“እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር የተለያዩ የወደብ መዳረሻዎች ያስፈልጉታል”- ጠ/ሚ ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ተሰብሳቢዎች ባደረጉት ንግግር ላይ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላለው እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የተለያዩ የወደብ መዳረሻዎች ያስፍለጉታል አሉ።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል ጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት 11 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    እስራኤል ዛሬ እሁድ ጠዋት በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት 11 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የፍልስጤም ሲቪል መከላከያ እና የጤና ባለስልጣናት ገለጹ።

    የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማህበር እንደገለጸው በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኝ የድንኳን መጠለያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ቢያንስ ስድስት ሰዎች ተገድለዋል። በደቡባዊ ጋዛ በደረሰ ሌላ ጥቃት ደግሞ አምስት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ ጥቃቱ የተፈጸመው ሐማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣሱ እንደሆነ ገልጿል። ከዋሻ ውስጥ ወጥተው የእስራኤል ጦር በሚቆጣጠረው የጋዛ ሰርጥ አካባቢ የተገኙ ታጣቂዎች በጥቃቱ መገደላቸውንም ተናግሯል።

    እስራኤል እና ሐማስ የተፈራረሙት የተኩስ አቁም ስምምነት በጥቅምት መጀመሪያ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንስቶ አንዳቸው ሌላኛቸውን ስምምነቱን በመጣስ ሲከስሱ ቆይተዋል።

    የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከጀመረ ወዲህ ቢያንስ 600 ሰዎች በእስራኤል ተገድለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 32 ያህሉ የተገደሉት እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት በፈጸመቻቸው ተከታታይ የአየር ጥቃቶች ነው።

    እስራኤል የዛሬውን ጥቃት የፈጸመችው በአሜሪካ አደራዳሪነት የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ሁለተኛ ምዕራፍ ትግበራ ሊጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተል የሰላም ቦርድ ባለፈው ወር ማቋቋማቸው ይታወሳል።

    በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት ስልጣን የተሰጠው ይህ ቦርድ፤ በጋዛ የድንበር አካባቢዎችን የሚጠብቅ ዓለም አቀፍ ኃይል የማቋቋም ኃላፊነት ተጥሎበታል። የሃማስን ትጥቅ የመፍታት ሂደት የመቆጣጠር ሥልጣንም አለው።

    ቦርዱ የመጀመሪያ ስብሰባውን በሚቀጥለው ሳምንት ዋሽንግተን ውስጥ እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን በባለሙያዎች የሚመራ ፍልስጤም መንግስት ምስረታን እንዲሁም የጋዛ የመልሶ ግንባታ ሥራን ይቆጣጠራል።

  2. የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ራሱን ለማቃጠል የሞከረን መምህር ማትረፉን ገለጸ

    በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የታርጫ ከተማ ፖሊስ ሰውነቱ ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ ራሱን ያቃጠለ መምህርን በነዋሪዎች ጥቆማ ደርሶ ማትረፉን አስታወቀ። የግል ትምህርት ቤት መምህር ነው የተባለው ግለሰብ፤ ሕክምና ላይ እንደሚገኝ የከተማው ፖሊስ ገልጿል።

    የዳውሮ ዞን ማዕከል የሆነችው ታርጫ ከተማ ፖሊስ ዛሬ እሁድ የካትቲ 8/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ግለሰቡ ራሱን ለማጥፋት የሞከረው አርብ ዕለት ረፋድ አራት ሰዓት ገደማ ነው። “ግለሰቡ አንድ ሊትር ቤንዝን ከነጋዴ በመግዛት ሰውነቱ ላይ እንዳርከፈከፈ” የፖሊስ መግለጫ ያስረዳል።

    ቀጥሎም “በኪሱ ይዞት የነበረውን ክብሪት በመጫር በለበሰው ልብስ ላይ በመለኮስ ሰውነቱን በእሳት ማያያዙን" የታርጫ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ገልጿል። ይህን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች “የድረሱልን ጥሪ” ማሰማታቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ በሥፍራው ሥራ ላይ የነበሩ የትራፊክ ፖሊስ አባላት መድረሳቸውን ተናግሯል።

    የከተማው ፖሊስ፤ “ከአካባቢው ሰዎች ጋር በመተባበር በግለሰቡ ሰውነት ላይ የነበረውን እሳት በማጥፋት በፍጥነት ታርጫ ጠቅላላ ሆስፒታል በማስገባት የሕክምና እርዳታ እንዲያገኝ [ተደርጓል]” ብሏል። የግለሰቡ ሕይወት እንደተረፈ እና በአሁኑ ሰዓትም ሕክምና ላይ እንደሚገኝ አክሏል።

    በ7ኛ ቀን አድቬንቲስት ትምህርት ቤት መምህር የሆነው ግለሰብ ራሱን ለማቃጠል የሞከረው “ከግል ሕይወቱ እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች” ምክንያት እንደሆነ መናገሩን ፖሊስ ገልጿል።

    ግለሰቡ የመንግሥት ተቀጣሪ እንዳልሆነ በመጥቀስም “ምንም ዓይነት ከመንግሥት መዋቀር ጋር የሚያገናኝ ነገር እንደሌለ እና በየትኛውም የመንግሥት መዋቀር የደረሰበት የመልካም አስተዳደር በደል” አለመኖሩን አረጋግጫለሁ ብሏል።

    መምህሩ “የመልካም አስተዳደር በደል እንደደረሰበት በማስመሰል” ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጨው መረጃም “ከእውነት የራቀ ውሸት” ነው ሲል አስተባብሏል።

  3. ጋና ከሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙነት በምሥጢር ቀርጿል የተባለው ሩሲያዊ ተላልፎ እንዲሰጣት ጠየቀች

    ጋና ከበርካታ ሴቶች ጋር የነበረውን ወሲባዊ ግንኙነት በሕገ ወጥ መንገድ ቀርጾ ያለፈቃዳቸው ኢንተርኔት ላይ ለቅቋል የተባለው ሩሲያዊ ግለሰብ ተላልፎ እንዲሰጣት ጠየቀች።

    የአፍሪካ እና የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ይህ ራሱን “የጠበሳ (ፒክ አፕ) አርቲስት” ብሎ የሚጠራው ግለሰብ ዕድሜው በ30ዎቹ ውስጥ ነው።

    ሩሲያዊው የኦንላይን ይዘት ፈጣሪ፤ ወደ ጋና ተጉዞ ከሴቶች ጋር የነበረውን ግንኙት በምሥጢር እንደቀረጻ ዘገባዎቹ ገልጸዋል።

    እንደ መገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ ግለሰቡ ሴቶቹን ሲቀርጽ የነበረው ካሜራ የተገጠመለት መነጽር በማድረግ ሲሆን ኋላ ላይም ቪዲዮዎቹን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለቅቋል። የአገሪቱ ባለሥልጣናት ግን ቪዲዮው በዚህ መንገድ ስለመቀረጹ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም።

    ይኸው ግለሰብ ኬንያ ውስጥም ተመሳሳይ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን እንደፈጸመ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

    የጋና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሳም ጆርጅ ቅዳሜ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ተፈጽሟል ስለተባለው ድርጊት ለመነጋገር የሩሲያ አምባሳደርን መጋበዛቸውን ተናግረዋል።

    አንድ የጋና ባለሥልጣን በበኩላቸው፤ መንግሥት ያደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ተጠርጣሪው አገሪቱን ለቅቆ ወጥቶ ሊሆን እንደሚችል ማመላከቱን ገልጸዋል።

    ይህም ቢሆን ግን “ተፈጽሟል የተባለውን ድርጊት አሳሳቢነት ወይም መንግሥት ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተጣለበትን ኃላፊነቱን አይቀንሰውም" ብለዋል።

    የቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ጆርጅ፤ ተጎጂዎች ፍትሕ እንዲያገኙ የሚደረገው ጥረት ላይ ሞስኮ እንድትተባበር በጋና ዋና ከተማ አክራ ለሚገኙት የሩሲያ አምባሳደር ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

    ሚኒስትሩ ይህንን ቢሉም ሩሲያ እጅግ ከባድ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ካልሆነ በቀር ዜጎቿን አሳልፋ አትሰጥም።

    “ጋና ውስጥ የሚገኙትን አምባሳደር ለስብሰባ ጋብዣቸዋለሁ” ሲሉ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል። “የሩሲያዊው ዜጋ ድርጊት የሳይበር ደኅንነት ሕጋችንን የሚጥስ ነው። ይፋዊ አቋማችንን ለአምባሳደሩ እገልጻለሁ” ብለዋል።

    ይህንን ለቢቢሲ ከመናገራቸው አስቀድሞ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ “ግለሰቡን እያፈላለግን ነው፤ ያለንን አቅም በሙሉ ተጠቅመን ከኢንተርፖል ጋር በንቃት እንሠራለን” በማለት ተናግረው ነበር።

    “የሩሲያ ባለሥልጣናት ከሕግ አስከባሪዎቻችን ጋር እንዲሠሩ እንጠይቃለን፤ የሩሲያውን አምባሳደር የጠራሁትም ለዚሁ ነው” ብለዋል። ግለሰቡ ለጋና ተላልፎ ተሰጥቶ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድበት እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።

    ተጠርጣሪው ወደ ጋና የማይመለስ ከሆነ በሌለበት እንደሚፈረድበት የቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። በጋና ሕግ መሠረት የሕጻናትን ወይም ሙሉ ፈቃድ ሳያገኝ የአዋቂ ሰዎችን ልቅ ምሥሎች የለቀቀ ሰው እስከ 25 ዓመት በሚደርስ እስራት ይቀጣል።

  4. በአሜሪካ ድጋፍ ጊኒ ቢሳው ውስጥ ሊካሄድ የነበረ የጨቅላዎች ክትባት ሙከራ ውግዘት ደረሰበት

    በጊኒ ቢሳው ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው እና አሜሪካ በገንዘብ የደገፈችው የሄፕታይተስ ቢ ክትባት ሙከራ “ከሙያዊ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ነው” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አወገዘ።

    በሺዎች የሚቆጠሩ ጨቅላዎች ላይ የክትባት ሙከራው ሊካሄድ ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ተሰርዟል።

    ከአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ያገኘው የክትባት ሙከራ ጨቅላዎች ሲወለዱ እና ከተወለዱ ለስድስት ሳምንታት በኋላ የሚሰጥ ነበር።

    የዓለም ጤና ድርጅቱ “ዕቅዱ እጅግ አስጊ ነው” ብሏል። ጨቅላዎች እንደተወለዱ ክትባት መስጠት “ጉልህ የኅብረተሰብ ጤና ቀውስ እንደሚያመጣ የተረጋገጠ ነው” ሲልም ተችቷል።

    በሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ጁንየር የሚመራው የአሜሪካ የጤና ቢሮ ክትባቶች ላይ ጥያቄ ሲያስተጋባ ቆይቷል።

    በጊኒ ቢሳው ታቅዶ የነበረው ሙከራ፤ ክትባት ጤና ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ለመረዳት ያለመ ነበር ተብሏል።

    የዓለም ጤና ድርጅት ግን ሙከራው ላይ ሳይንሳዊ እና የሙያዊ ሥነ ምግባር ጥያቄ አንስቷል።

    በሰዎች ላይ የሚደረግ የክትባት ሙከራን በተመለከተ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን እንደሚጻረርም ጠቅሷል።

    ጨቅላዎች ሕይወታቸውን ከሚያድን መድኃኒት ውጭ ከወሰዱ “ሊቀለበስ የማይችል ጉዳት” እንደሚደርስባቸው የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

    ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጊኒ ቢሳው ዜጎች በሄፕታይተስ ቢ ተይዘዋል። በሙከራ የተረጋገጡ ክትባቶችን ጨቅላዎች ሲወስዱ በሽታው ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድሉ ከ70% እስከ 95% እንደሚወርድ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

    ሆኖም ግን ክትባት ላይ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ሙከራ የሚሠራው ውጤታማነታቸው ላልታወቀ የክትባት ዓይነቶች እንደሆነ አስረድቷል። የሄፕታይተስ ቢ ክትባት ሙከራ የተደረገበት መሆኑን በመጥቀስም በጊኒ ቢሳው የታቀደውን ሙከራ ኮንኗል።

    አሁን ላይ በጊኒ ቢሳው ስድስት ሳምንት የሞላቸው ልጆች ክትባት የሚሰጣቸው ሲሆን የአገሪቱ መንግሥት ከሁለት ዓመት በኋላ ለጨቅላ ልጆች ክትባቱን የመስጠት ዕቅድ ይዟል።

  5. የመጨረሻው የኢራን ንጉሥ ልጅ አሜሪካ በኢራን ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ አሳሰቡ

    የኢራን መንግሥት ተቃዋሚ የሆኑት ረዛ ፓህላቪ፤ አሜሪካ ቴህራን ውስጥ እርምጃ ብትወስድ የብዙ ኢራናውያንን ሕይወት ልትታደግ ትችላለች አሉ።

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የኒውክሌር ስምምነት ላይ ለመድረስ ከኢራን እስላማዊ መንግሥት አመራሮች ጋር የሚያደርገው ድርድር ላይ ረዥም ጊዜ እንዳያባክንም አሳስበዋል።

    ከሥልጣናቸው የተፈነቀሉት የመጨረሻው የኢራን ሻህ ልጅ የሆኑት እና በስደት የሚኖሩት ፓህላቪ ይህንን ያሉት ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው።

    አባታቸው በአውሮፓውያኑ 1971 ኢስላማዊ አብዮት ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ከአገር የሸሹት ፓህላቪ ኑሯቸውን በአሜሪካ አድርገዋል።

    የኢራን መንግሥት እንዳይሳተፍ ከተከለከለበት የሙኒክ የጸጥታ ኮንፈረንስ ጎን ለዜና ወኪሉ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ኢስላማዊው መንግሥት ለመውደቅ ጫፍ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ ምልክቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።

    አሜሪካ የምትፈጽመው ጥቃት መንግሥቱን ሊያዳክመው ወይም ውድቀቱን ሊያፋጥነው እንደሚችልም ገልጸዋል።

    “የጊዜ ጉዳይ ነው። ይህ ጥቃት ሂደቱን ያፋጥነዋል፤ በመጨረሻም ሕዝቡ ወደ ጎዳናዎች በመውጣት አገዛዙን እስከ ውድቀቱ ያደርሰዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።

    የቀድሞው ንጉሥ ልጅ ይህንን ቢሉም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን ባለፈው ወር ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፓህላቪ በኢራን ውስጥ ምን ያህል ድጋፍ አላቸው የሚለው ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ወታደራዊ ኃይል እያጠናከረ ያለው የትራምፕ አስተዳደር፤ የኒውክሌር ስምምነት ላይ መድረስ ይቻል እንደሆነ ለማየት ከኢራን ጋር ንግግር ጀምሯል።

    የአሜሪካ እና የኢራን ዲፕሎማቶች ባለፈው ሳምንት ኦማን ውስጥ የተነጋገሩ ሲሆን በሚቀጥለው ሳምንትም ተጨማሪ ንግግሮች እንደሚደረጉ ይጠበቃል።

    ፓህላቪ፤ “ሰዎች፤ የሆነ ነጥብ ላይ ምንም ጥቅም የሌለው ውሳኔ ላይ እንደሚደረስ ያስባሉ። ምንም ጥቅም የለውም፤ በድርድር የትም አንደርስም። ስለዚህ አሜሪካ ጣልቃ የምትገባበት እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሕዝቡን ለማገዝ የገቡትን ቃል የሚፈጽሙበት ጊዜ አሁን ነው" ብለዋል።

  6. ጣሊያን የአፍሪካ አገራት በከባድ የአየር ንብረት ሁኔታ በሚጎዱበት ወቅት የእዳ ክፍያቸውን እንዲያዘገዩ ልትፈቅድ ነው

    የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አገራቸው ከአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉባዔ በእዳ አከፋፈል ላይ መነጋገራቸውን ገለፁ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ የካቲት 6/2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከአፍሪካ መሪዎች ጋር በነበራቸው ጉባዔ ወቅት አገራቱ በአስከፊ የአየር ንብረት ሁኔታ በሚጠቁበት ወቅት የሚከፍሉት እዳ እንዲቋረጥላቸው እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    ሜሎኒ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት “ዛሬም፣ ዳግም፣ ለአፍሪካ ማዕከላዊ የሆነ ጉዳይ ላይ አተኩረን ተነጋግረናል፤ ይህም ስለ ዕዳ ነው” ብለዋል።

    "ለጋራ ልማት ፕሮጀክቶች ብድርን የመለወጥ ሰፊ ተነሳሽነት ጀምረናል። ለዚህም በአስከፊ የአየር ንብረት ክስተቶች ለተጎዱት አገራት የዕዳ መክፈያ ጊዜያዊ እፎይታ የሚሰጡ አንቀጾችን ማስተዋወቅ ይጨምራል" ብለዋል።

    ሜሎኒ በ39ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ መሪዎች ጋር በመሆን እየተሳተፉ ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዚህ ንግግራቸው የቀረበው ምክረ ሃሳብ የዕዳ መክፈያ እፎይታ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን ወይም የትኞቹ አገራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለፁት ነገር የለም።

    ጣሊያን ከአፍሪካ አገራት ጋር የተለያዩ ትብብሮችን ታደርጋለች።

    በተለይ ሮም በአፍሪካ አገራት በኢነርጂ፣ በግብርና እና በመሠረተ ልማት ረገድ የረጅም ጊዜ አጋርነት ለመፍጠር አልማ የተለያዩ ሥራዎችን እየሰራች ነው።

  7. የሶማሊያው ፕሬዚዳንት የአፍሪካ አገራት ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት ውድቅ እንዲያደርጉ ጠየቁ

    የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ በትናንትናው ዕለት የአፍሪካ ኅብረት አባል አገራት "ዓለም አቀፍ ሕግን የሚያዳክም፣ ቀጠናውን የሚያናጋ እና በአገራት መካከል ያለውን መተማመን የሚሸረሽር" የውጭ አካላት የሚፈጽሙትን ጣልቃ ገብነት እና የአንድ ወገን እርምጃ ሁሉ ውድቅ እንዲያደርጉ ጥሪ አቀረቡ።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት የካቲት 6 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተካሄደው የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ ላይ ነው።

    "የአፍሪካ ልማት ከተባበሩት መንግሥታት ቻርተር እና ከአፍሪካ ኅብረት የሕግ መርሆዎች ጋር በሚጣጣም መልኩ ለአገሮች ሉዓላዊነት፣ ለግዛት አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነት በፅኑ አክብሮት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት" ሲሉ ሞሃሙድ በኢትዮጵያ በተካሄደው የጣሊያን አፍሪካ ጉባኤ ላይ ተናግረዋል።

    "እነዚህ መርሆዎች ምኞት አይደሉም፤ ለጋራ ደኅንነታችን መሠረት የሆኑ አስገዳጅ ቃል ኪዳኖች ናቸው።"

    ሞሃሙድ እስራኤል ሶማሊላንድን እንደ ሉዓላዊት አገር እውቅና መስጠቷንም አውግዘዋል።

    እንዲህ ያሉት እርምጃዎች "ይህንን መሠረት ለማፍረስ ብቻ የሚያገለግሉ ናቸው፤ ይህንንም በጥብቅ ማውገዝ አለብን" ብለዋል።

    ጣሊያን በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮን እና ሁለቱ አገራት "በተለያዩ ዘርፎች ላይ ያላቸውን የጋራ የትብብር ታሪክ " ስለምትደግፍ" አመስግነዋል።

    የኢትዮጵያ መንግሥት እስራኤል ለሶማሌላንድ ስለሰጠችው እውቅና እስካሁን ድረስ በይፋ ያለው ነገር የለም።

  8. የቅድመ ጋብቻ ሥልጠና አስገዳጅ አለመሆኑን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ

    የኢትዮጵያ የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፍቺን ለመቀነስ ባለመው እቅዱ የቅድመ ጋብቻ ሥልጠናን ቢያበረታታም አስገዳጅ አለመሆኑን ገለጸ።

    ሚኒስቴሩ ቅዳሜ የካቲት 7/ 2018 ዓ.ም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ባጋራው ጽሑፍ "ለመጋባት የቅድመ ጋብቻ ሥልጠና የምስክር ወረቀት መያዝ አስገዳጅ ነው" በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው ብሏል።

    ይህ የሚኒስቴሩ መግለጫ የወጣው እየጨመረ የመጣውን ፍቺ ለመቀነስ ሲባል ጥንዶች የቅድመ ጋብቻ ሥልጠና የምስክር ወረቀት ሳይዙ ጋብቻ መመስረት የማይችሉበት አሰራር ሊዘረጋ መሆኑ ከተዘገበ በኋላ ነው።

    ጉዳዩም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኗል።

    ሚኒስቴሩ ጋብቻ ጠንካራ ቤተሰብ ለመመስረት እና ለአገር ግንባታ መሠረት በመሆኑ “የቅድመ ጋብቻ የግንዛቤ ሥልጠና አስፈላጊ እንደሆነ እንደሚያምን እና ሃይማኖታዊዎቹን ጨምሮ አንዳንድ ተቋማትም ይህንን እንደሚያደርጉ ገልጿል።

    “ሥልጠናውን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ አስገዳጅ ለማድረግ ያለመ አሰራር እየተዘጋጀ ነው” መባሉ ግን ሐሰት ነው ብሏል።

    ጥንዶች የቅድመ ጋብቻ ሥልጠና መውሰድ የሚችሉበትን ሁኔታን ለመፍጠር ጥረቱን እንደሚቀጥል የገለፀው ሚኒስቴሩ፤ ቤተሰብ ላይ ያተኮረ የምክር አገልግሎትን ለማስፋት እየሰራ እንደሚገኝ አክሏል።

    ሚኒስቴሩ በዚህ መግለጫው “ስለትዳር በቂ ግንዛቤ ባለመኖር እና በሌሎች ምክንያቶች ፍቺ እንደሚስተዋል ቢጠቅስም፤ ምጣኔው ምን ያህል እንደሆነ አልገለጸም።

    ሆኖም አገሪቷ በተለይ በከተሞች አካባቢ ፍቺ እየጨመረ እንደመጣ ይነገራል።

    ከጥቂት ዓመታት በፊት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የፍቺ ቁጥር መጨመሩ እንዳሳሰበው በድረገፁ ላይ ገልጾ ነበር።

    የፍርድ ቤቱ በወቅቱ ባወጣው መረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ 16 ሺህ 35 ፍቺዎች እንደተፈፀሙ አመልክቷል።

  9. “እንደ ኢትዮጵያ ያለ አገር የተለያዩ የወደብ መዳረሻዎች ያስፈልጉታል”- ጠ/ሚ ዐቢይ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ተሰብሳቢዎች ባደረጉት ንግግር ላይ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላለው እንደ ኢትዮጵያ ላለ አገር ቀጣይነት ያለው እድገት የተለያዩ የወደብ መዳረሻዎች ያስፍለጉታል ሲሉ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ባስተላለፉት መልዕክት አስተማማኝ የባሕር በር መዳረሻ በሰላማዊ ትብብር ማረጋገጥ "መሠረታዊ ነው" ብለዋል።

    "ለአፍሪካ ቀንድ አገራት የወደፊት የምጣኔ ሃብት እና ለረዥም ጊዜ መረጋጋት” አስተማማኝ የባሕር በር አስፈላጊ መሆኑንም በንግግራቸው ላይ ገልጸዋል።

    አሁን የምንገኘው የዓለም አቀፍ ሽግግር ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በዚህ እርግጠኝነት በጠፋበት ዘመን የአፍሪካ ጥንካሬ የሚመሰረተው በራስ መተማመን እና በአንድነት በሚቆም ሕብረት ላይ ነው ብለዋል።

    ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቷን በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

    ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ 130 ሚሊዮን ሕዝብ "የጂኦግራፊ እስረኛ" መሆን የለበትም ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት “የሕልውና ጉዳይ ነው” ካሉ በኋላ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ያላቸው ግንኙነት እየተካረረ መጥቷል።

  10. "በመላው አፍሪካ ወንዞች ለጋራ ጥቅም ሲውሉ የመረጋጋት ምንጭ መሆን ይችላሉ"- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

    በመላው አፍሪካ ወንዞች ለጋራ ጥቅም ሲውሉ የመረጋጋት ምንጭ መሆን እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በ39ኛው የአፍሪካ ጉባዔ ላይ ለተገኙ ተሰብሳቢዎች ውሃ ከሃብት በላይ ነው ካሉ በኋላ፣ “የእድገት መሠረት፣ የፈጠራ፣ የመረጋጋት መነሻ ነው” ብለዋል።

    የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ "ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ነው።

    ውሃ “ከተሞቻችንን፣ ግብርናችንን፣ ጤናችንን እና ሰላማችንን ይቀርጻል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ኃላፊነት የተሞላበት የውሃ አስተዳደር እድገትን በብልሃት ለመምራት ወሳኝ መሆኑን መማሯን በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።

    ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ለመኖሪያ ቤቶች እና ለኢንዱስትሪዎች የኃይል አቅርቦት ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር ወደ ጎረቤት አገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አፍሪካውያን የውሃ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም ከቻልን በአፍሪካ ዕድገት ከፍ ያለ ተፅዕኖ ማሳደር እንችላለን ብለዋል።

    ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ አጠናቅቃ ያስመረቀችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌትሪክ ኃይል ያመነጫል።

    ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል ሲሉ ይናገራሉ።

    ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን እና ከግብፅ ጋር አለመግባባት ውስጥ ቆይታለች።

    ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ላለፉት አስራ አራት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።

  11. የዓለማችን ግዙፉ የወደብ አስተዳዳሪ ስማቸው በኢፕስቲን ሰነዶች ውስጥ የተጠቀሰውን ሥራ አስፈጻሚውን ከሥልጣን አነሳ

    የዓለማችን ግዙፍ የወደብ አስተዳዳሪ የሆነው የዱባዩ 'ዲፒ ወርልድ' ዋና ሥራ አስፈፃሚውን ሱልጣን አህመድ ቢን ሱለየምን ከሥልጣን ማንሳቱን አስታወቀ።

    እርምጃው የተወሰደው ቢን ሱለየም ከዚህ ቀደም የፆታዊ ጥቃት ወንጀለኛ ከነበረው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር የነበራቸው የጠበቀ ግንኙነት አዲስ በተለቀቀው ሰነድ ውስጥ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ነው።

    አዲስ ይፋ የሆኑት የኢፕስቲን ሰነዶች ቢን ሲለየም በአስርት ዓመት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢሜል ልውውጥ ማድረጋቸውን ያሳያሉ።

    በኢፕስቲን ዶሴዎች ውስጥ የአንድ ግለሰብ ስም ተጠቀሰ ማለት ግን ወንጀል ስለመስራታቸው ያሳያል ማለት አይደለም።

    ቢቢሲ ሱለይም በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የጠየቀ ቢሆንም መልስ አላገኘም።

    ዲፒ ወርልድ አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ “ዋና ሥራ አስፈጻሚው “ከአሁን ጀምሮ ከሥልጣናቸው ተነስተዋል” ያለ ሲሆን ኢሳ ካዚምን የቦርድ ሰብሳቢ፣ ዩቭራጅ ናራያንን ደግሞ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ መሾሙን ገልጿል።

    በዱባይ ባለቤትነት የተያዘው ግዙፉ የሎጀስቲክስ ድርጅት ዲፒ ወርልድ በስድስት አህጉራት ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

    በዓለም ንግድ መሠረተ ልማት ላይ ግዙፍ ሚና የሚጫወተው ይህ ኩባንያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አብረውት ከሚሰሩት አገራት እና ድርጅቶች ከፍተኛ ጫና ገጥሞታል።

    በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ የዩኬ እና የካናዳ ኩባንያዎች ከድርጅቱ ጋር ያላቸውን አዲስ ኢንቨስትመንት ማቋረጣቸውን ገልጸው ነበር።

  12. ከገንዘብ ኖት እቅፍ አበባ እንዳይሰራ በከለከለችው ኬንያ የፍቅረኞች ቀን እንዴት እየተከበረ ነው?

    ዛሬ ዓለም አቀፍ የፍቅረኞች ቀን ነው።

    በየዓመቱ በአውሮፓውያኑ የካቲት 14 በሚከበረው የፍቅረኞች ቀን በተለይ በከተሞች አካባቢ ቀይ ቀለም ነግሶ ይታያል።

    ከተሞች በቀይ ቀለም ይጥለቀለቃሉ፤ ፍቅረኛሞች ቀይ ይለብሳሉ፤ የተፈጥሯዊ አበቦች እና የስጦታዎች ገበያም ይደራል። ይህ ለዓመታት የቆየ ልማድ ነው።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በኬንያ በዚህ ዕለት የተፈጥሯዊ አበባ እቅፍ ከመለዋወጥ ይልቅ ቡናማ፣ ሰማያዊ ወይም ሐምራዊ ቀለም ያላቸውን የገንዘብ ኖቶችን በመጠቅለል፣ በማጠፍ እና በማያያዝ እቅፍ አበባ ሰርተው ስጦታ መለዋወጥ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል።

    ኬንያውያን ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች ከገንዘብ የተሠራ የአበባ እቅፍ ይዘው የሚሠሯቸው ቪድዮዎች ዝነኛ ናቸው።

    ይህ ልማድ ወደ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት የተስፋፋ ሲሆን የኬንያን፣ የኡጋንዳ ፣ ሩዋንዳ ፣ ቦትስዋና እና ናሚቢያ ማዕከላዊ ባንኮችን ስጋት ላይ ጥሏል።

    ባንኮቹ እነዚህ የገንዘብ ኖቶችን በመጠቀም እቅፍ አበባ በሚሰራበት ወቅት የገንዘብ ኖቶቹ እንዳይጎዱ ወይም እንዳይበላሹ አስጠንቅቀዋል።

    “የገንዘብ ኖት ታጥፎ፣ ተጠቅልሎ፣ እርስ በርሱ ተጣብቆ እና በሌላም ቅርጽ አበባ እየሆነ ነው። ይህም ዋጋውን ያሳጣዋል” ብለዋል።

    የኬንያ ማዕከላዊ ባንክ የገንዘብ ስጦታዎችን መለዋወጥን ሳይሆን የገንዘብ ኖቶች ላይ ጉዳት ማድረሱን እንደሚቃወም ገልጿል።

    ይህ የባንኮች ጣልቃ ገብነት በገንዘብ ኖቶች የሚሰሩ የአበባ ስጦታዎችን ባህል ሊቀንሰው እንደሚችል ይታመናል።

    ሆኖም በዘርፉ ላይ የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ተናግረዋል።

    አበባ የምትሸጠዋ አንጀላ ሙቶኒ እርምጃው ከገንዘብ ኖቶች እቅፍ አበባ በማዘጋጀት በሚተዳዳሩ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ብታምንም ለአዳዲስ ፈጠራዎች ግን ቦታ አለ ብላለች።

    ሙቶኒ የገንዘብ ኖቶቹ ሳይበላሹ ገንዘቦቹ በሚታዩበት መልኩ የአበባ እቅፍ ሰርታለች። ሌሎች ፈጠራዎችን እያሰበች እንደሆነም ተናግራለች።

    አንዳንዶች ደግሞ የኬንያ ማዕከላዊ ባንክን ማስጠንቀቂያ ለማምለጥ የአሜሪካን ዶላር መጠቀም ጀምረዋል።

    በመሆኑም ከገንዘብ ኖቶች የሚሰራ እቅፍ አበባ በቅርቡ ሊጠፋ የሚችልበት እድል አነስተኛ ነው።

  13. የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ የተገኙበት የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ

    የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ፣ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር እና የሌሎች አገራት ተወካዮች የታደሙበት የአፍሪካ ኅብረት 39ኛው መደበኛ ጉባኤ አዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ ነው።

    ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 6/2018 ዓ.ም. በኅብረቱ ዋና ጽሕፈት ቤት በተጀመረው ስብሰባ መክፈቻ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የመንግሥቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እና የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ንግግር አድርገዋል።

    በስብሰባ ላይ በሰላም፣ በደኅንነት፣ በትብብር እና ዘላቂ ልማት እንዲሁም የአፍሪካን ድምጽ በማሰማት ዙሪያ በተያዙ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ይደረጋል።

    በተጨማሪም ሌሎች አህጉሪቱን የተመለከቱ በርካታ ጉዳዮች ላይ የመሪዎቹ ጉባኤ ላይ ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ይጸድቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  14. አሜሪካ እና ኢራን ለሁለተኛ ዙር ድርድር በሚቀጥለው ሳምንት በጄኔቫ ሊገናኙ ነው

    አሜሪካ እና ኢራን ሁለተኛውን ዙር የኒውክሌ ድርድራቸውን በሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 10 2018 ዓ.ም. በጄኔቫ እንደሚያካሂዱ ሮይተር ምንጮችን ጠቅሶ ዘገበ።

    ምንጮች ቅዳሜ ዕለት ለሮይተርስ የዜና ወኪል የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር የአሜሪካን ልዑካን ይመራሉ ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ ደግሞ የቴህራንን ልዑክ ይመራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ድርድሩን ኦማን የምትመራው ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ባድር አል-ቡሳይዲ ይገኛሉ ተብሏል።

    በጄኔቫ የሚካሄደው ድርድር ኦማን የጀመረችው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር ጥረት ቀጣይ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራን ባለሥልጣናት ለመደራደር ፈቃደኛ እንደሆኑ እና ውይይቱ በሚቀጥለው ወር ውስጥ መጠናቀቅ አለበት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እያስጠጋች ሲሆን ድርድሩ የማይሳካ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ የፕሬዚዳንት ትራምፕን ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

    ትራምፕ በዚህ ሳምንት ለአክሲዮስ “ወይ ከሥምምነት ላይ እንደርሳለን፤ አለበለዚያ ጠንከር ያለ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ተናግረው ነበር።

  15. ትራምፕ በኢራን ውስጥ የመንግሥት ለውጥ ዋነኛው አማራጭ መሆኑን ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ውስጥ የሚኖር የሥርዓት ለውጥ "ሊከሰት የሚችል ምርጥ ነገር" ነው በማለት በአገሪቱ የአገዛዝ ለውጥ ላይ ያላቸውን ድጋፍ ገለፁ።

    "ለ47 ዓመታት ሲያወሩ፣ ሲያወሩና ሲያወሩ ቆይተዋል። እስከዚያው ድረስ ግን ብዙ ሕይወት አጥተናል" ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።

    ትራምፕ ኢራንን ማን እንዲያሰተዳድራት እንደሚፈልጉ ለመግለጽ ፈቃደኛ ባይሆኑም፣ ሥልጣን ሊረከቡ የሚችሉ "ሰዎች አሉ" ብለዋል። የኢራን የበላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለትራምፕ የቅርብ ጊዜ አስተያየቶች እስካሁን ድረስ ምላሽ አልሰጡም።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ ኢራን የኒውክሌር ስምምነት እንድታደርግ ጫና ለማሳደር ሁለተኛ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልካለች።

    በዓለም ላይ ትልቁ እና አዲሱ የአሜሪካ የአውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ የሆነው ዩኤስኤስ ጄራልድ አር ፎርድ "በቅርቡ" ከካሪቢያን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለመንቀሳቀስ ተዘጋጅቷል ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።

    ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኘውን ሁለተኛውን የአሜሪካ የጦር መርከብ ለመቀላቀል የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቡ ሲንቀሳቀስ የሚያሳይ ምስል አጋርተዋል።

    ፔንታጎን የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቡን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የላከው በጥር ወር ነበር።

    ይህ የሆነው ዩናይትድ ስቴትስ የኢራን መንግሥት በሺዎች የሚቆጠሩ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያ ለማስቆም አገሪቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ካስፈራራች በኋላ ነው።

    ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የኒውክሌር ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ በኢራን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ቢዝቱም፣ ረቡዕ ዕለት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር በዋይት ሐውስ ከተወያዩ በኋላ ከቴህራን ጋር የሚያደርጉት ውይይት እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

  16. ከቤጂንግ ጋር ውጥረት ውስጥ የገባችው ጃፓን የቻይና መርከብን በቁጥጥር ስር አዋለች

    የጃፓን ባለስልጣናት ለምርመራ እንዲቆም ትዕዛዝ ሲሰጠው ለማምለጥ ሞክሯል ያሉትን የቻይና አሳ አጥማጅ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቁ።

    ይህ የጃፓን እርምጃ ከቻይና ጋር የገባችበትን ውጥረት ሊያባብሰው እንደሚችል ተነግሯል።

    የአገሪቱ የአሳ ሀብት አስተዳደር ኤጀንሲ እንደገለጸው መርከቡ ሐሙስ ዕለት በቁጥጥር ስር የዋለው በደቡብ ምዕራብ ናጋሳኪ ግዛት አቅራቢያ በሚገኘው የጃፓን ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ውስጥ ነው።

    የመርከቡ ካፒቴንም እንደተያዘ ተገልጿል። እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከሆነ በመርከቡ ላይ የ47 ዓመቱን ቻይናዊ ካፒቴንን ጨምሮ 11 ሰዎች ነበሩ።

    የተያዘው መርከብ ከፍተኛ አቅም ያለው "ታይገር ኔት አሳ አጥማጅ ጀልባ" እንደሆነ ባለስልጣናት እና የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

    መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤ "የመርከቡ ካፒቴን የአሳ ማጥመድ ተቆጣጣሪዎች ለምርመራ እንዲቆም አዝዘውት የነበረ ቢሆንም መርከቡ ትዕዛዙን ሊያከብር አልቻለም፤ አምልጧልም” ብሏል።

    ኤጀንሲው፤ የቻይናን አሳ አጥማጅ መርከብን በቁጥጥር ስር ሲያውል ከአውሮፓውያኑ 2022 ወዲህ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን ቻይና ምላሽ አልሰጠችም።

    ጃፓን ይህንን እርምጃ የወሰደችው አገሪቱ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት በሻከረበት በዚህ ወቅት ነው።

    የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳናኤ ታካኢቺ ባለፈው ኅዳር ላይ ቻይና ታይዋንን በኃይል ለመያዝ የምትሞክር ከሆነ ጃፓን ጣልቃ እንደምትገባ መጠቆማቸው ቤጂንግን አስቆጥቷል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ፤ የጃፓኑን መሪ ንግግር “በጣም መጥፎ” ሲል ገልጾታል። ቻይና ቶኪዮ ውስጥ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታ ያነጋገረች ሲሆን ለትምህርት ወደ ጃፓን የሚሄዱ ዜጎቿን ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ አስጠንቅቃለች።

  17. የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ የጂኦፖለቲካ ዘመን ላይ ነን ሲሉ አውሮፓን አስጠነቀቁ

    በሙኒክ የጸጥታ ኮንፈረንስ ላይ ተጠባቂ ንግግር ለማድረግ ወደ አውሮፓ የተጓዙት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፤ ወሳኝ ሲሉ ስለገለጹት ምዕራፍ እንዲሁም “አዲስ ዘመን” ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላለፉ።

    ጀርመን ውስጥ በሚካሄደው በዚህ ወሳኝ ጉባኤ ላይ የሚሳተፈው የአሜሪካ ልዑክ የሚመራው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነው።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል ያላቸውን ፍላጎት በአጽንኦት በመግለጽ የዴንማርክ ሉዐላዊነት ላይ አደጋ ከቃጡ በኋላ አሜሪካ በትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ስትሳተፍ ይህ የመጀመሪያው ነው።

    ሩቢዮ ጉዟቸውን ከመጀመራቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በዚህ ጉባኤ ላይ ለአውሮፓውያን የሚያስተላልፉት መልዕክት ባለፈው ዓመት ከተደረገው በተሻለ የሚያስታርቅ ይሆን እንደሆን ተጠይቀዋል።

    ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጉባኤ ላይ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የአውሮፓ አገራትን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እና የስደት ፖሊሲዎች በማንሳት ጠንካራ ትችት ሰንዝረዋል።

    የጄዲ ቫስ ንግግር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ውጥረት ፈጥሮ ቆይቷል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ ለጥያቄው ሲመልሱ፤ "ዓለም በፊታችን ላይ በፍጥነት እየተለወጠች ነው” ብለዋል።

    “የምንኖረው በአዲስ የጂኦፖለቲካ ዘመን ውስጥ ነው። ይህ [ሁኔታ] ሁላችንም አዲሱ ዘመን ምን እንደሚመስል እና የእኛ ሚና ምን መሆን እንዳለበት እንደገና እንድንመረምር የሚያደርገን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

    ከቀናት በፊት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት አማኑኤል ማክሮን፤ አውሮፓ ከአሜሪካ ጥገኝነት ለመላቀቅ መዘጋጀት እንዳለባት አሳስበው ነበር። የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ በበኩላቸው በአትላንቲክ ዙሪያ ያሉ አገራት ግንኙነት እየተጠናከረ መሆኑን እንዲሁም ይህንን ማድረግ ከመቼውምጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

    በሙኒክ የጸጥታ ኮንፈረንስ ላይ በዩክሬን የሚደረገው ጦርነት፣ ከቻይና ጋር የተፈጠረው ውጥረት፣ እንዲሁም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ሊደረግ የሚችል የኒውክሌር ስምምነት በአጀንዳነት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

  18. ደቡብ አፍሪካ ወንበዴዎችን ለመቆጣጠር ሠራዊቷን ልታሰማራ ነው

    የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ የወንጀል ቡድኖችን እና ሕገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮን ለማስቆም ፖሊስ የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ የአገሪቱን ሠራዊት እንደሚያሰማሩ ተናገሩ።

    ከፍተኛ ቁጥር ያለው ግድያ ከሚፈጽማባቸው የዓለም አገራት አንዷ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በወንበዴዎች የሚፈጸም ጥቃት ትልቅ ችግር ነው።

    ፕሬዝዳንት ራሳፎሳ የአገሪቱን ሁኔታ በተመለከተ ሐሙስ ዕለት ባደረጉት ዓመታዊ ንግግር፤ “በአሁኑ ወቅት የተደራጀ ወንጀል ለዴሞክራሲያችን፣ ለማኅበረሰባችን እና ለኢኮኖሚ እድገታችን ድርስ ስጋት ሆኗል" ብለዋል።

    "የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ፖሊስን እንዲደግፍ አሰማራለሁ" ሲሉም ዕቅዳቸውን ይፋ አድርገዋል።

    ባለፈው ወር የፖሊስ ሚኒስትሩ ፊሮዝ ካቻሊያ፤ ፖሊስ የሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፉ ወንጀሎችን የሚፈጽሙትን ወንበዴዎች እስካሁን ማሸነፍ እንዳልቻለ አምነዋል። ይህ የሚኒስትሩ ንግግርም በአገሪቱ ያለውን የወንጀል ቀውስ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ የሚያመለክት ሆኗል።

    ራማፎሳ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ የፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አዛዦች "በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የፀጥታ ኃይሎች የት መሰማራት እንዳለባቸው" የሚያሳይ ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

    ሠራዊቱ የወንበዴዎች ጥቃት እና ሕገ ወጥ የማዕድን ቁፋሮ ወደተባባሰባቸው ዌስተርን ኬፕ እና ጋውቴንግ ግዛቶች ሊሰማራ እንደሚችል ጠቁመዋል።

    “ዌስተርን ኬፕ ውስጥ ያሉ ልጆች በወንበዴዎች ጦርነት የተባራሪ ጥይት ሰለባ እየሆኑ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ "እዚህ ዌስተርን ኬፕ ውስጥ ልጆች በወንጀል ቡድኖች የተኩስ ልውውጥ መካከል እየተቀጠፉ ነው። ጋውቴንግ ደግሞ ሕዝቡ ሰዎች በሕገ ወጥ ማዕድን አውጪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እየተባረሩ ነው” ብለዋል።

    የደቡብ አፍሪካ ባለሥልጣናት፤ በአገሪቱ ለሚታየው የተደራጀ የወንጀል እንቅስቃሴ ተጠያቂ የሚያደርጉት "ዛማ ዛማስ" ተብለው የሚጠሩትን አካላት ነው። እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎችን በአባልነት ይዘዋል።

    በአገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የወንጀል ምጣኔ ለመግታት ሠራዊት ከማሰማራት በተጨማሪ ሌሎች እርምጃዎችም እንደሚወዱ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ገልጸዋል።

    5,500 አዳዲስ የፖሊስ መኮንኖች መቅጠርን፣ የመረጃ (አቅምን ማጠናከርን እንዲሁም የተደራጁ ወንጀል ቡድኖችን ዒላማ ማደርግ ከአዲሶች እርምጃዎች መካከል ተጠቅሰዋል።

    የፖሊስ መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ከሚያዝያ እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ውስጥ በአንድ ቀን በአማካይ 63 ሰዎች ይገደሉ ነበር።

  19. የሶማሊያው መሪ ጎረቤት አገራት እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና ይደግፋሉ ሲሉ ከሰሱ

    የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ስማቸውን ያልጠቀሷቸው ጎረቤት አገራት እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን የአገርነት ዕውቅና ይደግፋሉ ሲሉ ከሰሱ።

    ፕሬዝዳንቱ ለንደን ውስጥ ለሚታተመው አሽራቅ አል-አውሳጥ ለተባለው የአረብኛ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ አገራቱ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና ለራሳቸውን ጥቅም ሊያውሉት ይፈልጋሉ ሲሉ ከስሰዋል።

    ፕሬዝዳንት ሐሰን ለዚህ ክሳቸው የትኛውንም አገር በስም ያልጠቀሱ ሲሆን፣ “አንዳንድ የቀጣናው አገራት ይህንን አጋጣሚ የሶማሊያን አንድነት እና የቀጣናው መረጋጋት ለአደጋ አጋልጠው ጠባብ እና የአጭር ጊዜ ጥቅማቸውን ለማሳካት ይፈልጋሉ” ብለዋል።

    ለዚህ ክሳቸው “የትኛውንም አገር በስም መጥቀስ አልፈልግም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “ነገር ግን ይህንን ዕውቅና አንዳንዶች ውስን ጥቅም ማግኘት የሚያስችላቸው አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል።

    እስራኤል ባለፈው ታኅሣሥ ወር ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ ለምትቆጥራት እና የራሷን ነጻ አገርነት ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅና ከሰጠች በኋላ ሶማሊያን በመደገፍ በርካታ አገራት እና ተቋማት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

    ነገር ግን የሶማሊያ ጎረቤት ከሆኑት አገራት መካከል አስካሁን በይፋ ተቃውሟቸውን ወይም ድጋፋቸውን ያልገለጹት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ናቸው።

    ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ከሁለት ዓመት በፊት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ላይ በደረሰችበት ጊዜ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል።

    የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የአገራቸው የግዛት አንድነት ሊታለፍ የማይገባው “ቀይ መስመር” ነው በማለት አስጠንቅቀው፤ መንግሥታቸው የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የተለያዩ ፖሊሲዎችን እየተጠቀመ ነው ብለዋል።

    ሶማሊላንድ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የራሷን መንግሥት መሥርታ በነጻ አገርነት ብትቆይም በቅርቡ የአገርነት ዕውቅና ከሰጠቻት እስራኤል ውጪ ከየትኛውም አገር ዕውቅናን አላገኘችም።

  20. የሳዑዲ አረቢያ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

    የሳዑዲ አረቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሊድ አብዱልከሪም አል ካሪጅ ከኤርራው ፕሬዚዳንት ጋር በአሥመራ ተገናኝተው መወያየታቸው ተገለፀ።

    የኤርትራው ፕሬዚዳንት ከሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር የተገናኙት ሐሙስ የካቲት 5/2018 ዓ.ም. መሆኑን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስትር በይፋዊ የኤክስ ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል።

    የሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢንጂነር ማሌን ቢን አብዱልካሪም አል ካሬጂ እና ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ወዳጅነት እና ትብብር ለማጠናከር መነጋገራው ተገልጿል።

    ከዚህም በተጨማሪ የሳዑዲ ልዑካን ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር በቀጠናው እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል።

    በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ የሳዑዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአዲስ አበባ በሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የሳዑዲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውይይት በዝርዝር ባይገለጽም "በቁልፍ ዘርፎች ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር" እንዲሁም "የሁለቱም አገራት ፍላጎት በሆኑ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መተባበር" ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተገልጿል።

    የሳዑዲ አረቢያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ሁለቱ አገራት ጉብኝት ያደረጉት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዳግም ወፈደ ግጭት ይገባሉ የሚለው ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።

    የኤርትራው ፕሬዚዳንት እና የሳዑዲ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚገኙ አገራት የቀጠናውን ሰላም እና ደኅንነት ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ የሚኖራቸው ሚና ላይ መነጋራቸውን የአገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጿል።

    የሳዑዲ አረቢያ ልዑክ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ጋር “በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚገኙ አገራት ተለዋዋጭ በሆነው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች እና አዝማሚያዎች ባሻገር የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት በማረጋገጥ ረገድ ስለሚኖራቸው አስተዋጽኦ ተነጋግረዋል።”

    ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በደኅንነት፣ በባህል እና በማኅበራዊ ዘርፎች ከዚህ ቀደም የደረሱባቸውን ሁለትዮሽ ስምምነቶች ተግባራዊ ለማድረግ መነጋገራቸው ተገልጿል።

    ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አወርቂ በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት ከአልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

    የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ባለፈው ሳምንት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዘው ከልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

    ከሳዑዲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሐን ጋር በተደረገው ውይይት "ሁለቱ አገራት የአፍሪካ ቀንድን ሰላም እና መረጋጋትን ለማስጠበቅ" በጋራ ለመሥራት እንደተስማሙ ተገልጿል።