝ የሆነው ይህ የዓለም ትልቁ የጦር መርከብ ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ በጂብራልታር ሰርጥ በኩል ሲሻገር የሚያሳዩ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተዘዋውረዋል።

    ምሥሎቹ እንደሚያሳዩት ግዙፉ የጦር መርከብ በጂብራልታር ሰርጥ አድርጎ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደ ሜድትራኒያን ባሕር ተሻግሯል።

    ቢቢሲ ቬሪፋይ የመርከቦችን እንቅስቃሴ በሚከታተለው ድረ ገጽ አማካኝነት ጉዞውን ማረጋገጥ ችሏል።

    ከጦር መርከቡ በቅርብ ርቀት የሞሮኮ ተራሮች ይታያሉ። በዚህ ሳምንት ውስጥ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተቃረበ ሁለተኛው የአሜሪካ የጦር መርከብ ነው።

    አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብሯን እንድታቋርጥ ጫና ማሳደሯን ቀጥላለች። በጂብራልታር ሰርጥ የተሻገረው ይህ ግዙፍ መርከብ አሜሪካ ካሏት ዘመናዊ የጦር መርከቦች ዋነኛው ነው።

    ከዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ የጦር መርከብ በተጨማሪ ዩኤስኤስ ማሀን የጦር መርከብም በጂብራልታር ሰርጥ አልፎ ሜድትራኒያን ደርሷል።

    ይህ አውሮፕላን ተሸሚ የጦር መርከብ አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ጥቃት ከመሰንዘሯ በፊት ወደኢያው አሰማርታው የነበረ ሲሆን፣ አሜሪካ ጥቃት በፈጸመችበት ጊዜ ወሳኝ ሚና ነበረው።

    አሁን ደግሞ ከኢራን ጋር ውዝግብ በበረታበት እና አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ እየገለጸችበት ባለበት ጊዜ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ስምሪት ተሰጥቶት ወቀጣናው እመያራ ነው።

  3. ኢራናውያን የቴክኖሎጂ ምሥጢሮችን በመስረቅ ወደ ኢራን በማስተላለፍ አሜሪካ ውስጥ ተከሰሱ

    የጉግል ዋና መሥሪያ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ ውስጥ በሚገኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሠሩ ሦስት ኢራናውያን የኮምፒውተር ኢንጂነሮች ከጉግል እና ከሌሎች ተቋማት የንግድ ምሥጢሮችን በመስረቅ መረጃን በሕገ ወጥ መንገድ ኢራንን ጨምሮ ወደ ሌሎች አስተላልፈዋል በሚል ተከሰሱ።

    ሦስቱ ኢራናውያን የቤተሰብ እና የጋብች ትስስር ያላቸው ሲሆን በአሜሪካ ሲሊከን ቫሊ ውስጥ ከሚገኙት ከጉግል እና ከሌሎች ዋነኛ የቴክኖሎጂ ተቋማት የንግድ ምሥጢር ለመስረቅ በማሴር እና ፍትሕን በማደናቀፍ ተከስሰዋል።

    እዚያው አሜሪካ ሳንሆዜ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ሦስቱ ኢራናውያን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ከአንድ ቀን በፊት ሲሆን፣ ፌደራል ፍርድ ቤት የቀረቡት ካሊፎርኒያ ውስጥ ነው።

    ጉዳዩን የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እና በአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ያለ ልዩ ክፍል እንዲሁም ምርመራውን በማካሄድ ኤፍቢአይ ይዘውታል።

    “የንግድ ምሥጢር ስርቆት ድርጊቱ ውስጥ ተካሳሾቹ ያላቸውን ኃላፊነት ምሥጢራዊ እና ጥብቅ መረጃዎችን ለማግኘት ችለዋል” ሲል የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

    ጨምሮም ግለሰቦቹ የመረጃ መረብ ደኅንነትን የሚመለከቱ፣ የተመሰጠሩ ቀመሮችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን የያዙ መረጃዎችን ጨምሮ ከጉግል እና ከሌሎችም ተቋማት ኢራንን ጨምሮ ወዳልተፈቀዱ ሥፍራዎች አሸጋግረዋል ብሏል።

    ግለሰቦቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ እያንዳንዳቸው እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስር እና የ250 ሺህ ዶላር ቅጣት ለእያንዳንዱ የንግድ ምሥጢር ስርቆት እንዲሁም አስከ 20 ዓመት እስር እና 250 ሺህ ዶላር ቅጣት ደግሞ ፍትሕን በማደናቀፍ ይጠብቃቸዋል።

  4. ማንነታቸው ያልታወቀ ግለሰብ የጃፓኗ ከተማ የውሃ መስመር እንዲታደስ 21 ኪሎ ወርቅ አበረከቱ

    ወርቅ

    የፎቶው ባለመብት, Osaka City Waterworks Bureau

    የጃፓኗ ኦሳካ ከተማ ያረጀውን የውሃ አቅርቦት መስመሯን እንድታድስ በሚል ማንነታቸው ካልታወቀ ግለሰብ 21 ኪሎግራም የሚመዝን ወርቅ በስጦታ ተበረከተላት።

    3.6 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን ወርቅ ለከተማዋ ያበረከቱት ግለሰብ ማንነታቸው እንዲገለጽ እንደማይሹ የኦሳካ ከተማ ከንቲባ ሂዴዩኪ ዮኮማያ ተናግረዋል።

    በጃፓን ካንሳይ ግዛት በምትገኘው ኦሳካ ከተማ ወደ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ይገኛሉ።

    በጃፓን ሦስተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ኦሳካ ውስጥ የውሃ መስመሮች በማርጀታቸው የጤና ስጋት ደቅነዋል። በአውሮፓውያኑ 2024 ብቻ ከ90 በላይ የውሃ መስመሮች ፈንድተዋል።

    ከንቲባው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ያረጁትን የውሃ መስመሮች ለማደስ ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል” ብለው የወርቅ ስጦታ ያበረከቱትን ግለሰብ አመስግነዋል።

    ለከተማዋ የተሰጠው ወርቅ “እጅግ ብዙ” እንደሆነ ገልጸው፤ ስሜታቸውን ለመግለጽ “ቃላት እንደሚያጥራቸው” አክለዋል።

    ማንነታቸው ያልታወቀው ለጋሽ ከዚህ ቀደም ለማዘጋጃ ቤት ሠራተኞች 500 ሺህ የን (የጃፓን ገንዘብ) አበርክተዋል።

    በጃፓን ከ20 በመቶ በላይ የውሃ መስመሮች አገልግሎት መስጠት የሚጠበቅባቸው ጊዜ (40 ዓመታት) አልፏል።

    በተለያዩ ከተሞች የውሃ መስመሮች ፈንድተው የተፈጠሩ ጉድጓዶችም ለሕዝቡ አደገኛ ሆነዋል። አምና ያልተደፈነ ጉድጓድ ውስጥ ታክሲ ገብቶ አሽከርካሪው ሞቷል።

    የጃፓን መንግሥት ያረጁ የውሃ መስመሮችን ለማደስ ዕቅድ ቢይዝም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ ሥራው ተጓትቷል።

  5. ትራምፕ ኢራን ከስምምነት እንድትደርስ ውስን ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ መሆኑ ተነገረ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ከአሜሪካ ጋር እያካሄደች ባለው ድርድር ላይ ከስምምነት እንድትደርስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ውስን የአየር ጥቃት ለመፈጸም እያሰቡ መሆናቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ጋዜጣው ስማቸው ያልተገለጸ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ትራምፕ እያሰቡት ያለው “ቀዳሚ ጥቃት በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ የሚፈጸም ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ይሁንታቸውን ከሰጡ የተወሰደኑ ወታደራዊ እና መንግሥታዊ ተቋማት ዒላማ ይሆናሉ” ብለዋል።

    ምንጮቹ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆነች “አሜሪካ ከኢራን መንግሥት ጋር ግንኙነት ባላቸው ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደምታካሂድ እና ይህም የኢራን መንግሥትን ለመጣል የሚካሄድ ዘመቻ ይሆናል” ማለታቸውን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።

    ሐሙስ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ ስለሚፈጸመው ጥቃት አማራጮች ገለጻ እንደተደረገላቸው እና በቀጣይ አስር ቀናት “ትርጉም ያለው ስምምነት” ላይ ካልተደተሰ “መጥፎ ነገሮች እንደሚከሰቱ” መናገራቸው ተዘግቧል።

    ባለፉት ሳምንታት እና ቀናት አሜሪካ ቁልፍ የባሕር ኃይል መርከቦችን እና የአየር ኃይል ተዋጊ እንዲሁም ደጋፊ አውሮፕላኖችን ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ አሰማርታለች።

    ከኢራን ጋር ውጤታማ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ መሆኑን ለረዥም ዓመታት በተደረጉ ሙከራዎች መረጋገጡን የጠቀሱት ትራምፕ፤ አሁንም በዚያው የሚቀጥሉ ከሆነ “ተጨማሪ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈልግን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ከኢራን ጋር ለ12 ቀናት ጦርነት ውስጥ የገባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ኢራን “ስህተት ፈጽማ የምታጠቃን ከሆነ፣ ከሚያስቡት በላይ የሆነ ምላሽ ይጠብቃቸዋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

  6. ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቱኒዚያው ፕሬዝዳንት የተሳለቁት የፓርላማ አባል ተፈረደባቸው

    የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የቱኒዚያ ፕሬዝዳንት ካይስ ሰኢድ የሚወርፍ ጽሁፍ ያጋሩት የፓርላማ አባል የስምንት ወር እስር እንደተፈረደባቸው የአገሪቱ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

    አህመድ ሳይዳኒ የተባሉት ሕግ አውጪ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ካጋሩት ልጥፍ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት ጥር መጨረሻ ላይ ነበር።

    የፓርላማ አባሉ፤ በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን የጎበኙትን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት “የንህፅና እና የዝናብ ፍሳሽ ጠቅላይ አዛዥ” ሲሉ ጠርተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ዋና ከተማዋ ቱኒስን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የጎርፍ አደጋ የደረሰባቸውን አካባቢዎች በጎበኙበት ወቅት የፓርላማ አባሉ ባጋሩት ጽሁፍ፤ "በትርፍ ጊዜያቸው ከድሆች እና ችግረኞች ጋር ፎቶ የመነሳት ልምድ አካብተዋል” ሲሉ ተሳልቀዋል።

    ከዚህ ጋር በተያያዘ በኮሚዩኒኬሽን አውታር ሰዎችን በመስደብ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የአገሪቱ የዳኝነት መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

    የአገሪቱን የቴሌኮሚዩኒኬሽን ሕግ በመጣስ የተከሰሱት ሳይዳኒ፤ “በማኅበራዊ ሚዲያ ሌሎችን መጉዳት” የሚል ክስ እንደቀረበባቸው ጠበቃቸው ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።

    የፓርላማ አባሉ የተከሰሱበት ሕግ እስከ ሁለት ዓመት በሚደረስ እስራት የሚያስቀጣ ነው።

    ከዚህ ቀደም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሥልጣናቸውን ለማጠናከር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲሁም የተቃዋሚዎችን እስር ሲደግፉ የነበሩት የፓርላማ አባሉ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጠንካራ ተቃዋሚ ሆነዋል።

    ፕሬዝዳንቱን የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓቱን በብቸኝነት እንደተቆጣጠሩ እንዲሁም ኃላፊነት ሳይወስዱ ሌሎችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ በመግለጽም ከስሰዋል።

    ሮይተርስ ያነጋገራቸው የፓርላማ አባሉ አጋር የሆኑ ሌላ ተመራጭ፤ እስሩን “ሕገ ወጥ” ሲሉ ጠርተውታል። “ይህ የሕግ ጥሰት እና በተቋማት ላይ የተፈጸመ ጥቃት ነው።

    ፓርላማው በሂሳዊ ዕይታ ምክንያት ሕገ ወጥ እስር የሚፈጽም ከሆነ እንዴት አድርጎ አስፈፃሚውን አካል ተጠያቂ ማድረግ ይችላል?” ብለዋል።

  7. ኢራን ጥቃት ከተፈጸመባት በቀጣናው የሚገኙ የጦር ሰፈሮች ዒላማ እንደሚሆኑ ለተመድ አስታወቀች

    የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒም

    የፎቶው ባለመብት, EPA/UN

    ከአሜሪካ ጋር የተካረረ ውጥረት ውስጥ የገባችው ኢራን፤ ወታደራዊ እርምጃ የሚወሰድባት ከሆነ በቀጣናው የሚገኙ "የጠላት ኃይሎች” የጦር ሰፈሮችን፣ ተቋማትን እና ይዞታዎችን ሕጋዊ የጥቃት ዒላማ አድርጋ እንደምትቆጥር ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አስታወቀች።

    በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ቋሚ ልዑክ ለአንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ፤ ኢራን ለሚሰነዘርባት ጥቃት “ቆራጥ እና ተመጣጣኝ" ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራንን በተመለከተ የሚያራምዱት ትርክት "እውነተኛ የወታደራዊ ጥቃት ስጋት" እንዳለ እንደሚጠቁም ደብዳቤው መግለጹን የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ቋሚ ልዑኩ፤ ኢራን ጦርነት እንደማትፈልግም ለመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጉቴሬዝ በጻፈው ደብዳቤ አስረድቷል።

    ደብዳቤው "የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ውጥረትም ሆነ ጦርነት እንደማትፈልግ እንዲሁም ማንኛውንም ጦርነት እንደማትጀምር በተደጋጋሚ በከፍተኛ ደረጃ ገልጻለች" ይላል።

    "ይሁን እንጂ፤ ወታደራዊ ጥቃት የሚፈጸምባት ከሆነ ኢራን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 51 መሠረት ያላትን ተፈጥሯዊ ራስን የመከላከል መብት በመጠቀም ቆራጥ እና ተመጣጣኝ ምላሽ ትሰጣለች" ሲል ማስፈሩንም የቱርኩ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል።

    "በኢራን ራስን የመከላከል ምላሽ ውስጥ፤ በቀጣናው የሚገኙ የጠላት ኃይሎች የጦር ሠፈሮች፣ ተቋማት እና ይዞታዎች በሙሉ ሕጋዊ የጥቃት ዒላማዎች ይሆናሉ" ሲልም አስጠንቅቋል።

    ይህንን ተከትሎ ለሚመጣው "ተገማች ያልሆነ እና መቆጣጠር የማይቻል መዘዝ አሜሪካ ሙሉ እና ቀጥተኛ ኃላፊነት ትወስዳለች" ሲልም አሳስቧል።

    ኢራን ቋሚ ልዑክ፤ የተባበሩት መንግሥታት ፀጥታው ምክር ቤት እና ዋና ፀሐፊው “ጊዜው ከመርፈዱ አስቀድሞ፣ ሳይዘገዩ” እርምጃ እንዲወስዱም ጠይቋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አገራቸው ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ትደርስ ወይም ወታደራዊ እርምጃ ትወስድ እንደሆነ በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ እንደሚታወቅ ተናግረዋል።

  8. አሜሪካ በኢራን ላይ ለምትፈጽመው ጥቃት የዩኬ የጦር ሰፈሮችን ለመጠቀም እንዳልተፈቀደላት ተገለጸ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የዩናይትድ ኪንግደም ብሪታኒያ መንግሥት፤ አሜሪካ ኢራን ላይ ልትፈጽም ለምትችለውን ጥቃት የዩናይትድ ኪንግደም ሠራዊትን የጦር ሰፈር እንድትጠቀም ፈቃድ አለመስጠቱን ቢቢሲ ያገኘው መረጃ አሳየ።

    ከዚህ ቀደም አሜሪካ መካለኛው ምሥራቅ ውስጥ ጥቃቶችን ለመፈጸም የእንግሊዝ ከተማ በሆነችው ግሎስተርሻየር የሚገኘውን ‘አርኤኤፍ ፌይርፎርድ’ የጦር ሰፈር ትጠቀም ነበር።

    ዩናይትድ ኪንግደም የባሕር ማዶ ግዛት እንደሆነ የሚቆጠረው በዲዬጎ ጋርሲያ የሚገኘው የጦር ሰፈርንም በቀጣናው ለምትፈጸመው ጥቃት ተጠቅማ ታውቃለች።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከትናንት በስቲያ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ "ዲያጎ ጋርሲያን አትስጡ" ሲሉ ዩናይትድ ኪንግደም የቻጎስ ደሴቶችን ለሞሪሺየስ ለማስረከብ ማቀዷን ተቃውመው ነበር።

    ዩናይትድ ኪንግደም ደሴቶቹን ካስረከበች በኋላ ከአሜሪካ ጋር የጦር ሰፈር ለመመሥረት መልሳ በሊዝ ለመከራየት አቅዳለች።

    የብሪታኒያው ‘ዘ ታይምስ’ ጋዜጣ ያወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው፤ ትራምፕ እዚህ ዕቅድ ላይ ወቀሳ ያሰሙት የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አሜሪካ የጦር ሰፈሩን እንዳትጠቀም ፈቃድ ባለመስጠቷ ነው።

    ስለ ጉዳዩ ጥያቄ የቀረበላቸው የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ “እንደ ሁልጊዜው ሁሉ፤ በወታደራዊ ኦፕሬሽን ጉዳዮች ላይ አስተያየት አንሰጥም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለመሰረዝ እንድትስማማ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። ስምምነት ላይ ማይደረስ ከሆነም ጥቃት እንደሚፈጽም ዝቷል።

    በቀጣናው ሊፈጸም ለሚችለው ጥቃት ዝግጅ እያደረገ ያለው የአሜሪካ መንግሥት የጦር መርከቦች፣ ተዋጊ አውሮፕላኖች እና ሌሎች ወታደራዊ ኃይሎቹን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አስጠግቷል።

    በሌላ በኩል አሜሪካ እና ኢራን ስዊትዘርላንድ ውስጥ ያደረጉት ንግግር የተወሰነ መሻሻል እየታየበት እንደሆነ ተገልጿል።

    የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ፤ “በአሜሪካ እና ኢራን መካከል እየተደረገ ያለ ፖለቲካዊ ሂደት አለ፤ ዩኬ የምትደግፈው እርሱን ነው” ብለዋል።

    “ኢራን በጭራሽ የኒውክሌር መሣሪያ መገንባት መቻል የለባትም፤ እኛ ቅድሚያ የምንሰጠውም ለቀጠናው ደኅንነት ነው" ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

  9. የቀድሞው የብሪታኒያ ልዑል ከሰዓታት እስር በኋላ ተለቀቁ

    አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ከእስር ሲለቀቁ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የቀድሞው የብሪታኒያ ልዑል አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር በብልሹ አሰራር ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ተለቀዋል።

    ፖሊስ ሐሙስ ጠዋት ላይ የ66 ዓመቱን የቀድሞ ልዑል በመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሲሆን፤ በሁለት መኖሪያ ቤቶቻቸው ላይም ብርበራ አድርጓል።

    ወንድማቸው ንጉስ ቻርለስ ሳልሳዊ የአንድሪውን እስር በሚመለከት በሰጡት ምላሽ “ሕጉ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ መሆን አለበት” ያሉ ሲሆን፤ ለፖሊስ ሙሉ ድጋፍ እና ትብብር እንደሚያደርጉም ገልፀዋል።

    ፖሊስ ከዚህ ቀደም አንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ከአሜሪካዊው የወሲብ ብዝበዛ ወንጀለኛ ጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር ባላቸው ግንኙነት እና ሚስጢራዊ መረጃዎችን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል ጥርጣሬ ምርመራ ለመክፈት ስለማሰቡ አሳውቆ ነበር።

    በሁለቱ ግለሰቦች መካከል የነበረው የመልዕክት ልውውጥ በቅርቡ በአሜሪካ መንግሥት ይፋ ሆኗል።

    ሐሙስ ምሽት ፖሊስ አንድሪው በምርመራ ላይ እያሉ ከእስር መለቀቃቸውን አስታውቋል።

    ከጄፍሪ ኤፒስቲን ጋር በተያያዘ ለበርካታ ዓመታት ስማቸው ሲነሳ የነበሩት የቀድሞው ልዑል በቁጥጥር ስር ሲውሉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

    ባለፉት ዓመታት ምንም ወንጀል አለመስራታቸውን በተደጋጋሚ ተናግረዋል።

    ፖሊስ ካደረገው “ጥልቅ ግምገማ” በኋላ በአንድሪው ማውንትባተን-ዊንዘር ላይ ይፋዊ ምርመራ መከፈቱን ገልጿል።

    የቀድሞው ልዑል በቁጥጥር ስር ሲውሉ የተጠረጠሩበት ወንጀል ከወሲባዊ ጥቃት ጥርጣሬ ጋር የተያያዘ አይደለም።

  10. ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ10 ቀናት ውስጥ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ይደረሳል ወይም "መጥፎ ነገሮች ይፈጠራሉ" አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ “ምናልባት በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ” አሜሪካ ከኢራን ጋር ስምምነት ላይ ትደርስ አልያም ቴህራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ትወስድ እንደሆነ ዓለም ይመለከታል በማለት ተናገሩ።

    ትራምፕ ባቋቋሙት የጋዛ የሰላም ቦርድ የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ከኢራን ጋር እየተደረገ ስላለው የኒውክሌር ፕሮግራም ድርድር አንስተዋል።

    "ትርጉም ያለው ስምምነት መፈጸም አለብን፤ ካልሆነ ግን መጥፎ ነገሮች ይፈጠራሉ" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ውስጥ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘው ኃይሏ ማጠናከሯን ቀጥላለች። በሌላ በኩል ደግሞ ስዊዘርላንድ ውስጥ ከኢራን ጋር የምታደርገው ድርድር ለውጥ እየታየበት እንደሆነ ተነግሯል።

    የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሕግ አውጪዎች እና አንዳንድ ሪፐብሊካኖች በበኩላቸው፤ ኮንግረስ ሳይፈቅድ ኢራን ላይ ሊወሰድ የሚችል ማንኛውንም ወታደራዊ እርምጃ በተመለከተ ከአሁኑ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

    ትራምፕ በንግግራቸው፤ በድርድሩ አሜሪካን የወከሉት ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እና አማቻቸው ጃሬድ ኩሽነር ከኢራን ጋር "በጣም ጥሩ ውይይቶችን" ማድረጋቸውን ገልጸዋል።።

    "ባለፉት ዓመታት እንደተመለከትነው፤ ከኢራን ጋር ትርጉም ያለው ስምምነት ላይ መድረስ ቀላል አይደለም" ብለዋል። ስምምነት የማይፈጸም ከሆነ ግን "መጥፎ ነገሮች ይፈጠራሉ" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ ይህንን ከማለታቸው አንድ ቀን አስቀድሞ ዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬታሪያት የሆኑት ካሮሊን ሌቪት፤ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ብትደርስ "በጣም ብልህነት" ነው ሲሉ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሁንም ቢሆን የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራምን በመለከተ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ይገኛል የሚል ተስፋ መሰነቃቸውንም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ አክለዋል።

    ባለፉት ሳምንታት ውስጥ አሜሪካ ‘ዩኤስኤስ አብራሃም ሊንከን’ የተሰኘውን ግዙፍ የጦር መርከብ ጨምሮ በርካታ ኃይሎቿን ወደ ቀጣናው አስጠግታለች።

    ኢራንም በበኩሏ ወታደራዊ ተቋማቶቿን ከጥቃት ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ እያጠናከረች እንደሆነ የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል።

    የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒም የአሜሪካ ኃይሎች ላይ የተሰነዘሩ ዛቻዎችን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ለጥፈዋል።

  11. ተጨማሪ 6 የአሜሪካ አውሮፕላኖች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲጓዙ ታዩ

    የአውሮፕላኖቹ የጉዞ መስመር

    የፎቶው ባለመብት, Flightradar24

    የምስሉ መግለጫ, የአውሮፕላኖቹ ጉዞ የሚያሳየው ድረ ገጽ

    ቢያንስ ስድስት የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከአውሮፓ ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ሲጓዙ ፍላይትራዳር24 በተባለው ታዋቂ የበረራ መከታተያ ድረገጽ ላይ ታይተዋል።

    ከእነዚህ አውሮፕላኖች መካከል ሁለት ኢ-3 የቅኝት ጄቶች፣ ሁለት ሲ-17 ወታደራዊ የመጓጓዣ አውሮፕላኖች፣ አንድ ኬሲ-135 አየር ላይ ነዳጅ የሚሞሉ ነዳጅ ጫኝ አውሮፕላን እና ሌሎች ኤችሲ-130 የውጊያ ጄቶች ይገኙበታል።

    እነዚህ ተጨማሪ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከአውሮፓ ተነስተው ዛሬ ሐሙስ የካቲት 12/2018 ዓ.ም. ጠዋት ሲጓዙ ታይተዋል።

    የወታደራዊ ማጓጓዣ አውሮፕላኖቹ አውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ የጦር ሠፈሮች ተነስተው ወደ ሜዲትራኒያን አቅጣጫ አምርተዋል።

    የፍላይትራዳር24 መረጃ እንደሚያመለክተው የተወሰኑት አውሮፕላኖች ከጣሊያን ኔፕልስ ተነስተው ኳታር ወደ ሚገኘው የአሜሪካ አል-ኡዴይድ የአየር ኃይል ሰፈር በርረዋል።

  12. አሜሪካ ወሳኝ የጦር አውሮፕላኖችን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ማሰማራቷ ተረጋገጠ

    አውሮፕላኖች

    የፎቶው ባለመብት, Getty

    አሜሪካ ከኢራን ጋር በሁለት ዙር ያካሄደቻቸው ድርድሮች ተጨባጭ ውጤት ባላስገኙበት በአሁኑ ጊዜ፤ በቀጣይ ቀናት ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት አይሏል።

    ዋይት ሐውስ ዛሬ እንዳስታወቀው ኢራን በአስቸኳይ ከስምምነት ላይ የማትደርስ ከሆነ ቴህራን ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ ወታደራዊ አማራጮች ለፕሬዝዳንት ትራምፕ ቀርቦላቸው ውይይት ተደርጓል።

    ይህም በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክቷል።

    አሜሪካ እየዛተችበት ላለው ወታደራዊ እርምጃ ዝግጅት ለማድረግ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ግዙፍ አውሮፕላን ተሸካሚ እና ሌሎች የጦር መርከቦችን አሰማርታለች።

    በተጨማሪም ሰሞኑን የቢቢሲ የመረጃ ማጣሪያ ቡድን “ቢቢሲ ቬሪፋይ” ወሳኝ የተባሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ጄቶች ወደ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ ሲያመሩ የሚያሳዩ መረጃዎችን መርምሮ ለማረጋገጥ ችሏል።

    እነዚህ የጦር አውሮፕላኖች በተመለከተ በጄንስ የመረጃ ተቋም የአውሮፕላን በረራ ዘርፍ ተንታኝ የሆኑት ሳም ዋይዝ ስለ አውሮፕነኖቹ ምነንት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

    በዚህም መሠረት አሜሪካ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የላከቻቸው የጦር አውሮፕላኖች የሚከተሉት ናቸው።

    • ኤፍ-35 – ስቲልዝ የተባሉት ተዋጊ ጄቶች “በከፍተኛ ሁኔታ ጥበቃ የሚደረግላቸው ዒላማዎችን” ለመምታት የሚውሉ አውሮፕላኖች ናቸው
    • ኤፍ-22 – እጅግ ዘመናዊ የውጊያ ጄቶች ሲሆኑ፣ ጥቃት የመፈጸም ጥምር ብቃት ያላቸው ናቸው። እነዚህ የጦር ጄቶች “በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታ እና ብቃት ስላላቸው ከዚህ በፊት በአብዛኛው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተልከው አያውቁም”
    • ኬሲ-135 እና KC-46 – እነዚህ ደግሞ ነዳጅ ጫኝ አውሮፕላኖች ሲሆኑ ረጅም ርቀት ተጉዘው ጥቃት የሚፈጽሙ የጦር ጄቶችን አየር ላይ ሳሉ ነዳጅ የሚሞሉ ወሳኝ ድጋፍ ሰጪ አውሮፕላኖች ናቸው። ቀድሞውንም በአካባቢው ተሰማርተው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል
    • ኢ-3 – ይህ የማዘዣ እና የቅኝት አውሮፕላን ሲሆን፣ አሜሪካ የምታካሂዳቸውን “መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ዘመቻዎች ለመምራት እና ለመቆጣጠር” የሚያስችል ነው

    ተንታኙ፤ ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ የተሰማሩ አውሮፕላኖችን በመመልከት እንደገለጹት፤ ይህ ስምሪት ቀላል የሚባል አይደለም። የአውሮፕላኖቹ ብቃት “ትልቅ የአየር ኃይል ዘመቻ ሊካሄድ እንደሆነ በግልጽ የሚያመለክት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ቬሪፋይ ተናግረዋል።

  13. የናይጄሪያ እስላማዊ ፖሊስ ረመዳንን ያልጾሙ ዘጠኝ ሙስሊሞችን አሰረ

    የናይጄሪያ እስላማዊ ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, Sani Maikatanga

    በሰሜናዊ ናይጄሪያ የምትገኘው ካኖ ግዛት እስላማዊ ፖሊስ፤ በረመዳን የመጀመሪያ ቀን ሲመገቡ የተገኙ ዘጠኝ ሙስሊሞች በቁጥጥር ስር አዋለ።

    አብዛኛው ነዋሪ ሙስሊም በሆነበት ካኖ ግዛት፤ የሸሪዓ ሕግ ከመደበኛው የሕግ ጋር ጎን ለጎን ተግባራዊ ይደረጋል።

    "ሂስባ" በመባል የሚጠራው እስላማዊ ፖሊስ በየዓመቱ በረመዳን ወር ሙስሊሞች የጾም ሰዓትን እያከበሩ መሆኑን ለማረጋገጥ በካፌዎች፣ ምግብ ቤቶች እና የገበያ ስፍራዎች ፍተሻ ያካሂዳል። በብዛት ክርስቲያኖች በሚኖሩባቸው የግዛቱ አካባቢዎች የሚገኙ የተወሰኑ ተቋማት ክፍት ይሆናሉ።

    የእስላማዊው ፖሊስ ምክትል አዛዥ ሙጃሂድ አሚኑዲን፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰባት ወንዶች እና ሁለት ሴቶች ረመዳን መጀመሩን እንደማያውቁ ማስመሰላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ምክትል አዛዡ፤ "አስረናቸዋል፤ ከእኛ ጋር ናቸው። የጾምን አስፈላጊነት፣ እንዴት እንደሚጸለይ፣ ቁርአን እንዲያነቡ እና የተሻሉ ሙስሊሞች እንዲሆኑ እናስተምራቸዋለን" ብለዋል።

    እስላማዊው ፖሊስ ታሳሪዎቹም መቼ እንደሚለቅቃቸው ግልጽ አይደለም። ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሁኔታዎች በተፈጠሩበት ወቅት ፖሊስ የታሳሪዎቹን ከቤተሰብ አግኝቶ፤ ግለሰቦቹ ከተፈቱ በኋላ እስከ ወሩ መጨረሻ ድረስ መጾማቸውን ክትትል እንዲያደርጉ ያሳስብ ነበር።

    በአብዛኛው ሙስሊም ነዋሪዎችን በያዙት የሰሜናዊ ናይጄሪያ 12 ግዛቶች ውስጥ ሸሪዓ ከመደበኛው የሕግ ስርዓት ጎን ለጎን ተግባራዊ እንዲሆን የተደረገው ከ20 ዓመታት በፊት ነበር።

    በእስልምና የዘመን ስሌት ውስጥ ዘጠነኛው ወር የሆነው ረመዳን፤ በሙስሊሞች ዘንድ ልዩ ስፍራ ይሰጠዋል። ሙስሊሞች፤ የቅዱስ ቁርአን የመጀመሪያዎቹ አንቀጾች ለነቢዩ መሐመድ የወረዱት በዚህ ወር እንደሆነ ያምናሉ።

    የዘንድሮው የረመዳን ጾም በናይጄሪያ የተጀመረው ትናንት ረቡዕ ሲሆን በመጋቢት 12 ወይም 13 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

  14. በጋምቤላ ክልል በተሃድሶ ሥልጠና ላይ “አጭበርበረዋል” የተባሉ 48 የፖሊስ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ

    የጋምቤላ ክልል አድማ ብተና አባላት የምርቃት ትርኢት ላይ

    የፎቶው ባለመብት, Gambella Press Secretariat

    በቅርቡ በጋምቤላ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ለፖሊስ አባላቱን በሙሉ የተሃድሶ ሥልጠና እየሰጠ ያለው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፤ በግምገማው ወቅት ማጭበርበር ፈጸመዋል የተባሉ 28 ሰዎች እስከ አንድ ዓመት ተኩል የሚደረስ ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው አስታወቀ።

    ሌሎች 20 የፖሊስ በአባላት ደግሞ ጉዳያቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ገልጿል።

    ባለፈው ኅዳር የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ መገደላቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በአቦል ወረዳ ለሳምንታት የዘለቀ ግጭት መከሰቱ ይታወሳል።

    የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው እና የተቋማት እንቅስቃሴ እንዲቆም ያደረገውን ግጭት ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ሁሉም የፖሊስ እና አድማ ብተና አባላት በእጃቸው ላይ ያለውን የጦር መሣሪያ እንዲያስረክቡ አዝዟል። በፍቃድ፣ በሕመም እና በወሊድ ምክንያት ሥራ ላይ ያልሆኑ አባላትን ጨምሮ ሁሉም የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች የተሃድሶ ሥልጠና እንዲወስዱ አድርጓል።

    በዚህ “የተሃድሶ ግምገማ” አማካኝነት “ሁሉም የመደበኛ ፖሊስ አባላትና የአድማ ብተና ፖሊሶች” ለሥልጠና ወደ “ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ማሠልጠኛ” እንዲገቡ መደረጋቸውን የክልሉ ፖሊስ ረቡዕ የካቲት 11/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

    ይሁን እንጂ በዚህ ሥልጠና ወቅት “የማጭበርበር” ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ የፖሊስ አባላት መኖራቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስረድቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት 48 የፖሊስ አባላት ፈጽመዋል ያላቸውን ድርጊቶችንም በመግለጫው ዘርዝሯል።

    በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል “ከሥራ ገበታቸው በራሳቸው ጊዜ ጥለው የወጡ” እንዲሁም “በሥነ-ምግባር እና በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው ከሠራዊቱ የተሰናበቱ” እንደሚገኙበት ተገልጿል።

    “ምንም ዓይነት ፖሊሳዊ ሥልጠና ሳይሰለጥኑ ወይም ሲቪል ሆነው የገቡ” ግለሰቦችም ይገኙበታል ተብሏል። ከዚህ ቀደም “ሚሊሻ የነበሩ” ነገር ግን “በ2017 ዓ.ም. በነበረው የቦንጋ ፖሊስ ማሠልጠኛ ተቋም ሾልከው የገቡ” አባላትም በተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸዋል።

    መግለጫው እንደሚያስረዳው በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል “ከፌደራል ፖሊስ እና ከአገር መከላከያ” ቀርተው “ወደ ፖሊስ ያልተካተቱ” አሉበት። “ከብልሹ አሠራር፣ ከሙስና እና ከሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ጋር በተያያዘ” የተያዙ እንዳሉም ተገልጿል።

    እነዚህን ድርጊቶች ፈጽመዋል ከተባሉት 48 ተጠርጣሪዎች ውስጥ 28 ያህሉ “ፈጣን ችሎት” መቅረባቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ እያንዳንዳቸው ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል የሚደርስ ፅኑ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ እንደተፈረደባቸው አስታውቋል።

    ቀሪዎቹ 20 የፖሊስ አባላት ደግሞ “ጉዳያቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ የምርመራ መዝገባቸው” እየተደራጀ ነው ተብሏል።

    በእነዚህ የፖሊስ አባላት ላይ የተወሰደው የሕግ እርምጃ ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ መሆኑን ያስረዳው የክልሉ ፖሊስ፤ ወደ ተሃድሶ ሥልጠናው በገቡት የፖሊስ አባላት ላይ የሚደረገው “አጠቃላይ የግምገማ ውጤት” ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ ገልጿል።

  15. ሩሲያ በኢራን ላይ ጥቃት እንዳይፈጸም ስታስጠነቅቅ፤ ፖላንድ ዜጎቿ ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች

    ስርጌይ ላቭሮቭ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, ስርጌይ ላቭሮቭ

    የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች መዘዙ አስከፊ ስለሚሆን ከወታደራዊ እርምጃ ተቆጥባ ኢራን ኒውክሌርን ለሰላማዊ ዓላማ የምትጠቀምበትን መንገድ እንድትመርጥ አሳሰቡ።

    አሜሪካ በቀጣይ ቀናት በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ትወስዳለች የሚል ስጋት እያየለ በመጣበት በአሁኑ ጊዜ ፖላንድ በኢራን ውስጥ ያሉ ዜጎቿ በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡ በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል አዝዛለች።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ኢራን እና አሜሪካ ስዊትዘርላንድ ድርድር ካደረጉ በኋላ ለሳዑዲው አል አረቢያ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

    “በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት ጥሩ ውጤት አያስገኝም። ቀደም ሲል በዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቁጥጥር ስር ባሉ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። እንደምንረዳው የኒውክሌር አደጋ ይከሰታል የሚል ስጋት አለን” ብለዋል ላቭሮቭ።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም “በቀጣናው ኣሉ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና የአረብ አገራት የሚኖራቸውን ምላሽ በተመለከተ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው። ሁኔታው በእሳት መጫወት እንደሆነ ስለሚያውቁ፤ ማንም ውጥረቱ ወደ ግጭት እንዲሸጋገር አይፈልግም።”

    ውጥረቱ የሚባባስ ከሆነ ኢራን ከሳዑዲ አረቢያ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር የነበራትን ግንኙነት ማሻሻልን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት የተገኙ መልካም ውጤቶችን ያበላሻል የሚል ስጋት እንዳላቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ገልጸዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖላንድ በኢራን የሚገኙ ዜጎቿ በአስቸኳይ በሰዓታት ውስጥ ለቅቀው እንዲወጡ ማዘዟን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሳሰቡ።

    ለዚህም ምክንያታቸው በኢራን ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ሊከሰት ይችላል በሚል ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዜጎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት "እባካችሁ ኢራንን በአስቸኳይ ለቅቃችሁ ውጡ...በምንም ሁኔታ በደዚያ አገር አትሂዱ ሲሉ” አስጠንቅቀዋል።

  16. የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ልዑል አንድሪው ማውንትባተን ዊንዘር በቁጥጥር ስር ዋሉ

    ፖሊስ የቀድሞውን ልዑል በቁጥጥር ስር ለማዋል ቤታቸው ሲገኝ

    የፎቶው ባለመብት, Bav Media

    ከጄፍሪ ኤፒስቲን የወሲብ ብዝበዛ ጋር በተያያዘ የልዑልነት ማዕረጋቸው የተገፈፈው የዩናይትድ ኪንገደሙ አንድሪው ማውንባተን ዊንዘር በሥራ ላይ እያሉ ያልተገባ ባሕሪ በማሳየት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

    ፖሊስ የዩናይትድ ኪንግደም ንጉስ ቻርለስ ሳልሳዊ ወንድም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን እና ቤታቸው ብርበራ እየተደረገበት መሆኑን አስታውቋል።

    እስሩ የመጣው ፖሊስ የቀድሞው ልዑል ሚስጢራዊ ሰነዶችን በወሲብ ወንጀል ለተፈረደበት ጄፍሪ ኤፒስቲን አጋርተዋል በሚል እንደጠረጠራቸው ካሳወቀ በኋላ ነው።

    ፖሊስ የቀድሞው ልዑል በቁጥጥር ስር የዋሉት በተከፈተባቸው ምርመራ “ጥልቅ ግምገማ” ከተደረገ በኋላ ነው።

    ዛሬ 66ተኛ ዓመታቸው የያዙት አንዲሪው ከጄፍሪ ኢፒስቲን ጋር በተያያዘ የሚቀርቡባቸውን ክሶች በተደጋጋሚ ውድቅ አድርገዋል።

  17. የተባበሩት መንግሥታት በሱዳን የተፈጸሙ ጥቃቶች “የዘር ማጥፋት ማሳያዎች” ናቸው አለ

    የሱዳን ግጭት የተፈናቀለች ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የመንግሥታቱ ድርጅት እውነት አፈላላጊ ተልዕኮ የሱዳኗ ኤል ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር በዋለችበት ወቅት የተፈጸሙ ወንጀሎች የዘር ማጥፋትን እንደሚያመለክቱ ገለጸ።

    የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) በምዕራብ ዳርፉር የምትገኛውን ኤል ፋሸርን ለ18 ወራት በከበባ ስር ካቆየ በኋላ በቁጥጥሩ ሥር ያዋላት በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።

    ይህም ለሦስት ዓመት በቀጠለው የሰዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በጣም አስከፊው ጊዜ ነበር የተባለ ሲሆን ዓለም አቀፍ ውግዘትንም አስከትሏል።

    የመንግሥታቱ ድርጅት በግጭቱ ወቅት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል የሚል ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    አርኤስኤፍ በመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት ላይ አስተያየቱን ባይሰጥም ከዚህ ቀድም በቀረቡ ተመሳሳይ ውንጀላዎች ላይ ማስተባባያ ሰጥቷል።

    የእውነት አፈላላጊ ተልዕኮው ባለሙያ የሆኑት ሞና ሪሽማዊ “የሰበሰብናቸው ማስረጃዎች የተራዘመ ከበባ፣ ረሃብ እና የሰብዓዊ እርዳታን መከልከልን ጨምሮ የጅምላ ግድያ፣ ደፈራ፣ ስቅይት እና አስገድዶ መሰወር፣ ስልታዊ ማዋረድ መፈጸማቸውን ያሳያል በተጨማሪም የጥቃት ፈጻሚዎቹ ቃል እነዚህ ድርጊቶች መፈጸማቸውን ያረጋግጣል” ብለዋል።

    “አርኤስኤፍ በኤልፋሽር የሚገኙ የዛግሃዋ እና የፉር ማኅበረሰቦችን ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ለማጥፋት ሆን ብሎ በማሰብ ተንቀሳቅሷል። እነዚህም የዘር ማጥፋት ማሳያዎች ናቸው።”

    ሪፖርቱ በማጠቃለያው ሦስት የዘር ማጥፋት ድርጊቶች መፈጸማቸውን ደምድሟል።

    ከእነዚህም መካከል ከለላ ያላቸው የማኅበረሰብ ቡድኖችን መግድል፣ ከባድ የሆነ የአካል እና የአእምሮ ጉዳት ማድረስ፣ ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ቡድኑ ላይ አካላዊ ውድመት ለማድረስ ይሁነኝ ተብሎ እርምጃ መውሰድ ይገኙበታል።

    የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ሪፖርቱን “አሰቃቂ” ያሉት ሲሆን መደምደሚያውን ደግሞ ሐሙስ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።

    ሚኒስትሯ በመግለጫቸው ለወንጀል ፈጻሚዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ እና ለተጠቂዎች ፍትህ ለመስጠት እንዲሁም ወደ ግጭቱ የሚሄደውን የጦር መሳሪያ ፍሰት ለማስቆም ዓለም አቀፍ ወንጀል ምርመራ መካሄድ አለበት ብለዋል።

    የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቱ ጦር አዛዥ እና በምክትላቸው መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ የተነሳ እአአ በ2023 ተጀምሯል።

  18. ክራይስስ ግሩፕ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው ውጥረት ወደ ከባድ ግጭት የመመለስ ስጋት እንዳለው አስጠነቀቀ

    የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዓለም አቀፉ ክራይስስ ግሩፕ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት፣ በትግራይ ክልል እና በጎረቤት ኤርትራ መካከል እየተባባሰ የመጣው ውጥረት የአፍሪካ ቀንድን ከሦስት ዓመታት በኋላ መልሶ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሊከት ይችላል ሲል አስጠነቀቀ።

    ተቋሙ ባወጣው መግለጫ የተለያዩ ምክንያቶች ጦርነቱን ሊያፈነዱት እንደሚችሉ ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ ወደ ጦርነት ዘው ብሎ ለመግባት ቀላል ቢሆንም ጦርነቱን ለማቆም ግን በጣም ከባድ ይሆናል ብሏል።

    የአፍሪካ የፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ሙሪታ ሙቲጋ “ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን እና ትግራይ ክልልን የሚያፋልም አዲስ ጦርነት መቋቋም የማይቻል ዋጋ ያለው ነው። አደጋው ሦስቱንም ወገኖች ለአሁኑ እንዲታቀቡ ያደረጋቸው ይመስላል። ሆኖም እንዳያገረሽ ከዚህ በላይ መደረግ አለበት” ብለዋል።

    የድርጅቱ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ማግነስ ታይለር ከትግራይ ጦርነት መቋጨት በኋላ በዋናነት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ምክንያት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት መሻከሩን አንስተዋል።

    ኤርትራ ይህ ፍላጎት “ወረራን ሊያካትት ይችላል” የሚል ስጋት እንዳላትም ጠቁመዋል።

    ምክትል ዳይሬከተሩ አዲስ አበባ ህውሓት ከኤርትራ ጋር ስውር ትብብር መስርቷል ስትል እንደምትከስ ተናግረዋል።

    የክራይስስ ግሩፕ መግለጫ በቅርቡ በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች የድሮን ጥቃትን ያካተተው ግጭት ኤርትራንም በመሳብ ወደ ሰፊ ጦርነት ሊቀየር እንደሚችል ያሳያል ብሏል።

    ተቋሙ አክሎም በሰሜን ኢትዮጵያ አዲስ የሚቀሰቀስ ግጭት በሱዳን ካለው ግጭት ጋር ተደርቦ ኃያላን የውጭ ተዋንያንን እንደሚስብ እና ተለዋዋጭ የሆነውን የቀይ ባህር ቀጣናን እንደሚያውክ አስጠንቅቋል።

    ክራይስስ ግሩፕ ተፅዕኖ ፈጣሪ የአፍሪካ አገራት እና ዓለም አቀፍ አጋራት የዲፕሎማሲያዊ ሥራቸውን እንዲጨምሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓትን እንዲያሸማግሉ ጠይቋል።

    አክሎም የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ፍላጎትን እና የኤርትራን ሉዓላዊነቷ ላይ ጥቃት የመሰንዘር ስጋትን ጨምሮ በሁለቱም በኩል ያሉ ወገኖች ቁርሾዎችን እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል።

    “ሰሜን ኢትዮጵያ የባሩድ በርሜል ነው። እናም በግጭት በተጎዳው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ከዚህ በላይ የሚያናውጥ አዲስ አክሳሪ ጦርነት ሊያቀጣጥል ይችላል” ብሏል።

  19. የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት የእድሜ ልክ እስር ተፈረደባቸው

    የደቡብ ኮሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዮል

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንት መንግሥት ላይ አመጽ በማነሳሳት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የእድሜ ልክ እስር ተፈረደባቸው።

    የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት የቀድሞ ፕሬዚዳንት እአአ በታሕሳስ 2024 በአገሪቱ ላይ ወታደራዊ አመራር ለመጫን ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ ነው ክስ የተሰረተባቸው።

    የአገሪቱ ፍርድ ቤት ዛሬ በሰጠው ውሳኔ ዮን ሱክ ዮል መንግሥት ላይ አመጽ በማነሳሳት ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የእድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸዋል።

    በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኪም ዮንግ ሂዩንም ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የ30 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

    ዮል ሱክ ዮልን በወቅቱ ተቃዋሚ የነበሩት እና አሁን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሊ ጃይ ሚዩንግ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር ተበሏል።

    ከዚህ በፊት ዮል ሥልጣንን ያለ አግባብ በመጠቀም እንዲሁም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓትን በመጣስ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው ነበር።

    ዮል እና ከእርሳቸው ጋር የተፈረደባቸው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ይግባኝ መጠየቅ ይችላሉ ተብሏል።

  20. ትራምፕ እስከ ቅዳሜ ድረስ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸም ስለሚቻልበት ሁኔታ ከአማካሪዎቻቸው ጋር መወያየታቸው ተነገረ

    ትረምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ከፍተኛ የብሔራዊ ደህንነት ባለሥልጣናት ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የአገሪቱ ጦር እስከ ቅዳሜ ድረስ ኢራን ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶችን ዝግጁ መሆኑን ማሳወቁን በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

    ትረምፕ በኢራን ላይ ጥቃት መቼ ሊፈጸም እንደሚችል ከአማካሪዎቻቸው ጋር ቢነጋገሩም ከውሳኔ ላይ አለመድረሳቸው ተገልጿል።

    ሲቢኤስ ይህ እቅድ ወደፊት ሊገፋ እንደሚችል ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

    ምንጮች የትራምፕ አማካሪዎች የተፈጠረውን ውጥረት እንዲሁም “ጥቃቱ ባይፈጸም” የሚኖረውን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አደጋ እየፈተሹ መሆኑ ተገልጿል።

    በሚቀጥሉት ሦስት ቀናት ፔንታጎን የተወሰኑ ወታደራዊ ኃይሎችን ከመካከለኛው ምሥራቅ በማስውጣት ወደ አውሮፓ ወይንም ወደ አሜሪካ ያሰማራል ተብሏል።

    ሲቢኤስ ምንጮቹን ጠቅሶ አንደዘገበው ፔንታጎን ያሉትን ወታደራዊ ኃይሎች ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስ የተለመደ አሰራር መሆኑ የገለጸ ሲሆን በኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት የማይቀር መሆኑን አያሳይም ተብሏል።