ኢትዮጵያ ዛሬ መተግበር ለጀመረችው በገበያ ሥርዓት የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ስርዓት እና ሌሎች ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ የሚውል 13.5 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና ወዳጅ ሀገራት “በድጋፍ” እና ሌሎች አማራጮች መገኘቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።
ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 10.7 ቢሊዮን ዶላሩ የገንዘብ “ድጋፍ” የተገኘው ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ)፣ ከዓለም ባንክ እና “ከአበዳሪዎች” እንደሆነ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ አስታውቀዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይህንን ያስታወቁት ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 22/2016 ዓ.ም. ንጋት ላይ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓት ማሻሻያን አስመልክቶ በወጣ መግለጫ እና ማብራሪያ ላይ ነው።
መንግሥት መተግበር የጀመራቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የሚያመጡት “የሽግግር ወቅት ወጪዎችን” እንደሚኖሩ እንዲሁም አዲሱ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓት “የሚያስከትላቸው ጫናዎች” እንደሚኖሩ አቶ ማሞ በመግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል።
ይሁንና እነዚህን ጫናዎች ለመቀነስ የሚውል 10.7 ቢሊዮን ዶላር “ትልቅ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች” እንደተገኘ ገልጸዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው፤ “ይህ የገንዘብ ድጋፍ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን ይህንን ሪፎርም የሚመለከተውን ይጨምራል” በማለት “ድጋፍ” ሲሉ የጠሩት ገንዘብ ምንጮችን ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባሻገር ከኢትዮጵያ “ወዳጅ ሀገራት” በሌሎች አማራጮች ተጨማሪ 2.8 ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘ አቶ ማሞ አስታውቀዋል።
ይህ ገንዘብ የተገኘው “በማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ ሂሳብ (central bank diposite) እና በሀገራት የገንዘብ ልውውጥ (currency swap)” መልክ እንደሆነም አብራርተዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው በእነዚህ አማራጮች ገንዘብ የተገኘባቸውን ሀገራት ባይጠቅሱም ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት ኢትዮጵያ እና የተባበሩት የአረብ ኢምሬቶች የገንዘብ ልውውጥ ስምምነት ተፈራርመው ነበር።
ማሞ ዛሬ በሰጡት መግለጫቸው ላይ በሌሎች አማጮችም ተጨማሪ ገንዘብ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
“እነዚህ አሃዞች [የተገኘው 13.5 ቢሊዮን ዶላር ] ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (IFC)፣ ከሌሎች ባለብዙ ወገኖች ፕሮጀክትን አስመልክቶ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን እና በሂደት ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት ይፋ የሚደረገውን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ አያካትትም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ”የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክ እና ከወዳጅ ሀገራት” ያገኘው ገንዘብ ሀብት “የመንግሥትን የሪፎርም ስራዎች ጥንካሬ ያገናዘበ” እንደሆነ አቶ ማሞ ጠቅሰዋል።
“በአፍሪካ አህጉር ትልቁ ከሚባሉት የገንዘብ ድጋፎች አንዱ ነው” ሲሉም አሞካሽተውታል።