ቻይና እንደ ብሉቱዝ ያሉ መረጃ መቀባበያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ገደብ ልትጥል ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና እንደ ብሉቱዝና ኤርድሮፕ ያሉ መረጃ መቀባበያ ቴክኖሎጂዎች በገደብ ጥቅም ላይ እንዲውል ልታደርግ ነው።
ብሔራዊው የበይነ መረብ ተቆጣጣሪ ባለፈው ረቡዕ ለአንድ ወር የሚዘልቅ ምክክር ጀምሯል።
የዚህ አዲስ ሐሳብ ዋና ምክንያት ተብሎ የተቀመጠው ሕገ-ወጥ እና “አላስፈላጊ” የሆነ መረጃ ልውውጥን መግታት ነው።
ነገር ግን የመብት ተሟጋቾች ይህ ረቂቅ አዋጅ መረጃ የመለዋወጥ ባሕሉን የበለጠ ያዳክመዋል የሚል ስጋት አላቸው።
ቻይና ዓለማችን ላይ ካሉ በጣም ጥብቅ የበይነ-መረብ ቁጥጥር ከሚያደርጉ ሃገራት አንዷ ናት።
ለዚህ ነው ብሉቱዝና ኤርድሮፕ እንዲሁም ሌሎች የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች እጅግ አስፈላጊ የሆኑት።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ የሚያደርጉ ሰዎች ፖለቲካዊ አቋማቸውን ለመለወዋጥ ኤርድሮፕ የተሰኘው መረጃ መጋሪያ ይጠቀማሉ።
ለምሳሌ ባለፈው ጥቅምት የተወሰኑ የመብት ተሟጋቾች ይህን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው ፀረ-ዢ-ጂንፒንግ ‘ፖስተር’ ሲቀባበሉ ነበር።
በወቅቱ ጂንፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ የሃገሪቱ መሪ ለመሆን ሽር ጉድ ላይ ነበሩ።
በርካቶች ኤርድሮፕን የሚመርጡት ቴክኖሎጂው የአንድ ግለሰብ ግላዊ መረጃዎች ሳያሳውቅ አጠገብ ከሚገኝ ሰው ጋር መረጃ መለዋወጥ ስለሚያስችል ነው።
አልፎም ቴክኖሎጂው መረጃ ለመለዋወጥ ምርመራ ሊደረግበት የሚችል ኔትዎርክ አይጠቀመም።
ይህ ቴክኖሎጂ የአሜሪካዊው ግዙፍ ኩባንያ አፕል ምርቶች ላይ ነው የሚሠራው።
ነገር ግን ባለፈው ዢ ለሶስተኛ ጊዜ መንበረ ሥልጣኑን በያዙ ወቅት አፕል የቴክኖሎጂውን አቅም ቻይና ውስጥ ዝቅ አድርጎታል።
ተጠቃሚዎች የስልክ ቁጥር መዝገባቸው ውስጥ ከሌለ ሰው መረጃ ለመቀበል 10 ደቂቃ ብቻ ነው የሚሰጣቸው።
የአፕል ምርት የሚጠቀሙ ሰዎች ያለገደብ መረጃ መለዋወጥ የሚችሉ የስልክ ቁጥር መዝገባቸው ውስጥ ካለ ሰው ጋር ብቻ ነው ማለት ነው።
አፕል ለምን ይህ ቴክኖሎጂ ቻይና ውስጥ ብቻ ይፋ እንደተደረገ ባይገልጥም ኩባንያው ለቻይና መንግሥት ‘ተገዢ' በመሆን ይታማል።
ምንም እንኳ ቻይና ረቂቅ አዋጁ ዋና ዓላማው የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው ብትልም የመብት ተሟጋቾች በዚህ ጭራሽ አይስማሙም።
የቻይና ሳይበርስፔስ አስተዳደር ባለፈው ማክሰኞ ለውይይት ያቀረበው ረቂቅ እንደሚለው ተጠቃሚዎች “አላስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ከመቀበል እና ከማሰራጨት የማይቆጠቡ ከሆነ ለፖሊስ ጥቆማ ሊደረግባቸው ይገባል።”
ይህ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚዎች እኒህን ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም ትክክለኛ ስማቸውን ሊያሰፍሩ ይገባል ይላል።












