ቀጥታ, ትራምፕ፣ ቴህራን አሜሪካ በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ትፈልጋለች አሉ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን” እና የመሪዎቿን ሁኔታ እስክታውቅ ድረስ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን በፍጥነት እንድትከፍት መጠየቋን ተናገሩ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ፣ ቴህራን አሜሪካ በተቻለ ፍጥነት የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ትፈልጋለች አሉ

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን” እና የመሪዎቿን ሁኔታ እስክታውቅ ድረስ አሜሪካ የሆርሙዝ ወሽመጥን በፍጥነት እንድትከፍት መጠየቋን ተናገሩ።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ከኢራን ጋር መልዕክቱን መቼ እንደተለዋወጡ ያልገለጹ ሲሆን ከቴህራን ወገንም የተሰማ ምላሽ የለም።

    “ኢራን ‘የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን’ ነግራናለች። የመሪዎቻቸውን ሁኔታ እስኪለዩ ድረስ (ያንን ማድረግ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ) በተቻለ ፍጥነት ‘የሆርሙዝ ውሽመጥን በተቻለ ፍጥነት እንድንከፍት’ ይፈልጋሉ” ብለዋል።

    ሮይተርስ ለዋይት ሐውስ በትራምፕ የማኅበራዊ ልጥፍ ዙሪያ ላቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አላገኘም።

    ትራምፕ ኢራን ለሁለት ወራት የቆየውን ጦርነት ለመፍታት ባቀረበችው አዲስ የመደራደሪያ ሃሳብ ደስተኛ አለመሆናቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

  2. የባሕረ ሰላጤው አገራት ለኢራን ጥቃቶች ስለሚሰጡት ምላሽ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሊወያዩ ነው

    የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገራት መሪዎች የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ሊሰበሰቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘገበ።

    የመሪዎቹ ስብሰባ የሚያተኩረው ሁለት ወር በሞላው ጦርነት ለዘነቡባቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የኢራን የሚሳዔል እና ድሮን ጥቃቶች ምላሽ ማዘጋጀት ላይ እንደሚሆን ዜና ወኪሉ ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

    በአሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት የተከፈተባት ኢራን በስድስቱም የባሕረ ሰላጤው ትብብር ምክር ቤት አባል አገራት የሚገኙ የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት እና ሌሎች የሲቪል መሠረተ ልማቶችን እንዲሁም ወታደራዊ ይዞታዎችንም አጥቅታለች።

    ሮይተርስ የጠቀሰው የሳዑዲ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለክተው የኳታር፣ ኩዌት እና ባህሬን መሪዎች እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በስብሰባው ለመሳተፍ ጅዳ ገብተዋል።

    የምክር ቤቱ አባል የሆነችው ኦማን በማን እንደምትወከል እስካሁን አለመታወቁም ተጠቅሷል።

    የባሕረ ሰላጤው ምክር ቤት ለጦርነቱ በቂ ምላሽ አልሰጠም በሚል ከኤምሬቶች ትችት ቀርቦበት ነበር።

  3. ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ቢፒ የኢራን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ ትርፉ በእጥፍ ማደጉን ገለጸ

    ግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ ቢፒ የኢራን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ ትርፉ ከእጥፍ በላይ ማደጉን አስታወቀ።

    ቢፒ በነዳጅ ንግድ ውስጥ "እጅግ በጣም ጥሩ" አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጾ ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ወራት ብቻ 3.2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።

    ይህ አሃዝ ተንታኞች ከጠበቁት በላይ መሆኑን የገለጸው ኩባንያው፣ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገበው 1.38 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ በእጥፍ እንደሚበልጥ ተናግሯል።

    ይህ ትርፍ የተመዘገበው አዲሷ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሜግ ኦኔል ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ በኋላ ነው።

    የካቲት 21/2018 ዓ.ም. የተጀመረው የኢራን ጦርነት የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

    ጦርነቱን ተከትሎ 20 በመቶ የሚሆነውን የዓለም የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት የሚያጓጓዝበት የሆርሙዝ ቁልፍ የባህር ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል።

    ብሬንት ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት በአሁኑ ወቅት በበርሜል 110 ዶላር እየተሸጠ ሲሆን፣ የኢራን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ዋጋው 73 ዶላር አካባቢ ነበር።

    ኦኔል "ኢንዱስትሪውን በግጭት እና ተግዳሮት በሞላበት ወቅት" ኩባንያውን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

    ቢፒ "ደንበኞች እና መንግሥታት በሚፈልጉበት ቦታ ነዳጅ እንዲያገኙ፣ በሰዎች ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን መስተጓጎል ለመቀነስ በመሥራት እየረዳ" እንደሆነ ተናግረዋል።

  4. የጀርመኑ ቻንስለር የኢራን አመራሮች አሜሪካን “እያሳፈሯት ነው” አሉ

    የጀርመኑ ቻንስለር ፍሬድሪክ መርዝ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር የኢራን አመራሮች አሜሪካ ወደ ፓኪስታን አምርታ ያለ ውጤት እንድትመለስ በማድረግ “አሳፍረዋታል” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘገበ።

    ቻንስለሩ ይህንን ያሉት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ይደረጋል ተብሎ የነበረው የሁለተኛ ዙር የሰላም ውይይት ሳይካሄድ ከቀረ በኋላ ነው።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል መርዝ አሜሪካ ከኢራን ጦርነት ለመውጣት ያዘጋጀችው ስልት መኖሩ እንደማይታያቸው መናገራቸውን ጨምሮ ገልጿል።

    በአሜሪካ እና በአውሮፓውያኑ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) አባል አገራት መካከል በኢራን ጦርነት ዙሪያ ልዩነት አለ።

    ቻንስለሩ ሰኞ ዕለት በመርስበርግ ከተማ ለተማሪዎች ንግግር ባደረጉበት ወቅት አሜሪካኖች ወደ ኢዝላምባድ እንዲጓዙ እና ያለ ምንም ውጤት እንዲመለሱ በማድረግ ረገድ "ኢራናውያን በመደራደር በጣም የተካኑ ናቸው፤ ወይም ባለመደራደር ክህሎት ያላቸው ናቸው" ብለዋል።

    “በኢራን አመራር ሙሉ ሕዝቡ [አሜሪካውያን] ነው እንዲያፍር የተደረገው፤ በተለይ የአበዮታዊ ዘብ በሚባለው። እናም ተስፋ የማደርገው በተቻለ ፍጥነት [ጦርነቱ] እንዲጠናቀቅ ነው” ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ አጋሮችን የሆርሙዝ ወሽመጥን ለማስከፈት የባሕር ኃይላቸውን ባለመላካቸው ተችተዋል። የኢራን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ወሽመጡ በመዘጋቱ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

  5. የሩሲያ ቅንጡ መርከብ እግድ በተጣለበት በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አለፈች

    ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቁልፍ አጋር ጋር ግንኙነት ያላት ቅንጡ መርከብ በአሜሪካ እና ኢራን እገዳ በተጣለበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል አለፈች።

    142 ሜትር የምትረዝመው እና ማዕቀብ ከተጣለበት ሩሲያዊው ቢሊየነር አሌክሲ ሞርዳሾቭ ጋር ግንኙነት ያላት መርከብ ከዱባይ ወደ ሙስካት በሳምንቱ መጨረሻ ተጉዛለች።

    ኖርድ የተሰኘችው ይህች ቅንጡ መርከብ ከቅርብ ወራት ወዲህ በወሽመጡ በኩል ካለፉ ጥቂት መርከቦች መካከል አንዷ ሆናለች።

    የኢራን ልዑካን በዚህ ሳምንት ወደ ሩሲያ በማቅናት ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ተወያይተዋል።

    አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ (ኤልኤንጂ) የሚያልፉት በዚህ የባሕር ወሽመጥ በኩል ነው።

    ከፑቲን ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ሞርዳሾቭ የቅንጦት ጀልባው ባለቤት መሆኑ በግልጽ አይታወቅም።

    ሆኖም ስለ ኖርድ የሰፈሩ መረጃዎች እአአ በ2022 በሚስቱ ባለቤትነት በተያዘ ድርጅት መመዝገቧን ያመለክታሉ።

    500 ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣ የተገመተችው ኖርድ፣ ከዱባይ የተነሳችው አርብ ዕለት ምሽት ነበር።

    ቅዳሜ ማለዳ በኦማን አል ሞኡጅ መድረሷ ተገልጿል። የሩሲያን ባንዲራ የምታውለበልበው ኖርድ የኢራን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ የግል መርከቦች ከአካባቢው ቢርቁም መርከቧ ግን በወሽመጡ ላይ ያለችግር መቅዘፍ ችላለች።

  6. ኢራን ባቀረበችው የድርድር ነጥብ ላይ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደስተኛ አለመሆናቸውን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናገሩ

    ለሁለት ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለመቋጨት ኢራን በቅርቡ ያቀረበችው የመደራደሪያ ነጥብ ዶናልድ ትራምፕን እንዳላስደሰታቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

    ይህም የኃይል አቅርቦትን ያስተጓጎለውን፣ የነዳጅ ዋጋን ያናረውን እና የሺዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ጦርነት ለማስቆም የነበረውን ተስፋ የሚያጨፈግግ ነው ተብሏል።

    ኢራን በቅርቡ ያቀረበችው የመደራደሪያ ነጥብ ጦርነቱ እስኪቆም ድረስ የኒውክሌር ድርድርን ወደ ጎን የተወ እና በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነጻ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እልባት የሚሰጥ ነው።

  7. የአሜሪካ ግምጫ ቤት ኃላፊ ከኢራን አየር መንገዶች ጋር ‘የሚተባበር ማዕቀብ ይጣልበታል’ አሉ

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሴንት ከኢራን አየር መንገዶች ጋር የሚተባበሩ ኩባንያዎች ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው አስጠነቀቁ።

    ኃላፊው በኤክሰ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ እርምጃ አገራቸው ኢራን ላይ የምታደርገው የምጣኔ ሃብት ጫና አካል መሆኑን ተናግረዋል።

    ቤስንት መንግሥታት በሥራቸው የሚገኙ ኩባንያዎች ለኢራን አውሮፕላኖች አገልግሎት ላለመስጠት አስፈላጊውን ጥንቀቄ እንዲያደርጉ አስጠንቅቀዋል።

    ቤሴንት መንግሥታት ለኢራን አውሮፕላኖች “ነዳጅ መቅዳት፣ የምግብ አቅርቦት አገልግሎት መስጠት እና የአውሮፕን ማሳረፊያ ክፍያዎች ወይም አውሮፕላን ጥገናዎችን” እንዳይሰጡ አስጠንቅዋል።

    የአገሪቱ ግምጃ ቤት “ከኢራን ጋር ንግድ በሚያካሄዱ ወይንም በሚያመቻቹ ሦስተኛ ወገኖች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አያመነታም” ብለዋል

    የኢራን አየር መንገዶች በሳምንቱ መጨረሻ ከጦርነቱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ መጀመራቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከቴህራን መንገደኞችን የጫኑ አውሮፕላኖች ወደ ኢስታንቡል፣ ኦማን፣ ኢረቅ፣ ኳታር እና ወደ ሳዑዲ ከተማ መዲና መብረራቸውን ዘግበዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ዋሸንግተን በኢራን መንግሥት ላይ “ጠናካራ የፋይናንስ ማነቆ” ማስቀመጧን ገልጿል።

    ቤሴንት በኤክስ ገጻቸው ላይ “ማዕቀብ ከተጣለባቸው አየር መንገዶች ጋር መስራት ለአሜሪካ ማዕቀብ ያጋልጣል” ሲሉ ጽፈዋል።

    የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣን የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት "የኢራንን እንቅስቃሴ ማቀላጠፍ በሚቀጥሉ" በውጭ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ እንደሚጥል ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት በተለይም የኢራንን የነዳጅ ኤክስፖርትና የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የተለያዩ ማዕቀቦችን ጥሏል።

  8. ቴህራን አሜሪካንን በዓለም አቀፍ ውሃ ላይ "የባህር ላይ ውንብድና" በመፈጸም ወነጀለች

    ኢራን በሕንድ ውቅያኖስ ስለተያዘባት ድፍድፍ ነዳጅ ጫኝ መርከብ በሰጠቸው ምላሽ ይህ “የባሕር ላይ ውንብድና ነው” አለች።

    አሜሪካ የኢራንን ነዳጅ የጫነች መርከብ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ በቁጥጥር ስር ያዋለችው ባለፈው ሳምንት ነበር።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ የአሜሪካን እርምጃ “የባሕር ላይ ውንብድና” ሲሉ በኤክሰ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    “ይህ ድርጊት በግልጽ የባሕር ላይ ውንብድናን ሕጋዊ ማድረግ ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ “በባሕሮች ላይ የሚፈጸም በትጥቅ የታገዘ ሽፍትነት ነው” ሲሉ አክለዋል።

    “ወደ ባሕር ላይ ውንብድና እንኳን በደህና መጣችሁ። አሁን ይህ የሚከናወነው ይፋዊ የመንግሥት ፈቃድ ባለው፣ በይፋ ባንዲራውን በሚያውለበልብ እና ወንጀሉን ‘ሕግ ማስከበር’ ሲል በሚጠራ አካል መሆኑ ነው” ሲሉ ቃል አቀባዩ የአሜሪካን እርምጃ ኮንነዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አክለውም “ዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ በሙሉ ለዚህ ሕገወጥ ባሕሪዋ ተጠያቂ መሆን አለባት” በማለት ድርጊቱ “የዓለም አቀፍ ሕጎች እና የዓለም ነጻ ንግድ መሠረቶችን የሚጥስ የባሕር ላይ ትራንስፖርት መርሆችን የሚንድ ነው” ብለውታል።

    ቃል አቀባዩ ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጄኒን ፌሪስ ፒሮ የነዳጅ ጫኝ መርከቧን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል መያዣ ማውጣታቸውን መግለጻቸውን ተከትሎ ነው።

    የአሜሪካ ጦር ባለፈው ሳምንት በሕንድ ውቅያኖስ ላይ 1.9 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የጫነች የኢራን መርከብን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቆ ነበር።

  9. ፑቲን ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት ማንኛውንም ነገር ታደርጋለች አሉ

    የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም ለማምጣት ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ መናገራቸውን ታስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር በሴንት ፒተርስበርግ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸው ወቅት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ለቴህራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢራን ሕዝቦች ለሉዓላዊነታቸው በድፍረት መታገላቸውን መናገራቸውን የሩሲያ ብሔራዊ የዜና ወኪል ታስ ዘግቧል።

    ታስ አክሎም ፑቲን ኢራን ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ካለፈች በኋላ ሰላም እንደምትፈልግ ያላቸውን ተስፋ መግለጣቸውን ጠቅሷል።

    የዜና ኤጀንሲው ፑቲን ለኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራጋቺ፣ ሩሲያ “በመካከለኛው ምሥራቅ በተቻለ ፍጥነት ሰላም ለማምጣት ማንኛውንም ነገር እንደምታደርግ” መናገራቸውን ዘግቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በሞስኮ እና በቴህራን መካከል ያለው ግንኙነት "እየተጠናከረ የሚሄድ" ስትራቴጂካዊ አጋርነት መሆኑን መናገራቸውን የሩሲያ የመንግሥት ቴሌቪዥን ዘግቧል።

    የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ለማነጋገር ወደ ሞስኮ የተጓዘው የኢራን ልዑካን ቡድን ውስጥ ምክትል የውጭጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ እና በሞስኮ የኢራን አምባሳደር ካዜም ጃላሊ ይገኙበታል።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሩሲያ ቴህራን እና ዋሺንግተን በሚያደርጉት ቀጣይ ድርድሮች "በሁለቱም ወገኖች ተቀባይነት ያለው የማደራደር አገልግሎት" ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

    “የተረጋገጠ ሰላም፤ በዘላቂነት የሚቆይ እና ወደ ግጭት ዳግም መመለስ የሌለበት ሰላምን ለማረጋገጥ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነን” ሲሉ መናገራቸውን መገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

    አራግቺ በሴንት ፒተርስበርግ ለጋዜጠኞች ኢራን “የዓለም ታላቅ ልዕለ ኃያል [ዩኤስ] በመፋለም ላይ ነች” በማለት ዋሽንግተን “አንድም ግቧን አላሳካችም” ብለዋል።

    "ለዚህም ነው ድርድር የጠየቁትና እየተመለከትን ያለነው" ሲሉም አክለዋል።

    አሜሪካ ግን ድርድር ስለመጠየቋ ምንም ያለችው ነገር የለም።

    የኢራን ከፍተኛ ዲፕሎማት ጦርነቱ ኢራን “እንደ ሩሲያ ያሉ ታላላቅ ወዳጆች እና አጋሮች እንዳሏት” ያሳየ ነው ብለዋል።

  10. የሊባኖስ ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁሙን በመጣስ ሄዝቦላህን ተቹ

    የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት “የሚያሳፍር ስምምነት” እንደማይቀበሉ ገለፁ።

    ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው ከድርድሩ መጀመርያው ጀምሮ ለአሜሪካ “የተኩስ አቁም አስፈላጊ የመጀመርያ እርምጃ” መሆኑን መናገራቸውን ገልጸዋል።

    አክለውም በደቡባዊ ሊባኖስ የሚኖሩ “የሌሎች ጦርነትን ዋጋ በግዛታችን ላይ እየከፈሉ ነው” ብለዋል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ የደረሱት የተኩስ አቁም በሦስት ሳምንት የተራዘመው ባለፈው ሳምንት ነው።

    ነገር ግን እስራኤል እና በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ የሚያደርጉት ውጊያ ቀጥለዋል።

    ሄዝቦላህ በቀጠናው ስላለው ሰላም በሚደረግ ድርድር ላይ አልተካተተም።

    ኦውን ጦርነቱ የተካሄደው “ለሊባኖስ ተብሎ ቢሆን” እደግፈው ነበር፤ ነገር ግን “ጦርነቱ የሚካሄደው የሌሎችን ፍላጎት ለማሳካት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደርገዋለሁ” ብለዋል።

    “እኛ እያደረግን ያለነው የአገር ክህደት አይደለም፤ ይልቁንም የአገር ክህደት የሚፈጸመው የውጭ ጥቅሞችን ለማስከበር አገራቸውን ወደ ጦርነት በወሰዱት ነው” ሲሉ ሄዝቦላህን ሸንቁጠዋል።

    በደቡባዊ ሊባኖስ የእስራኤል የአየር ድብደባ እንደቀጠለ ነው። እሁድ ዕለት ብቻ በእስራኤል የአየር ድብደባ 14 ሰዎች ሲገደሉ ሁለት ሕጻናት እና ሁለት ሴቶችን ጨምሮ 37 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የአገሪቱ ጦር ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ “የሄዝቦላህ ዒላማዎችን በኃይለኛው እንዲያጠቁ” ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በዚሁ ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።

  11. የኢራን ባለሥልጣናት በጦርነቱ የፈራረሱ ሕንጻዎችን ለመጽዳት 200,000 መኪናዎች ያስፈልጋሉ አሉ

    የኢራን አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በጦርነት ምክንያት የፈራረሱ የመኖሪያ ሕንጻዎችን ለማጽዳት “200 ሺህ የጭነት መኪናዎች” ያስፈልጋሉ አለ።

    የአካባቢ ጥበቃ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቡ አሊ ጎልዛሪ እስራኤል እና አሜሪካ በፈጸሙት የአየር ድብደባ “በሺህዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ሕንጻዎች ወድመዋል፤ እንዲሁም 10 ሚሊዮን ቶን ፍርስራሾች ተቆልለዋል። በተጨማሪም ይህንን ፍርስራሽ ለማንሳት ወደ 200,000 የጭነት መኪናዎች እንፈልጋለን” ብለዋል።

    ጎልዛሪ አክለውም “በኢራን ውሃ፣ አፈር፣ አየር እና የብክለት አስተዳደርን ጨምሮ ከባድ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ቀውስ ገጥሞናል። እነዚህ ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት የተባባሱ ናቸው” ብለዋል።

  12. ክሬምሊን ከኢራን ጋር የሚደረገው ውይይት በጣም ጠቃሚ መሆኑን ገለጸች

    የሩሲያው ፕሬዚዳንት ከኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አባስ አጋራቺ ጋር ዛሬ በሴንት ፒተስበርግ እንደሚገናኙ ክሬምሊን አስታወቀ።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለመንግሥት የዜና ወኪል ታስ እንደተናገሩት "ይህ ውይይት በጣም አስፈላጊ መሆኑን በኢራን እና በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ሁኔታ እንዴት እየጎለበተ ነው የሚለውን በመመልከት መናገር ይቻላል" ብለዋል።

    አራጋቺ አገራቸው ጦርነቱን ይቋጫል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ንግግር ከአሜሪካ ጋር ማድረግ ሳትችል ከቀረች በኋላ ወቅት ሰኞ ማለዳ ሩሲያ ደርሰዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን የሚያደርጉት ሁለተኛው ዙር የሰላም ንግግር ቅዳሜ ዕለት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ልዑካኖቻቸው ወደ ኢዝላማባድ እንዳይሄዱ ካደረጉ በኋላ ባለበት ቆሟል።

  13. ኦማን ከቴህራን ጋር በሆርሙዝ ላይ ባላቸው “የጋራ” ኃላፊነት ላይ መነጋገራቸውን አስታወቀች

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ሩሲያ ከማምራታቸው በፊት እሁድ ዕለት ኦማን ደርሰው ከአገሪቱ መሪ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መወያየታቸው ታውቋል።

    የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አልቡሳይዲ በኤክስ ገጻቸው ላይ ከአባስ አረጋቺ ጋር በሆርሙዝ ወሽመጥ ዙሪያ “ጥሩ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    አክለውም ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በወሽመጡ ላይ “ለዓለም አቀፉ ማኅበረስብ ስለሚኖር የጋራ ኃላፊነት እንዲሁም ለረዥም ጊዜ መንቀሳቀሻ አጥተው ለተቀመጡ ባህረተኞች ስለሚያስፈልግ አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ” መነጋራቸውን አስታውቀዋል።

    የኢራን ከፍተኛ ዲፕሎማት “ኦማን በክብር ተቀብላ ስላስተናገደችኝ” በማለት አመስግነዋል።

    አራጋቺ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ንግግራቸው ቁልፍ በሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ የመርከቦች እንቅስቃሴ “ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን” መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

  14. ወደ ሩሲያ የተጓዙት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድርድሩ ላለመሳካቱ አሜሪካ ያቀረበቻቸውን ጥያቄዎች ወቀሱ

    ወደ ሩሲያ ያመሩት የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በፓኪስታን ሲደረግ የነበረው የሰላም ድርድር ያልተሳካው አሜሪካ ባቀረበቻቸው ከልክ ያለፉ ጥያቄዎች ምክንያት ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃን ተናገሩ።

    በሩሲያዋ ሴንት ፒተርስፐርግ ከተማ ያረፉት አራግቺ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚደረገውን ጦርነት በተመለከተ ከሩሲያ አጋሮች ጋር እንደሚነጋገሩ በፐርሺያ ቋንቋ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል።

    ከሩሲያ በፊት ወደ ፓኪስታን አቅንተው የነበሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢስላማባድ የነበራቸው ቆይታ በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ድርድሩ ሊቀጥል ይችላል የሚለው ላይ ያተኮረ እንደነበር አስረድተዋል።

    አራግቺ በቃለ መጠይቃቸው በኢራን ስለተዘጋው የሆርሙዝ ወሽመጥ አንስተዋል። በወሳኙ የባሕር መስመር በኩል ደኅንነቱ የተጠበቀ ጉዞ ማድረግ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን የጠቀሱት ጠቅሰዋል።

    እንደ ኦማን ያሉ ጎረቤት አገራት ወሽመጡን በተመለከተ ከኢራን ጋር ባላቸው የጋራ ፍላጎት ላይ እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

    ኢራን እና ኦማንን የሚያስማሙ በርካታ ነጥቦች መኖራቸውን ጠቁመውም፤ ሁለቱ አገራት ሆርሙዝን በተመለከተ ተጨማሪ ንግግር ለማድረግ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ተናግረዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሩሲያ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል።

    የፓኪስታን ቆይታቸውን “እጅግ ውጤታማ” ሲሉ የገለጹት አራግቺ፤ “ኢራን ላይ የተከፈተውን ጦርነት በዘላቂነት ለመቋጨት የሚያስችል ማዕቀፍን በተመለከተ የኢራንን አቋም” ማሳወቃቸውን ጠቅሰዋል።

    “እውነትም አሜሪካ ዲፕሎማሲን በቁም ነገር ትወስደው እንደሆነ እናያለን” ሲሉ ቅዳሜ ዕለት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ኢራን መደራደር ከፈለገች በስልክ መነጋገር እንደሚቻል እና ልዑካኖቻቸውን ወደ ፓኪስታን እንደማይልኩ ተናግረዋል።

  15. “መቼ ወደ ቤታቸው እንደሚመለሱ እርግጠኛ አይደሉም” - በሆርሙዝ መውጫ ያጡት ባሕርተኞች

    የነዳጅ ጫኝ መርከብ ኩባንያዎች ማኅበር መረጃ እንደሚያመለክተው በሺህዎች የሚቆጠሩ ባሕርተኞች እና ከ105 በላይ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ምክንያት መንቀሳቀስ አልቻሉም።

    ኢራን ከዓለም ነዳጅ እና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ 20 በመቶው በሚጓጓዝበት ይህ የባሕር መስመር አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት “ግልጽ የተኩስ አቁም ጥሰት” ምክንያት እንደማይከፈት አስታውቃለች።

    ከቢቢሲ ‘ቱዴይ’ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት ‘ኢንተርታንኮ’ የተሰኘው የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ማኅበር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቲም ዊልኪንስ፤ የወሽመጡ መዘጋት በኢራን ባሕር ዳርቻ መንቀሳቀሻ ያጡ ባሕርተኞች ላይ ያደረሰውን ተጽዕኖ አስረድተዋል።

    ዊልኪንስ እንደሚናገሩት፤ የመርከብ ሠራተኞች እንደ ምግብ፣ ውሃ ማቅረብ እንዲሁም ቆሻሻዎችን እንደማስወገድ ያሉ መሠረታዊ ተግባራት የማስተዳደር ኃላፊነት ስላለባቸው “ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት፣ ውጥረት እና መታከት” ተፈጥሮባቸዋል።

    “ብዙዎቹ መቼ መመለስ እንደሚችሉ ምንም እርግጠኝነት ሳይኖራቸው መርከብ ላይ መውጫ አጥተዋል” ብለዋል።

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስም አሁንም በቀጣናው ግጭቶች ቀጥለዋል።

    ባለፈው ሳምንት ኢራን ሁለት በወሽመጡ ሊያልፉ የነበሩ የጭነት መርከቦች “ለምርመራ” መያዟን ገልጻለች። በወሽመጡ ለማለፍ የሞከሩ ሌሎች መርከቦችም ጥቃት እንደተከፈተባቸው ተዘግቧል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎችን ያገደችው አሜሪካም በርካታ መርከቦችን ጠልፋለች።

  16. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራት ግብዣው ላይ ተኩስ ሲከፈት “አልሰጋሁም ነበር” አሉ

    ቅዳሜ ምሽት ሲካሄድ በነበረው የጋዜጠኞች ራት ግብዣ ላይ የተከፈተው ተኩስ ፕሬዝዳንቱን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልታናትን ዒላማ በማድረግ እንደሆነ ቢታመንም ዶናልድ ትራምፕ በወቅቱ “ሰግተው እንዳልነበረ” ተናግረዋል።

    ትራምፕ ከሲቢኤስ ኒውስ ’60 ሚኒትስ’ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ “አልሰጋሁም ነበር። ሕይወትን እረዳለሁ። የምንኖረው ያበደ ዓለም ውስጥ ነው” ብለዋል።

    የዋይት ሀውስ ዘጋቢ ጋዜጠኞች ራት ግብዣ ላይ የተፈጠረው ክስተት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ እንደተቃጣ ሦስተኛ የግድያ ሙከራ ተወስዷል። ሐምሌ 2016 ዓ.ም. ፔንስልቬኒያ ውስጥ የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ሰዓት እንዲሁም ባለፈው መስከረም ላይ በጎልፍ ክለባቸው ውስጥ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጄዲ ቫንስ በመጀመሪያ እንዲወጡ የተደረገበት የቅዳሜው ጥቃት እንዴት እንደተከሰተ ትራምፕ ተጠይቀዋል። ፕሬዝዳንቱ የሴክሬት ሰርቪስ አባላት ከክፍሉ እንዲያስወጧቸው ሁኔታዎች “ቀላል እንዳላደረጉ” በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል።

    “ምን እንደተፈጠረ መመልከት ፈልጌ ነበር… ምን እየተካሄደ መሆኑን ማየት ፈልጌ ነበር። ሁኔታውን በተገነዘብኩበት ሰዓት፤ ምናልባትም መጥፎ ሁኔታ ነበር” ብለዋል።

    ከክፍሉ ሲወጡ “እንዲያጎነብሱ” ስለመደረጉ የተነሳላቸው ትራምፕ፤ “[ከደኅንነት አባላት ጋር] መራመድ ጀመርኩ። ዞርኩ፣ መራመድ ጀመርኩ፤ ከዚያም ‘እባክህ አጎንብስ፣ እባክህ ወደ ወለሉ አጎንብስ’ አሉኝ” በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።

    “ስለዚህ አጎነበስኩ፤ ቀዳማዊት እመቤቷም አጎነበሰች” ሲሉም አክለዋል።

    በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ከተጠርጣሪው ኮል አለን ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚታመን በእጅ የተጻፈ ሰነድን ተመልክቷል። ሰነዱ፤ “ከከፍተኛ ደረጃ እስከ ታች” ያሉ የትራምፕ አስተዳደር አባላትን ዒላማ ማድረግ እንደሚፈልግ ያሳያል።

    ጽሑፉ ላይ “የህጻናት ወሲብ ጥቃት ፈጻሚ፣ ደፋሪ እና ከሃዲ” በሚል ስለሰፈሩት አገላለጾች በቃለ መጠይቁ በተነሳበት ወቅት በትራምፕ እና በጋዜጠኛዋ ኖራህ ኦ’ዶኔል መካከል ውጥረት ተስተውሎ ነበር።

    ጋዜጠኛዋ ስለ እነዚህ አገላለጾች በመጠየቋ “ወራዳ” ሲሉ ጠርተዋታል። “ይህንን በማንበብሽ ልታፍሪ ይገባል፤ ምክንያቱም እኔ ከእነዚህ ነገሮች አንዱንም አይደለሁም” ብለዋል።

  17. ኢራን ሆርሙዝ እንዲከፈት እና የኒውክሌር ንግግር እንዲዘገይ የሚጠይቅ እቅድ ለአሜሪካ ማቅረቧ ተዘገበ

    ኢራን የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲከፈት እና ጦርነቱ እንዲቋጭ፤ የኒውክሌር ጉዳይ ግን በስምምነቱ ቀጣይ ደረጃ ንግግር እንዲደረግበት የሚጠይቅ የሰላም እቅድ ማቅረቧን የአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ዘገበ።

    አክሲዮስ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣንን እና ከጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን ጠቅሶ ያወጣው ዘገባ እንደሚያስረዳው፤ ኢራን እቅዱን ያቀረበችው በአሸማጋይዋ ፓኪስታን በኩል ነው።

    እቅዱ በዋነኛነት የሚያተኩረው ከሁሉም በፊት በሆርሙዝ ወሽመጥ እና አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ በጣለችው እገዳ ምክንያት ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሔ ማበጀት ላይ ነው።

    በዚህም መሠረት የተኩስ አቁሙ ለረጅም ጊዜ እንዲራዘም ወይም ሁለቱ አገራት በቋሚነት ጦርነት ለማቆም እንዲስማሙ የሚጠይቅ ሀሳብ እቅዱ ውስጥ መካተቱን ዘገባው ጠቅሷል።

    በኢራን እቅድ መሠረት የኒውክሌር ድርድር የሚጀመረው የሆርሙዝ ወሽመጥ ከተከፈተ እና የአሜሪካ እገድ ከተነሳ በኋላ ነው።

    ዋይት ሀውስ የኢራን እቅድ የደረሰው ሲሆን የትራምፕ አስተዳደር የኢራንን እቅድ ይመለከተው እንደሆነ አለመታወቁን አክሲዮስ ዘገቧል።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ፓኪስታን ሲጓዙ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገው ንግግር በድጋሚ ይጀምራል የሚል ተስፋን ጭሮ ነበር። አራግቺ እንደተጠበቀው ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ባይነጋገሩም ስለ ሰላም ድርድር ማንሳታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

    አክሲዮስ እንዳስነበበው ከሆነ፤ አራግቺ በኢስላማባድ ቆይታቸው የኒውክሌር ጉዳይን ወደ ጎን የማድረግ ሀሳብን አንስተዋል።

    አክሲዮስ ያነጋገራቸው አንድ ምንጭ የአሜሪካ ጥያቄ የሚመለስበትን መንገድ በተመለከተ በኢራን አመራር መካከል ስምምነት አለመኖሩን አራግቺ ለፓኪስታን፣ ግብጽ፣ ቱርክ እና ኳታር አሸማጋዮች መናገራቸው ገልጸዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ከኢራን ጋር ለሚደረግ ድርድር ልዑካኖቻቸውን እንደማይልኩ እና በስልክ ንግግር ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።

  18. እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት 14 ሰዎች ተገደሉ

    እስራኤል እሁድ ዕለት ሊባኖስ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት 14 ሰዎች ሲገደሉ፤ ሁለት ሕጻናት እና ሁለት ሴቶችን ጨምሮ 37 ሰዎች መጎዳታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

    የደረሰው ጉዳት ከመገለጹ አስቀድሞ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ በተለያዩ የደቡባዊ ሊባኖስ መንደሮች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲጡ አስጠንቅቀው ነበር።

    ነዋሪዎች በአፋጣኝ “መውጣት እንዳለባቸው” የሚያስጠነቅቅ መልዕክት የጻፈው ጦሩ፤ እዚያው መቆየት “ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥለው” ገልጿል።

    የእስራኤል ጦር ከቆይታ በኋላ የሄዝቦላህ ወታደሮች እና “የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ወታደሮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም” ይውላሉ ያላቸው የደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራዎችን “በከባድ መሣሪያ እና የአየር ጥቃት” መምታቱን አስታውቋል።

    ሄዝቦላህ በፈጸመው ጥቃት የ19 ዓመት የእስራኤል ወታደር መገደሉን እና ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውንም ገልጿል።

    እስራኤል እና ሊባኖስ ለሦስት ሳምንት የሚቆይ ተኩስ አቁም ተግባራዊ እንዲሆን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት መስማማታቸው ይታወሳል።

    ይህ ስምምነት “በየትኛውም ጊዜ ራሷን ከታቀደ፣ አይቀሬ እና ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ በሙሉ የመውሰድ መብትን” ለእስራኤል ሰጥቷል።

    ተኩስ አቁሙ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንስቶ እስራኤል እና ሄዝቦላህ አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን በመጣስ ከስሰዋል።

    14 ሰዎችን ከገደለውን ጥቃት አስቀድሞ ቅዳሜ ዕለትም የእስራኤል ጦር የሄዝቦላህ “ወታደራዊ ይዞታዎች” ባላቸው ስፍራዎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

    ጦሩ ይህንን ጥቃት የፈጸመው በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ሁለት ፈንጂ የተሸከሙ ድሮኖችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል በሚል ነው።

    ቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የአገሪቱ ጦር ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ “የሄዝቦላህ ዒላማዎችን በኃይለኛው እንዲያጠቁ” ትዕዛዝ ሰጥተዋል። በዚሁ ዕለት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ በተፈጸሙ ጥቃቶች ስድስት ሰዎች ተገድለዋል።

  19. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኢራን ጋር በስልክ መነጋገር እንደሚመርጡ እና ተደራዳሪዎቻቸውን እንደማይልኩ ተናገሩ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ሁለት ወር ሊደፍን የተቃረበውን ጦርነት የሚቋጭ ድርድር ማድረግ የምትፈልግ ከሆነ በስልክ መነጋገር እንችላን አሉ።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ “መነጋገር ከፈለጉ፤ ማውራት እንችላለን። ሰዎችን ግን አንልክም” ብለዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ይህንን የተናገሩት አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረግ ጉዞ ላይ እንደጣለችው ገደብ ያሉ የስምምነት እንቅፋቶች እንዲወገዱ ከጠየቀች በኋላ ነው።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት ተደራዳሪዎቻቸው ስቲቭ ዋትኮፍ እና ጃሬድ ኩሽነርን ወደ ፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ እንደሚልኩ ከተናገሩ በኋላ ሁለቱ አገራት በድጋሚ ድርድር ይጀምራሉ የሚል ተስፋ ጭሮ ነበር።

    አርብ ዕለት ፓኪስታን ገብተው የነበሩት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ ግን የአሜሪካኑ ልዑካን ከመድረሳቸው አስቀድሞ ወደ ኦማን ተጉዘዋል።

    ትናንት እሁድ ለአጭር ቆይታ ተመልሰው ወደ ፓኪስታን ተጉዘው የነበረ ቢሆንም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተደራዳሪዎቻቸውን የመላክ እቅዳቸውን አስቀድመው ሰርዘዋል።

    አራግቺ ከፓኪስታን ወጥተው ወደ ሩሲያ አምርተዋል። በዚያም ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ይጠበቃል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከዚህ ቀደም ኢራን እና አሜሪካን ስታደራድር ወደ ነበረችው ኦማን ባደረጉት ቆይታ ስለ ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ሆርሙዝ እንደተነጋገሩ ተገልጿል።

    ትራምፕ በፎክስ ቃለ መጠይቃቸው “መነጋገር ከፈለጉ ወደ እኛ መምጣት ወይም ሊደውሉልን ይችላሉ። ታውቃለህ፤ ቴሌፎን አለ። ጥሩ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ መስመር አለን” ሲሉ በድጋሚ ልዑካን እንደማይልኩ ጠቁመዋል።

    አክለውም፤ “ስምምነቱ ውስጥ ምን መኖር እንዳለበት ያውቃሉ። በጣም ቀላል ነው፤ የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራቸው አይችልም። ይህ ካልሆነ የምንገናኝበት ምክንያት አይኖርም” ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ከቆይታ በኋላ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ “ማድረግ ያለባቸው መደወል ነው” በማለት ጽፈዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት የፓኪስታን የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች በቴህራን እና ዋሽንግተን መካከል የተኩስ አቁም እንዲፈረም እየጣሩ ባሉበት ወቅት ነው።

    የዜና ወኪሉ አሶሺዬትድ ፕሬስ ያነጋገራቸው አንድ የፓኪስታን ባለሥልጣን ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮች መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት እንዲቆይ የተስማሙት ተኩስ አቁም ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ቢጠናቀቀም፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላልተወሰነ ጊዜ አራዝመውታል። ይህም የካቲት ላይ የተጀመረው ውጊያ እንዲገታ አድርጓል።

    በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት እና የዓለምን ኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ የከተተውን ጦርነት በዘላቂነት የሚቋጭ መፍትሔ ላይ ግን እስካሁን አልተደረሰም።