በቅርቡ በጋምቤላ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ለፖሊስ አባላቱን
በሙሉ የተሃድሶ ሥልጠና እየሰጠ ያለው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፤ በግምገማው ወቅት ማጭበርበር ፈጸመዋል የተባሉ 28 ሰዎች
እስከ አንድ ዓመት ተኩል የሚደረስ ጽኑ እስራት እንደተፈረደባቸው አስታወቀ።
ሌሎች 20 የፖሊስ በአባላት ደግሞ ጉዳያቸው
በመደበኛ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን ገልጿል።
ባለፈው ኅዳር የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት
ቤት አዛዥ መገደላቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በአቦል ወረዳ ለሳምንታት የዘለቀ ግጭት መከሰቱ ይታወሳል።
የሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው እና የተቋማት እንቅስቃሴ
እንዲቆም ያደረገውን ግጭት ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ሁሉም የፖሊስ እና አድማ ብተና አባላት በእጃቸው ላይ ያለውን የጦር መሣሪያ
እንዲያስረክቡ አዝዟል። በፍቃድ፣ በሕመም እና በወሊድ ምክንያት ሥራ ላይ ያልሆኑ አባላትን ጨምሮ ሁሉም የክልሉ ፀጥታ ኃይሎች የተሃድሶ ሥልጠና እንዲወስዱ አድርጓል።
በዚህ “የተሃድሶ ግምገማ” አማካኝነት “ሁሉም
የመደበኛ ፖሊስ አባላትና የአድማ ብተና ፖሊሶች” ለሥልጠና ወደ “ዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ ማሠልጠኛ” እንዲገቡ መደረጋቸውን የክልሉ
ፖሊስ ረቡዕ የካቲት 11/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ይሁን እንጂ በዚህ ሥልጠና ወቅት “የማጭበርበር”
ድርጊት ሲፈጽሙ የተገኙ የፖሊስ አባላት መኖራቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስረድቷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት
48 የፖሊስ አባላት ፈጽመዋል ያላቸውን ድርጊቶችንም በመግለጫው ዘርዝሯል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል “ከሥራ ገበታቸው
በራሳቸው ጊዜ ጥለው የወጡ” እንዲሁም “በሥነ-ምግባር እና በተለያዩ ወንጀሎች ተፈርዶባቸው ከሠራዊቱ የተሰናበቱ” እንደሚገኙበት ተገልጿል።
“ምንም ዓይነት ፖሊሳዊ ሥልጠና ሳይሰለጥኑ ወይም
ሲቪል ሆነው የገቡ” ግለሰቦችም ይገኙበታል ተብሏል። ከዚህ ቀደም “ሚሊሻ የነበሩ” ነገር ግን “በ2017 ዓ.ም. በነበረው የቦንጋ
ፖሊስ ማሠልጠኛ ተቋም ሾልከው የገቡ” አባላትም በተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸዋል።
መግለጫው እንደሚያስረዳው በቁጥጥር ስር ከዋሉት
መካከል “ከፌደራል ፖሊስ እና ከአገር መከላከያ” ቀርተው “ወደ ፖሊስ ያልተካተቱ” አሉበት። “ከብልሹ አሠራር፣ ከሙስና እና ከሕገ-ወጥ
የጦር መሣሪያ ጋር በተያያዘ” የተያዙ እንዳሉም ተገልጿል።
እነዚህን ድርጊቶች ፈጽመዋል ከተባሉት 48 ተጠርጣሪዎች
ውስጥ 28 ያህሉ “ፈጣን ችሎት” መቅረባቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ እያንዳንዳቸው ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል የሚደርስ
ፅኑ እስራት እና የገንዘብ መቀጮ እንደተፈረደባቸው አስታውቋል።
ቀሪዎቹ 20 የፖሊስ አባላት ደግሞ “ጉዳያቸው
በመደበኛ ፍርድ ቤት እንዲታይ የምርመራ መዝገባቸው” እየተደራጀ ነው ተብሏል።
በእነዚህ የፖሊስ አባላት ላይ የተወሰደው የሕግ
እርምጃ ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ መሆኑን ያስረዳው የክልሉ ፖሊስ፤ ወደ ተሃድሶ ሥልጠናው በገቡት የፖሊስ አባላት ላይ የሚደረገው
“አጠቃላይ የግምገማ ውጤት” ወደፊት ይፋ እንደሚደረግ ገልጿል።