ትራምፕ በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ

ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባለቸው አገራት ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ የፈረሙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አገራቱ ከቴህራን ጋር መገበያየት የሚቀጥሉ ከሆነ ቀረጡን ሊጥሉ እንደሚችሉ ተናገሩ። ኦማን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ንግግር ኢራን "ስምምነት ላይ ካልደረሰች ውጤቱ በጣም ከባድ ይሆናል" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የጣሊያን ፖሊስ በሚላን የተነሳን ግጭት ተከትሎ ተቃዋሚዎችን አሰረ

    ፖሊሶች ተቃዋሚዎችን ሲከላከሉ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, በሚላን የተፈጠረው ግጭት ያጋጠመው ቀደም ብሎ በቱሪን በተከሰተ ተቃውሞ ከ100 በላይ ፖሊሶች ላይ ጉዳት ከደረሰ ከቀናት በኋላ ነው።

    በጣሊያኗ ሚላን ከተማ ቅዳሜ ዕለት በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ስድስት ሰዎች ታሰሩ።

    ከክረምት ኦሊምፒክ አዘጋጆች አንዷ በሆነችው ሚላን ተቃውሞው የተቀሰቀሰው በመጀመሪያው የውድድር ቀን ነው።

    በዕለቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የኑሮ ውድነትን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት በሰሜናዊ ጣሊያን ከተማ አደባባይ ወጥተው ነበር።

    አንዳንዶች እሳት በማቀጣጠል እና በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ፖሊስም ውሃ በመርጨት ምላሽ ሰጥቷል።

    በከተማዋ ይህ ተቃውሞ የተካሄደው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በቱርኒ የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን ተከትሎ አገሪቷ የተቃውሞ ሕግን ካጠበቀች በኋላ ነው።

    በቱርኒ ተቃውሞ ከ100 በላይ ፖሊሶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግሥት መረጃዎች አመልክተዋል።

    አንድ የፖሊስ መኮንን በመዶሻ ጥቃት የደረሰበት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስተር ጆርጂያ ሜሎኒ ድርጊቱን “ የግድያ ሙከራ” ብለውታል።

    ይህንን ተከትሎም ከ30 በላይ ሰዎች ታስረዋል።

    የአገሪቷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሳልቪኖ በሚላኑ ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር በተፈጠረው ግጭት የተሳተፉትን “ ወንጀለኞች” ብለዋቸዋል።

    በቱርኒ አሳፋሪ ጥቃት ከተፈፀመ ከቀናት በኋላ ተጨማሪ ግጭቶች በሕግ አስፈፃሚዎች ላይ ጥቃቶች ተፈፅመዋል” ብለዋል።

    "ዘራፊዎች እና በወንጀለኞች" ያሏቸውን ለመከላከልም አዲስ የደኅንነት ማዕቀፍ መጽደቁንም ገልጸዋል።

    በቱሪን ከተፈጠረው ሁከት በኋላ የፀደቀው የደኅንነት ማዕቀፍ፣ ፖሊስ አመጽ ያዛምታሉ ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦች ከተቃውሞ ሰልፉ አስቀድሞ ለ12 ሰዓታት አስሮ ለማቆየት ያስችለዋል። ተቺዎች ግን ይህንን "አፋኝ" ብለውታል።

    የክረምት ኦሊምፒክ እስከ አውሮፓውያኑ የካቲት 22 ድረስ ሚላንን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ይካሄዳል።

  2. የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ከመደራደር ውጭ አማራጭ የለም" አሉ

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ለአገሪቱ ብሔራዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኮንግረስ "ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም" ሲሉ በድርድሩ ወቅት ይህንኑ ለአሜሪካ ተወካዮችም መናገራቸውን ገለፁ።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ኦማን ውስጥ ቅዳሜ ዕለት የተደረገው ድርድር “ለጊዜው” መጠናቀቁን የኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን አስታውቋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አራግቺ “ስለ ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ማንኛውንም ግርታ እና ጥያቄ እንመልሳለን” ብለዋል።

    መብታችንን እንዲያረጋግጥልን ማንንም አንጠይቅም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ “መብታችን እንዲከበር እንፈልጋለን” ሲሉ ተናግረዋል።

    ከእስራኤል ጋር አገራቸው ለአስራ ሁለት ቀናት የዘለቀ ጦርነት ባደረገችበት ወቅት በኒውክሌር ተቋማት ላይ የተፈጸመውን የቦምብ ድብደባ በመጥቀስም “እውቀት በቦምብ ድብደባ አይጠፋም” ብለዋል።

    የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ባለሥልጣናት ተቋሙን መጎብኘት ስለሚችሉበት ሁኔታም ሲናገሩ “የኤጀንሲውን ኃላፊ ከመጎብኘቱ በፊት መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መኖራቸውን ነግሬዋለሁ። ምክንያቱም የደኅንነት እና የፀጥታ ጉዳዮች አሉ። ያልፈነዱ ቦምቦች አሉ። መስማማት ያለብን ጉዳዮች አሉ፤ ከዚያ በኋላም ፍተሻውን ማካሄድ ይቻላል” ብለዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ድርጊት "ወደ ጫካው ሕግ መመለስ" ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ አመክንዮ ላይ በመመስረት "ጠንካራ የሆነ አካል ፈቃዱን በሌሎች ላይ ይጭናል" ማለት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

    "በጫካ ሕግ ውስጥ ደካማዎቹ ይረገጣሉ፤ ኃያላኑም በሕይወት ይተርፋሉ። ለዚህም ነው ጠንካራ ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ የሌለን” ብለዋል።

  3. ሳዑዲ አረቢያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ግመሎቿ ፓስፖርት ልትሰጥ ነው

    ግመል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሳዑዲ አረቢያ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ግመሎች ፓስፖርት ለመስጠት ዕቅድ እንዳላት ይፋ አደረገች።

    ይህ የሳዑዲ ውሳኔ አገሪቱ በባህል እና ምጣኔ ሃብት ረገድ ትልቅ ሃብት አድርጋ የምትቆጥራቸውን ግመሎች ለመቆጣጠር እና በአግባቡ ለማስተዳደር ያስችላታል ተብሏል።

    በዚህ ሳምንት የሳዑዲ አካባቢ፣ውሃ እና ግብርና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ እርምጃው በማዕከል የሚሰበሰብ አስተማማኝ የመረጃ ቋት እንዲኖር ያደርጋል ብሏል።

    አክሎም ግመሎች ፓስፖርት እንዲኖራቸው መደረጉ በዘርፉ “ምርታማነትን እና ውጤታማነትን” ከማበረታታቱ ባሻገር የግመሎቹን ባለቤቶች ለመቆጣጠር ያስችላል ሲል ገልጿል።

    የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው አል ኢክህባሪያ ፓስፖርቱ ሽያጭን፣ ከቦታ ቦታ ማጓጓዝን እና ንግድን ለመቆጣጣር ያገለግላል ሲል ዘግቧል።

    ከዚህም በተጨማሪ የግመሎቹን ባለቤቶች መብት የሚጠብቅ ሲሆን የባለቤትነት ማረጋገጫም ሆኖ ያገለግላል።

    የሳዑዲ ባለሥልጣናት እአአ በ2024 ይፋ የሆነን መረጃ በመጥቀስ በአገሪቱ 2.2 ሚሊዮን ግመሎች እንዳሉ ይናገራሉ።

    ግመሎች በሳዑዲ ባህል እና ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸው ሲሆኑ በዋናነት ለመጓጓዣ እንዲሁም የሀብትና የኩራት ምንጭ ተደርገው ይቆጠራሉ።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግመሎችን በማዳቀል ከፍተኛ የሆነ የውድድር ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ መጥቷል።

    በእነዚህ ውድድሮች ላይ የሚያሸንፉ ግመሎች በሺህዎች በሚቆጠር ገንዘብ ይሸጣሉ።

    ይህ እያደገ የመጣው ንግድ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ቁጥጥራቸውን እንዲያጠብቁ አድርጓቸዋል።

    በተለይ የግመሎች የቁንጅና ውድድር በሚል የተጀመሩት ፉክክሮች የባለሥልጣናቱን ትኩረት ከሳቡት መካከል ናቸው።

    የውድድሩ አዘጋጆች የግመሎችን ከንፈር፣ አፍንጫ እና ሻኛ ለማተለቅ የሚሰጡ ክትባቶችን አግደዋል።

    የሳዑዲ አረቢያ ባለሥልጣናት ለግመሎች የሚሰጠው ፓስፖርት ግብርናን ያዘምናል፤ የአገሪቱ ባህል ተጠብቆ እንዲቆይ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።

  4. በለንደን አንድ ግለሰብ ከወሲብ ጋር የተያያዙ 33 ወንጀሎችን ፈጽሟል በሚል ተከሰሰ

    የኒው ስኮትላንድ ያርድ ታፔላ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አንድ ግለሰብ በደቡብ ለንደን በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ተከታታይ የወሲብ ጥቃቶችን ፈጽሟል በሚል ተከሰሰ።

    አንዳንዶቹ ወንጀሎች የተፈጸሙት እንደ አውሮፓውያኑ በ2003 ነው ተብሏል።

    የ58 ዓመቱ አዴባዮ አዴዬሚ እአአ ከ2003 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ አስገድዶ መድፈርንና የወሲብ ጥቃትን ጨምሮ 33 የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽሟል በሚል ተከሷል።

    የሜትሮፖሊታን ፖሊስ እንደገለጸው ክሶቹ ስድስት የአስገድዶ መድፈር፣ የአስገድዶ መድፈር ሙከራ፣ ጥቃት እና 21 የወሲብ ጥቃቶችን ይዘዋል።

    ግለሰቡ ጥቃት የፈጸመባቸው አምስቱም ተጎጂዎች ሴቶች ናቸው።

    አዴዬሚ ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ሥር የዋለው በጥቅምት 20/ 2020 እንደሆነ ፖሊስ ገልጿል።

    ሰኞ ዕለት በብሮምሌይ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።

  5. የትራምፕን ዛቻ ተከትሎ ካናዳ እና ፈረንሳይ በተመሳሳይ ቀን ግሪንላድ ውስጥ ቆንስላ ከፈቱ

    በግሪንላንድ የካናዳ ባንዲራ ሲሰቀል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል መዛታቸውን ተከትሎ፤ ካናዳ ለግዛቷ አጋርነቷን ለማሳየት የመጀመሪያውን የዲፕሎማሲ ጽሕፈት ቤት በግሪንላንድ ከፈተች።

    የካናዳ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ መርከብን ይዘው ወደ ግሪንላንድ ዋና ከተማ ኑክ ያመራው የካናዳ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ልዑክ፤ አርብ ዕለት የቆንስላ ጽሕፈት ቤቱን በይፋ ከፍቷል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የካናዳ ጠቅላይ ገዥ ሜሪ ሲሞን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አኒታ አናንድን ጨምሮ ከፍተኛ የካናዳ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

    በዚሁ ተመሳሳይ ቀን የፈረንሳይ ባለሥልጣናትም የግሪንላድ ቆንስላ ጽሕፈት ቤታቸውን ከፍተዋል። የካናዳ እና የፈረንሳይ ቆንስላ መከፈት በግሪንላድ የታየ ታሪካዊ የውጭ ግንኙነት መጠናከር ተደርጎ ተወስዷል።

    በካናዳው ዲፕሎማሲያዊ ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናንድ፤ ቆንስላው ካናዳ "ከግሪንላንድ እና ከዴንማርክ ሕዝብ ጋር አብሮ ለመቆም" ያላትን የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

    እስከ አርብ ዕለት ድረስ በግሪንላድ ውስጥ ይፋዊ የቆንስላ አገልግሎት ያቀርቡ የነበሩት አሜሪካ እና አይስላንድ ብቻ ነበሩ።

    የእነዚህ ቆንስላዎች መከፈት የኔቶ አባል አገራት፤ ለብሔራዊ ደኅንነት ሲባል አሜሪካ ግሪንላንድን “የራሷ ማድረግ” አለባት የሚለው የትራምፕ ዛቻ ለተደቀነባት ዴንማርክ አጋርነታቸውን ማሳየት እንደቀጠሉ የሚያመለክት ነው ተብሏል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ ከዴንማርክ፣ ከአውሮፓ አገራት እና ከካናዳ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ የመጠቅለል ሐሳባቸውን አርግበዋል። ስምምነት ለመፈጸም የሚያስችሉ አማራጮችን እያተመለከቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

  6. አስከሬኖችን በማንገላታት የተከሰሰው የቀብር አስፈጻሚ የ40 ዓመት እስራት ተፈረደበት

    ቀብር አስፈጻሚው ድርጅት

    የፎቶው ባለመብት, CBS

    በአሜሪካ፣ ኮሎራዶ ግዛት አስከሬኖች ላይ ብዝበዛ ሲፈጽም የነበረ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ኃላፊ የ40 ዓመት እስራት ተፈረደበት።

    በድርጅቱ ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ አስከሬኖች በመበስበስ ላይ ሳሉ በፖሊስ የተገኙ ሲሆን፤ ጆን ሀልፎርድ የተባለው ግለሰብ ፍርድ ቤት ቀርቦ የሟቾችን ቤተሰቦች ይቅርታ ጠይቋል።

    አስከሬኖቹ ላይ በደረሰው እንግልት እጅግ የተቆጡት ቤተሰቦች “አውሬ” ሲሉ አንቋሽሸዋል።

    የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቱ ባለቤት ጆን ሀልፎርድ እና የቀድሞ ባለቤቱ ኬሪ ሀንፎልድ ናቸው። የቀድሞ ባለቤቱ ላይ ተመሳሳይ ክስ ቀርቦ ፍርድ እየተጠባበቀች ትገኛለች።

    ‘ዘ ሪተርን ቱ ኔቸር’ የተባለው ቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ለሟቾች ቤተሰቦች ሐሰተኛ የአስከሬን አመድ እየሰጠ ነበር። በድርጅቱ ውስጥ 189 አስከሬኖች ተገኝተዋል።

    በቀረበበት ክስ የመጨረሻው ብይን የሆነው የ50 ዓመት እስራት እንዲፈረድበት የሟቾች ቤተሰቦች ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

    ከተገኙት አስከሬኖች መካከል የሕጻናት ይገኙበታል።

    ኬሊ ማከን የተባለች ተጎጂ “እናቴ እንደ ቆሻሻ ተጥላ ነበር። ልቤ ተሰብሯል” ብላለች።

    ዳኛው ኤሪክ ቤንትሊ “የሰው ልጅ ከሥሪቱ ደግ ነው ብዬ አምናለሁ። ሆኖም በየቀኑ እምነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ይገጥሙናል። ጆን ሀልፎርድ እምነታችንን ከፈተኑን አንዱ ነው” ብለዋል።

    ጆን ሀልፎርድ “ድርጊቴን ለማቆም ብዙ ዕድል ነበረኝ። ከትውልድ ትውልድ የሚያስተጋባ ስህተት ነው የፈጸምኩት” ሲል ይቅርታ ጠይቋል።

    አስከሬኖችን ያለ ኬሚካል እንደሚቀብር በመግለጽ ድርጅተን ቢያስተዋውቅም አስከሬኖች ማቀዝቀዣ ውስጥ ሳይገቡ ተከማችተው ተገኝተዋል።

  7. ትራምፕ በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ፈረሙ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ባላቸው አገራት ላይ ታሪፍ መጣል የሚያስችላቸውን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ትናንት አርብ የፈረሙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አገራቱ ከቴህራን ጋር መገበያየት የሚቀጥሉ ከሆነ ቀረጡን ሊጥሉ እንደሚችሉ ተናገሩ።

    ትራምፕ የፈረሙት ትዕዛዝ የሚጣለውን የታሪፍ መጠን በግልጽ ባይወስንም የ25 በመቶ የቀረጥ ምጣኔን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። ታሪፉ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድንም በተመለከተ እስካሁን ተጨማሪ ማብራሪያ አልተሰጠም።

    አዲሱ ትዕዛዝ ተፈጻሚ የሚሆነው "በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኢራን ማንኛውንም ዕቃ ወይም አገልግሎት ከሚገዙ፣ ወደ አገራቸው ከሚያስገቡ ወይም በሌላ መንገድ በሚያገኙ" አገራት ላይ ነው። እነዚህ አገራት ወደ አሜሪካ የሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ ታሪፍ ይጣላል።

    ትራምፕ ስለ አዲሱ ትዕዛዛቸው በቀጥታ አስተያየት አልሰጡም። ነገር ግን አርብ ምሽት በፕሬዝዳንታዊው ‘ኤር ፎርስ ዋን’ አውሮፕላን ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል፤ ኢራን "የኒውክሌር መሣሪያ ሊኖራት አይገባም" የሚለውን አቋማቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል።

    ፕሬዝዳንቱ ይህንን እርምጃ የወሰዱት ለሳምንታት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የቆዩት አሜሪካ እና ኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣኖቻቸውን ወደ ኦማን ልከው ንግግር እያካሄዱ ባለበት ወቅት ነው።

    ዋይት ሀውስ፤ አዲሱ ፕሬዝዳንታዊውን ትዕዛዝ "ከኢራን ጋር በተያያዘ የቀጠለውን ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን" የሚያረጋግጥ እንደሆነ ገልጿል። ፕሬዚዳንቱ ሁኔታዎች ሲቀየሩ ትዕዛዙን ሊያሻሽሉት እንደሚችሉም ጠቁሟል።

    የትራምፕን የታሪፍ ትዕዛዝ በተመለከተ እስካሁን ከኢራን በኩል አስተያት አልተሰጠም።

    አሜሪካ ባለፈው ሰኔ በኢራን ሦስት ዋና ዋና የኒውክሌር ተቋማት ላይ ቦምብ ከጣለች በኋላ ንግግር ሲያደርጉ የአርብ ዕለቱ የመጀመሪያው ነው።

    በኦማኑ ንግግር የኢራን ተደራዳሪ ልዑክ የተመራው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራግቺ ነው። የፕሩዝዳንት ትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ያሬድ ኩሽነር ደግሞ አሜሪካን ወክለዋል።

    ትራምፕ በአውሮፕላኑ ላይ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የአርብ ዕለቱን ንግግር "በጣም ጥሩ" ሲሉ ገልጸውታል። ኢራን "በጣም ስምምነት ላይ መድረስ የምትፈልግ ይመስላል" ብለዋል።

    "ስምምነት ላይ ካልደረሱ ግን ውጤቱ በጣም ከባድ ይሆናል" ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ሌላ ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

  8. የናይጄሪያ ፍርድ ቤት በቅኝ ግዛት ዘመን ለተገደሉ ማዕድን ቆፋሪዎች ብሪታንያ 567 ሚሊዮን ዶላር እንድትከፍል ወሰነ

    በቅኝ ግዛት ፖሊስ የተገደሉት ማዕድን ቆፋሪዎች መታሰቢያ ሐውልት

    የፎቶው ባለመብት, Centre for memories

    የምስሉ መግለጫ, በቅኝ ግዛት ፖሊስ የተገደሉት ማዕድን ቆፋሪዎች መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል

    የናይጄሪያ ፍርድ ቤት፤ የብሪታንያ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 1949 በቅኝ ግዛት አስተዳደር ለተገደሉ 21 የከሰል ማዕድን ቆፋሪዎች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 27 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል አዘዘ።

    አውሮፓውያን እና ናይጄሪያውያን አባላት ያሉት የወቅቱ የቅኝ ግዛት ፖሊስ፤ የሥራ ሁኔታቸው እንዲስተካከልላቸው የጠየቁ ሠራተኞችን በጥይት ደብድቦ ገድሏል።

    በርካታ ናይጄሪያውያንም በዚህ እርምጃ ጉዳት እንደደረሰባቸው በመንግሥት የሚመራው የናይጄሪያ የዜና አገልግሎት ዘገባ ያመለክታል።

    የከሰል ማዕድን ሠራተኞቹ አድማ የመቱት በስፍራው በነበራው አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ፣ በዘር ልዩነት ላይ በመሠረተው የደመወዝ ክፍያ እና ባልተከፈለ ውዝፍ ደመወዝ ምክንያት ነበር።

    የናይጄሪያው የዜና ወኪል፤ በብሪታንያ ቅኝ ግዛት አስተደዳር ሥር ከተፈጸሙት እጅግ አሳዛኝ የጭቆና ተግባራት አንዱ ሲል ይገልጿታል።

    ይህ ክስተት ከ11 ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1960 ነፃነት ላስገኘው የፀረ ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ማድረጉን ታሪክ ፀሐፊዎች ይናገራሉ።

    የሟቾች ቤተሰቦች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይህ የግፍ ድርጊት ይፋዊ ዕውቅና እንዲሰጠው እና ካሳ እንዲከፈልበት ለአስርት ዓመታት ሲታገሉ ቆይተዋል።

    አሁን ጉዳዩን የተመለከተው የአገሪቱ ፍርድ ቤት ጭፍጨፋው ሕገ ወጥ እና የሕይወት መብትን የጣሰ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ እንደሆነ መግለጹን የናይጄሪያ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    ክሱን የመሩት ዳኛ፤ የብሪታንያ መንግሥት ተጠያቂ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦችም ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ ወስነዋል።

    በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት የብሪታኒያ መንግሥት በድምሩ 567 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ለተጎጂ ቤተሰቦች መክፈል ይኖርበታል። ቢቢሲ የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ጠይቋል።

  9. የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር ተጠናቀቀ፤ እንደሚቀጥል ይጠበቃል

    የኢራን ተደራዳሪ ቡድን

    የፎቶው ባለመብት, @FMofOman

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ተደራዳሪ ቡድን

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ኦማን ውስጥ ዛሬ የተጀመረው ድርድር “ለጊዜው” መጠናቀቁን የኢራን መንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን አስታወቀ።

    በዛሬው ዕለት ስለተካሄደው ንግግር ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ ያልወጣ ሲሆን፣ ድርድሩ በመጪዎቹ ቀናት ስለመቀጠሉ የተባለ ነገር የለም።

    በአሜሪካ እና በኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኦማን ዋና ከተማ መስካት ውስጥ በአገሪቱ ባለሥልጣናት አሸማጋይነት መካሄድ የጀመረው ንግግር በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ወደ ግጭት የሚያመራ ውጥረት ያረገበ ነው።

    ነገር ግን በዚህ ድርድር ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መረሃ ግብሯን ለማቆም የማትስማማ ከሆነ አሜሪካ ወታደራዊ እርምጃ እንደምትወስድ በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ነበር።

    የተጀመረው ድርድር “የተራዘመ እና ለተከታታይ ቀናት” የሚደረግ እንደሚሆን የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ማሠራጫ ጣቢያ ዘግቧል።

    ተንታኞች ይህ ድርድር በጣም ወሳኝ እና ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው ሲሉ የተራዘመ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ግምታቸውን ገልጸዋል።

  10. በፓኪስታን መስጂድ ውስጥ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ተገደሉ

    በፍንዳታው የተጎዱ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል የሚወስድ አምቡላንስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ውስጥ በሚገኝ አንድ የሺዓ መስጂድ ለአርብ ጸሎት በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በተፈጸመ የፍንዳታ ጥቃት ቢያንስ 30 ሰዎች ተገደሉ።

    በመስጂድ ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ሆስፒታሎች የአደጋ ጊዜ ታውጆ የተጎዱ ሰዎችን አንዲያክሙ ተደርጓል።

    አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን እንዳስታወቁት በፍንዳታው ከተገደሉት ከ30 በላይ ሰዎች በተጨማሪ ከ160 በላይ ሰዎች የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

    የፍንዳታው ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ ዘገባዎች ግን ፍንዳታው በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት የተፈጠረ መሆኑን እያመለከቱ ነው።

    በመስጂድ ውስጥ ለጸሎት በተሰበሰቡ ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን የፍንዳታ ጥቃት የፓኪስታን ፕሬዝዳንት አሲፍ አሊ ዛርዳሪ በጽኑ አውግዘውታል።

    ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት “ንጹሃን ሰዎችን ዒላማ አድርጎ ጥቃት መፈጸም በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው።”

    ጨምረውም አጠቃላዩ የፓኪስታን ሕዝብ በጥቃቱ ከጎዱት ሰዎች ቤተሰቦች ጎን ይቆማሉ በማለት መናጋራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

  11. የኢራን እና የአሜሪካ ድርድር በቀጥታ በመገናኘት የሚደረግ እንዳልሆነ ተነገረ

    የአሜሪካ እና የኢራን ተደራዳሪዎች ከኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር

    የፎቶው ባለመብት, FMofOman

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ እና የኢራን ተደራዳሪዎች ከኦማን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር

    አሜሪካ ኢራን እያካሄደችው ነው ባለችው የኒውክሌር እና የሚሳዔል ግንባታ መርሃ ግብር ምክንያት በኢራን ላይ ልትሰነዝር የምትችለውን ጥቃት ለማስቀረት የታለመው ድርድር ኦማን ውስጥ ዛሬ አርብ ተጀምሯል።

    ነገር ግን አሁን ከድርድሩ ስፍራ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመልክቱት በሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል እየተደረገ ያለው የቀጥታ ንግግር አይደለም።

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ተወካይ በስቲቭ ዊትኮፍ እና በኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ የሚደረገው ንግግር በኦማን ዲፕሎማቶች አማካይነት የሚካሄድ እንደሆነ ተገልጿል።

    አሜሪካ በዚህ ድርድር ኢራን የኒውክሌር እና የሚሳዔል ግንባታዎቿን ለማቆም እንድትስማማ የምትፈልግ ሲሆን፣ ኢራን ግን በኒውክሌር መረሃ ግብሯ ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆኗን ገልጻ፤ የሚሳዔል ግንባታዋ ግን ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ አሳውቃለች።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከድርድሩ በፊት በሰጡት ቃል አገራቸው ከአሜሪካ በኩል የሚቀርቡ “ከልክ ያለፉ ጥያቄዎችን” አትቀበልም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    በስቲቭ ዊትኮፍ የሚመሩት የአሜሪካ ተደራዳሪዎች ወደ ኦማን በገቡበት ጊዜ የአገራቸው ወታደራዊ ኃይል ከኢራን ድንበሮች አቅራቢያ ከሳምንት በፊት ተሰማርቶ ይገኛል።

  12. አንድ የሩሲያ ከፍተኛ ጄነራል ሞስኮ ውስጥ በበርካታ ጥይቶች ተመትተው ሆስፒታል ገቡ

    ሌትናል ጄነራል ቭላድሚር አሌክሲየቭ

    የፎቶው ባለመብት, Russian Defence Ministry

    የምስሉ መግለጫ, ሌትናል ጄነራል ቭላድሚር አሌክሲየቭ

    ከፍተኛ የሩሲያ ወታደራዊ ጄነራል በዋና ከተማዋ ሞስኮ ውስጥ በበርካታ ጥይቶች ተመትተው እንደቆሰሉ ተዘገበ።

    ሌትናል ጄነራል ቭላድሚር አሌክሲየቭ በመኖሪያ ሕንጻ አካባቢ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ያሉበት ሁኔታ አልታወቀም።

    ጄነራሉ በሩሲያ ወታደራዊ አመራር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ መኮንን ሲሆኑ፣ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ በገባችባቸው ባለፉት አራት ዓመታት ዒላማ ከተደረጉ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መካከል የቅርብ ጊዜው ናቸው።

    ጄነራሉ በአውሮፓውያኑ 2018 በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከተፈጸመ የነርቭ ጋዝ ጥቃት ጋር በተያያዘ በአውሮፓ ኅብረት ዕቀባ ተጥሎባቸዋል።

    ሌትናል ጄነራል ቭላድሚር ሆስፒታል መግባታቸውን እና ስለጥቃቱ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል።

    ጄነራሉ በዩክሬን ጦርነት ውስጥ ጉልግ ሚና ያላቸው ሲሆን፣ በፑቲን ላይ አምጾ የነበረውን የቫግነር መሪ የቭጌኒ ፐሪጎዢንን ለማግባባት እንዲሁም በሌሎች ንግግሮች ውስጥም ተሳታፊ ነበሩ።

    ዛሬ አርብ ጠዋት ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ ማን እንዳለ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ከዚህ ቀደም በሩሲያ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ዩክሬን ኃላፊነቱን ወስዳ ነበር።

    ከሁለት ዓመት በፊት የሩሲያ የባዮሎጂካል እና ኬሚካል ጦር መሣሪያ መከላከያ ጦር አዛዥ የነበሩት ሌተናል ጄነራል ኢጎር ኪሪሎቭ ሞስኮ ውስጥ በመኪና ላይ በተጠመደ ቦንብ መገደላቸው ይታወሳል።

  13. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የድርድሩን ውጤት እየተጠባበቁ መሆኑን ጽሕፈት ቤታቸው አስታወቀ

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቬት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቬት

    አሜሪካ ከኢራን ጋር ዛሬ አርብ ኦማን ውስጥ በሚደረገው ድርድር ከስምምነት ሊደረስ ይችል እንደሆነ ለመወሰን ሂደቱን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርበት እንደሚከታተሉ ተነገረ።

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቬት ኦማን፣ መስካት ውስጥ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ሐሙስ ሌሊት በሰጡት መግለጫ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከንግግሩ ውጤት እንደሚጠብቁ አመልክተዋል።

    “ወዳጆቻችን ይሁኑ ጠላቶቻችን በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ፕሬዝዳንታችን ሁልጊዜም ዲፕሎማሲ የመጀመሪያ ምርጫቸው ነው” ብለዋል።

    ስለዚህም ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ ተወካያቸውን ስቲቭ ዊትኮፍ እና የልጃቸውን ባል ጃሬድ ኩሽነርን ለድርድር ልከዋል በማለት “ውጤቱ ምን ሊሆን እንደመችል የምናየው ነው። ፕሬዝዳንቱ ከተደራዳሪዎቻቸው ውጤቱን ለመስማት እየተጠባበቁ ነው።”

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይዋ እንዳሉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን መንግሥት የሚፈልጉት ነገር በጣም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው፤ እሱም ምንም ዓይነት የኒውክሌር አቅም እንዳይኖር ማድረግ ነው።”

    ካሮላይን ሌቬት ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ለኢራን ባለሥልጣናት አሜሪካ ሁሉም ዓይነት አማራጮች ስላሏት ከስምምነት እንዲደረስ ግልጽ የማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    “ድርድሩ ሊጀመር በተቃረበበት ጊዜ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዓለም ታሪክ በጣም ኃያሉ የጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆናቸው ከዲፕሎማሲው ባሻገር በርካታ አማራጮች እንዳሏቸው የኢራን መንግሥትን ላስታውስ እፈልጋለሁ።”

  14. አሜሪካ ከኢራን ጋር የምታደርገው ድርድር ከመጀመሩ በፊት ዜጎቿ ኢራንን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዘች

    አራቅቺ

    የፎቶው ባለመብት, FARS

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኦማን ለመሄድ ከቴህራን ሲነሱ

    በአሜሪካ እና በኢራን መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ኦማን ውስጥ የሚደረገው የመጀመሪያው ንግግር ሰዓታት ሲቀሩት የአሜሪካ ዜጎቿ ከኢራን ለቅቀው እንዲወጡ አስጠነቀቀች።

    ይህ ማስጠንቀቂያ የወጣው የአሜሪካ መንግሥት በተለይ ለኢራናውያን የተለያዩ መረጃዎችን በሚያቀርብበት “ዘ ዩናይትድ ስቴትስ ቨርቹዋል ኤምባሲ በተባለው” የበይነ መረብ እና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ነው።

    አሜሪካ ዜጎቿ ከመላው ኢራን ለቅቀው እንዲወጡ እንደምክንያት ያቀረበችው በአገሪቱ እየተጠናከረ ያለው የደኅንነት ጥበቃ እርምጃ፣ መንገዶች መዝጋት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት መቋረጥ እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥን ነው።

    ማስጠንቀቂያው ጨምሮም ትውልደ ኢራናዊ የሆኑ አሜሪካውያን አገሪቱን ለቅቀው በሚወጡበት ጊዜ ኢራን ጥምር ዜግነትን ሕጋዊ አድርጋ ስለማትቀበል የኢራን ፓስፖርታቸውን እንዲጠቀሙ መክሯል።

    ጨምሮም የአሜሪካ ዜጎች በኢራን ውስጥ የኢንተርኔት መቋረጡ ቀጣይ ሊሆን እንደሚችል አውቀው ችግር የማይፈጥርባቸው አማራጭ የግንኙነት ዘዴዎችን እንዲያመቻቹ እንዲሁም በመንገድ ጉዞ የኢራን አጎራባች ወደሆኑት አርሜኒያ ወይም ቱርክ እንዲወጡ መክሯል።

    አሜሪካ ዜጎቿ በአስቸኳይ ኢራንን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ የሰጠችው በኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ እንዲሁም በፕሬዝዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ ልጅ ባለቤት ጃሬድ ኩሽነር መካከል ኦማን ዋና ከተማ መስካት ውስጥ ውይይት በሚጀመምሩበት ዕለት ነው።

    ለሳምንታት ከተካሄደው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የኢራን መንግሥት የጣለውን የሞባይል፣ የመደበኛ ስልክ እና አገር አቀፍ የኢንተርኔት አገልግሎቶች እቀባ አስካሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው። የተለያዩ አየር መንገዶችም ወደ ኢራን እና ከኢራን የሚያደርጓቸውን በረራዎች ውስን አድርገዋል ወይም ሰርዘዋል።

  15. በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለው ሁኔታ “ሊፈነዳ የሚችል ነው” ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች

    ሰርጌይ ላቭሮቭ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ሰርጌይ ላቭሮቭ

    የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ያለውን ሁኔታ “ሊፈነዳ የሚችል” በማለት አደገኛነቱን ገለጹ።

    ላቭሮቭ ለሩሲያ መንግሥት ዜና አገልግሎት ታስ እንደተናገሩት፤ አገራቸው በኢራን እና በአሜሪካ መካከል አደራዳሪ ሆና መቅረብ እንደማትፈልግም ተናግረዋል።

    ሩሲያ “ያለውን ሁኔታ በመከታተል እና በመገምገም ላይ ናት” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ በድርድሩ ውስጥ ሚና እንደሌላት አመልክተዋል።

    ጨምረውም ኢራን ለሩሲያ የቅርብ አጋር እና ጎረቤት ናት በማለት “ሁኔታው እንዴት እዚህ እንደደረሰ በመረዳት በኩል ግድ የማይሰጠን አይደለንም። ሁኔታው ለኢራን ብቻ ሳይሆን ለመላው የመካከለኛው ምሥራቅ ጭምር አደገኛ ነው” ብለዋል።

    ሰርጌይ ላቭሮቭ በምሳሌ “በአካባቢው ባልሰታበ ሁኔታ ሊፈነዱ የሚችሉ ቦምቦች አሉ” በማለት “የትኛውም ስምምነት ላይ ከተደረሰ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለመርዳት ዝግጁ መሆናችንን ኢራኖች እና እስራኤሎች ያውቃሉ” ብለዋል።

  16. 459 ሕጻናት ላይ ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ተከሰሰ

    ግለሰቡ አውስትራሊያን ጨምሮ በ15 አገራት የሚገኙ 459 ሕጻናት ላይ ጥቃት ፈጽሟል

    የፎቶው ባለመብት, Getty

    የምስሉ መግለጫ, ግለሰቡ አውስትራሊያን ጨምሮ በ15 አገራት የሚገኙ 459 ሕጻናት ላይ ጥቃት ፈጽሟል

    በማኅበራዊ ሚዲያ እና የጌም መጫወቻ ድረ ገጾች አማካኝነት ሕጻናት ላይ ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ ተከሰሰ።

    የአውስትራሊያ ፖሊስ እንዳለው፤ ግለሰቡ አውስትራሊያን ጨምሮ በ15 አገራት የሚገኙ 459 ሕጻናት ላይ ጥቃት ፈጽሟል።

    የ27 ዓመቱ ግለሰብ በ596 ጥቃቶች የተከሰሰ ሲሆን፤ ጥቃት መፈጸሙን የሚያሳዩ ከ23 ሺህ በላይ ቪድዮዎች በኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎቹ ላይ መገኘታቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

    የክዊንስላንድ ፖሊስ መርማሪ ሱፐርኢንቴንደንት ዴንዘል ክላርክ “የተገኙት ምሥሎች እና ቪድዮዎች በርካታ ስለሆኑ ተጎጂዎችን ለመለየት ጊዜ ወስዷል” ብለዋል።

    እስካሁን 360 ተጎጂዎች የተለዩ ሲሆን ምርመራው እንደቀጠለ ነው። ጥቃት የደረሰባቸው ሕጻናት ወንዶች ከሰባት ዓመት እስከ 15 ዓመት ይሆናቸዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ እና የጌም መጫወቻ ድረ ገጾች ላይ ሕጻናት ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ምሥሎች እንዲነሱ የሚደርስባቸው ጫና እና ማስፈራሪያ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ፖሊስ ገልጿል።

    የተከሰሰው ግለሰብ በበይነ መረብ ላይ ራሱን እንደ ሴትም እንደ ወንድም በማቅረብ ሕጻናቱን ዒላማ ያደረገው በአውሮፓውያኑ ከ2018 እስከ 2025 እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።

  17. የአሜሪካ እና የኢራን መሪዎች በቀጥታ ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ፍንጭ ሰጡ

    ቫንስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በቀጥታ መነጋገር ካልቻሉ የሚደረገው ድርድር ውስብስብ እና አስቸጋሪ ያደርገዋል አሉ።

    የፕሬዝዳንት ትራምፕ ምክትል ቫንስ ሲሪየስኤክስኤም ከተባለው የአገራቸው ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ አገራቸው ከኢራን አንጻር ያላትን ፖሊሲ አንስተው ተናግረዋል።

    በተለይም በኢራን አጠቃላይ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ዋናው ሥልጣን ካላቸው ጠቅላይ መሪው ጋር ቀጥተኛ ንግግር ካልተደረገ በሌሎች የአገሪቱ ባለሥልጣናት በኩል የሚደረገው ድርድር አስቸጋሪ እንደሚሆን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    "በኢራን ውስጥ ዋነኛው ውሳኔ ሰጪ የእስላማዊው ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ ነው። ስለዚህም በተግባር ሲታይ ፕሬዝዳንቱ ውስን ሚና ነው ያለው።

    “አሁን ግንኙነት እያደረግን ያለነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኩል ነው ከጠቅላይ መሪው ጋር እየተነጋገርን ያለነው። አገሪቱን በተግባር እየመራ ካለው ሰው ጋር በቀጥታ መነጋገር አይቻልም፤ ይህም ከእንዲህ ያለው አገር ጋር የሚዲረግ ዲፕሎኣመሲ በታም አስቸጋሪ ነው።” ሲሉ ቫንስ ተናግረዋል።

    ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ጨምረውም ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከአቻዎቻቸው ከቭላድሚር ፑቲን እና ከ ዢ ጂንፒንግ ጋር እንዳደረጉት ሁሉ ከኢራን ጠቅላይ መሪ ጋር በቀጥታ በስልክ የመነጋገር ዕድል እንዳለ አመልክተዋል።

    "ከኢራን ዋነኛ መሪ ጋር በቀጥታ መነጋገር አለመቻሉ በእውነት ኣልተለመደ እና የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው” በማለት የኢራን መሪ ከአሜሪካ መሪ ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ዕድል እንዳለ ፍንጭ ሰጥተዋል።

  18. በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ስልክ እና ኢንተርኔት ለቀናት ተቋረጠ

    የኢንተርኔት አገለግሎት እንደሌለ የሚያሳይ መልዕክት የሚታይበት የሞባይል ስክሪን

    በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ የሰሜን ሸዋ ከተሞች የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ነዋሪዎች እና የኢትዮቴሌኮም የአካባቢው የኃላፊ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናገሩ።

    ቢቢሲ ያነጋገራቸው በደገም፣ ኩዩ፣ ሂዳቡ አቦቴ እና ዋራ ጃርሶ የሚኖሩ ግለሰቦች የስልክ እና የኢንተርኔት አገልገሎት የተቋረጠረው ካለፈው እሁድ ጀምሮ መሆኑን ተናግረዋል።

    ቢቢሲ በኩዩ እና ዋራ ጃርሶ ወረዳዎች እንዲሁም በሂዳቡ አቦቴ ወደሚገኙ ነዋሪዎች በመደወል ሰዎችን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም የስልክ አገልግሎቱ እየሠራ አለመሆኑን አረጋግጧል።

    የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጠባቸው ወረዳዎች የፀጥታ ችግር ያለባቸው የሰሜን ሸዋ ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ችግሩ የተከሰተው የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎቹ ላይ እኣካሄዱት ባለው ዘመቻ ሊሆን ይችላል።

    በአካባቢው የኢትዮ ቴሌኮም ኃላፊ በተጠቀሱት ወረዳዎች የሞባይል ስልክ እና የዳታ አገልግሎት መቋረጡን አረጋግጠዋል።

    ኃላፊው የአገልግሎቶቹ መቋረጥ ምክንያት ምን እንደሆነ አልገጹም።

    በተጨማሪም ኃላፊው ረቡዕ ዕለት በሰጡት ቃለ ምልልስ አገልግሎቱ ከተቋረጠ ሦስተኛ ቀን መሆኑን ገልጸው፣ የሞባይል ስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች እንደተቋረጡ፤ ነገር ግን መደበኛ ስልኮች እና የዋይፋይ አገልግሎቶች እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    የተቋረጠው የስልክ አገልግሎት መቼ እንደሚመለስ አይታወቅም።

    የሰሜን ሸዋ በተለይም የስልክ አገልግሎት አሁን የተቋረጠባቸው ወረዳዎች፣ መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት የሚፈጽሙባቸው ናቸው።

    በዚህም ምክንያት ላለፉት አራት ዓመታት እነዚህ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ዝርፊያ፣ የንብረት ውድመት፣ ግድያ እና መፈናቀል መከሰቱ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ነበር።

    ወረዳውን የሚያቋርጠው ዋና መንገድ ላይም እንዲሁ ታጣቂዎች ብዙውን ጊዜ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም ተሳፋሪዎችን ይዘረፋሉ፣ ያግታሉ።

  19. ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን ለመነጋገር ከተስማሙ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳየ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና የኢራኑ የበላይ መሪ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters/Getty Images

    አሜሪካ እና ኢራን አርብ ዕለት በኦማን ንግግር ለመጀመር ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ በ2 በመቶ ቅናሽ አሳየ።

    የሁለቱ አገራት ዳግም ተገናኝቶ ለመወያያት መስማማት አሜሪካ ኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚለውን ስጋት አርግቦታል።

    በዚህም የተነሳ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ነዳጅ አቅራቢ አገራት መካከል አንጻራዊ የነዳጅ ገበያ መረጋጋት ታይቷል።

    የነዳጅ ዋጋ ከሦስት ቀን በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ቅናሽ ያሳየው ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለድርድር ለመቀቀመጥ ዝግጁ መሆኗን ካሳወቀች በኋላ ነው።

    የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 4.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ የነበረ ሲሆን የሁለቱ አገራት ውይይት ከተሰማ በኋላ ግን ወደ 68 ዶላር ወርዷል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ አርብ ዕለት በኦማን ንግግር እንደሚጀመር ተናግረዋል።

    አሜሪካ እና ኢራን በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ገና ከስምምነት አልደረሱም።

    ኢራን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኗ ሲገለጽ፣ ትራምፕ ግን በባሌስቲክ ሚሳዔሎቿ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ስለምትደግፋቸው ታጣቂ ቡድኖች መወያየት እንደሚፈልጉ ተገልጿል።

    ኢራን የዓለማችን አራተኛዋ ግዙፍ ነዳጅ አምራች አገር ናት።

    ትራምፕ በአገሪቱ ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ ከሆነ የባህረ ሰላጤው አገራትን የነዳጅ ምርት እና አቅርቦት ያስተጓጉላል።