ቀጥታ, የአሜሪካ ጦር ከዛሬ ጀምሮ የኢራን ወደቦችን እንደሚዘጋ ሲገልጽ ትራምፕ ቴህራን ወደ ድርድሩ ባትመለስ “ግድ እንደማይሰጣቸው” ተናገሩ

የአሜሪካ ጦር የኢራን ወደቦችን ከሰኞ ጀምሮ እንደሚዘጋ ገልጾ ነገር ግን በወሽመጡ ላይ ወደ ሌላ አገራት የሚንቀሳቀሱ መርከቦቸን ላይ “መስተጓጎል እንደማይፈጥር” አስታውቋል። ትራምፕ በበኩላቸው በዋሺንግተን አቅራቢያ በሚገኘው የአንድሪው የጦር ሠፈር ለጋዜጠኞች ኢራን ወደ ድርድሩ ባትመለስ “ምንም እንደማይሰማቸው” ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ትራምፕ በኢራን ላይ ዳግም ጥቃት ለመክፈት እያጤኑ መሆኑን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ

    አሜሪካ እና ኢራን በፓኪስታን ያካሄዱት ድርድር ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ትራምፕ ቴህራን ላይ ዳግም ጥቃት የመክፈት ሃሳብ እንዳላቸው ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ዎል ስትሪት ጆርናል ስማቸውን ያልገለጻቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ ከሌሎች እርምጃዎች በተጨማሪ ኢራን ላይ ድብደባ ለመጀመር እያጤኑ መሆኑን ዘግቧል፥።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት የባሕር ኃይላቸው የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

    ዋይት ሐውስ ቢቢሲ ስለ ጋዜጣው ዘገባ ላቀረበው ጥያቄ ሁሉም አማራጮች ጠረጴዛ ላይ ናቸው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

    የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ኦሊቪያ ዌልስ “ፕሬዚዳንቱ የሆርሙዝ ወሽመጥን እንዲዘጋ ባሕር ኃይሉን አዝዘዋል። የኢራንን ዝርፊያ ያበቃል እና ሁሉንም ተጨማሪ አማራጮች በጠረጴዛው ላይ ተቀምጠዋል። ለዎል ስትሪት ጆርናል ፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ የሚያደርጉትን መረጃውን የሰጠ ማንኛውም ሰው በግልጽ ግምቱን ነው ያስቀመጠው” ብለዋል።

  2. ትራምፕ ኢራን አሁንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ትፈልጋለች አሉ

    ኢራን እና አሜሪካ ያካሄዱት ድርድር ያለ ምንም ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ትራምፕ ቴህራን አሁንም የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፍላጎት አላት ሲሉ ተናገሩ።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኢራን አሁንም የኒውክሌር ፍላጎት እንዳላት በኢዝላማባድ ድርድር ወቅት መናገሯን ጠቅሰዋል።

    “አሁንም ይፈልጋሉ፤ ይህንን ደግሞ የዚያን ዕለት ምሽት [ድርድር በተካሄደበት ዕለት] ግልጽ አድርገዋል። ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሊኖራት አይችለም።”

    ከዚህ በፊት ትራምፕ ከቴህራን ጋር ያደረጉት የቀጥታ ንግግር ያልተሳካውቴህራን “የኒውክሌር ፍላጎቶቿን ለመተው ፈቃደኛ ሳትሆን ስለቀረች ነው” ብለዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በበኩላቸው ሁለቱ አገራት ከስምምነት ለመድረስ “ስንዝር ቀርቷቸው ነበር” ካሉ በኋላ ነገር ግን አገራቸው “የተለጠጠ ፍላጎት፣ የግብ ለውጥ፣ የወደብ መዝጋት” እንደገጠማት ተናግረዋል።

  3. አሜሪካ የኢራን ወደቦቸን ከሰኞ ጀምሮ እንደምትዘጋ አስታወቀች

    የአሜሪካ ጦር የኢራን ወደቦችን ከሰኞ ጀምሮ እንደሚዘጋ ገልጾ ነገር ግን በወሽመጡ ላይ ወደ ሌላ አገራት የሚንቀሳቀሱ መርከቦቸን ላይ “መስተጓጎል እንደማይፈጥር” አስታውቋል።

    ትራምፕ በበኩላቸው በዋሺንግተን አቅራቢያ በሚገኘው የአንድሪው የጦር ሠፈር ለጋዜጠኞች ኢራን ወደ ድርድሩ ባትመለስ “ምንም እንደማይሰማቸው” ተናግረዋል።

    “ተመለሱ አልተመለሱ ግድ አይሰጠኝም። ካልተመለሱም ችግር የለብኝም” ብለዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት በሁለቱ አገራት መካከል በፓኪስታን ኢዝላማባድ የተደረገው የቀጥታ ንግግር ሳይሳካ ከቀረ በኋላ ነው።

    ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም “በመልካም ሁኔታ እንደቀጠለ” መሆኑን ተናግረዋል።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ወደ ኢራን ወደቦች የሚገቡ እና የሚወጡ መርከቦችን ሰኞ ዕለት ከ11 ሰዓት ጀምሮ (14:00 GMT) እንደሚዘጋ አስታውቋል።

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን “ሆን ብላ” የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም ሳትከፍት ቀርታለች ካሉ በኋላ ወደቦቹ አንዲዘጉ አዝዘዋል።

    ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚሞክር “መዓት እንደሚወርድበት” አስታውቀው ማንኛውም መርከብ በወሽመጡ ላይ ለማለፍ ቀረጥ እንዳይከፍል አስታውቀዋል።

    በአሜሪካ እና በኢራና መካከል በፖኪስታን የተደረገው ድርድር ሳይሳካ ቀርቶ ዳግም የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ መሸጥ ጀምሯል።

    ትራፕም ከኢራን ጋር የተደረገው የቀጥታ ንግግር ያልተሳካለው “ኢራን የኒውክሌር ፍላጎቷን ለመተው ፈቃደኛ ሳትሆን ስለቀረች ነው” ሲሉ ወንጅለዋታል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በበኩላቸው ቴህራን “በቀና ልብ” በድርድሩ ላይ መሳተፏን ሲናገሩ የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋልቢፍ ደግሞ ኢራን “ለማስፈራሪያዎች አትንበረከክም” ብለዋል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ ወደ ወሽመጡ የሚጠጉ መርከቦች የተኩስ አቁሙን እንደጣሱ ይቆጠራሉ ሲል አስጠንቅቋል።