ቀጥታ, ኢራን በፍጥነት ወደ ድርድር ካልመጣች “ከባድ ጥቃት” እንደሚጠብቃት ትራምፕ አስጠነቀቁ

ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ማስጠንቀቂያ ወደ ባሕረ ሰላጤው ያሰማሩትን ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ጫኝ መርከብን እና ሌሎችንም በመጥቀስ፣ አስፈላጊ ሲሆን “በፍጥነት እና በአደገኛ ሁኔታ” የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸ ምዝግጁ መሆናቸውን ተቁመዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ኢራን በፍጥነት ወደ ድርድር ካልመጣች “ከባድ ጥቃት” እንደሚጠብቃት ትራምፕ አስጠነቀቁ

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር በአስቸኳይ ስምምነት ላይ ካልደረሰች ከአሜሪካ የሚገጥማት ቀጣዩ ጥቃት ከዚህ በፊት ከነበረው “በጣም የከፋ ይሆናል” ሲሉ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዝዳንቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ማስጠንቀቂያ ወደ ባሕረ ሰላጤው ያሰማሩትን ግዙፍ የጦር አውሮፕላን ጫኝ መርከብን እና ሌሎችንም በመጥቀስ፣ አስፈላጊ ሲሆን “በፍጥነት እና በአደገኛ ሁኔታ” የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመፈጸ ምዝግጁ መሆናቸውን ተቁመዋል።

    በቬንዙዌላ ላይ የወሰዱትን እርምጃ ያነሱት ትራምፕ፤ ኢራን ጊዜው እየሄደባት እንደሆነ እና የኒውክሌር መረሃ ግብሯን በተመለከተ በፍጥነት “ወደ ድርድር ጠረጴዛ” ትመጣለች ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

    ቀደም ሲል “ወደ ድርድር መጥተው ከስምምነት እንዲደርሱ ነግሬያቸው ነበር፤ ነገር ግን አልመጡም” በማለት ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት መከተሉን ገልጸዋል።

    የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአገራቸው መገናኛ ብዙኃን ምንም ዓይነት ንግግር አንዳልተጀመረ፤ ነገር ግን ከአቀራራቢ አገራት ጋር ግንኙነት መጀመሩን ጠቁመዋል።

    ይህ የትራምፕ ማስጠንቀቂያ የተሰማው አብርሃም ሊንከን የተባለው ግዙፍ የጦር መርከብ እና በርካታ ተዋጊ መርከቦች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ባለፈው ሳምንት ተነስተው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ከደረሱ በኋላ ነው።

    ኢራን ውስጥ ከተከሰተው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ ከባድ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ትራምፕ ሲዝቱ ቆይተው ተቃውሞው ጋብ ብሏል።

    አሁን ደግሞ የኢራን ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ያስተባበሉትን እና ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ ነው የሚውል ነው የሚሉትን የኒውክሌር ግንባታቸውን በተመለከተ በፍጥነት ወደ ድርድር ቀርበው ካተልስማሙ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ምትፈጽም ከሆነ በምትሰጠው የአጸፋ ምላሽ ቀጣናዊ ግጭት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት በባሕረ ሰላጤው አገራት ዘንድ ተጠናክሯል። በዚህ ሳቢያም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ታይቶበታል።

  2. ኢኳዶር የአይስ ፖሊስ ወደ ቆንስላ ጽ/ቤቷ ለመግባት መሞከሩን አስታወቀች

    የአይስ ፖሊስ ባጅ ያለበት ልብስ

    የፎቶው ባለመብት, Jim Watson - Pool/Getty Images

    የኢኳዶር መንግሥት የአሜሪካ የፌዴራል ስደተኞች ቁጥጥር ፖሊስ ሚኒያፖሊስ ወደ ሚገኘው ቆንስላ ለመግባት ሞክሯል በሚል ወቀሳውን አሰማ።

    ፖሊሱ "ቆንስላው ውስጥ ያሉ ኢኳዶራዊያንን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል" ወደ ውስጥ ዘልቆ እንዳይገባ መከልከሉን የኢኳዶር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።

    ፕሬዝደንቷ የትራምፕ ወዳጅ የሆኑት ኢኳዶር ይፋዊ ቅሬታዋን አቅርባለች።

    ከቀናት በፊት አሌክስ ፕሬቲ የተባለ አሜሪካዊ ዜጋ በአይስ ፖሊሶች መገደሉን ተከትሎ በሚኒያፖሊስ ከተማ አመፅ በተነሳበት ወቅት ነው ይህ የተሰማው።

    የኢኳዶር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የአሜሪካ የስደተኞች እና የጉምሩክ አስፈፃሚ ኤጀንሲ (አይስ) ፖሊስ ማክሰኞ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ጥዋት 5፡00 "ወደ ቆንስላው ለመግባት ሞክሯል" ብሏል።

    በአውሮፓውያኑ 1963 በፀደቀው በቪየና ኮንቬንሽን የቆንስላ ግንኙነት መመሪያ መሠረት ቆንስላ ጽ/ቤቶች "የማይጣሱ" ናቸው።

    መመሪያው እንደሚለው ቆንስላው ያለበት ሀገር ባለሥልጣናት "ከቆንስላው ኃላፊ ፈቃድ ካልተሰጣቸው በቀር" ወደ ቅጥር ግቢው "መግባት አይችሉም።"

    በኢኳዶር መገናኛ ብዙኃን የተዘዋወረ ቢቢሲ በግሉ ያላጣራው ቪድዮ የአይስ ፖሊስ ወደ ቆንስላው ለመግባት ሲሞክር እና የቆንስላው ሠራተኛ "ይህ ቆንስላ ነው መግባት አትችልም" ሲለው ያሳያል።

    የአይስ ፖሊስ የሆነው ግለሰብ የቆንስላውን ሠራተኛ "ከነካኸኝ እይዝሀለሁ" ሲለው ይሰማል።

    የቆንስላው ባልደረባ "እዚህ መግባት አትችልም፤ ይህ ቆንስላ ነው፤ የውጭ መንግሥት ቢሮ ነው" ብሎ በሩን ይዘጋበታል።

    የኢኳዶር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይፋዊ የተቃውሞ ደብዳቤ በዋና ከተማዋ ኩዊቶ ለሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማስገባቱን ገልጿል።

    ከሁለት ወራት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢኳዶሩ አቻቸው ዳንኤል ኖቦዋ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

  3. ጋና ለታዋቂው ዩቲዩበር አይሾውስፒድ ፓስፖርት እንደምትሰጥ አስታወቀች

    ታዋቂው አሜሪካዊ ዩቲዩበር እና ስትሪመር አይሾውስፒድ

    የፎቶው ባለመብት, CLIFFORD OWUS PEPRAH

    ጋና ለታዋቂው አሜሪካዊ ዩቲዩበር እና ስትሪመር አይሾውስፒድ ፖስፖርት እንደምትሰጥ አስታወቀች።

    የአያቶቹ ሀገር የሆነችው ጋና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣቸው መግለጫ "አይሾውስፒድ ከጋና ጋር ያለው ግነኙነት መጣራቱን ተከትሎ" ፓስፖርት እንደሚሰጠው አስታውቃለች።

    የ21 ዓመቱ ታዋቂ ዩቲዩበር በአህጉረ አፍሪካ ለ28 ቀናት የሚቆይ ጉብኝት እያደረገ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ናይጄሪያ፣ ደቡበብ አፍሪካ እና ሞሮኮ ከጎበኛቸው ሀገራት መካከል ናቸው።

    በመዝገብ ስሙ ዳረን ዋትኪንስ ጁኒየር በመባል የሚታወቀው ዩቲዩበር "ስፒድ በአፍሪካ" በተሰኘው ጉብኝቱ በርካታ አድናቂዎቹ በተሰበሰቡበት የየሀገራቱን ባሕል እና የቱሪስት መዳረሻዎች ጎብኝቷል።

    ሰኞ ወደ ጋና ያቀናው ስፒድ "ወደ ቤቴ መጥቻለሁ" ሲል ደስታውን የገለፀ ሲሆን፣ ታዋቂ ሥፍራዎችንም እየተዘዋወረ ተመልክቷል።

    በዩቲዩብ ገፁ ከ50 ሚሊዮን በላይ ተከታዮች ያሉት ስፒድ ወደ ምሥራቃዊ ጋና አቅንቶ በባሕላዊ መንገድ "ባሪማ ኮፊ አኩፎ" የተባለ ስም ወጥቶለታል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሙኤል ኦኩዜቶ አብላክዋ ጋናዊው ታዋቂ ዩቲዩበር ዎዴ ማያን ጨምረው አድንቀው "ጋና ሁለታችሁንም ታከብራለች። የኛ አምባሳደሮች ናችሁ" ሲሉ ማያን እና ስፒድን አወድሰዋል።

    ጋናዊው ዩቲዩበር ዎዴ ማያ፤ አይሾውስፒድ አዲስ አበባን ከመጎብኘቱ ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የተለያዩ ስፍራዎችን የሚያስጎበኝ ይዘት በዩቲዩብ ገፁ መልቀቁ ይታወሳል።

    ጋና ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 2024 ጀምሮ ለ500 አፍሪካዊያን ዳያስፖራዎች ፓስፖርት የሰጠች ሲሆን፣ አብዛኞቹ አፍሪካዊያን አሜሪካዊያን ናቸው።

  4. ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ጥያቄ አላቀረብኩም አለች

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የኢራኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት አለመጀመራቸውን ተናገሩ።

    የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው አባስ ከአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋርም አልተገናኙም።

    የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ሌሎች ግዙፍ የጦር መርከቦች ወደ ኢራን እየተጠጉ እንደሆነ ተናግረው፤ ቴህራን ከዋሺንግተን ጋር ስምምነት እንደምትፈፅም ተስፋቸውን ገልፀዋል።

    ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከአውሮፓውያኑ 1979 እስላማዊው አብዮት በኋላ ደም አፋሳሽ የተባለለት ተቃውሞ በኢራን መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ ወደ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ ተጨማሪ ወታደራዊ መርከቦችን አሰማርታለች።

    "በእኔ እና ዊትኮፍ መካከል ባለፉት ቀናት የተደረገ ምንም ግንኙነት የለም። እኛ ለድርድር ጥያቄም አላቀረብንም" ሲሉ አራቅቺ መናገራቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

    ነገር ግን የተለያዩ አደራዳሪዎች "ምክክር እያደረጉ እና ከኢራን ጋር ግንኙነት እያደረጉ መሆኑን" መናገራቸውን የሮይተርስ ዜና ወኪል ዘገባ ያሳያል።

    "አቋማችን ግልፅ ነው። ድርድር ከማስፈራራት ጋር አብሮ አይሄድም። ንግግር ሊኖር የሚችለው እብደት እና ከአቅም በላይ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ከሌሉ ነው" ብለዋል።

    የኢራኑ ፕሬዝደንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ማክሰኞ ቴህራን ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ እንዲሁም ጦርነትን ማራቅ የሚችል የትኛውም ዓይነት ሒደትን ትቀበላለች ሲሉ ለሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን እንደተናገሩ ሮይተርስ ዘግቧል።

  5. በኢልሃን ኦማር ላይ ምንነቱ ያልታወቀ ፈሳሽ የረጨው ግለሰብ በጥቃት ወንጀል ተከሰሰ

    የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ቪዲዮ፦ የሚኒሶታ ተወካይ በሆነችው ኤልሃን ኦማር ላይ ጥቃት የተፈጸመበትን ቅጽበት ይመልከቱ

    የሚኒሶታ ግዛት የኮንግረስ ተወካይ በሆነችው የኢልሃን ኦማር ላይ ምንነቱ ያልታወቀ ፈሳሽ በመርጨት ጥቃት የፈጸመው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የአካባቢው የፖሊስ ኃላፊዎች አስታወቁ። ግለሰቡ ድርጊቱን የፈጸመው ኢልሃን በከተማ አዳራሽ ውስጥ ንግግር እያደረገች ባለበት ሰዓት ነው።

    ግለሰቡ በድንገት ተነስቶ በመርፌ ስሪንጅ የያዘውን ፈሳሽ ረጭቶባታል። ስፍራው ላይ የነበረው የቢቢሲ ዘጋቢ፤ ፈሳሹ የሚሰነፍጥ ሽታ ያለው ኬሚካል መሰል ነገር እንደሆነ ገልጿል።

    ፖሊስ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው አንቶኒ ጄምስ ካዝሚርቻክ የተባለው ይህ ግለሰብ 55 ዓመቱ ነው። ግለሰቡ ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር ውሎ ስፍራው ላይ የፎረንሲክ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል። በሦስተኛ ደረጃ የጥቃት ወንጀል መከሰሱንም ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

  6. ኢራን ለእስራኤል ‘ሲሰልል’ ነበር የተባለ ግለሰብን በሞት ቀጣች

    ቀይ አበባ ሸምቀቆው ላይ የተቀመጠባቸው መስቀያ ገመዶች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለእስራኤል የስለላ ተቋም ሞሳድ ኢራን ውስጥ ሲሰልል ከወራት በፊት ተይዟል ተብሎ በቁጥጥር ሥር የነበረ አንድ ግለሰብ በሞት መቀጣቱን የኢራን መንግሥት አስታወቀ።

    ‘ሚዛን’ የተባለው የኢራን የፍትሕ ተቋማት የዜና ምንጭ እንደዘገበው ሃሚድሬዛ ሳቤት ኢስማኤልፑር የተባለው ግለሰብ ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ ነበር በስለላ ተከስሶ የተያዘው።

    የኢራን ፍትሕ ተቋም እንዳለው ግለሰቡ እስራኤል በአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር የሚሳዔል ማዕከላት ላይ አሻጥር እንድትፈጽም ምሥጢራዊ ሰነዶችን እና መረጃዎችን ማስተላለፍ ውስጥ ተሳትፏል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

    በወጣው ዜና ላይ እንደተጠቀሰው የኢራን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በግለሰቡ ላይ ያሳለፈው የቅጣት ውሳኔ ከተገመገመ በኋላ ግለሰቡ በስቅላት ተቀጥቷል።

    አሁን የሞት ቅጣቱ የተፈጸመበት ሃሚድ ሬዛ ሳቤት ኢስማኤልፑር ለእስራኤል በመሰለል በሚል ክስ በዚህ ወር በሞት የተቀጣ ሁለተኛው ሰው ነው።

    ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ እስራኤል እና ኢራን ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ለእስራኤል ሲሰልሉ ነበር በሚል ተከስሰው በሞት የተቀጡ ኢራናውያን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

  7. ስፔን ለግማሽ ሚሊዮን ሰነድ አልባ ስደተኞች ሕጋዊ ዕውቅና ልትሰጥ ነው

    መድረክ ላይ የቆሙ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Europa Press via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, 'ፖዴሞስ' የተባለው ቀኝ አክራሪ ፓርቲ "ወደ ሕጋዊ ማዕቀፍ መግባት መብት ነው" በሚል መፈክር ለሰነድ አልባ ስደተኞች ዘመቻ ሲያካሂድ ነበር

    የስፔን መንግሥት ሕጋዊ ሰነድ ለሌላቸው ስደተኞች ሕጋዊ ዕውቅና የመስጠት ዕቅድ እንዳለው አስታወቀ። የአገሪቱ መንግሥት ይፋ ያደረገው ይህ እርምጃ ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

    ሕጋዊ ዕውቅና የሚሰጠው የወንጀል ሪከርድ ለሌለባቸው እና ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 31 ቀን 2025 በፊት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ቢያንስ ለአምስት ወራት በስፔን መኖራቸውን ማረጋገጥ ለሚችሉ የውጭ አገር ዜጎች እንደሆነ ተገልጿል።

    የስፔን የማካተት፣ ማኅበራዊ ዋስትና እና ፍልሰት ሚኒስትር የሆኑት ኤልማ ሳይዝ፤ "ይህ ለአገራችን ታሪካዊ ቀን ነው" ብለዋል።

    በአገሪቱ መንግሥት ዕቅድ መሠረት፤ የእርምጃው ተጠቃሚ የሚሆኑ ስደተኞች በመጀመሪያ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የመኖሪያ ፈቃድ የሚሰጣቸው ሲሆን ጊዜው ሲጠናቀቅ ሊራዘምላቸው ይችላል።

    መንግሥት፤ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ለመግባት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መቀበል የሚጀምረው ከሚያዝያ አንስቶ እንደሆነ ተገልጿል። እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስም ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

    ስፔን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዋነኛነት ከላቲን አሜሪካ የሚመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛለች።

    'ፉንካስ' (Funcas) የተባለው የወግ አጥባቂ የቲንክ ታንክ ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በአውሮፓውያኑ 2017 ስፔን የሚገኙ ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ቁጥር 107,409 ነበር። በተጠናቀቀው 2025 ይህ ቁጥር የስምንት እጥፍ ጭማሪ በማሳየት ወደ 837,938 ከፍ ብሏል።

    ስፔን ውስጥ ከሚገኙት ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ከኮሎምቢያ፣ ፔሩ እና ሆንዱራስ የሄዱ ሰዎች እንደሆኑ ይታመናል።

    በሶሻሊስት ፓርቲ የሚመራው የስፔን ጥምር መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ የያዘው አቋም ከትልልቅ የአውሮፓ አገራት ፖሊሲ የተለየ ነው። የአገሪቱ መንግሥት ስደተኞች ለስፔን ኢኮኖሚ ላላቸው ጠቀሜታ አጽንኦት ይሰጣል።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስፔን ከሌሎች ዋና ዋና የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የተሻለ የኢኮኖሚ አፈጻጸም እያስመዘገበች ነው። የስፔን ኢኮኖሚ የረዥም ጊዜ ተግዳሮት የነበረው ሥራ አጥነት ከ2008 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ10% በታች እንደወረደ ማክሰኞ ዕለት የወጡ መረጃዎች አሳይተዋል።

  8. በኢራን ተቃውሞ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሺህ መብለጡ ተነገረ

    በተቃውሞው ወቅት ከተገደሉ ሰዎች መካከል የተወሰኑት አስከሬኖች ተሸፍነው ይታያሉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በተቃውሞው ወቅት ከተገደሉ ሰዎች መካከል የተወሰኑት አስከሬኖች ተሸፍነው ይታያሉ

    የኢራን የሰብአዊ መብቶች ዜና ተቋም አዲስ ባወጣው ሪፖርት ባለፉት ሳምንታት በአገሪቱ ውስጥ በተካሄዱ ተቃውሞዎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሺህ በላይ መሆኑን ገለጸ።

    መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የመብት ተቆርቋሪ ቡድኑ እያሰባሰበ ባለው መረጃ እስካሁን 6,126 ሰዎች መገደላቸውን እንደደረሰበት አስታውቋል። ከሟቾቹ መካከል ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ 86 ታዳጊዎች እንደሚገኙበት እና 214 የመንግሥት የፀጥታ አባላትም መገደላቸውን አመልክቷል።

    የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል በመጥቀስ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የሞቱ ሊሆኑ ይችላሉ በሚባሉ ወደ 17 ሺህ በሚደርሱ ሰዎች ሞት ላይ ተቋሙ ምርመራ እያካሄደ ነው።

    ለሦስት ሳምንታት በዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢራን ባለሥልጣናት ባለፈው ሳምንት አረጋግጠዋል።

    ከተገደሉት በተጨማሪም 11,009 ሰዎች በከባድ ሁኔታ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና 41,880 የሚሆኑ ደግሞ በመንግሥት ኃይሎች ተይዘው በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

    የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች መንግሥት በኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች ላይ የመንግሥት ቁጥጥር መቀጠሉን፣ ሰዎች በስፋት በፀጥታ ኃይሎች እየተያዙ መሆናቸውን እና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሕክምና የማግኘት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ መሆኑን እያመለከቱ ነው።

    የተባበሩት መንግሥታት ተወካይ የሆኑት ማያ ሳቶ የቆሰሉ ሰዎች ከሕክምና ማዕከላት ወደ እስር ቤቶች እየተዘዋወሩ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እንደደረሷቸው ቢገልጹም የኢራን የእስር ቤት ባለሥልጣናት ግን አስተባብለዋል።

    ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ የኢንተርኔት እና ሌሎች የግንኙነት መስመሮች መዘጋታቸው ትክክለኛውን የተገደሉ፣ ጉዳት የደረሰባቸው እና የታሰሩ ሰዎችን አሃዝ ማግኘት አዳጋች እንዳደረገው የመብት ድርጅቶች ይናገራሉ።

    በቅርቡ የተከሰተው ተቃውሞ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ሥልጣናት ላይ በቆየባቸው ባለፉት 47 ዓመታት ውስጥ ከተካሄዱት ከፍተኛው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉበት እንደሆነ ይነገራል።

  9. ኢልሃን ኦማር ‘ምንነቱ ባልታወቀ ፈሳሽ’ ጥቃት ደረሰባቸው

    የሚኒሶታ የኮንግረስ አባል ኤልሀን ኦማር

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የሚኒሶታ የኮንግረስ አባል ኤልሃን ኦማር

    የሚኒሶታ የኮንግረስ አባል የሆኑት ኢልሃን ኦማር በማዘጋጃ ቤት ሳሉ ‘ምንነቱ ባልታወቀ ፈሳሽ’ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የግዛቱ ፖሊስ አስታወቀ።

    ከታዳሚዎች አንደኛው ስሪንጅ በመጠቀም ምንነቱ ያልታወቀውን ፈሳሽ ኤልሃን ኦማር ላይ እንደረጨ ተገልጿል።

    ኢልሃን ኦማር ጉዳት ሳይደርስባቸው “ወደፊት እንቀጥላለን. . . የሚኒሶታ ነዋሪዎች ጠንካራ ነን” በማለት ንግግር ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ፤ ግለሰቡን ፖሊሶች ከማዘጋጃ ቤቱ አስወጥተዋል።

    ኢልሃን በኤክስ ገጻቸው “ደኅና ነኝ። ብርቱ ሰው ስለሆንኩ እንዲህ ያለ ትንሽ ነገር አያናውጠኝም፤ ሥራዬንም አያሰናክለኝም። ጉልበተኞች እንዲያሸንፍ አልፈቅድም” ብለዋል።

    ኢልሃን ላይ ጥቃት የሰነዘረው ግለሰብ ከማዘጋጃ ቤቱ ሲወጣ “እርስ በራሳችን እያጣላችን ነው” ሲል ተደምጧል።

    በክፍሉ ውስጥ የነበረ የቢቢሲ ዘጋቢ እንደታዘበው በኤልሀን ላይ የተረጨው ፈሳሽ ጠንካራ ሽታ ያለው ኬሚካል ነው።

    የሚኒሶታ ከንቲባ “በሚኒያፖሊስ ጥቃት እና ማስፈራራት ቦታ የላቸውም። ሰዎችን ሳንጎዳ የተለያየ ሐሳብ ማራመድ እንችላለን” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።

    የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፀጥታ ባልደረቦች በሚኒሶታ እየወሰዱ ባለው እርምጃ ምክንያት ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስቷል።

    ሁለት አሜሪካውያን መገደላቸውን ተከትሎ በሚኒሶታ ግዛት የሚወሰደው እርምጃ "በጥቂቱ ረገብ እንደሚል" ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል።

    በማዘጋጃ ቤቱ ውስጥ የነበረው ጃኩሊን ጎስሊንግ “ከኤልሃን ረዳቶች አንዱ የሆነ ሰው ማስታወሻ ሊያቀብላት ነበር የመሰለኝ” ብሏል።

    ሌላ በክፍሉ የነበረ ታዳሚ አልፍሬድ ፍላወርስ ጁንየር “በማዘጋጃ ቤቱ ንግግሯን በመቀጠሏ ጀግንነቷን አደንቃለሁ” ብሏል።

    እአአ በ2019 ኢልሃን የመጀመሪያዋ ሶማልያዊ-አሜሪካዊት፣ የመጀመሪያዋ አፍሪካ የተወለዱ አሜሪካዊት እና የመጀመሪያዋ ሙስሊም አሜሪካዊት የኮንግረስ አባል ሆነው ተመርጠዋል።

    ኢልሃን ጥቃት የደረሰባቸው ወደ 100 ሰዎች በተገኙበት የማዘጋጃ ቤት ስብሰባ ላይ ነው።

    በሚኒሶታ ታኅሣሥ መግቢያ ላይ ረኔ ጉድ የተባለችው የ37 ዓመት ሴት በስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት የፀጥታ ባልደረቦች ስትገደል ባለፈው ሳምንት ደግሞ አሌክስ ፕሬቲ የተባለው ግለሰብ መገደሉ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።

    ሕዝባዊ ተቃውሞ ያስነሳው የአሌክስ ግድያ ዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖችም ጭምር አስቆጥቷል።

    የትራምፕ አስተዳደር የሚወስደውን እርምጃ ለማርገብ የወሰነውም ለዚህ ነው።

    ሰኞ ዕለት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በሚኒሶታ የሚወሰደውን እርምጃ የሚመሩት የድንበር ጥበቃ ኃላፊ ግሪጎሪ ቦቪኖ ከግዛቱ ለቅቀው እንዲወጡ ወስኗል።

    የትራምፕ የድንበር ጉዳዮች ሹመኛ ቶም ሆማን ግሪጎሪ ቢቪኖን ተክተው ወደ ሚኒሶታ አቅንተዋል።

    ኤልሃን በማዘጋጃ ቤት ባደረጉት ንግግር የስደተኞች እና ጉምሩክ ክፍል “ከሥራ መታገድ አለበት” ብለዋል። የአገር ውስጥ ደኅንነት ጸሐፊ ክርስቲ ኖም “ከሥራ ተባረው በሕግ ይጠየቁ” ሲሉም አክለዋል።

    “መናገራችንን እንቀጥላለን። እኔን አድምጡኝ። ትርክቱን እንዲቆጣጠሩ አትፍቀዱላቸው” በማለት ኤልሃን ተናግረዋል።

    ትራምፕ እና ኤልሃን ለረዥም ጊዜ የቆየ ቁርሾ አላቸው። ትራምፕ በሚኒሶታ እርምጃ እየወሰዱ ያሉት ለኤልሃን ካላቸው ጥላቻ ተነስተው ነው የሚሉም አሉ።

    ትራምፕ “ኤልሃን መታሰር አለባት። ወደ ሶማሊያ ትመለስ። ከዓለም የከፋው አገር ነው። ሶማሊያ ሄዳ አገሯን ታላቅ ታድርግ” ማለታቸው ይታወሳል።

    ሚኒሶታ አብዛኞቹ የሶማሊያ ስደተኞች የሚኖሩባት ግዛት ናት።

    ትራምፕ በሚኒሶታ ግዛት ያሰማሯቸውን 3,000 የስደተኞች ኦፊሰሮች እንዲያስወጡ ጫናው በርትቷል።

    ትራምፕ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሚኒሶታ ያሰማሩትን ኃይል ተከላክለዋል።

    "በሺዎች የሚቆጠሩ ወንጀለኞችን ከግዛቱ አስወጥተናል። የወንጀል ቁጥሩ ከፍተኛ ነበር። ቶም ሆማን በቦታው ይገኛል። የሚወሰደውም እርምጃ ይረግባል" ሲሉም ምላሽ ሰጥተዋል።

  10. አሜሪካ ኢራንን ካጠቃች ሔዝቦላህ እና ሌሎች ቡድኖች ከኢራን ጎን እንደሚቆሙ ገለጹ

    የሂዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ናይም ቃሲም ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲደያርጉ

    የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY

    የምስሉ መግለጫ, የሂዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ናይም ቃሲም ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲደያርጉ

    ባለፉት ሳምንታት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲዝቱ እንደነበረው አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ከፈጸመች ኢራንን እንደሚደግፉ ሔዝቦላህ እና በኢራቅ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች አስታወቁ።

    በአሜሪካ እና በኢራን መከካል ያለው ውጥረት ዳግም እየበረታ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የአሜሪካ የጦር መርከቦች ወደ ቀጣናው መድረሳቸው ተዘግቧል።

    ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች የሚል ስጋት የተፈጠረ ሲሆን፣ የሊባኖሱ ሔዝቦላህን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ጥቃት ከተፈጸመባት ከኢራን ጎን እንደሚቆሙ እየገለጹ ነው።

    የሔዝቦላህ ዋና ፀሐፊ ናይም ቃሲም በኢራን ላይ የሚፈጸም ጥቃት በእነሱም ላይ እንደተፈጸመ የሚቆጠር ገልጸው፤ የአዲስ ጦርነት ነበልባል አጠቃላይ ቀጣናውን የሚለበልብ ይሆናል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    የቡድኑ መሪ በተጨማሪም በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ላይ የመግደል ሙከራ “በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዓለም መረጋጋት ላይ የሚፈጸም የሽብር ጥቃት” ይሆናል ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢራን የሚደገፉ ኢራቅ ውስጥ የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች በተመሳሳይ በኢራን ላይ ከአሜሪካ እና ከእስራኤል ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ከኢራን ጎን ለመሰለፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

    የሊባኖሱ ሔዝቦላህ በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ገጥሞ በነበረው ጦርነት መሪዎቹን ጨምሮ በርካታ አባላቱ ተገድለውበት ክፉኛ ተዳክሟል። አሁንም ድረስ እስራኤል ወደ ሊባኖስ ዘልቃ በመግባት ቡድኑ ላይ ጥቃት ትፈጽማለች።

    ኢራን የፍልስጤሙን ሐማስ እና የየመኑን ሁቲ ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ፀረ አሜሪካ እና እስራኤል የሆኑ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ትታወቃለች።

  11. የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ እና ጦር ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ አየር ኃይል

    ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን እና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው

    የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force

    የምስሉ መግለጫ, ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን እና ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው

    ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደተለያዩ አገራት እየተጓዙ ያሉት የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው እና የአሜሪካ ሠራዊት የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ያዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የአቪየሽን ኤክስፖ ጎበኙ።

    ኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሠረተበትን 90ኛ ዓመት እያከበረ ያለ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተገኙባቸው ዝግጀቶች እና አየር ኃይሉ የታጠቃቸው ዘመናዊ አውሮፕላች እንዲሁም ተቋማዊ ብቃቱን የሚያሳዩ ትዕይንቶች ቀርበዋል።

    የኢትዮጵያ መከከላያ ሠራዊት እንደገለጸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና የጦር ሠራዊት ባለሥልጣናት በአየር ኃይሉ ዝግጅት ላይ ተገኝተው ገብኝት አድርገዋል።

    የአሜሪካ ምክትል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክርስቶፎር ላንዳው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ለመወያየት ሲሆን በግብፅ፣ በኬንያ እና በጂቡቲም ጉብኝቱ እንደሚያደርጉ መሥሪያ ቤታቸው ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

    ላንዳው በኋላ ለተደረገላቸው አቀበባል ማመስገናቸው እና “በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጠል” መናገራቸውም ተዘግቧል።

    የአሜሪካ ሠራዊት የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን “ለቀጣናው ሰላም በተለይም እንደ አልሸባብ እና አይኤስኤስ ያሉ ሽብረተኞችን ለመከላከል እና ለመደምሰስ በጋራ እንሠራለን” ብለዋል።

    ኤክስፖው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አካል በሆኑት አየር ኃይል፣ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንዱስትሪ ግሩፕ፣ የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን፣ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ እና በሌሎችም ዓለም አቀፍ ደርጅቶች ተሳታፊነት የቀረበ መሆኑ ተገልጿል።

  12. ግዙፉ አውሮፕላን ተሸካሚ የአሜሪካ የጦር መርከብ መካከለኛው ምሥራቅ ደረሰ

    ተዋጊ አውሮፕላኖችን የጫነው መርከብ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ተዋጊ አውሮፕላኖችን የጫነው መርከብ

    የባሕር ላይ ተዋጊ መርከቦችን ያስከተለው ግዙፉ የአሜሪካ ተዋጊ አውሮፕላኖች ጫኝ የጦር መርከብ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መድረሱን ሁለት የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሮይተርስ የዜና ወኪል አስታወቁ።

    ለሳምንታት በኢራን የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በኢራን ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ሲናገሩ የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ መርከቦቹ ወደ አካባቢው መላካቸውን ባለፈው ሳምንት አሳውቀው ነበረ።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀጣናው ያላቸውን ወታደራዊ ኃይል ከመጠናከሩ ባሻገር ኢራን ላይ እርምጃ ሊወሰዱ እንደሚችልም ተጠቁሟል።

    ተዋጊ አውሮፕላኖችን የጫነው መርከብ ዩኤስኤስ አብርሃም ሊንከን እንዲሁም ሌሎች የሚሳዔል መሣሪያዎች ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ያቀኑት በአሜሪካ መከላከያ ማዕካለዊ ዕዝ ትዕዛዝ መሆኑ ተዘግቧል።

    ባለፈው ሳምንት ትራምፕ የአሜሪካ የጦር መሣሪያ ወደ ኢራን አቅራቢያ እንደሚላክ ሲገልጹ “አንጠቀምበትም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው ነበር።

    በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ያለው ውጥረት ከመባባሱ ጋር በተያያዘ የጦር መሣሪያዎቹ ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶ ከእስያ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ማቅናት ጀምረዋል።

    ከጦር መርከብ በተጨማሪ አሜሪካ ተዋጊ ጀቶችንም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ማስጠጋቷን ፔንታጎን አስታውቋል።

    በኢራን የተነሳውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ መንግሥት ተቃዋሚዎችን መግደል የሚቀጥል ከሆነ አሜሪካ ጣልቃ እንደምትገባ ትራምፕ መናገራቸው ይታወሳል።

    ከዚህ ቀደምም በመካከለኛው ምሥራቅ ያለው ውጥረት ሲባባስ አሜሪካ የጦር መርከቦችን ወደ ቀጣናው ታስጠጋ እንደነበር አይዘነጋም።

  13. ሕንድ እና የአውሮፓ ኅብረት "ታሪካዊ" የተባለ የንግድ ስምምነት ተፈራረሙ

    የሕንድ መሪ ናሬንድራ ሞዲ (መሐል) የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኧርስላ (በስተቀኝ)

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተወሳሰበው የአውሮፓ ኅብረት እና ሕንድ ታሪካዊ የሚባል የንግድ ስምምነት መፈረማቸውን ይፋ አድርገዋል።

    “የስምምነቶች እናት የሆነ ስምምነት ላይ ደርሰናል” ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ኧርስላ ቮን ደር ላየን በኤክስ ገፃቸው ፅፈዋል።

    ፕሬዝደንቷ ወደ ደልሒ ተጉዘው ከሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የተገናኙ ሲሆን ሞዲ ስምምነቱን “ታሪካዊ” ብለውታል።

    27 አባል ሀገራት ባሉት የአውሮፓ ኅብረት እና በሕንድ መካከል በተፈረው ስምምነት መሠረት ምርቶች በነፃ ይጓጓዛሉ። ከ2 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያላቸው ኅብረቱ እና ሕንድ በጋራ ከዓለም ንግድ 25 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ።

    ስምምነቱ ታሪፍን በከፍተኛው ደረጃ እንደሚቀንስ እና ለሁለቱም የተሻለ ገበያ እንደሚፈጥር ታምኖበታል።

    የአውሮፓ ኅብረት እንዳለው ስምምነቱ በኬሚካል፣ በማሽኖች እና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች ላይ የተጣለውን ታሪፍ ዝቅ ለማድረግ ይጠቅማል። ወደ ሕንድ የሚሄዱ ምርቶችን ዋጋም ዝቅ እንደሚያደርገው ይታመናል።

    የአውሮፓ ኅብረት እና ሕንድ ከዩናይትድ ስቴትስ የምጣኔ ሀብት እንዲሁም ጂኦፖለቲካዊ ጫና እየደረሰባቸው ነው።

    ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት ሕንድ ላይ 50 በመቶ ታሪፍ መጣላቸው ይታወሳል።

    ባለፈው ሳምንት ደግሞ አሜሪካ ግንሪንላንድን ለመቆጣጠር ያመጣችውን ሐሳብ የተቃወሙ የአውሮፓ ሀገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል ዝተው እንደነበር ይታወሳል።

  14. በአሜሪካ በተከሰተው ከባድ የአየር ሁኔታ ቢያንስ 21 ሰዎች ሞቱ

    በጎዳና ላይ የበረዶ ክምር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በአብዛኛው የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ በተከሰተው ከባድ ቅዝቃዜ እና የበረዶ ወጀብ የተነሳ እስካሁን ድረስ ቢያንስ 21 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።

    የተለያዩ ግዛቶች ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት ከተከሰተው ከባድ የክረምት ቅዝቃዜ ጋር በተያያዘ በበርካታ ግዛቶች ውስጥ እስከ ሰኞ ሌሊት ድረስ የ21 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።

    ከባዱ የበረዶ ወጀብ ባለፉት ቀናት ከነበረባቸው አካባቢዎች እየተስፋፋ በርካታ ግዛቶችን እያካተተ ነው። በዚህም ሳቢያ ከ200 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን በከባዱ የአየር ሁኔታ ስጋት ውስጥ ናቸው።

    እየጣለ ባለው በረዶ ምክንያት በጎዳናዎች፣ በአየር ማረፊያዎች እና በሌሎችም መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ክምር በመፍጠሩ፣ እንቅስቃሴዎች ከመስተጓጎላቸው ባሻገር የኤሌክትሪክ አቅርቦት በበርካታ ቦታዎች ተቋርጧል።

    ባለፉት ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን በረራዎች የተሰረዙ ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናትም የሚኖሩ በረራዎች የመሰረዝ ወይም የመዘግየት ዕጣ ይገጥማቸዋል ተብሏል።

    በበርካታ ግዛቶች ሰዎች ከቤታቸው መውጣት ስለማይችሉ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ተቋማት ተዘግተዋል። ግዛቶች አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ቡድኖችን በማሰማራት ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን ከበረዶ ክምሮች ለማጽዳት እየሞከሩ ቢሆንም የአየር ሁኔታው በመቀጠሉ ያሰቡትን ያህል ስኬታማ አልሆኑም።

  15. ናይጄሪያ በመፈንቅለ መንግሥት ሤራ የከሰሰቻቸውን ግለሰቦች ወታደራዊ ፍርድ ቤት ልታቀርብ ነው

    የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ቦላ ቲኑቡ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የናይጄሪያ ጦር ሠራዊት የፕሬዝደንት ቦላ ቲኒቡን መንግሥት “ለመገልበጥ አሲረዋል” ያላቸውን ግለሰቦች ወታደራዊ ፍርድ ቤት እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

    ባለፈው ጥቅምት 16 መኮንኖች “የዲሲፕሊን እና የአገልግሎት መመሪያን በመጣስ” በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

    በወቅቱ የናይጄሪያ ጦር የመንፈቅለ መንግሥት ሙከራ ተፈፅሟል መባሉን አስተባብሎ ነገር ግን ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

    ናይጄሪያ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1966 እስከ 1993 ባለው ጊዜ በርካታ መፈንቅለ መንግሥታት አስተናግዳለች። በዚህ ምክንያት የመንግሥት ግልበጣ ስሱ ከሚባሉ ጉዳዮች አንዱ ነው።

    ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ባለው አለመረጋጋት እና የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ከጦር ሠራዊቱ መካከል አንዳንድ ሰዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ ቢነገርም የናይጄሪያ ጦር ይህን አይቀበልም።

    ናይጄሪያ ከ1999 ጀምሮ በሲቪል መንግሥት እየተመራች የቆየች ሲሆን የጦር ሠራዊቱ አዛዦች ለሲቨል መንግሥት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚገልፁ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ያወጣሉ።

    የናይጄሪያ ጎረቤት የሆኑት ምዕራብ አፍሪካዊያኑ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኒጀር እና ጊኒ ባለፉት ዓመታት በርካታ መፈንቅለ መንግሥት አስተናግደዋል።

  16. የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ከአሜሪካ እና ቻይና “መካከል እንደማይመርጡ” ተናገሩ

    የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በቅርቡ ወደ ቤጂንግ ለመጓዝ እየተዘጋጁ ያሉት የዩናይት ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ከአሜሪካ ወይም ከቻይና ጋር ባላቸው ግንኙነት ውስጥ "ከሁለቱ አንዱን ለመምረጥ" እንደማይገደዱ ገለጹ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዩናይትድ ኪንግደም በንግድ፣ ደኅንነት እና መከላከያ ዘርፎች ከአሜሪካ ጋር ያላትን “የቅርብ ግንኙነት” እንደምታስጠብቅ ተናግረዋል። አክለውም ግን “ጭንቅላትህን አሸዋ ውስጥ ቀብረህ ቻይናን ችላ ማለት... ስሜት የሚሰጥ ነገር አይሆንም” ብለዋል።

    ስታርመር ከዜና ወኪሉ ብሉምበርግ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ የዓለም ሁለተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ወደሆነችው ቻይና የሚያደርጉት ጉብኝት ለብሪታኒያ ኩባንያዎች “ጉልህ እድሎችን” ሊያስገኝ እንደሚችል ገልጸዋል።

    በርካታ የዩናይትድ ኪንግደም የንግድ አመራሮች አብረዋቸው ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉብኝት የሚያደርጉት አገራቸው ለንደን ውስጥ አዲስ ሰፊ የቻይና ኤምባሲ ለመገንባት የተያዘውን አከራካሪ እቅድ ባጸደቀች በቀናት ልዩነት ውስጥ ነው።

    ለረጅም ጊዜ የተጓተተው ይህ ውሳኔ የተላለፈው ታዋሚዎች የሚገነባው ኤምባሱ የቻይና ሰላዮች ማዕከል ይሆናል የሚል ማስጠንቀቂያ እየሰጡ ባሉበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

    “ብዙውን ጊዜ በቀላሉ ከአገራት መካከል እንድመርጥ እጋበዛለሁ። ይህንን አታድርጉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    “አስታውሳለሁ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ስምምነት ስፈጽም ሁሉም ሰው ከአሜሪካ እና አውሮፓ መካካል መምረጥ እንዳለብኝ ይነግረኝ ነበር። ‘ይህንን ምርጫ አላደርግ” ብያቸዋለሁ” ሲሉ በቃለ መጠይቁ ተናግረዋል።

    “ከአሜሪካ ጋር በጣም ቅርብ ግንኙነት አለን፤ በእርግጥም እንገልገዋለን። ከደኅንነት እና መከላከያ ጎን ለጎን ያልንን ንግድ እናስጠብቃለን” በማለት አክለዋል

    “በእኩል ደረጃ፤ የዓለም ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ሆና እያለ ችና የንግድ እድሎች እያሉ ጭንቅላትህን አሸዋ ውስጥ መቅበር እና ቻይናን ችላ ማለት ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም” ሲሉም አቋማቸው ገልጸዋል።

  17. ከሚኒያፖሊስ ግድያ በኋላ “ሁሉንም ነገር እየገመገሙ” እንደሆነ ትራምፕ ተናገሩ

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸው በሚኒያፖሊስ ያለውን ሁኔታ እየገመገመ እንደሆነ ተናገሩ።

    ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ቅዳሜ እለት በሚኒያፖሊስ የ37 ዓመቱ ነርስ አሌክስ ፕሪቲ በኢሚግሬሽን መኮንኖች በተተኮሰበት ጥይት ከተገደለ በኋላ በተነሳ ተቃውሞ ሰበብ ነው።

    ትራምፕ እሁድ ዕለት ለዎል ስትሪት ጆርናል ሲናገሩ ፕሪቲን ተኩሶ የገደለው መኮንን ስለወሰደው እርምጃ ትክክለኛነት በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ቀጥተኛ መልስ ሳይሰጡ ቀርቷል።

    በምትኩ አስተዳደራቸው “ሁሉንም ነገር እየገመገመ እንደሆነ እና ከውሳኔ ጋር እንደሚመጡ” ተናግረዋል።

    ትራምፕ ለጋዜጣው ሲናገሩ ማንኛውንም ዓይነት ተኩስ እንደማይወዱ እና ማንም ቢሆን በጣም ኃይለኛ እና ሙሉ ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ ታጥቆ ወደ ተቃውሞ መሄዱ ደስ እንደማይላቸው . . . ይህም ጥሩ ነገር እንደማያስከትል ተናግረዋል።

    አስተዳደራቸው ቀደም ብሎ ፕሪቲን የገደለውን መኮንን የተከላከለ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም፣ ፕሪቲ የተገደለው "ሽጉጡን ሲያሳይ" እንደነበር ተናግረዋል።

    የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን ይህን አስተባብለዋል።

    ባለሥልጣናቱ የሟች ሽጉጥ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ እንደሆነ ገልጸው፤ የተተኮሰበትም መሣሪያውን ከተነጠቀ በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል።

  18. የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማርበርግ ምክንያት ያቋረጠውን በረራ ሊጀምር ነው

    የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, ET

    በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ውስጥ ተከስቶ የነበረው የማርበርግ ቫይረስ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጦት የነበረውን በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

    በኅዳር ወር መጀመሪያ ላይ በተከሰተው ወረርሽኝ በጂንካ ሆስፒታል ስድስት ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ነው በሽታው ማርበርግ መሆኑን መንግሥት ያስታወቀው።

    በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጂንካ ያደርግ የነበረውን በረራ አቋርጦ የቆየ ሲሆን፣ በአካባቢው በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ ሳይቀር ዕገዳ ተጥሎ ነበር።

    ከሦስት ወራት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ ዞን የተከሰተው የማርበርግ ቫይረስ አሁን በቁጥጥር ሥር መዋሉን የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ጥር 18/2018 ዓ.ም. አስታውቋል።

    ይህንንም ተከትሎ አየር መንገዱ ለክልሉ እና ለዞኑ ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ ከአዲስ አበባ ጂንካ እና ከጂንካ አዲስ አበባ አቋርጦት የነበረውን በረራ አርብ ጥር 22/2018 ዓ.ም. እንደሚጀምር ከአየር መንገዱ የተጻፈውን ደብዳቤ አያይዞ የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ አሳውቋል።

    የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደተናገሩት ቫይረሱ ከኢትዮጵያ “ጨርሶ እንደተወገደ” ይፋ የተደረገው በዓለም የጤና ድርጅት አሠራር መሠረት ላለፉት “42 ተከታታይ ቀናት ምንም አዲስ ታካሚ ባለመመዝገቡ” ነው።

    ማርበርግ ቫይረስ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ከታወቀ በኋላ በነበሩት ወራት 14 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ በላብራቶሪ ምርመራ ተረጋግጧል። ከመካከላቸውም የዘጠኙ ሕይወት ሲያልፍ አምስት ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

  19. በአየር ሁኔታ ምክንያት በአሜሪካ ከ10 ሺህ በላይ በረራዎች ተሰረዙ

    በበረዶ የተሸፈነ የኒው ዮርክ ላጉዋርዲያ አየር ማረፊያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የኒው ዮርክ ላጉዋርዲያ አየር ማረፊያ

    በአሜሪካ እየከፋ በመጣው የበረዶ ወጀብ እና ቅዝቃዜ ምክንያት ሰኞ ዕለት ብቻ ከ10 ሺህ በላይ የአውሮፕላን በረራዎች መሰረዛቸውን የበረራ መረጃዎችን የሚያመለክተው ፍላይትአዌር አስታወቀ።

    ከፍተኛው የአየር ትራንስፖርት መስተጓጎል ያጋጠማት ኒው ዮርክ ስትሆን፤ በከተማዋ ከሚገኙት ጄኤፍኬ፣ ላጉዋርዲያ እና ኒዋርክ አየር ማረፊያዎች ይነሱ የነበሩ 379 በረራዎች ሲሰረዙ ከ30 የሚበልጡት ደግሞ እንዲዘገዩ ተደርገዋል።

    የክረምቱ የበረዶ ወጀብ በቦስተን ሎጋን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲሁም በዋሽንግተን ዳላስ፣ ሬጋን እና ባልቲሞር አየር ማረፊያዎች በርካታ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል።

    በተጨማሪም የአየር ሁኔታው ከአሜሪካ ባሻገር በካናዳ ቶሮንቶ ፒርሰን አየር ማረፊያ በርካታ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎች ላይ መዘግየት ወይም መሰረዝን አስከትሏል።

  20. በአሜሪካ ከተከሰተው ከባድ የአየር ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሰዎች እየሞቱ ነው

    የበረዶ ክምር ከዋይት ሐውስ አቅራቢያ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በበርካታ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ በተከሰተው እጅግ ከባድ ቅዝቃዜ ያለበት የአየር ሁኔታ ምክንያት በተለያዩ ቦታዎች የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑ ተዘገበ።

    ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ቀናት አንስቶ ባጋጠመው የበረዶ ወጀብ ምንም እንኳን የአንዳንዶቹን ምክንያት በትክክል ለማረጋገጥ ገና ቢሆንም እስካሁን ቢያንስ 14 ሰዎች በተለያዩ ግዛቶች ውስጥ ሞተዋል።

    እስካሁን የተመዘገቡት የሚከተሉት ናቸው:

    • የቴኒሲ ግዛት ባለሥልጣናት ከአየር ሁኔታው ጋር በተያያዘ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል
    • ከበረዶው ወጀብ ጋር በተያያዘ የሁለት ሰዎች ሞት በሉዊዚያና ግዛት ውስጥ ተመዝግቧል
    • ቴክሳስ ውስጥ በአንድ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ሞቶ የተገኘ ግለሰብ ምክንያቱ የጤና ወይም ከቅዝቃዜው ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ፖሊስ ገልጿል
    • እዚያው ቴክሳስ አንዲት የ16 ዓመት ታዳጊ በረዶ ላይ ስትንሸራተት በገጠማት አደጋ ሕይወቷ አልፏል
    • ማሳቹሴትስ ውስጥ አንዲት ሴት በረዶ ተደርምሶባት ሞታለች
    • ካንሳስ ውስጥ ደግሞ አንዲት ሴት በበረዶ ተሸፍና ሞታ ተገኝታለች
    • የሞታቸው ምክንያት ገና ባይረጋገጥም ኒው ዮርክ ውስጥም አምስት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል